የህብር ሬድዮ 4ተኛ ዓመቱን በሕዝባዊ ውይይት የተለያዩ ምሁራንን ጋብዞ በላስ ቬጋስ ከተማ ፌብሩዋሪ 26 ቀን 2014 በከተማዋ በጎልድ ኮስት ካዚኖ ያከብራል።
በዕለቱ እውቁ የኢኮኖሚስት ባለሙያ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ በጥናት ላይ የተደገፈ በልማት ስም ግርዶሽ በሚል ርዕስ ገለጻ የሚያደርጉ ሲሆን ኦባማ ኬር ሬዲዮው በዚህ ዓመት በስፋት ሲዘግብባቸው ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ ሁለተኛ ዙር ምዝገባው ከሚጠናቀቅበት ማርች 31/2014 በፊት በዚህ በዓል ላይ ዶ/ር ኤፍሬም መኮንን እና አቶ ተካ ከለለን ከአትላንታ ገለጻ እንዲሰጡ ጋብዟል። በዕለቱ ለውይይት የሚቀርቡትን ጉዳዮች በተመለከተ በዶ/ር አክሎግ ቢራራና በዶ/ር ኤፍሬም መኮንን በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች እና በኔቫዳ ግዛት የኦባማ ኬርን በተመለከተ የተዘጋጀውን መግለጫ ለተሳታፊዎች መዘጋጀቱን የበዓሉ አስተባባሪዎች ለዘሐበሻ ገልጸዋል።
ህብር ሬዲዮ በተለያዩ አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ወቅታዊ መረጃዎችን ከማቅረብ አልፎ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ እንግዶችን በመጋበዝ በቀጥታ በሬዲዮ፣ በኢንተርኔት እና በስልክ በተጨማሪ ሰፊ ተነባቢነት ባለው በዘሐበሻ ድህረ ገጽ አማካኝነት በየሳምንቱ ይደመጣል።