Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ወያኔ: የነፃው ፕሬስ ፀር!

$
0
0

በቅዱስ ዩሃንስ

ነፃ- ፕሬስ ለነፃነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት የሚኖረውን አስተዋፅኦ የሚገነዘቡ ገዢዎች ፕሬሱ ለአንባገነንነት አገዛዛቸው የሚመች ስለማይሆን ይፈሩታል፤ ይጠሉታል፤ ያጠፉታል። ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው።
freedom
ነፃ ፕሬስ የሀሳብ ነፃነት መብት አልፋና ኦሜጋው ነው ብል ማጋነን አይሆንም። የነፃ ፕሬስ መኖር የሚያረጋግጠው ጋዜጠኞች ያለምንም ጭንቀትና ፍርሃት የሚያስቡትን፡ የሚሰማቸውን፡ የሚሰሙትን እንዲሁም ምርምር አድርገው የደረሱበትን ዜናዎች በነፃ ለመፃፍና ለማሰራጨት ብሎም ሕዝብ እንዲወያይበት ለማድረግ ያላቸው ያልተገደበ መብት ነው። ይህም ጤናማ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ለእድገቶቹም ጉልህ ድርሻ አለው። ነፃ ፕሬስ የኃሳብ ነፃነት ተግባራዊ ለመሆኑ ዋስትናም መፈተኛም ነው። ኃሳብን ያለምንም ጭንቀትና ፍርሃት በነፃ ለመግለፅ መቻልና መለዋወጥ እንደ ምግብና መጠጥ፤ ሁሉ ሰብአዊ ክቡርነትን የተላበሰ ሕይወት ለመጎናፀፍም አስፈላጊም ናቸው። ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት መኖርና ዋስታናው ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሕግ መረጋገጥ ማለት ዘላቂነት ላለው ዴሞክራሲያዊ እድገት ለማገኘትም ዋና መሰረት ነው።

የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የነፃ ፕሬስ አስፈላጊነት ትልቅ ቦታ እንዳለው ከልብ ይታመናል፡፡ ያለነፃ ፕሬስ ዴሞክራሲ አለ ብሎ መናገር ማወናበድ እንጅ እውነት ሊሆንም አይችልም፡፡ የነፃ ፕሬስ መኖር በራሱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መኖር መገለጫ ነውና፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲኖርም ነፃ ፕሬስ ይኖራል፡፡ ወደ እኛ ሃገር ስመለስ ግን ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ወያኔ መንግስት ሆኖ ላለፉት 23 ዓመታት ሃገሪቱን ሲያስተዳድር ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በወረቀትና በቃል እንጂ ከዚያ በዘለለ በተግባር ሲፈፅም አላሳየንም፡፡ ለመተግበር የሞከራቸውንም እንደ ቀንዳውጣ ቀንድ መልሶ ሸሽጎታል፡፡ ስለዚህ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማያምን አምባገነን ስርአት ስለሆነ ለነፃው ፕሬስ ፀር በመሆን ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በመስጠት ፋንታ አጥፊና ደምጣጭ ሆኖ እየሰራ ይገኛል።

ዛሬ በዘመነ ወያኔ በኢትዮጵያችን ነፃ ፕሬስ በአሳሪና አስፈሪ የፕሬስ አዋጅ ተጠፍሯል። ጋዜጠኞች ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በየፍርድ ቤቱ እየተጎተቱ ነው። ወደ እስርቤት እየተጣሉ፤ እየተሰደዱም ነው። የጋዜጣ፣ የመጽሔት፣ የመጻሕፍት ማሳተሚያ ዋጋ ሰማይ ጠቅሷል። በሀገሪቱ ሕገመንግሥት ቀርቷል የተባለ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ጓሮ በኩል በእጅ ኣዙር ተመልሶ እንዲመጣ ተደርጔል። ሌሎች በከተማው ያሉ ማተሚያ ቤቶችም ሳንጃ የተከለ ጠመንጃ ወድሮ የሚያስፈራራ ኃይል ያለባቸው ይመስል “የተቃዋሚ ጋዜጣን አናትምም” ብለዋል። በቅርቡ በሰማያዊ ፖርቲ ‘‘ነገረ ኢትዮጵያ’’ ጋዜጣ ላይ የተሰተዋለው ችግር ይሄው ነው። ጋዜጣዋ ተዘጋጅታ ለማተምያ ቤት ብትበቃም ስርአቱ በፈጠረው የማደናቀፍ ተንኮል ለህትመት ሳትበቃ በመቅረቷ በፓርቲው ቀና ትብብር በድህረ ገፃቸው እንድናገኛት ተገደናል። ማተሚያ ቤቶች ሠርቶ የማትረፍና ሀብት የመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲሁም ሕዝብን የማገልገል ግዴታቸውን በፍርሀት ጨርቅ ገንዘው በየማተሚያ ቤታቸው ጓሮ ቀብረውታል። የሕዝብ ንብረት የሆኑ፣ በሕዝብ ሀብት የሚተዳደሩ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሃያ አራት ሰዓት በወያኔ በሞኖፖል ተይዘዋል፡ የገዥው ልሳን ብቻ መሆናቸውንም አስመስክረዋል። ሌሎችም የተለያየ ስም እየተሰጣቸው በአየር ላይ አለን የሚሉ ጣቢያዎች ልሳናቸው የበዛ ቢመስልም ከሞላ ጎደል ቋንቋቸው አንድ ነው። ያ ቋንቋ ግን የእውነተኛ ነፃ ፕሬስ ቋንቋ አይደለም። በዚህ ዓይነት የፕሬስ ሁኔታ በሀገራችን ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም።

ይህ ነፃ ፕሬስን ማቀጨጭ ብሎም ለመቃብር ማብቃት ደግም በአለም ላይ በስፋት እንደታየው የአምባገነን መንግስታት መለዬ ካባ ነው። አምባገነኖች የሚገዙትን ህዝብ ለመቆጣጠር ከሚወስዷቸው እርምጃዎች ቀዳሚው ፕሬስን መቆጣጠር ነው። በጉልበት የሚገዙት ህዝብ እነሱ ከሚሉት ውጭ እንዳይሰማ ለማድረግ ወደ ህዝብ ጆሮ የሚደርሱትን ነገሮች ሁሉ የመቆጣጠር ተግባር ይፈጽማሉ። ከዚህም በተጨማሪ ውሸትን ደጋግሞ በማውራት እውነት ለማስመሰል ይተጋሉ። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች ሁሉ የጋራ ባህርይ ነው። ስለዚህ ወያኔም ነፃ ፕሬስን የሚፈራበት ትልቁ ምክንያት በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት አምባገነንነቱንና የጥፋት ተልዕኮ ሚናውን አጋልጠው በሕዝብ እንዲተፋ ማድረጋቸውን በሚገባ ስለሚያውቅ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ነፃ ፕሬሶች ወያኔን ከሥልጣን ለማስወገድ በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን በማወቁ ጭምር ነው።

ወያኔ ለሙያቸው ክብር ያላቸው ጋዜጠኞችን በክሶች ብዛት፤ በእስርና እንግልት እንዲሁም ከአቅማቸው በላይ በሆነ የገንዘብ ቅጣት እንዲሸማቀቁ በማድረግ እውነት ዘጋቢ ስታጣ የኢትዮጵያ የመረጃ አየር በውሸት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል። ወያኔ በፈለገው መልክ ሊተረጉመው በሚችለው አንቀጽ ጋዜጠኞችን እያስፈራራና እያዋከበ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ነፃነት መብትን ይኸው እስካሁን ድረስ እንዳፈነ ይገኛል። ወያኔ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ለታሰሩ፥ ለተገደሉ፥ ለስደት ለተዳረጉ በርካታ ጋዜጠኞች ዋና ተጠያቂ ነው። የእስራት ፍርድ ተፈርዶባቸው በመማቀቅ ላይ የሚገኙ አሁንም በርካታ ናቸው። የተወሰኑትም ደግሞ ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርገዋል። በአገር ውስጥ የሚገኙ የመረጃ መረቦችን በማናለብኝነት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፤ ከውጭ አገራት የሚተላለፉ የሬድዮና የቴሌቪዥን ሞገዶችን በይፋ በማፈን ኢትዮጵያ አገራችን በመረጃ ከዓለም የተነጠለች ደሴት ለማድረግ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ሃብትንም ለዚህ እኩይ ስራው ያባክናል። ነፃ- ፕሬስ ለነፃነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት የሚኖረውን አስተዋፅኦ የሚገነዘቡ ገዢዎች ፕሬሱ ለአንባገነንነት አገዛዛቸው የሚመች ስለማይሆን ይፈሩታል፤ ይጠሉታል፤ ያጠፉታል። ወያኔም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው።

በመጨረሻም ወያኔ የነፃ ፕሬስ ጠላትነቱን ያረጋገጠው ሥልጣን እንደጨበጠ በመሆኑ ላለፉት 23 አመታት አንድን አፋኝ ሕግ በሌላ አፋኝ ህግ እየተካና እያጠናከረ የነፃ ፕሬስ ፀር መሆኑን ያስመሰከረ በኢትዮጵያ ላይ የመጣ መቅሰፍት ነው። ስለዚህ ለእውነት የቆመ ነፃ ሚዲያ መወለድና ማበብ በአገራችን እንዲኖር ለምንሻው ዲሞክራሲ የመሰረት ድንጋይ መሆኑን በማመን፤ ለእውነት የቆሙ ነፃ ፕሬሶች እንዲፈጠሩ መታገል የሁላችንንም ርብርብ የሚጠይቅ ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ራሷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ያለ ነፃ ፕሬስ ማሰብ አይቻልምና:: መረጃ የተጠማው የኢትዮጵያ ህዝብም ነፃ የሚዲያ ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ እንቅፋት የሆነውን የአንባገነኑን የወያኔ አገዛዝ ከጫንቃው ለማውረድ በጋራ መታገል ይኖርበታል። በተጨማሪም ነፃ ፕሬስ ለሃገራችን ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በመረዳትና፤ መብትም በትግል እንደሚገኝ በማመን የፕሬስን ነፃነትን ለማምጣት በአንድነት በመነሳት እንቅፋት የሆነውን አገዛዝ በቃህ ልንለው ይገባል።

በመረጃ የዳበረ ህዝብ አንባገነኖችን ቀባሪ ነው!

ለአስተያየትዎ፡ kiduszethiopia@gmail.com አድራሻየ ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>