ጋዜጣዊ መግለጫ
የካቲት 4፣ 2006
ከጅምራቸው ሕወሃትና በዙሪያው ያሰባሰባቸው ተለጣፊ የዘር ድርጅቶች ሥልጣንን ለመቆጣጠር ሆን ብለው ይዘው የተነሱትና ያካሄዱት የዘር ፖለቲካ መሠረት ያደረገው ‘የአማራውን’ ሕዝብ የሚወነጅል፣ የሚያጥላላና የሚያንቋሽሽ ብሎም ለጥፋት የሚዳርግ እንደሆነ የሚየሳዩ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። ይህንንም ዓላማቸውን ለማስፈፅም ከተጠቀሙበት መንገድ ዋናው የዚህን ሕብረተሰብ መሪዎችና የቅርስ ማዕከሎች ሚናና አስተዋፅዖ የሚያንኳስሱና የሚያዋርዱ የፈጠራ ታሪኮችና ወሬዎችን መፈብረክና ማሰራጨትን ያጠቃልላል።
በቅርቡ ያለፉት መለስ ዜናዊና ጓደኞቻቸው ከሰላሳ ዓመታት በላይ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ‘የአማራውን’ ሥም አጥፍተዋል፣ ጥላሸት ቀብተዋል፣ የሚያዋርዱና የሚያጥላሉ አባባሎችን ተጠቀመዋል፤ ለተለያዩ ዘውግ ልሂቃኖችም ‘አማራዎችን’ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬአቸው፣ መሬታቸው፣ ንብረታቸውና ቤታቸው እንዲያፈናቅሉ የሚያነሳሱና የሚገፋፉ መልክቶችን ሲያስተጋቡ ቆይተዋል። በቀደሙት ብዙ ዓመታት የሕወሃት/ኢህአዴግ መሪዎች ‘የአማራውን’ ሕዝብ በማፈናቀልና ለይቶ በማጥቃት የተፈፀመውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፤ ከአካባቢና ከክልል ጉዳይ ጋር ብቻ የሚያያዝ በማስመሰል ራሳቸውን ከሃላፊናትና ከተጠያቂነት ነፃ ለማውጣት ሲሞክሩ ቆይተዋል።
በቅርቡ ‘በአማራው’ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት በአቶ አለሙ መኮንን የተሰነዘረውን ለሰሚው የሚከብድ ሕዝቡን የሚያንቋሽሽ ቅጥ ያጣ ውንጀላና ዘለፋን ሽንጎው በጥብቅ ያወግዛል።በዚህ ድርጊቱም ያሳየው ለሕዝቡ ያለው ዝቅተኛ አስተያየትና ለሰብዓዊ ክብሩም ያለው ጥላቻና ንቀት በማንኛውም መለኪያ ከወንጀለኛ ሰው የማይተናነስ እንደሆነ ነው፤ የዚህ አይነቱ ተጋባር በማንም ይቅር ሊባልም ሆነ ሊረሳ የማይችል ነው። ይህ የዝቅተኛነት ስሜት የተጸናወተው ግለሰብ ቀድሞ በሕወሃት መሪዎች በተጠነሰሰው አስቀያሚና አፀያፊ የታሪክ ተውኔት የወቅቱ ተዋናይ የመሆን ዕድልን አግኝቷል።
በእኛ ዕምነት እንደዚህ ያለ መዘላበድ ሃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎች እንደ ዘር ማጥፋት ላሉ ያልታሰቡ እልቂቶች እንዲያመሩ አስተዋፅዖ ሊያደርግ የሚችል አደገኛ ተግባር በመሆኑ፤በሁሉም የሲቪክና የፖለቲካ ቡድኖች፤ በታወቁ ግለሰቦችና፤ በሃይማኖት መሪዎች ሊወገዝ የሚገባው ነው እንላለን።
ሸንጎው ለዚህ አሁን ለደረስንበት እጅግ አሳፋሪ ሁኔታና ጥፋት ሁሉ በዋነኛነት ተጠያቂ መሆን ያለበትና ሃላፊነቱን መውሰድ የሚገባው የሕወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነው ብሎ ያምናል። ይህ ዓይነቱ ድርጊት እንዲፈጠርና እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው በጥቂት ዘረኝነት በተጠናወታቸው ግበሰቦችና ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ካልተወገደ በቀር ተመሳሳይ ሁኔታዎች መቀጠላቸው አያጠራጥርም።
በመጨረሻም በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማሕበራት በመሐከላቸው ያለውን አነስተኛ ልዩነቶች በማቻቻል፤ ጠንካራና ሠፊ የጋራ ትብብር በመፍጠር ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በመከፋፈልና በማጋጨት ስልጣኑን በማራዘም የተካነውን አሰከፊ አምባገነን አገዛዝ፤ ለማስወገድና በምትኩም አንድነቷ በተከበረ ኢትዮጵያ ስር ሁሉንም እኩል የሚያሳትፍ ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ሥርዓት ለመገንባት ባንድ ላይ እንዲሰሩ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም በእውነተኛ ልጆቿ ሃይል ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!