Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

[የሚኒሶታው መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ] መድኃኔዓለም በእርቅና በሰላም ጎዳና ይምራችሁ

$
0
0

የተከበራችሁ የሚኒሶታ ደብረሰላም መድኅኒዓለም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምእመናን፤ አባቶች ካህናት፤ ወንድሞች ዲያቆናት ከሁሉ አስቀድሜ የከበረ የኢግዚአብሔር ሰላምታየ ከካናዳ ይድረሳችሁ። ሚኒሶታን በተለያየ ጊዜ ጎብኝቻታለሁ። . በመጣሁበት ጊዜ ሁሉ መድኅኒዓለም ቤተከርስቲአናንን ሳልሳለምና ፀሎት ሳላደርግ የተመልሱሁበትን ጊዜ አላስታውስም። የምእመናኑ ፍቅር፤ አንድነትና የምነት ጽናት ሁልጊዜ በአረያነት ስጠቅሰው ኖሬአለሁ።
debereselam Minnesota
በቅርቡ በኢትዮጵያዊያን ድረገጾች ላይ የሚወጡትን ዜናዎች ሳይ ግን አዘንሁ። ለማመንም ተቸገርሁ። ሰላማችሁ ተቃውሶ ፍቅራችሁ ደፍርሱዋል። ሠይጣን በናንትና በእምነታችሁ መካከል ገብቶ እያተራመሳችሁ ነው። በከባድ ፈተና ላይ እንዳላችሁ ይሰማኛል። በእምነት ፀንታችሁ ከገባችሁበት የችግር አረንቋ እንድትወጡ እፀልያለሁ። ችግርና ፈተና በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ያለና የሚኖር ስለሆነ ጽናቱን ይስጣችሁ።።

በርቀት እንዳነበብሁትና እንደተረዳሁት የችግሩ መንስዔ ቀላል ይመስለኛል። ችግሩ በቅርቡ ጠቅላላው ጉባኤ ቤተክርስቲአንዋ በገለልተኝነትዋ ትቀጥል ብሎ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ያጠነጠነ ይመስለኛል። ይህን ሕዝበ ውሳኔ የተወሰኑ የቦርድ አባላት ምላተ ጉባዔ የጎደለው ውሳኔ ስለሆነ አንቀበለውም ወይም በይደር ይቆይ የሚሉ በመኖራችው የተነሳ እንደሆነ ገምቻለሁ። እንደኔ አስተያየት ይህ የአሰራር ድክመት (procedural inconsistency ) በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የሚፈታ ጉዳይ ነው።

ውሳኔውን የተቃወመው የቦርድ ቡድን ሊቀመንሩን አውርደን ሌላ ተክተናል ብሎ ባወጣው መግለጫ ቤተክርስቲአንዋ በገለልትኝነቱዋ ትቀጥላለች ብሎ አውጁአል። ስለዚህ ጠቡ የት ላይ እንደሆነ ግራ ያጋባል። በአመራሩ (በሊቀመንበሩና በምክትል ሊቀመንበሩ) ላይ የተደረገ ዘመቻ ቢሆን እንኩዋን ለዚህ ሁሉ ብጥብጥ የሚዳርግ መሆን የለበትም ።

በአንጻሩ የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የሚበጠብጡ ካሉ ለችግሩ መፈጠርና ለሚያስከትለው መዘዝ ደንታ ላይኖራቸው ይችላል። ምክንያቱም የነዚህ ቡድን ዓላማ እምነታችንን፤ ባህላችንን፤ ቅርሳችንንና ታሪካችንን ማስከበር ሳይሆን የሃገርና የህብረተሰብ እሴቶችን ደፍጥጦ የፖለቲካ አሸናፊነትን ማግኘት ነው። ይህ ደግሞ ጊዚያዊ ግኝት እንጅ ዘላቂነት ያለው ማሸነፍ አይሆንም። የሊቀመንበሩን የአቶ ጥበቡን ስነልቡናና ባህሪ ሳጠያይቅ የተረዳሁት ግለሰቡ ልዩ ዓጀንዳ የሚኖራቸው ሰው ሆነው አይታዩም። ይህን አባባሌን በማስርጃ ላመሳክረው፥

ከጥቂት ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ተመርጠው ቤተክርስቲአኑዋን አገልግለዋል። ባገለገሉበት ጊዜ አብዛኛው ምእመን በምስክርነት የሚገልጸው-በሃቅ ሰርተው ለተተኪው ቦርድ እንዳስረከቡ ታውቁአል/ ሰምቻለሁ፤

ለሁለተኛ ጊዜ ሲመረጡ ዕድሜየ ገፍትዋል፣ የጤና ችግር አለብኝ ብለው ቢያንገራግሩም ህብረተሰቡ ያገልግሉን ብሎ በድጋሚ ስለመረጣቸው ሃላፊነቱን የተቀበሉ ናቸው። ለዚህም ይመስለኛል የቦርዱ አባላት በሊቀመንበርነት የመረጡአቸው። ደመወዝ ተከፍሉአቸው፤ጥቅማ ጥቅም አግኝተው አይሰሩም። ሰውናቸውና አይሳሳቱም ማለት ግን አይቻልም። የሚሳሳቱ ስለሚሰሩ ነው። ልዩ ዓጀንዳ ያላቸው አለመሆኑ ግን በግልጽ መታወቅ አለበት።

አገር ቤት በነበሩበት ጊዜ የነበራቸውን ስብእና ስንመለከት የግለሰቡን ሃቀኝነትና ባመኑበት የመቆም ባሕሪአቸውን ለመረዳት እንችላለን። በደርግ ዘመነ መንግስት በተለያዩ የመንግስት መስሪያቤቶች በመምርያ ኃላፊነት ሰርተዋል። በዚያን ዘመን በኢሰፓ መመሪያ መሰረት ማንኛውም የመምሪያ ኃላፊ የኢሰፓ አባል ሆኖ የካድሬነት ደብተር መያዝ የውዴታ ግዴታ ነበር። እኒህ ግለሰብ ግን እኔ ሙያዊ ስራ የምሰራ እንጅ የፖለቲካ ስራ የምሰራ ሰው አይደለሁም በማለት በአቍማቸው እንደፀኑ እስከደርግ ፍጻሜ ድረስ ያገለገሉ ሰራተኛ ናቸው። ይህን ስነምግባራቸውን በቅርብ ከሚአውቋቸው ሰዎች ለማጣራትና ለማወቅ ችያለሁ። ስለሆነም ግለሰቡ ድብቅ ዓጀንዳ ይኖራቸዋል ብሎ መጠርጠር የሚቻል አይሆንም። ችግሩ የሚመስለኝ በሃገራችን ባህል እውነትን ፊትለፊት ያለዲፕሎማሲ መናገር ብዙ ጠላትን እንጅ ወዳጅን አያስገኝም። በዚህም የካህናትንና ያንዳንድ ቦርድ አባላትን ቅሬታ የፈጠረባቸው መስሎ ይታየኛል።

የሰበካ ጉባኤ ቦርድ በጠቅላላው ጉባኤ ተመርጦ ስራውን ከጀመረ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ሆኖታል። ያገልግሎት ዘመኑን ሊጨርስ ስምንት ወራት ይቀረዋል። ሁላችሁም ምርጫውን ተቀብላችሁ በእግዚአብሔር ስም ቃል ገብታችሁ የቤተክርስቲያኒቱን መተዳደሪያ ደንብ አስከብራችሁ ለመስራት እንደሆነ የምታጡት አይመስለኝም። የምትሰሩትም የእግዚአብሔርን ቤት ለመጠበቅና ምእመናን በሙሉ ልብ፤ ቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል ነው። ማናችሁም (ከካህናቱ በስትቀር) ተከፍሎት የሚአገለግል የለም። የምትሰሩት የመንፈሳዊና የግብረሰናይ ስራ ብቻ መሆን አለበት። ባለፉት 13 ወራት በብዙ ጉዳዮች ላይ በህብረት ወስናችሁአል። በምትሰሩበት ጌዜ ስህተቶች ይኖራሉ። ሆን ብሎ ግን ስህተት የሰራ አለ ብሎ ማመን ግን ይቸግራል። ሁላችሁም የእግዚአብሔርን ቤት ሰሪዎች ናችሁና። የማይሳሳት የማይሰራ ብቻ ነው። ከስህተታችሁ ተምራችሁ ይቅር ለእግዚአብሔር ወርዳችሁ ሠላምን ልትፈጥሩ ይገባል። እስኪ ከኔልሰን ማንዴላ ይቅር ባይነትና ሰላም ፈጥሪነት ትምህርት ቅሰሙ። በፖለቲካው ዓለም ይቅርታን መፍጠር ከተቻለ በእግዚአብሔር ቤትማ የበለጠ መቻል አለበት እላለሁ። ሁላችሁም ደረጃው ይለያይ እንጅ የተማራችሁ ናችሁ። አገራችሁ ከናንተ ብዙ ትጠብቃለች። ይህን መለስተኛ ችግር መፍታት ይሳናችሁአል የሚል እምነት የለኝም።

ከዚህ የተለየ ዓላማና ዓጀንዳ ያለው ካለ የሕዝብን አደራ የብላ ስለሆነ ውጉዝ ከማሪወስ ሊባል ይገባዋል። አቶ በቀለ ገብረሚካኤል ከተባሉ ፀሃፊ መረዳት እንደቻልሁት ካህናቱ በሳቱ ላይ ውሃ በማርከፍከፍ ፋንታ በችግሩ ላይ ጭድ የጨመሩ መስሎ ይታያል። ይህን አርገው ከሆነ በእግዚአብሄር ቤት የሚጠይቁበት ይሆናል። አሳዛኝና አሳፋሪም ነው። የመጀመሪዎቹ (front line fire brigades) ችግር ፈቺ፤ አስታራቂ፤ አንተም ተው አንቺም ተይ ማለት የሚገባቸው ካህናት ናቸው። ፍቅርን፤ ሰላምንና ይቅርባይነትን ማስተማር ዋናው ተግባራቸው ነው። በመሃልቤት ቤተክርሲያንዋ ብትፈርስና ብትበጣበጥ በመንፈሳዊ ሕይወትና በዓለማዊ ፍላጎታቸው አይሞቱ ሞት፤ አይቀጡ ቅጣት፤ አይከስሩ ኪሳራ የሚደርስባቸው እነርሱ ናቸውና።

በከተማችሁ የሚታተመዉ ዘ-ሐበሻ የተባለው ድረገጽ እንዳለው ችግሩ በውይይትና በመደማመጥ ሊታረቅና ሊሰክን የሚችል ነው ያለውን ሃሳብና ምክር እጋራለሁ። ለእምነቴ ካለኝ ፍቅርና ጽናት የተነሳ የሚከተሉትን የመፍትሄ ሃሳቦች ወርውሬ ጽሁፌን ልቋጭ።

የመፍትሄ ሃሳቦች፥
1. ከሁለቱም የተውጣጣ የመፍሔ አፈላላጊ ኮሚቴ (conflict resolution committee) ባስቸኩይ አቐቁሞ ችግሩ በሰላም የሚፈታበትን መንገድ መሻት። በዚህ ቡድን የሚካተቱ ሰዎች በዕድሜአቸው ጠናያሉ፤ ነገሮችን በኣራቱም ማእዘናት መመልከት የሚችሉ፤ ያስተሳሰብ አድማሳቸው ሰፋያለ፤ የህበረሰባችሁ አመኔታና ተቀባይነት የተቸራቸው ሊሆኑ ይገባል፤

2. በቦርዱ አባላት መካከል ያለው አለመግባባት በአፈጻጸም ምክንያት የደረሰ ሲሆን ሁለቱም የከረረ አቁኣም ይዘው የተጋጩ ናቸው። ጉዳቱ ለቤተክርስቲአንዋ፤ ለምእመኑና ለቆምነልት ሃይማኖት ነው። ከላይ እንደጠቀስሁት ቦርዱ የቀረው የስራ ዘመን ስምንት ወራት ብቻ ስለሆነ የቦርዱን አጠቃላይ ኅላፊነት ዝቅ አድርጎ የቤተከርስቲያኑአን የዕለት ተዕለት ተግባር ብቻ እየሰራ የአገልግሎት ዘመኑን እንዲጨርስ ማድረግ። ባስቸኩይ አስመራጭ ኮሚቴ አቋቁሞ አዲስ ቦርድ የማስመረጡን ሂደት (nomination process) መጀመር። ይህ በዚህ እንዳለ ከካህናቱና ከምእመኑ የተውጣጣ ሽማግሌ መርጦ ሁለቱን ተቃራኒ ቡድኖች አቀራረቦ በይቅር ለእግዚአብሄር አስታርቆ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ፤

3. ከላይ የተጠቀሱት የማይሰሩ ሆኖ ቢገኝ ቦርዱን በሙሉ አውርዶ (ሊቀመንበሩን ጨምሮ) እንባ ጠባቂ ኮሚቴ ( care taker body) በማቋቋም ቀሪውን ስምንት ወር መወጣት። ይህ ኮሚቴ ስምንት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ አካሂዶ አዲስ ቦርድ አስመርጦ ኅላፊነቱን ለተመራጩ ቦርድ እንዲአስረክብ ማድረግ፤

4. ምናልባት ይህን ለማድረግ ገለልተኛ የሆነ አካል መኖር አስፈላጊ ሊሆን ይችል ይሆናል። ሁለቱም ቡድኖች ጠበቃ ገዝተው ጉዳዩን በፍርድ ቤት ለመቋጨት ይሞክሩ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። በሰሜን አሜሪካ (ካናዳን ጨምሮ) ፍርድ ቤቶች የግብረሰናይ ድርጅቶችን የሚዳኙበት ሁኔት ከንግድ/ግል ድርጅቶች የተለየ ነው። ስለሆንም ጉዳዩን በእርቀ ሰላም እንዲጨረስ በአጽኖት ይመክራሉ ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ በሁለቱ ቡድኖች የተቀጠሩት ጠበቆች ገለልተኛ ሆነው ይህን ችግር እንዲፈቱ ያጭር ጊዜ ያማካሪነት (short term consultancy ) ስራ መሰጠት። መተዳደሪያ ደንባችሁ ብዙ ድክመቶች ያሉት መስሎ ይታየኛል። እነኚሁ ጠበቆች አጥነተው የተሰተካከል መተዳደሪያ ደንብ እንዲቀርጹላችሁ ቢደረግ ይበጃል።

በመጨረሻም ምን አልባ ትመግባባት አቅትዋችሁ እርስ በርስ ብትፈርሱ እግዚአብሄርን ከማሳዘናችሁም ባሻገር በእናት ቤተክርስቲአናችን ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥላችሁ የምታልፉ መሆኑን አትዘንጉ። የሌሎች ሃይማኖቶች መሳቂያና መሳለቅያ መሆናችሁን ሰከን ባለ ልቡና አስቡት። ለዚህ ሁሉ ካህናት ከመላው ምእመን ጎን መቆም ይጠበቅባቸዋል። አንደኛውን ደግፎ ሌላውን የሚያወግዙ ከሆነ ሌላ ተልዕኮ እንዳላቸው የሚጋለጡበት ይሆናል። የካህናቱን ደመወዝና መኖሪያ የሚከፍለው ምእመኑ እንጅ ቦርዱ እንዳልሆነ ሊገነዘቡ ይገባል። ለሁላችሁም ልቦና ሰጥዋችሁ ቤተከርስቲያኑኣንና ምእመናን ለመታደግ እንድትችሉ እግዚአብሔርና መድኅኒዓለም በእርቅና በሰላም ጎዳና ይምርዋአችሁ።

አቢቹ ነጋ
ታህሳስ 23, 2006


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>