Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የቅኔው ንጉሥ ፈላስፋ –የትውልድ ግሥ፤ የኑሮ ስዋሰዋዊ –ምዕት፤ (የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ሙት ዓመት መታሰቢያ)

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 25.02.2013 (ሲወዘርላንድ – ዙሪክ)

(„ጥበብ ቤቷን ሠራች፣ ሰባቱን ምሰሶ አቆመች። ምሳሌ፤ ምዕራፍ 9 ቁጥር 1“)

ተግቶ ንጋትን ሠራት። በቀንበጥነት በዝግጁነት ሰማያዊ ጥሪን ታጥቆ ተቀበለ – ጀግና። የማያልቅ ሙቅ ሥነ – ጥበባዊ ስሜትን በተስፋ ስንቅነት ቀመረ፣ አንጥሮ በቅንነት ለገሰ፣ አንቆጠቆጠም። በስብዕናዎቹ ውስጥ ማንነቱን ሰንደቁ ያደረገ ጉልቶ የሚታይ የትውልድ ጌጠኛ ዓውራ። ተግባሩ ዋጋቸው ለዘመናት ሳይቀንስ እዬፈኩ – እዬደመቁ ከሩቅም ከቅርብ በቋሚነት የሚጠሩ ዘላቂ ማገሮች ናቸው። ሃብትነቱ – ሁለመና ሁለአቀፋዊ ሞዴል መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዳኝነቱ ጥልቅ ሥልጡን ውስጠ አዋቂ – መርማሪዎች ናቸው። የአፍሪካ ዋርካ፤ የፓን አፍሪካኒስትነት ጠበቃ፤ የሰብዕዊነት ዕጬጌ ነው የቅኔው ዐፄ ብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን! ሥጦታ! ምርቃት!
New Picture (4)

ቅኔው – ተዘረፈ
እቶኑም – አጠና …
ቅኔውም አፈራ፤
አብነት – ተጉዞ
ረጅም – ተመዞ
ቅኝተ – መዘዞ፤
ሀቅን – ጎዘጎዘ
ሚስጥርን አፈሰ።
ፈልነን – አፍልቶ
ትናንትን – ፈወሰ።
ዛሬን – አነገሠ …
ሥጦታ – አቀሰሰ።

ግሡ – ተገሰሰ፤
ዜማ ተንተራሰ
ጥበብ – ገሰገሰ።
መምህሩ ነገሠ፤
ድንቅነት – ለበሰ።
በዐለም አንደበት
ሎሬት – ተወደሰ!
ብዕርህ ወተት ናት፤ — ዕልፍን የፈጠረች
መንፈስህ ቅዱስ ናት፤ — ነገን የወለደች
ቃልህም ምህረት ነው፤ — መድህን የቀለበ
ትንቢትህ ዕውነት ነው፤ — ህይወት ያቀበለ
ዓለምን የዳኘ ግኘት – ያበቀለ።
ጥረትህ ዕንቁ ነው፤ – ጸጋን ያፈለቀ
ጨለማን ቆልፎ —- ፍካት ያስደመመ፤
ጸጋህ መድህን ነበር፤ — ጸሐይ የፈረመ።
ሊቅነትህ ቀንዲል – ልቅናህ ገረመው
ፈጠራህ ልዑቅ ነው፤ — ግርማ የነበረው።
ውድም አባት ነበርክ ሳትደክም የተጋህ
ትውፊትን ገንብተህ – ዘመንን የሠራህ።
New Picture (5)
እኔ ትቢያ ለዕውቁ ሁለገብ ፈላስፋ ለመጻፍ አቅሙ የለኝም – ብናኝ ግርድ ነኝና። ፍቅሩን አስቤ ሙት ዓመቱን የካቲት 18ትን ለማጠዬቅ እንጂ። የዲታው የአማርኛ ቋንቋ …. ውብ ቃላቶች ሆኑ ሳቢ ቅላፄዎች፣ እንዲሁም ጹዑም ፍሰቶች ሁሉ ቢቀመሩ ብቃቱን፣ አቅሙን፣ ችሎታውን፣ ጸጋውን፣ ተሰጥዖውን፣ ተንባይነቱን፤ ስበቱን፣ የተመረጠና የሰጠም መሆኑን የመናገር ኩነታቸው ያጠራጥረኛል። …. እሱ ልዩ – ተፈጥሮው ልዩ፣ ውስጡ ልዩ – ቅኝቱ ልዩ፣ ስምንትዮሽ ቤቱ – ጥበብ ግንብነቱ – ፍጹም ልዩ ያደርገዋል። ከጃፓኖች ሃይኩ፤ ከእንግሊዞች ሶኔት፤ ከጀርመኖች – ከኦስትራሾችና ከሲዊዞች ሌይሪክ ከእኛም የወል ቤት የተለዩ የሥነ ግጥም ዬግማድ መሰረት ነው። ቋንቋዎች ሁሉ ጸጋዬ ቤት መስቀላቸው ናቸው። የሥርዬት ድርና ማግ ዘላለማዊ ምጥቅ ብሩክ ….
ወይ ይህቺ አንቦ እንዴት የተባረክች ቅዱስ ቦታ ናት። የሰላሙ አባት የክቡር ማንዴላን ህይወት የታደገው ሚስጢር የሻንበል ጉታ ዲንቃም እትብት። ፈላስፋው ብላቴ ሎሬት ጸጋዬንም የሸለመችን – ጸጋውን በመድህን ጠልፋ በትጋት ባጋቱ ጋቶቿ የቀለበችን – የማትጠገብ ባዕት። ብቁ የእናት መቀነት ልዩ ዳኛ አንቦ።
የደም ገንቦ – አንቦ ጀግና
ቃል ዋና
የተግባር ገናና
የእማ ወዘና
ሥነ – ጥበብን ከነሙሉ አካሉና አቅሙ ወልዶ ዬሰጠ አንቦ – አንባ። ረ/ፕሮፌሰር ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን በፎለቄዋ ቦዳ በአምቦ ደቡባዊ ምዕራብ 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የጅባትና ሜጫ ግርማን በተላበሰች ገጠር ተራራማ ቦታ ከተከበሩ ክቡር አባቱ ከአቶ ገብረመድህን ሮባ ቀዌሳና ከተከበሩ ክብርት እናቱ ከወ/ሮ ፈለቀች ዳኜ በወርኃ ዬካቲት ወር 1929 ዓ.ም ተወለደ። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአምቦ ማዕረገ ሕይወት ቀኃሥ ትምህርት ቤት ከዚያም ሁለተኛ ደራጃ ትምህርቱን ጄኒራል ዊንጌት በመማር ላይ እንዳለ የንግድ ሥራ ኮሌጅ ተልዕኮውን አህዱ ሲል በዛው ትምህርቱን ቀጥሎ በወርቅ ሽልማትና በሚያስመካ ውጤት በማዕረግ ተመርቋል። በኋላም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩንቨርስቲ ቤተመጻህፍት እዬሰራ ሳለ አሜሪካን ቺካጎ ኤሊኖይ ወስጥ ከሚገኘው ብላክስቶች ስኩል ኦፍ ለው በህግ ሙያ በተልዕኮ ተምሮ ዲግሪውን አግኝቷል። ከሰማዩ ድግሪ ግን አቻ የሚሆን አይደለም። ያው በስወ – ሰውኛው ስናስበው … በቀለሙም ቢሆን ገፍቶ የሄደ ስለመሆኑ ለማጠዬቅ እንጂ።

የቅኔው ልዑል አውራና መምህር ብላቴ ጌታ ሎሬዬት ጸጋዬ ገ/መድህን በተጨማሪም ከዩኒስኮ ባገኘው ነፃ የትምህርት ዕድል በሼክስፒር የላቀ የትውና -ጥብብ አንባ ወደ ሆነው እንግሊዝ ሀገር ሄዶ Royal court Theatre፤ ፈረንሳይ Comedian Francaise፤ በኢጣሊያን ሀገር ደግሞ Opera መድረኮችን እዬጎበኘ የተውኔትን ጥበባትን አጥንቶ ተመልሷል። ይህ ወቅት ኢትዮጵያን በውስጡ እስቀምጦ በሥነ – ተውኔት ዘርፍ እኩል ደረጃ እንድታገኝ ኃላፊነቱን በቅንነት ወስዶ እናቱን ወደ ፊት እጅግ በበቃ ችሎታ ለማራመድ በመንፈሱ ውል ያሰረበት ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም በህይወት ዘመኑ ሁሉ የከወናቸው አይነታ ተግባራት የኪዳኑ ወርቃማ ማህተም ናቸውና።። በዘርፉ በመሪነት ኢትዮጵያን በእኩልነት ተርታ ትሰለፍ ዘንድ ታድጓታል። ፊት ለፊትም አምጥቷታል። በጸጋው ፍሬ ጠቀስ ጉልበት ኃይልና አቅም ፈጥሮላታል። አንቱነቷን በውስጥነት አፍልቆታል – አጸድቆታል።

የጋሼ ጸጋዬ ጥረት በመሆን የከበረ፤ በድርጊት የበለጸገ ስለሆነ ውለታውን ለመክፈል አድናቂዎቹ ሆነ አክባሪዎቹ ይህን የሚመጥን አቅም የለንም። ቀድሞ ነገር አልጀመርነውም። ፈርተነዋል። እንሆ ጊዜ ገቢረ ለእግዚአብሄር ነውና ሥነ – ጥበብ ፈልጋው ከሰማ ሰማያት ወርዳ ወደ ሳቂተኛዋ ቦዳ ተጉዛ ብላቴናውን ልጇን በቅዱስ መንፈስ ኃይል መረጠች። ውስጧ ሆኖ የልጅነት ጊዜውን ተጠበበባት። በወተቷም አድጎ በለጸገባት። በማህጸኗ ፍልስፍናን አዳጎሰባት። በህሊናዋ ማህደር ሆኖም ዛሬንና ነገን በቋሚነት አንፆ ሥነ ጥበብን ልዕለ – ሐሴት ብሎ ሰዬማት። ትውፊትን ሰርቶ በዘላቂነት በባለቤትንት እኛን ትሆን፤ ትመስልም ዘንድ፤ መከራችን፣ አሳራችን፣ ደስታ ፍሰኃችን ፈቅዳ ትጋራንም ዘንድ ሸለመን።
New Picture (6)
ዓራት ዓይናማው ፈለገ ህይወትም የአንደኛ ደረጃ ት/ቤትም ድልድይን አመሳጠረች። „ የሁለቱ ባህሎች ውጤት አካል ሆኜ ነው ያደኩት። ድልድይ ሆንኩኝ። አፍ የፈታሁት በኦሮምኛ፤ እርባታ የጀመርኩት ደግሞ የግዕዝ ግስ በመግሰስ ነበር“ ብሎ ሚስጢሩን ፈልቀቅ አድርጎ ያቃመሰን የቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን በሊጋባነቱ ተዝቆ በማያልቀው ዕውቅ የሊቃናት መንደር ልቅናውን ነፍስ የሰጠው፣ መክሊታዊ እስትንፋሱን ከቅዱስ መንፈስ ጋር በመስተጋብር ያዋኸደው በእናት አባቱ እልፍኝ ሥር ይልቁንም በእናቱ ወገኖች በነ አለቃ ማዕምር ዳዊት የመድገምና የቅኔ ግሥ የመግሰስ፤ ድንጋጌዎችንም የመቀለብ ቡቃያ እድል በማግኘቱ እሱም የትውልዱ የግሥ እሸትና ፍሬ እንዲሆን ምርጥኑቱን አትሞበታል። ድልድይነቱም የምህረት አባት፣ የፍቅር አብነት፣ የአብሮነት ጉልላት መሆኑን በብርኃናማ ድርጊቶቹ ያመሳጠረ „የተራራው ስብከት“ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ በትንግርትነት ይዘልቃሉ።

ዘመናዊ ትምህርቱን በአምቦ ማዕረግ ህይወት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የጀመረው ብላቴናው ጸጋዬ እንደ ባለቅኔው፤ ከእረኝነት እንደ ተመረጠው፤ ፈጣሪ አምላካችን መዳህኒተዓለም ክርስቶስ እንደ ልቤ እንደ አለው እንደ ንጉሥ ዳዊት ብላቴ ጸጋዬም በጥቁር መሬት የአፍሪካ የሥነ ጥበብ ሙሴና ብቁ ዕንቁ፤ እንዲሁም ተመራማሪ እንዲሆን የልቅና ማዕረግ የተሰጠው ገና በ13 ዓመቱ ነበር። ታምሩም በበኽሩ ቲያትሩ „የዲናስዮስ ዳኝነት“ በ1942 ዓ.ም አዲስ ምዕራፍነቱን ፏ ፍንትው አድርጎ በምልክትነት ተከፈተ።
New Picture (7)
ዕድለኛው ብላቴና ይህን ፍጹም ልዩ ጸጋ ቀምሞ፣ አንጥሮ፣ አብስሎ፣ አስመችቶ እንዲይዝ በሩን ቧ አድርጎ የከፈተለት ሌላው ወርቅ አጋጣሚ ደግሞ እሱም እንዳለው ከሁለቱም ታላላቅ ማህበረሰቦች ባህልና ወግ፤ ልማድና የህይወት ተመክሮ መብቀሉ፤ ቀለማም ውበቱ ዲካ የለሽ እንዲሆን አድርጎታል። ጋሼ ጸጋዬ ቀለም ነው – የማያልቅ። ጋሼ ጸጋዬ ጥበብ ነው የማይነፍስበት። ጋሼ ጸጋዬ ሰዋሰዋሰው ነው ያልተተበተበ። ጋሼ ጸጋዬ ሐረግ ነው – የሥርዐት፤ ጋሼ ጸጋዬ የእናት ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ፣ የዓለም የጥበብ አውደ ምህረት ነው – ክብር የሆነ ቅኔ ዘጉባኤ። የጋሼ ጸጋዬ አንዱ ነጠላ ሥራ … ቃናዊ ሀገር ነው። አንዱ ነጠላ ካራክተር የአንድ ትውልድን የኑሮ ዘይቤ ጌጣማ አድርጎ ያብራራል – ያወራርሳልም። አንዱ ዘለላ ንዑስ እርስ – የፊደል ገበታ ነው። ጥቅሉ ሲሰላ ለሺህ ዘመናት ማውጫ ነው። ጋሼ ጸጋዬ ሲተረጎም ሰንደቅዓላማችን ነው – ለሥርጉተና ሃሳቡን ለሚጋሩት።

የፋክት ውበት በብላቴ መንፈስ ይገለጻል …. ትንቢትም ቢሆን በሎሬት ህሊና ተለክቷል „ሰቆቃው ጴጥሮስ“ ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን – ከነገ አጋብቶ ይመሰክራል፣ ታሪክ ከትንሹ እሰከ በኽሩ የነፃነት ገድል በሃቅ ድባብ ተቀኝቶታል፤ ለመሆኑ አፍሪካን ነፃ ያወጣውን ገድል እንዴት ዘከረው … ንጉሡ ባለቅኔው። ከተቃኜው የማስተዋል ፍሬዎች ለማገናኛ ድልድይነት የተጠቀመበትን ብቻ በጥቂቱ ….

„ዋ አንቺ ዐድዋ ….“
„.. ዐድዋ የዘረ ዐፅም ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርዬት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት
ዓደዋ …
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያ ምስክርዋ
ዓድው“ (የካቲት 1964 ዓ.ም ዓድዋ)
ለእናት ሀገሩ ያለው ፍጹም ሊለካ የማይችል ፍቅርና ክብር ህይወቱን መሉ አንዲትም ሰከንድ ሳያስተጓጉል በታማኝነት አደግድጎ፤ በሎሌነት ፈቅዶ፤ እራሱን በቀጥታ ሰጥቶ አግልግሏታል። ከጋሼ ጸጋዬ የመንፈስ ማህጸን ውስጥ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ዘውዷን ደፍታ አለች። … ወደ ለንደን ጎራ ባላበት ጊዜ ፍቅሯ፣ ናፍቆቷና ስስቷ አላሰቀምጥ አላስቆም ሲለው፤ ፋታ ነስቶ ሲያስጨንቀው፤ መንፈሱን ሲያባትለው፣ ሲታገለው፤ ከውብ እቅፏ መራቁን አልችለው አለና ናፍቆቱን እያበባለ፣ ፍቅሯን እያደመጠ፣ ጸጋዋን ሲጨልጥ፤ የውስጡን የናፍቆት ዕንባ እዬለቀቀ ሰቀቀናዊ – ስስታዊ – ስሜታዊ ውስጡን በተመስጦ እዬተረጎመ …. ሁለመናዋን ጥልቅ በሆነ ፍጹም ሊገለጽ በማይችል የናፍቆት ረመጥ ላይ ሆኖ እንዲህ ይላታል እናቱን … በጥቂቱ … እናንተ ዝለቁት የማከብራችሁ።
ደህና ዋይ እማማ

„ …. እናት አለም የስሜ አርማ
የህይወቴ ወዝ የይኔ ማማ
እማትነፍጊ እማታቅማሚ
እማታሳጪ እማታሚ

እኔን በራበኝ በጠማኝ አብረሽኝ እምትጠሚ
ጥቃቴን እምትጠቂ ቁስሌን እምትታመሚ
ፍሰሃዬን፣ ፈገግታዬ ሳቄን ብቻ እምትፈልጊ
አንቺ እማማ
አንቺ የነፈሴ ልብ ዓልማ
የይኔ ማማ (ሎንደን 1953)

ረ/ፕሮፌሰር ብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የእናቱን – ውላታውንም በሚገባ የመለሰ ብርቅ ጠንቃቃ ልጇ በመሆኑ እሱን መሰል ልጅ ደግማ ለማግኘት እናት ኢትዮጵያ 200 ዓመት መጠብቅ ግድ ይላታል …. ። ለዛውም ከተሳካላት ብቻ። ሰቆቃው ጴጥሮስ ላይም ስለ እናቱ የቋጠረውን … መመልከት እንችላለን። በነገራችን ላይ …. ጋሼ ጸጋዬ
ትንቢት ራዕይ ይታዬው ነበር እንደ ንጉሥ ዳዊት ….. የሥነ ጥበብ ንጉሡ ብላቴ ጌታ ሰቆቃው ጴጥሮስ ሙሉውን ተመልከቱት። እርግጥ ነው ደራሲ ምስባክ ወርቁም „ዴርቶ ጋዳን“ የጸፉበት ጭብጥ ነው ረቂቅ ሥራ …. ከሰሞናቱም ከዚህ ረቂቃዊ ትንቢት ጋር የሚጋባ ከመጸሐፉ ታሪክ መነሻ መቼትና ልቦና ላይ የተነሳ የወርቅ እንክብል እያዬን ነው። መድህንና መድህን ሲገጣጠም – በትንቢት ሥነ -ግጥም። ምዕራፉን በግልብ ሳይሆን በማስተዋል ሆነን መንፈስ ቅዱስ እንዲገልጽልን ከልብ ጠይቀን እንመርምረው በአንክሮ – በተደሞ። ትናንት ገባ ሁዳዴ – የጸና መንፈሰ – ሱባኤ ….

„አዋጅ የምሥራች ብዬ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከናቴ ማኅጸን አርፌ
ካፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ …“ (1961 ቀበና?)
ሌላው አህጉራዊ ግንዛቤውና ፍቅሩ ሚዛንነቱን ያዘክራሉ፤ ብላቴው ተፈጥሮው የተሰበሰበ ህብርትን በሚዛንነት ይገልፃል። ዘልቆ ረጅም ተጎዞ ሚስጢራትን ይቀድማል። የወጣላት የመሆን ሻንፒዮን። ዩኒስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅቶት በነበረው የጥቁሮች ፌስቲባል ላይ ዳካር ሴኒጋል፤ የፓን አፍሪካ ፌስቲባል አልጀሪያ ላይ ተገኝቶ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከፍ ያለ ክብር አሰጥቷታል። የልቧናው ህሊና መጎናጻፊያው እናት ሀገሩ ዘንካቲት ኢትዮጵያ ናትና። የደም ዝውውሩ ሂደት ጤናማነት ጥበቃው ለእናቱ ከአለው ታማኝነትና ፍቅር መፍለቁን የተሰጠው ነውና አድርጎታል። ጥበቃው ማህሏ፣ ዳር ድንበሯ ትርፋማነቱን በማህበራዊነት አጋርቶናል። ዘብ የቆመላት ዘብ አደሯም ነበር። ቅጥር ደንበሯን አስጠባቂ። በዓይኗ ብቻ ትእዛዟን እዬተከተለ የሚከውን ንቁ አሥራቷ።

ረ/ፕሮፌሰር ብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ለእኔ ምዕተ ዐመት ነው። ፍጥረተ ነገሩ ለዬት ብሎ፤ ዘለግ ብሎ የተሰጠው ፍጹም እቅፍ ሙሉ ሽልማታችን ነው። ጋሼ ጸጋዬ የእርቅ ድልድይም ነው። ሳይሳሳ ውስጡን የሰጠ በመሆኑ እነሆ በውስጣችን ተደላድሎ መቀመጥ የቻለ የፍቅር ታላቅ ሐዋርያ ሀውልታችን ነው። ጋሼ ጸጋዬ የባህል፤ የታሪክ፤ የሥነ – ጹሑፍ፤ የተውኔት፤ የአስተዳደር፤ የቅኔ፤ የብቁ ዲፕሎማሲያዊ ጳጳስ፤ የገንቢ ትችት አፍላቂ – ዩንቨርስቲ ነው። ብላቴ እራሱኑ ሆኖ ኖሮ፤ እራሱን ሰጥቶ፤ ምንም ሳይቆጥብ ኢትዮጵያን በዘመናዊ የሥነ ጥበብ ዋልታ ብቁ እንድትሆን ብድግ ያደረገ የሰው ስው ነው። የተውኔት ጌታው ሰማያዊ ጥሪውን በተግባር ያሰበለ ትውልድ ከቶውንም ሊተካው የማይችል ዘረ – ቅኔ ነው። አዲስ የሥነ ጥበብ ትውልድን አምጦና አመሳጥሮ በመንፈስም በተግባርም የወለደ የዕውነት ዙፋን ነው። ጠረኑ የትውፊት ስንቅ ቅርስም ነው።

የቅኔው ልዑል አፍሪካን በኸረ የሥነ – ጥበብ ማዕከል እንድትሆን ያደረገ የተግባር አዝመራ ነው። የአፍሪካ የሥነ – ጥበብ ብሩክ ርትዑ አንደበት። ብላቴ ጌታ የቋንቋ ቃና ሥልጡን ፈላስፋና ተመራማሪ ነው። ነበር ማለት ይከብደኛል። ስለምን? የሥነ ጥበብ አድባር በጠራችን ቁጥር እሱ አለና። እንዲያውም ለእኔ ጋሼ ጸጋዬን እምተረጉመው እጅግ በበዙ ሙያዎች ብቃቱ ሙሉዑ የሆነው ጣሊያናዊ ታላቅ ሳይንቲስት ከሚዚያ 15. 1452 እስከ ግንቦት 2.1519 ለዘመኑ ሳይሆን ለ30ኛው ምዕተ -ዓመት ተፈጥሮ የነበረው ድንቅ ሊወናርዶ ዳንቤቺ ከሠራቸው ዕጹብ ሥራዎች ውስጥ አዳም ከመዳህኒታችን እዬሱስ ክርስቶስ መንፈሱን ሲቀበል ፍጹም በረቀቀ ሁኔታ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የቆረበበትን ጣታዊ ንክኪ ተግባሩን ሳስብ በዛ ውስጥ ለዬት ብለው ከተፈጠሩትን አንዱ የእኛው የቅኔው ልዑልን ጋሼ ጸጋዬን እንደሆነ ነው እማነበው።
ብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገመድህን የጥበብ ባለጸጋነቱን ከዚህ አንጻር ነው የማዬው። በዛ የመንፈስ ቅኝት ውስጥ፤ በዛ ርቁቅ ምርቃት ውስጥ ከኢትዮጵያ …. አንድ ብላቴና መመረጡን ሊወናርዶ ዳቤኔቺ አብስሮኛል። ቀድሞ የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ …. ጋሼ ጸጋዬን ሰጠን እላለሁ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ። ስለሆነም ነው ምርጦቹ በሥጋ ተለይተውን ልክ እንደ አሉ ሆነው የሚሰሙን። ነበር እያሉ መጻፍም የሚከብደው ለዚህ ነው። ለሰከንድ በመንፈሴ ውስጥ የኔው ሊቁ ሎሬት የአፍሪካ ቀንዲሉ ጋሼ ጸጋዬ ወጥቶ አያውቅም …. እኔ ስለ እሱ ቀናተኛ ነኝ። ንድፉ መንፈሴን በግልጽነትና በቅንነት ገርቶታል እና … ፍቅሩም ጥልቅ – ዝልቅ።

ጋሼ ጸጋዬ ኢትዮጵያዊነት ሚስጥር ስለመሆኑ ማንነትን በጥልቅ ምርምሩ የገለጸበት „እሳት ወይ አበባ“ መድብሉን አጠቃሎ አንብቦ ለተመረቀበት፤ ከውስጡ ላስቀመጠ ሆነ ድርሳኑ ላደረገ ሰብዕ ማንነቱን አውቆ እራሱን እንዲያከብር ፤ ማንነቱንም እንዲከበክብ – እንዲወደውም ያደርገዋል፤ ለአራት ዓይናማው ለሊቀ – ሊቃውንቱ ለብላቴ ጸጋዬ ገ/መድህን ኢትዮጵያ የፍጥረታት ጭማቂ ንጥር ርስት ስለመሆኗ በትጋት ሰብኳል፤ የአብነት መምህር ሆኖ በታታሪነት አስተምሯል፤

ገላጭ ሆኖ ዕውቅናዋን በዓለም ባባተሌነት መስክሯል አስውቧታል – በተግባሩ አድምቋታል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አህጉራዊ መዝመሩ ግጥሙ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አጀንዳ እንድትሆን አድርጓታል። ይህም ብቻ ሳይሆን በመዝሙሩ ቅመም ውስጥ የኢትዮጵያዊነት ሚስጥር ተቀምሞበታል። ተገደን ተቀበልን ለሚሉት መዳህኒቱ እሱ ነው። ታቦቱን ሲከበክባት፣ ሲያነግሥት – ሲያቀሳት – እጬጌነት ሲሾማት – ሲሸልማት – ማድመጥ ለተሰጣቸው መርምሮ ይገለጣል – ሥራዎቹ ያልባለቁ ደናግል ሃኪሞችም ናቸውና – ወደር የለሽ ፈውሶች።

ፈቅጃት ሳታዬኝ ዐመት ቋጠጣረች*(ዘመን ቆጠረች)
ስወዳት እራቀች ….
ስሳሳት ጨከነች
ሳልጠግባት ሾለከች
ስፈልጋት መጣች
ሳምጣት አጠባች
ስንቅም ቋጠጣረች*(መሃያ ሰፈረች፤ ቀለብ ሰፈረች)
በመንፈሴ ብሌን መሰረት ቸከለች።

እላለታለሁ እኔ የአባቴን የወርቅ ቀለጦ ጠብታቱን …. ለጥቄም – ለትጥቄ እንዲህ እላለሁ -

ናፍቆት አፍተልትሎ ሲወቃኝ ሲደቃኝ አንዲሁም ሲለካኝ
አንቆ ሲታገለኝ ትዝታ ሊውጠኝ ሊበላኝ እንዲህ ሲሟገተኝ
ጥልፋማ ብዕርህ በፅናቱ ቃኜኝ
በቃኝ አስተማረኝ፤
ትእግስት ኮለኮለኝ – ተስፋህም ቀለበኝ።

ረ/ፕሮፌሰር ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን „የእሾህ አክሊልን“ በ20ኛ ዐመቱ ቀጥሎ „በልግን“ „የደም እዝመራን“ ተውኔቶችን ለህዝብ በማሳዬት ለዘመኑ እጅግ የቀደሙ ሥራዎቹ ባለተሰጥዖነቱን ስለ አወጁ በ29 ዓመቱ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሽልማት በሥነ – ጹሑፍ ተሸልሟል። በተለያዩ አለምአቀፍ መድረኮችም ተወድሷል – ተሸልሟል። የጋሼ ጸጋዬ የሥራና የህይወት ተመክሮ ጥልቅ ከመሆን አልፎ ትጋቱና ጥንካሬውን እኛን እንድንታዘብ አዘውትሮ በትህትና ያስተምራል። ስለሆነም … በቅኔው ንጉሥ የባከነች አንዲትም ደቂቃ አልነበረችም። ዝቀሽ የሆነ ገቢራዊ ነበርና። ትንታግ! ስለሆነም ….

- ከ1957 1963 ዐ.ም በቀ.ኃ.ሥ ቲያትር አርቲስቲክ ዳሪክተርነት በ164 ዓ.ም የ ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ፕሬስ የአዲስ አበባ ቢሮ
- በ1964 – 1968 በባህልና ስፖርት እስክ ምክትል ሚኒስተርነት ማዕረግ አገልግሏል።
- በ1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩነቨርስቲ የትምህርት ክፈል በረዳት ፕ/ ማዕረግ የዩንቨርስቲው የቲያትር የትምህርት ክፍል በመመሥረት ዲያሪክተር በመሆን በአዲስ ግኝት ተውኔትን ተንከባክቦ ዘርቶ፣ አብቅሎ፣ አስብሏል።
- ከ1949 – 1969 አያሌ ተውኔቶችንና ሥነ ግጥሞችን በማያቋርጥ መክሊቱ በገፍ ያመረተው የቅኔው ንጉሥ ከዓለም ሥነ ጥበብ ሃብቶች የሚያድንቃቸውን ከሼክስፔር ሥራዎች እነኦቴሎን ሃምሌትን ወዘተ …. እና የሌሎችንም ወዳጆቹን ሥራዎች ወደ አማርኛ በመተርጎም የተዋጠለት የተግባር ጉልበታም ካስማ ጥሏል። እንግሊዘኛ ተውኔቶችን ግጥሞችን ጭምር በመድረስና ለመድረክ ዕውቅና በማብቃት ዓለም ዓቅፍ ድንቅነትንና ዕውቅናን አትርፏል። በብላቴ ጌታ ጸጋዬ ምግባራዊ እንቅስቃሴ ወስጥ ሁሉ ደግሞ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያና የክብሯ መግለጫ ሰንደቅዓላማዋ፤ የህዝቧ ቀለማም ሥነ – ተፈጥሮ ሁሉ የሥነ ጥበብ ታላቅ ብቁ ባለማዕረግ፣ ባለ ሙሉ ሥልጣን አንባሰደር ነበሩ ማለትም ይቻላል። ዕውደቱ ሁለገብና ትርፋማ ነውና።

ጋሼ ጸጋዬ በቀንበጥነት ዕድሜው፣ ከእሳት ውሃ በሚባልበት አፍላ የኩብልና ወቅቱ የሥነ -ጥበብን ሰማያዊ አደራዊ ጥሪን ተቀብሎ ኃላፊነቱን ለመወጣት ባገዙት ጉዞወቹ በ26 ዓመት ዕድሜው ወደ 30 ያህል ሀገሮችን እንደ ጎበኜ ባዮግራፊውን የጻፉት ሊቃናት ይገልጻሉ። በተጨማሪም በአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ባህልና ሥነ – ጥበባት ምርምሩ ፈላስማነቱንና ታሪክ ተማራማሪነቱ በአንድምታ ቀደምት ሊቃናት ይመሰክራሉ። ብላቴ ጌታ ሐዋርያው ሎሬት ጸጋዬ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር፤ የእፍሮ ኤሽያውያን ጸሐፊዎች ማህበር፤ የአፍሪካ አንድንት ድርጅት Think Tank Form አባል ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ ጸሐፊዎችና የአፍሪካ ተመራማሪዎች ማህበራት አባል በመሆን ሁለገብ ተሳትፎውን በብቃቱ ከሽኖ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ የፈካች – ብቁ – ተናፋቂ ማዕደኛ እንድትሆን አድርጓታል። አንባሳደርነቱም ከተለመደው በላይ የታሪካችን ባለፈርጥ ማህደር ነው።

የቅኔው ልዑል የዐለም ዐቅፍ ባለ ቅኔዎች ሎሬቶች ኅብረት አባል ስለነበር በዬአንዳንዱ ሥናዊ አጋጣሚ ሁሉ እናት ሀገሩን ኢትዮጵያንና ምክሊቱን ከፍ ለማደረግ ተጋድሎ እንደ ፈጸመ ይሳማሙበታል ዓራት ዓይናማዎቹ የኛዎቹ ሆኑ የውጭ ሀገር ሊቀ – ሊቃውንታት። … እንግሊዝ ሀገር ኪንግሻዬር የተከናወነው የዓለም ባለቅኔውችና ሎሬቶች ጉባኤ ላይ „ የዘመኑ ድንቅ ባለቅኔ ሲል የወርቅ አክሊል ሸልሞታል። ስለዚህ ኢትዮ – አፍሪካዊውን ብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንን ዓለምዓቀፍዊ የጥበብ ሰፊ ማሳ እንደ ዓይኑ ብሌን ይመለከተው የነበረ ታላቅ የብዕር ከዘመኑ በላይ የመጠቀ
ችሎታና ክህሎት የነበረው አርበኛ፣ የሥነ – ቋንቋ ሳይንቲሰት ስለነበር በአሜሪካን ሀገርም የላቀ ሽልማትን በክብር አግኝቷል። ሽልማቱ የማንነታችን አንጸባራቂ አሻራ ነው።

ድምቀት በተሰጥዖ
ፍቅር በተመስጦዖ
ታሪክ ደምቆ ዋለ
ጸጋዬ አዋዋለ
ጽናትን ሰንቆ ምጥን ገላገለ።
ረቂቅነቱ በዓለም ተናኘ
ከድንቅነሽ መንደር መላቅም ተገኘ።
አፍሪካ ደመቀች
ኢትዮጵያ ፈለቀች
መድህን ታሪክ ሰርቶ
ጥበብ ሁሉን ሰቶ
ሎሬትን መረቀ
ውስጥነን አጉልቶ።
ጧፉም – ለዘለአለም
የእምዬ ዓይንአለም።

የቅኔው ንጉሥ የተውኔት ልዑል ዝክረ ብቃቱ በሀገር ውስጥ ሆነ በልዩ ልዩ ዓለም ዐቀፍ መድረኮች የህይወት ታሪኩ ተተንትኗል፤ ለምርምር ተግባርም ውሏል – ለወደፊትም። ሲከወን – ባለቅኔ ሎሬዬት ብላቴን ጌታ ጸጋዬ ገ/መድህንን በተውኔት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ከጻፋቸው 41 ሥራዎች ውስጠ ከተረጎመውና በእንግሊዘኛም ከጻፋቸው ጭምር 12ቱ በሳንሱር ታግደዋል፣ 21 ተቆራርጠዋል፣ 3ቱ ግማሹ ለግማሽ ተሰርዞባታል፣ 4ቱ ድርሰቱን ሳንሱር እንደማይፈቅድለት አይሆኑ ሆኗል።

በሌላ በኩል ከሦስት የሥነ ግጥም መጸሐፍቶቹ ውስጥ 2ቱ ገና አልታተሙም፤ በአንዲት „ጆሮ ገድፍ፡ በምትባል ቲያትር ምክንያት በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ወቅት ለ24 ሰዓት በቁጥጥር ሥር ውሏል። በዬዘመኑ በነበሩ የሳንሱር ቢሮዎች በአማርኛ፤ በኦሮምኛ እንዲሁም በእንግሊዘኛ የጋሼ ጸጋዬ ሥራዎቹ ሁሉ ካለማዕቀብ ወጥተው ቢሆን ምን ሀገር ይበቃቸው ነበር?! በውስጣቸው ያያዟቸው ትንቢቶች፣ ትንግርቶች እንዴት ለመንፈስ ፍትኃትን በሰዬመ ነበር?! ባለመታደል አልቻለም እንደተከደኑ በሥጋ አለፈ …. … እጅግ አዝናለሁ። እሱን ያህል ታላቅ የሁለመና አባት ጸጋዬ
ፋውንዴሽን ሳይመሰረት፣ በሥሙ ትምህርት ቤት ወይንም ክሊንክ ወይንም ሙዚዬም ወይንም ዩንቨርስቲ ሳይገነባ ዘመናት አለፉ። ይህ ደምና መግል ማህጸንን የሚያስለቅስ ገመናችን ነው – ሁላችንም ልንጋራው የሚገባው ቁልጭ ያለም ድክመታችን።

የመንፈስ ሰብሎች እጅግ በርካታ ናቸው። ወላዊ ሥራ ወይንም ቲም ወርክ ልዩ መለያው የነበረው ጋሼ ጸጋዬ በግልና በጋራ የሠራቸው … „የዳኒሲዮስ ዳኝነት፤ በልግ፤ የደም አዝመራ፤ እኔምኮ ሰው፤ የእሹህ አክሊል፤ ክራር ሲከር፤ አስቀያሚ ልጃገረድ፤ እኔን ብዬ መጣሁ፤ ቴወድሮስ፤ ሚኒሊክ፤ ጵጥሮስ ያቺን ሰዓት፤ ዘርዓይ ደረስ፤ ጆሮ ደግፍ ገድፍ፤ ሀሁ በስድስት ወር፤ እናት ዓለም ጠኑ፤ መልእክተ ወዛደር፤ አቡጊዳ፤ ጋሞ፤ ሀሁ ወይም ፐፑ፤“
… የምጸት ኮሜዲ አልታዬም፤ ዐጽመ በዬገጹ – በወል ደግሞ ከሊቃናት ባልደረባዎቹ ጋር … „ጸጋዬ ገብረምድህንና ሃይማኖት ዓለሙ „ሰቆቃው ጵጥሮስ ትንሣኤ ሰንደቅ ዓለማ“ ጸጋዬና አባተ መኩሪያ „የመቅደላ ስንብት“ ጸጋዬና ተስፋዬ ገሰሰ „ጥላሁን ግዛው“ ጸጋዬና ገብረክረስቶስ ደስታ „ዐጽም ፈልጉ“ በርካቶቹ ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉመው አድናቆት አትርፈውለታል፤ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩትም ሳንሱርድ ያነቃቸው የሀቅ ጭብጦች ወደ ታዳሚዎቹ ሳይደርሱ ታዳፍነው በርካቶቹ ቀርተዋል። አንድ ትንሽዬ ተግባር ለመስራት ካራክተር መረጣው፤ ጭብጡን በማደላደል፤ ስሜቱን ወስዶ በማወራረስና በማዋህድ፤ መቼቱ፤ የመድረክ ቅንብሩ አመራሩ ቢሮክራሲው። እንዲሁም ምቀኛው ሸሩና ተንኮሎ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ ተውኔትን ፈጥሮ በሁለት እግሯ እንድትቆም አደረጋት ጀግናው። በሁሉም ለህዝብ ዕይታ ዕድል ባገኙት ሥራዎቹ ውስጥ እናት ሀገራችን ውቢት ኢትዮጵያ ዙፋን ላይ ሆና በካባ በተክሊል ተንቆጥቁጣ ትገኛለች። ታድሎ! ምርቃት አስታደለን። ተመርጦ! በፍቅር አስመረጠን። ተከብሮ! በማዕረግ አስከበረን።፡

ጋሼ ጸጋዬ በፈተና ታሽቶ አፍርቷል። በሳንሱር ቢሮ ግልምጫ – ገሳጼ – ዘለፋ – ዛቻ – ግልላ – ወቃሳ ባላበራ ሁኔታ ቢደርስበትም ፈተናዎችን ሁሉ በጽናት ረቶ ለዘለዓለም የማይጠፋ ብርኃንን ያበራ የትናት የዛሬ የነገም ጸሐያችን ነው። እኔ በግሌ እስከ ዕለተ ትንፋሽ እሰምታቆምበት ድረስ ስለ እሱ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ክብሬ – ኩራቴ፤ መጽናኛዬ – መሸሸጊያዬ ብዕሩ ሆነ ምስሉ እራሱ አድህኗዊ ነውና … ለእኔ። ሁለመናው ትውልድን በሰናይ የሚያይዙ ጥበብ ናቸው።
ተው ብለው አይሰማኝ
ልቤ እዬወሰደኝ
ዕንባ ስንቅ ሆኖ እንዲህ ሲፈትሸኝ
ስፈተግ በስደት ስታሽ በሰቀቀን …
አተረፈኝ አሱ ሁሌ ሕይወት ሆነኝ።
የቅኔው ንጉሥ እንደ ዛሬዋ ቀን የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም በ69 ዓመቱ አረፈ …… በሥጋ ተለዬን። መንፈሱ ግን ለፈቀድልነት እንሆ ይመራናል። መንገዳችንንም ያሳያናል። ሰውም ፈጥሯል የመጀመሪያዋ የተውኔት ጸሐፊና ብሄራዊ መሪ ለነገም የልቤ መሪ ድንቋን አርቲስት አለምጸሐይ ወዳጆን ያህል ታላቅ የሰው ሰው የሰጠነ እሱ ነው። አለምዬ ኧረ ተይ ተይ በሌሎች ዘርፍም ያፈራሻቸው አሉ። እባክሽን የተውኔት ልጆሽ ብቻ ሳይሆኑ እኛንም ከፈጠርሻቸው ልጆችሽ ዝርዝር አስገቢን። ሌሎችንም … በክህሎቱ ፈጥሯቸዋል፤ ቀርፆቸዋል … ገንብቷቸዋል። ያው እኔ ለሴቶች አዳላለሁ እንጂ

መሰናበቻ – ለመሰንበቻም – ብቻ ሳይሆን መዝለቂያም የወደድኩትን አገላላጽ ከመግቢያው ለቅምሻ ወስጄ ማሰረጊያውን ለጸሎተ ሥነ – ሕይወት መረጥኩት … እንሆ። ሙሉውን ደግሞ ከሊንኩ አስኪዱት – ክብሮቼ።
“Monday, May 15, 2006
እርሱ Ethiopian_Poet_Laureate_Tsegaye_Gabre-Medhin Honoring the Distinguished Ethiopian Poet Laureate Tsegaye“
መግቢያ በሩ የጸሐፊው „… Mr. CUMMINGS. Mr. Speaker, I rise today to honor the life and work of Ethiopian Poet Laureate Tsegaye Gabre-Medhin who passed away on February 25, 2006 at the age of 69 in his New York home.
Mr. Tsegaye Gabre-Medhin left behind a legacy of poetry and literary works that continue to inspire generations”.
እርገቱ …. የጸሐፊው ደግሞ እንዲህ ይላል …. ለሁልጊዜም የመንፈስ ማህተም።
“Through his literature, Tsegaye’s pride in Ethiopia and love for Africa will live with us forever. by Elijah Eugene Cummings“

ምንጭ …

 የምዕተ ዓመቱ የሥነ ጹሑፍ ምርት 2000 ዓ.ም
http://en.wikipedia.org/wiki/Tsegaye_Gabre-Medhin
Ethiopian Register Vol. no 9, September 1999 „Conversation with Poet Laurete Tsegaye Gebere Medehen“ by Elizabeth W. Giyorgis በጸሐፊ ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ ጥልቅና የሰከኑ ትንተናዎች ወስጥ ሃሳቦችና ፎቶዎችን ተውሻለሁ። ለዚህም ነው ከመጽሄት ላይ ፎቶውን ስለወሰድኩት የጥራቱ ጉዳይ እንደፈለኩት ያልወጣልኝ።
http://www.ethiopians.com/tsegaye/ by Professor Negussay Ayele ሥራዎቹን ከሥነ – ተፈጥሮው ጋር ሙሁራዊ ህይወት ያለው ነፍስ ትንተና ….
http://en.wikisource.org/wiki/Honoring_the_Distinguished_Ethiopian_Poet_Laureate_Tsegaye_Gabre-Medhin Honoring the Distinguished Ethiopian Poet Laureate Tsegaye Gabre-Medhin by Elijah Eugene Cummings

ዛሬ ማክሰኞ ነው። ሃሙስ መደበኛ የጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራም አለኝ። ልዩ ዝግጅት ይኖረኛል። እንደ ኤ.አ.አ 27.02.2014 ሰዓት ከ15.00 – 16.00 የቻላችሁ ላይፍ ላይ ማድመጥ ትችላላችሁ። ካልሆነም በማግስቱ አርኬቡ ላይ ማዳመጥ ይችላል። www.lora.ch.tsegaye

ድህረ ገፁንም ጎራ እያላችሁ በቋሚነት በቴክስትና በአውዲዮ የተሰሩባቸውን እነ – ማዕዶትን ስለ ድርጅት ጽንሰ ሃሳብ እንዲሁም ሌሎችን መምሪያዎች ኮምኩሙ። www.tsegaye.ethio.info ለአጠቃላይ መረጃ ደግሞ …
http://ethio.info/tsegaye/Part1LaureateTsegayeWebsiteBigarLfinal.doc በድምጽም በቴክስትም።

በጀግኖቻችን በሐሤት እንኮራለን!
እናት ሀገራችን ኢትዮጵያንና ልጆቿን አምላካችን ይጠብቅልን። አሜን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>