የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ትላንት ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት መከበር ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠት በቅርቡ 93ኛ ዓመታቸውን ላከበሩት ሌተናል ጀነራል ጃገማ ኬሎ የክብር መግለጫ ምስክር ወረቀት እንዳበረከተላቸው የማህበሩ ምክትል ጸሀፊ ለፍኖተ ነፃነት ገለፁ::
የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ም/ጸሀፊ ወጣት ጥላዬ ታረቀኝ ለፍኖተ ነፃነት የሚከተለውን ብሏል “ሌተናል ጄነራል ጃገማ ኬሎ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ታላቅ ተጋድሎ የፈፀሙ ናቸው፤ ማህበራችንም በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ስለሚሰራ እንደነዚህ አይነት ጀግኖችን ክብር ይሰጣል፡፡ ለዚህም ነው ለሌተናል ጀረናል ጃገማ የክብር ምስክር ወረቀት የሰጠናቸው፡፡ ” አያይዞም “የብሔር ግጭቶች እንዳይፈጠሩና ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ እንዲያተኩሩ የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡” ሲል ለሌተናል ጄነራል ጃገማ ኬሎ ስለተሰጠው የክብር መግለጫ አብራርቷል፡፡
የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር አመራሮችና አባላት ለሌተናል ጄነራል ጃገማ ኬሎ በመኖሪያ ቤት በመገኘት የክብር መግለጫ ምስክር ወረቀት ሲያበረክቱላቸው የአካላቸውን መድከም ተቋቁመው በሙሉ ወኔ ወጣቱ ትውልድ በዘር መከፋፈሉን ትቶ ኢትዮጵያን እንደቀድሞው አንድ ለማድረግ እንዲታገል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ወጣት ጥላዬ ተናግሯል፡፡
ምንጭ ፦ፍኖተ ነጻነት