ሳይነስ ቁስል ከፊት ጀርባ የሚገኙት በአየር የተሞሉት ቀዳዳዎች (sinuses) መቁሰል (inflammation) ነው፡፡ ይኽ ቁስል በአብዛኛው በራሱ ጊዜ የሚድን ሲሆን በአፍንጫ እና በአይን ዙሪያ ህመምን ያስከትላል፡፡ ከፊትህ ጀርባ በአፍንጫ ቀዳዳ ዙሪያ አራት ጥንድ የሆኑ ቀዳዳዎች(sinuse) ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ቀዳዳዎች ንፍጥ (mucus) በሚያመርቱ ህዋሳት የተሸፈኑ ሲሆን ይህም ንፍጥ በትንንሽ ፀጉሮች ተገፍቶ ወደአፍንጫ ይገባል፡፡እነዚህ ቀዳዳዎች ከአፍንጫ ጋር የሚገናኙበት ትንንሽ በሮች አላቸው፡፡ እነዚህም አየር፣ ፈሳሽ እና ንፍጥ እንደፈለገው እንዲሄድ ይረዳሉ፡፡ ቀዳዳዎቹ ውስጥ የሚመረተው ንፍጥ በጤናማ ጊዜ ቀዳዳዎቹ ውስጥ አይጠራቀምም፡፡ ነገር ግን ቀዳዳዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ከተዘጉ አሊያም የትንንሽ ፀጉሮቹ እንቅስቃሴ ከተገታ ፈሳሹ በመጠራቀም የሳይነስ በሽታ ምልክቶች እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ጉንፋን ሲይዝህ ቀዳዳዎቹን የሚሸፈነው የላይኛው ክፍል በማበጥ ከአፍንጫ ጋር የሚያገናኛቸውን በሮች ይደፍናቸዋል፡፡ስለዚህም ቀዳዳው ውስጥ የሚመረተው ንፍጥና ፈሳሽ እዛው ውስጥ ይጠራቀማል፡፡ይኼ የተጠራቀመ ፈሳሽ ለጀርሞች ምቹ መራቢያ ቦታን ይፈጥራል፡፡ ሁለት አይነት የሳይነስ ቁስል አይነቶች ሲኖሩ እነሱንም በሚኖራቸው የጊዜ ቆይታ እንከፍላቸዋለን፡፡ ከሁለት ሳምንት በላይ የሚቆየው አይነት ሳይነስ መቁሰል በአብዛኛው በቀላል ህክምና የሚድን ሲሆን ሌላኛው አይነት ደግሞ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ እና በተለያዩ መድሃኒቶች በቀላሉ የማይድን ሲሆን አስቸጋሪ በሽታ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች በተለየ በዚህ በሽታ በተደጋጋሚ ይጠቃሉ፡፡ በተፈጥሮ ለብዙ ነገሮች አለርጂክ የመሆን ባህሪ ካላቸው የሳይነስ ቁስል በተደጋጋሚ ያጠቃቸዋል፡፡ እንደአስም በሽታ ሁሉ ለአበባ ብናኝ፣ ለአዋራ እና ለመሳሰሉት ነገሮች አለርጂክ መሆን በነዚህ ሰዎች ላይ የሳይነስ መቁሰልን ሲያስከትል ከሱ በተጨማሪ ደግሞ በአለርጂ ምከንያት በቀዳዳዎቹ ውስጥ የሚጠራቀመው ፈሳሽ ውስጥ ጀርሞች በመራባት በሽታውን የበለጠ ያጎሉታል፡፡ ስለዚህም በተደጋጋሚ በዚህ በሽታ ይጠቃሉ፡፡
የሳይነስ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
በሽታው የሚከሰተው ሳይነስ ቀዳዳዎች ሲደፈኑ አሊያም ትንንሾቹ ፀጉሮች እንቅስቃሴን የሚያግድ ነገር ሲከሰት ነው፡፡ ኢንፌክሽን ወይም ኢንፌክሽን ያልሆኑ መንስኤዎች ሲኖሩት በአብዛኛው የላይኛው የመተንፈሻ አካላት በሽታን ተከትሎ ይከሰታል፡፡
ኢንፌክሽን ካልሆኑት መንስኤዎች መካከል አለርጂ፣ የማቁሰል ብቃት ላላቸው ኬሚካሎች ተጋላጭ መሆን፣ አፍንጫ ላይ የሚበቅሉ የተለያዩ እንግዳ ነገሮች፣ ካንሰር ሊያመጡት ይችላሉ፡፡ እንደ አስም ሁሉ ለተለያዩ ነገሮች አለርጂ መሆንን ተከትሎ የሚመጣው አይነት የሳይነስ ቁስል ወቅትን ተከትሎ የመባባስ አዝማሚያ አለው፡፡ በአስም በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ይኼኛው በሽታም ያጠቃቸዋል፡፡
በኢንፌክሽን የሚመጣው በባክቴሪያ፣ በቫይረስ አሊያም በፈንገስ ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡ በቫይረስ የሚመጣው በሽታ በጣም በብዛት የሚታየው እና በራሱ የመዳን ባህሪ ያለው ነው፡፡ ከጥርስ ኢንፌክሽን ተነሰተው ወደቀዳዳዎቹ በመግባት የሳይነስ ቁስል የሚያመጡ ባክቴሪያዎች አሉ፡፡ ፈንገስ ደግሞ መጀመሪያውኑ የበሽታ የመከላከል አቅሙ በተዳከመ ሰው ላይ ለምሳሌ ለካንሰር በሽታ መድሃኒት (ኬሞቴራፒ) ላይ ያለ ሰው ላይ ይከሰታል፡፡ ይህም ከቀላል ሳይነስ ይልቅ ለህይወት የሚያሰጋ ኢንፌክሽን ያመጣል፡፡
የሳይነስ ቁስል ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የሳይነስ መቁሰል በብዛት ከላይኛው የመተንፈሻ አካላቶች በሽታ ጋር ተያይዞ ስለሚከሰት ምልክቶቹን ለብቻው ለይቶ ለማወቅ ይከብዳል፡፡ ጉንፋን የያዘው ሰው የሳይነስ ቀዳዳዎች ቁስለትም አብሮት መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡
የሳይነስ በሽታ አፍንጫ በፈሳሽ መታፈን፣ የፊት ህመም፣ እራስ ምታት ይኖረዋል፡፡ የሚኖረው ህመም ጎንበስ ሲባል ወይም በጀርባ ሲተኛ የመባስ ባህሪ አለው፡፡ ወፍራም፣ ቢጫ ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ ካለ የባክቴሪያ መንስኤነትን ያመላክታል፣ ነገር ግን በቫይረስ በሚመጣው ጉንፋን መጀመሪያ አካባቢም የዚህ አይነት የአፍንጫ ፈሳሽ ሊያስከትል ስለሚችል ለባክቴሪያ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሌሎች ምልክቶች ለምሳሌ ማስነጠስ፣ ሳል እና ትኩሳትን የመሳሰሉ ምልክቶችም ሊኖሩት ይችላል፡፡ የጥርስ ህመም እና የአፍ ሽታም በባክቴሪያ ከሚመጣው ሳይነስ ጋር ተያያዥነት አላቸው፡፡ አይን እንቅስቃሴን ተከትሎ የሚኖር ህመም ይኖራቸዋል፡፡ የማሽተት አቅምህም ከበፊቱ ሊቀንስ አሊያም እስከነጭራሹ ሊጠፋ ይችላል፡፡ በአለርጂ የሚመጣው በሽታ ደግሞ ወቅትን እየተከተለ ይነሳብሃል፡፡ በክረምት እና በፀደይ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሊያስቸግርህም ይችላል፡፡
የሳይነስ በሽታ ከያዘኝ በኋላ ምን ላድርግ ?
በሽታው በብዛት በራሱ የሚድን ሲሆን የተዘጋውን ሳይነስን እና አፍንጫን የሚያገናኘውን በር መክፈት ጥሩ የህክምናው መንገድ ነው፡፡ ውሃ አሙቆ እንፋሎቱን መታጠን ውስጥ የተጠራቀመውን ንፍጥ ስለሚያቀጥን ፈሳሹን በቀላሉ ማስወጣት ትችላለህ፡፡ ንፁህ (ተፈልቶ የቀዘዘ ) ውሃ ቀጭን አፍ ባለው እቃ አድርጎ የአፍንጫን የውስጥ ክፍል ማጠብ ጥሩ መንገድም ነው፡፡ ብዙ ፈሳሽ መጠጣትም እንመከራለን፡፡ ከሳምንት ለበለጠ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ አሊያም በጣም ሀይለኛ ህመም ካለው ወደሆስፒታል ሄዶ መታየቱ ተመራጭ ነው፡፡ በጀርሞች የሚመጣው በቀላል መድሃኒቶች ስለሚድን ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ካሉብሽ ወደሆስፒታል ሄደሽ መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡ ከሱ በተጨማሪም በአለርጂ ምክንያት የሚመጣው ቁስለት ከሆነ በሽታውን ከሚያባብስብሽ ነገር እራስሽን መጠበቅ ጠቃሚ ነው፡፡
የሳይነስ ቁስለት አንዴ ከያዘሽ በኋላ ህመሙን በተለያዩ መንገዶች መቀነስም ትችያለሽ፡፡ የሙቀት እና ቅዝቅዜ መለዋወጥ ህመሙን ስለሚያብሰው በተቻለሽ አቅም በጣም ሞቃት እና ቀዝቃዛ ቦታዎች ላይ አትሁኚ፡፡
ከጉንፋን ጋር ተያያይዞ በሳይነስ በሽታ በተደጋጋሚ የምትጠቂ ከሆነ ደግሞ በምትተኚበት ጊዜ ጭንቅላትሽን ከፍ የሚያደርግ ትራስ ማድረግ የሳይነስ በሮች እንዳይዘጉ በማድረግ ሊረዳሽ ይችላል፡፡