ኤዲን ሃዛርድ ኳሷን የግሉ አደረጋት፡፡ የቡድን ጓደኞቹም በላይዋ ላይ ፊርማቸውን አኖሩ፡፡ በኒውካስል ዩናይትድ ላይ ላስቆጠረው ሃትሪክ ማስታወሻ ትሆነዋለች፡፡ በመጀመሪያው ግማሽ ስምንት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለቱን ጎሎች ካገባ በኋላ የሃትሪክ ምኞቱ እንዲሳካ የፍራንክ ላምፓርድ ተባባሪነት አስፈላጊው ነበር፡፡ እንግሊዛዊው ፍፁም ቅጣት ምቱን አሳልፎ ባይሰጠው ኖሮ ቤልጅየማዊው ኳሷን ለመውሰድ ባልበቃ ነበር፡፡ ላምፓርድን አመስግኖ ወደ መኖሪያ ቤቱ አመራ፡፡
ሃዛርድ በቤቱ አልጋ ላይ ተንጋሎ ከቼልሲ ጋር ፕሪሚየር ሊጉን በሻምፒዮንነት ስለመደምደም ያልማል፡፡ ይህንኑ ምኞቱን ለቼልሲ ኦፊሴላዊ ቴሌቪዥን ተናግሯል፡፡ ‹‹በሊጉ ሠንጠረዥ አናት ላይ ተቀምጠናል፡፡ ወደ አልጋዬ ስሄድ ሻምፒዮንነትን አስባለሁ፡፡ የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ምኞቴ እውን ይሆናል ብዬ ተስፋ አለኝ›› በማለት በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ከፍተኛ ፉክክር የታየበትን የውድድር ዘመን በሰማያዊዎቹ የበላይነት እንዲጠናቀቅ ያለውን ህልም ይገልፃል፡፡
ለቼልሲ ሃዛርድ የጨዋታ ውበትን ያላብሳል፡፡ በሁለት እግሩ የሚጫወት፣ ሚዛኑን የጠበቀና የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጀመር እይታን የታደለ ወጣት ነው፡፡ በማንችስተር ሲቲን በገዛ ሜዳው ባሸነፉበት ምሽት ሃዛርድ የጨዋታው ኮከብ ነበር፡፡ ለሲቲ ተከላካዮች አልጨበጥ ብሎ ለተደጋጋሚ ስጋት ሲዳርጋቸው አምሽቷል፡፡
በዕለቱ የቼልሲ የማጥቃት ቅመም ሃዛርድ ነበር ካልን የቤልጅየም ተጨዋች ተልዕኮ አመቺ የኋላ ደጀን በመሆን ጀርባውን ሲጠብቅ የነበረው ኔማኒያ ማቲች ነበር፡፡ በጨዋታው የማቲችን ያህል ሰፊ ርቀት የሸፈነ ተጫዋች በሜዳው ላይ አልነበረም፡፡ 12.6 ኪሎ ሜትር ባካለለው ብርታቱ የቼልሲን የመሀል ሜዳ ከሲቲ ጥቃት ሲከላከልና ኳስን ሲቀበል እና ሲሰጥ አምሽቷል፡፡ ሃዛርድ 1.72 ብቻ የሚረዝምና ለመሬት ቅርብ የሆነ ተክለሰውነቱ የባላጋራ ተከላካዮችን ሚዛን እያሳጣ ለማለፍ ያስችለዋል፡፡ ማቲች ደግሞ 1.94 ሜትር የሚለካውን ግዙፍ አካሉ የቼልሲ መሀል ሜዳ ጉልበትና የአየር ላይ ደጀን እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ የማያቋርጥ ታጋይነቱን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ከ12 ኪሎ ሜትር የላቀ ርቀት በመሸፈን አረጋግጧል፡፡ ቁመቱ እንደ ያያ ቱሬ ፍጥነቱን አልገታውም፡፡ በሜዳው ዙሪያ ፈጣንነቱን አረጋግጧል፡፡ ጠንካራ ሸርተቴዎችን የሚወርድ ተጨዋች ቢሆንም ኳስን በእግሩ ስር ሲቆጣጠርም ምቾት ይሰማዋል፡፡ በተክለሰውነት፣ በአካል ብቃትና በቴክኒክ ተሰጥኦ የታደለውን ተጨዋች ጆዜ ሞውሪንሆ ወደ ቼልሲ ሲያስመጡት የተከፈለበት 21 ሚሊዮን ፓውንድ የጥርጣሬ ጥያቄዎችን አስከትሎባቸው ነበር፡፡ ቆፍጣናው ፖርቹጋላዊ አሁን ስለመሳሳታቸው የሚናገር እንዳይኖር አድርገዋል፡፡ የማቲች አገልግሎት ለተከፈለበት ገንዘብ ትክክለኛ ምላሽ መሆኑን የቼልሲ ደጋፊዎችም መስክረዋል፡፡ ቼልሲ ሁሉን ያሟላ ዘመናዊ አማካይ አግኝቷል፡፡
ሞውሪንሆ በማቲችና ሃዛርድ የወቅቱ ብቃት ፍፁም ደስተኛ ናቸው፡፡ ሃዛርድ ከፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ተጨዋቾች አንዱ ስለመሆኑ እየተነገረ ባለበት ሰዓት ጆዜ ግን ለአድናቆታቸው ንፅፅራቸውን ከእንግሊዝ ይልቅ በዓለም ደረጃ አሳድገውታል፡፡ ‹‹በዚህ ሰዓት ከሁሉም ወጣት ከዋክብት ተጨዋቾች ሁሉ ምርጡ ይመስለኛል፡፡ ከግዙፎቹ ጋር ላነፃፅረው አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ትልልቆቹ ተጨዋቾች የ10 ዓመታት ዋንጫዎችን የማሸነፍ እና ጎሎችን የማስቆጠር ታሪክ አላቸው፡፡ ስለዚህ ትልልቆቹንና ይህንን ልጅ በአንድ ሚዛን መመዘን አይገባም፡፡ እንደ ወጣት ተጫዋች ግን ከእርሱ የተሻለ መኖሩ አይታየኝም፡፡ ኔይማር ድንቅ ተጨዋች ቢሆንም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ብቃቱ እየዋዠቀ ይገኛል፡፡ ይጎዳል፣ ይጫወታል፣ ይጎዳል፣ አይጫወትም…›› በማለት ሞውሪንሆ ለሃዛርድ ያላቸውን አድናቆት ገልፀውለታል፡፡
የቀድሞው የቤልጅየም ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዠርዥ ሊከንስ በበኩላቸው ሃዛርድ ከፕሪሚየር ሊጉም አልፎ በብራዚል የዓለም ዋንጫ ከክሪስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሲ ጥላ ውስጥ በኮከብነት ብቅ እንደሚል ተንብየዋል፡፡ ባለፈው ነሐሴ ሞውሪንሆ ተጫዋቹን ከወጣት ባለተሰጥኦነት ወደ ትልቅ ተጫዋች እንዲያድግ ምክር ለግሰውት ነበርር፡ በመላው 90 ደቂቃው በመከላከል ስራ ላይ እንዲሳተፍና ኳስም በእግሩ ስትገባም እንዳይሰስትበት ጥሪ አስተላልፈውለት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከማንችስተር ሲቲ እና ከኒውካስል ጋር ሲጫወቱ ለጆዜ ጥሪ ትክክለኛውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
‹‹በሊል ሳለ ሃዛርድ የችሎታውን 70%-80% እየተጫወተ በፈረንሳይ ምርጡ ተጨዋች ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከችሎታው 100% በማበርከት ላይ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ልምምዱን በቀላሉ የመመልከት ጥፋተኛነት ይሰነዘርበት ነበር፡፡ አሁን ግን በልምምድ ሰዓት ብዙ ይለፋል፡፡ ጆዜም የአድናቆት ደረጃቸውን ከፍ አድርገውለታል›› በማለት ሊከንስ ስለሀገራቸው ኢንተርናሽናል ተጨዋች መጎልበት ያስረዳሉ፡፡ ሸርተቴዎችንም እንዲወርድ ይጠብቁበታል፡፡
በታክቲካዊም መስክ የሃዛርድ ጥቅም ይለያል፡፡ ቼልሲ ከሳሙኤል ኤቶ በስተጀርባ ሶስት የማጥቃት ባህሪይ ያላቸውን አማካዮችን ያሰልፋል፡፡ ሃዛርድ ወደ ጎን እየገባ ለጎል ከመምታቱም በተጨማሪ ከዊልያንና አስካር ጋር በነፃነት ቦታ እየተቀያየረ ይጫወታል፡፡ ከኒውካስል ጋር ኳስ ባገኘ ቁጥር የተጋጣሚ ተለካካዮች ላይ አደጋ ይፈጥር ነበር፡፡ በዚሁ እንቅስቃሴ ወደ ቀኝ ሲወጣ ክሮሶችን ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ይጥላል፡፡ በመሀል ሲገኝ ደግሞ ለፈጠራው የሚያመች ክፍተት ያገኛል፡፡
ማቲች ከጥቂት ዓመታት በፊት በቼልሲ ስለተጫወተ ለፕሪሚየር ሊጉ አዲስ አይደለም፡፡ ሊጉን ፈጥኖ ለመልመዱም ምክንያቱ ይኸው ሊሆን ይችላል፡፡
በኤፍ.ኤ ካፕ ከስቶክ ጋርማቲች እንደ አስፈላጊነቱ ወደ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች እየተመለሰ የፒተር ክራውችን እንቅስቃሴ ተቆጣጥሯል፡፡ በተለይ በአየር ላይ የነበረው ብቃት ረጅሙን አጥቂ ፍሬ ቢስ ለማድረግ አመቺ ነበር፡፡ ማንቸስተር ሲቲን ሲገጥሙ ደግሞ ዴቪድ ሲልቫን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ አስደናቂ የመከላከል አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ከኒውካስል ጋር አማካይ ክፍሉን እንደልቡ ሲዟዟርበትና ሲሶኮን በአካላዊ እንቅስቃሴ ይጋፈጠው እንደነበር ታይቷል፡፡ መካከለኛና ረጃጅም ኳሶችንም በአስፈላጊው ሰዓት እየሰጠ ተመልካቹን አስደምሟል፡፡ በዚህም ምክንያት በቼልሲ አማካይ ግራ ወገን በመጫወት ያለፉትን 10 ዓመታት ያሳለፈው ላምፓርድ ለግራ እግሩ ማቲች የኳስ ስርጭት ቦታ ለመልቀቅ ሲል ወደ ቀኝ አማካይነት ተቀይሯል፡፡ ሰርቢያዊው ኳስ በእግሩ ስር ስትገባ ወደ ፊት በመጠጋት በሚደነቅ ሁኔታ ተንቀሳቅሷል፡፡ ሳይታሰብ በማጥቃት ለሃዛርድ የመጀመሪያ ጎል መነሻ ምክንያት ሆኗል፡፡ ቼልሲ ይህን ብቃት ከጆን ኦቢ ሚኬል አያገኘውም፡፡ ማቲች ግን በሶስት አይነት የአማካይ ክፍል ጨዋታ ይልቃል፡፡ ኳስን በመንጠቅ፣ በሰፊ ቀጠና ውስጥ በመንቀሳቀስ እና በአስፈላጊ ርቀት ኳሶችን በማቀበል ተክኗል፡፡ የቼልሲ የዋንጫ ጉዞም በሃዛርድና ማቲች አስደናቂ ብቃት ተጠናክሯል፡፡