Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የማለዳ ወግ …በጅዳ አለም የኢትዮጵያውያን አቀፍ ት/ቤት ከትምህርት ጥራት እስከ ባለሙያው ፈተና

$
0
0

ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ አረቢያ
Saudi arabia ethiopian school
ባሳለፍነው ሃሙስ የወላጅ መምህራን ስብሰባ ላይ ስለጅዳው አለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ትምህርት ቤት አስተዳደር ፍትሃዊነት የቅጥር ሂደት እና በትምህርት ጥራቱ ዙሪያ ላይ አንድ በኢኮኖሚክስ ትምህት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀ ወጣት የሰላ ሂስ አቀረበ። በቀረበው የወጣቱ የዩኒቨርስቲ መምህር ስደተኛ ስራ ፈላጊ አስተያየት ድጋፍና ተቃውሞ ቤቱን በየተራ ናጠው ። በትምህት ጥራት አለመኖር የሚስማማው ወላጅ በጭብጨባ ድጋፉን ሲገልጽ የትምህርት ጥራቱን አንድ ከኢትዮጵያ ትምህርት ቤት የ12 ኛ ክፍል ተማሪ ጋር በእንግሊዝኛ ትምህርት እውቀታቸው የኤርትራ ኢንባሲ የ7ኛ ክፍል ተማሪ እንደሚልቅ በንጽጽር ማቅረቡ የተከፉ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ፖርቲ አባላትና ደጋፊዎች ውግዘት አስከተለበት ። አንዲት የወላጅ መምህራን ህብረቱ አባል ለትምህርት ጥራቱ ንጽጽር “ኤርትራ” የምትባለውን ሃገር ከአፉ ያወጣውን ወጣት ምሁር በአደባባይ ወጥተው ወረፉት። የወላጆችና መምህራን በሆነው ስብሰባ ለምን ይሳተፋል ሲሉም ከስብሰባው እንዲዎጣ ሲሉ በድፍረት እስከመናገር ደርሰው ብዙሃን ተሰብሳቢውን አሳፈሩ :(

ግማሽ ሌሊት በዘለቀው ስብሰባ የሚጨበጥ መፍትሔ ሳይያዝ ተበተነ ። ስብሰባው አብቅቶ ወደ የቤታችን ለመሔድ ከግቢው እንደወጣን ከአዳራሹና ከኮሚኒቲው ግቢ ውጭ ” የተከበሩት ” የድርጅት ሰዎች ወጣቱን ከበው ሲያዋክቡት ደረስኩ ። ምክንያቱን መጠየቅ አላስፈለገኝምና ግርግሩን በአርምሞ መታዘብ ጀመርኩ። ወጣቱን ከመካከል አድርገው ሲያዋክቡት ቁልጭ ቁልጭ እያለ ለሚሰነዘርበት ትችት መልስ ለመስጠት ይሞክራል ። እነሱ ይዝታሉ ፣ ያንቋሽሹታል። ” የትምህርት ንጽጽሩን በተጨባጭ ካየው እውነታ ጋር የመናገር ነውርነቱ ምኑ ላይ ነው? ” የሚሉት በአንጻሩ የባለጊዜወችን ቁጣ በመቃወም በእሰጣ ገባው መካከል ለወጣቱ ድጋፋቸውን መግለጽ ሲጀምሩ ክርክሩ ሜዳ ላይ ለአፍታም ቢሆን ተፋፋመ ። አፍ የፈታበት ትግርኛ ቋንቋ አፉን ያዝ እያደረገው መልስ የሚሰጠውን ወጣት ምሁርን በራስ መተማመን ስመለከት የመቀሌው አብርሃ ደስታ ትዝ አለኝ። ልዩነቱ አብርሃ መቀሌ ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ስርአት አልበኝነትን የሚቃወም ሆኖ ሳለ ይህኛው ወጣት የሚሞግተው ፖለቲከኛ ሆኖ ስለፖለቲካና ኢ ፍትሃዊ አስተዳደር እያወራ አለመሆኑ ነው። ወጣቱ በ3000 ታዳጊዎች የትምህርት ማዕከል ላይ የሚታየውን የአስተዳደር ኢ ፍትሃዊነትና የትምህርት ጥራት አለመኖር በድፍረት በመናገሩ በወንዙ ልጆች ዘንድ ” አይንህን ላፈር ” አስብሎ በእርጉም አስፈርጆታል ። ግርግሩ በረድ ሲል ወጣቱ ወደ ቤቱ ለመሄድ ከአንድ ወዳጀ ጋር የሚያደርሳቸው ሲያፈላልጉ አየኋቸውና እግረ መንገዴን ላድርሳቸው ጠራኋቸው። ወጣቱ ኢኮኖሚስትና “አላጠፋም አትንኩት! ” ሲል ይሞግትለት የነበረው ወዳጀ ከእኔው ጋር ተሳፍረው መጓዝ ጀመርን … እናም ከሰላምታ በኋላ እኔ እንደለመደብኝ መጠየቅ እሱም መመለስ ያዘ …

ገና ልጅ እግር ነው ። እድሜው ከሃያዎቹ አያልፍም። በ1990 ዎቹ ከትግራይ ክልል ተነስቶ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ዘመነኛውን የኢኮኖሚክስ አስተዳደር ትምህርት ለስድስት አመታት ተከታትሎ በማዕረግ ተመርቋል ። ከ2000 ዓም ወዲህ በትምህርቱ የላቀ ውጤት በማምጣቱም እዚያው አዳማ ለስድስት አመታት ዩኒቨርሲቲ አስተምሯል ። በሃገር ቤት የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቶ አልመቸህ ቢለው ባንድ ክፉ ቀን ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ወደ ውጭ ሃገር ሄደው በስደት የተሻለ ገቢ አግኝተው በሚሰሩት ሁኔታ ዙሪያ ተመካከረ። “በሳውዲ በኩል ወደ ሌላ አውሮፖ ሃገር መውጣት ይቻላል!” የሚባል መረጃ ለእርሱና ለጓደኞቹ ስለደረሳቸው በአሳር በመከራ ያጠራቀሟትን ጥሪት በመሰባሰብ ቪዛ ገዝተው ከአመት በፊት ወደ ሳውዲ ጅዳ ከተፍ አሉ።

… ሳውዲ አረቢያ ግን እነሱ እንዳሰቧት ሆናም ሆነ ወደ አውሮፖ የሚደረገው ስደት የቀለለ አለመሆኑን የአረቦቹን ኑሮ በተቀላቀሉ ቅጽበት ማገናዘብ ቻሉ ። በቃ እሱና ጓደኞቹ ሳውዲን እንዳሰቡት አላገኟትምና ብዙ ሳይቆዩ በጅዳ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ስራ ፍለጋ ጀመሩ … በሰው በሰው በጅዳ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ” የመምህራን እጥረት አለ !” ሲባል ሰምተው ከአንድ ጓደኛው ጋር ወደ ትምህርት ቤቱ አስተዳደር በመሄድ የትምህርት መረጃቸውን አቀረቡ። ምንም እንኳን ትምህር ቤቱ ካላቸው ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ አንጻር ባይመጥናቸውም እንደ ዜጋ ዝቅ ብለው ለመስራት እና ለዚህ ትውልድ እውቀታቸውን ለማካፈል እድል አገኘን ብለው ያቀረቡት አቤቱታ ግን በትምህርት ቤቱ አስተዳደር በኩል ለውድድር ቀርበው ግልጋሎት መስጠት የሚችሉበት እድል የተነፈጋቸው መሆኑን ወጣቱ አጫወተኝ ! ይህ ወጣት ምሁር አክሎ እንዳጫወተኝ ከሁሉም የሚያስገርመው የ11 ኛ እና የ12 ኛ ተማሪዎችን በኢኮኖሚክስ ያልተመረቀ መምህር ታዳጊዎቹን በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት እንዴት በሙያው የተካንን ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዩኒቨርሲቲ የማስተማር ብቃት ያለው ዜጋ ዝቅ ብየ ላስተምር ሲል እንዴት እድሉን ይነፈጋል ? ሲል የሚያጠይቀው ወጣት የትምህርት መረጃዎችን ተቀብሎ ማወዳደር መጠየቅና ተገቢውን ለታዳጊዎች የሚጠቅም እርምጃ መውሰድ ሲገባ ” ስትፈለጉ እንጠራችኋል! ” በሚል መልስ መሸንገላቸውን በስሜት ገልጾልኛል!

“በዜጎች ላይ አንቀልድ ፣ በነገ የሃገሪቱ ተስፋዎች ልንቀልድባቸው አይገባም ” ሲል ስሜትን በሚነካ መንገድ የገለጸልኝ ይህ ወንድም በአሁኑ ሰአት የተለያዩ ተማሪዎችን በየቤታቸው እየሄደ በማስተማር ትምህርት ቤቱ ሊከፍለው ከሚችለው ገንዘብ በላይ ገቢ እንዳለው የገለጸልኝ ሲሆን ያም ሆኑ ትምህርት ቤቱ ለመደገፍ ይቻል ዘንድ ባለው ትርፍ ጊዜ መምህራን እንዴት ራሳቸውን ብቁ አድርገው ማስተማር እንዳለባቸው የተለያዩ ትምህርት ማጎልመሻ ስልጠናዎችን በነጻ ለመስጠት ከጓደኞቹ ጋር ጥያቄ ቢያቀርብም ትምህርት ቤቱም ሆነ ለባለቤት ተብየው ለጅዳ ኮሚኒቲ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት እንዳላገኘ በቁጭት አጫውቶኛል። እስኪ እሰበው ” ዜጎችን እንደግፍ ስንል ለምን እድሉ አይሰጠንም ? ” በማለት ያጠይቃል ! ወጣቱ እውነት አለው !

3000 ታዳጊዎች የምናስተምርበት ትምህርት ቤት ባልረባባ ምክንያት በአደጋ ላይ እንዳለ በስብሰባው በግልጽ ተመልክቷል። የመምህራንን እጥረትን መሰረት አደረገ የሚባለው የትምህርት ጥራት እያደረ ማሽቆልቆል በስብሰባው በአደባባይ በወላጅ እና መምህራን ህብረቱ ፣ በስብሰባው ተሳታፊ ወላጆች እና በመምህራን በግልጽ ተነግሮናል። ይህ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ እያለ ለትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆል የመምህራን እጥረት ምክንያት በሆነበት የትምህርት ማዕከል የላቀ እውቀት ያላቸው አቤቱታ ወገኖች አቤቱታ ለምን ተፈነገለ ? የ11ኛ እና የ12 ኛ ክፍል ወሳኝ ክፍሎች ለምን አዋቂ ሳይጠፋ እውቀቱ በሌላቸው መምህራን እንዲማሩ ማድረግ ለምን አስፈለገ ? በዚህ መሰል አስተዳደር የሚመራው ትምህርት ቤት የትምህርተ ጥራቱን አስጠብቆ ልጆቻችን ወደ ተሻለ የእውቀት ጎዳና ያደርሳቸዋል ብሎ ማሰብስ እንዴት ይቻላል? ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ያለባቸው ወጣቱን በመረጃ በአደባባይ መሞገት ያልቻሉት ወገኖች እና አጫፋሪዎቻቸው ቢሆኑ ደስ ይለኛል ። ኤርትራ የምትለው ሃገር ስለተነሳች ያንገበገባቸው ወገኖች ንጽጽሩ ከሱዳን አለያም ከፖኪስታን ተማሪዎች ጋር ቢሆን እንዲህ ያንገበግባቸው ነበርን ? ጉዳዩን በቅንነት ማሰብ ከቻሉ ኤርትራን የምትለውን ቃል ትተው የትምህርት ጥራት የለም ለሚለው የወጣቱና የብዙሃን ወላጅ አስተያየት ለምን በአደባባይ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም ? ለነገሩ ይህንን ለማድረግ ሞራል የላቸውምና አልፈርድባቸውም ። እኔም ቢያንስ ከዚህ ተነስቸ ይህንን ደረቅ እውነት ለመገምገም የተለየ ክህሎት ይጠይቃል ብየ ስለማላምን በማለዳ ወጌ ተነፈስኩት …
ቸር ያሰማን
ነቢዩ ሲራክ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>