Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ፍቅረኛ ልታጡ የቻላችሁባቸው 8 ምክንያቶች

$
0
0

በሊሊ ሞገስ

አንዳንድ ሰዎች መርጠው ብቸኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ቅርብ ጊዜ ከጥሩ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ በመውጣታቸው ምክንያት እና የሚመስላቸውን ሰው እስከሚያገኙ ድረስ ብቸኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የዚህ ፅሑፍ አላማ ብቸኛ ሆኑ ወንዶችን እና ሴቶችን በሙሉ አንድ ሳጥን ውስጥ ጨምሮ ብቸኛ ልትኑ የቻላችሁት በዚህ በዚህ ምክንያት ነው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ዕድሜያችሁ ከ30 በላይ የሆነ እንደሆነ እና እንዴት እስከ ዛሬ ድረስ ብቸኛ ልሆን ቻልኩ? የሚለው ጥያቄ እንቆቅልሽ ከሆነባቸው ለጥያቄያችሁ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ውስጣችሁ የሚገኙ ያልተለመዱ ምላሾችን እነሆ ብለናል፡፡

ከተቃራኒ ፆታ ፍቅር ግንኙነት ጋር በተያያዘ የትኛውም ሰው ቢሆን እንደው አንድም ጊዜ እንኳ ተጎድቼ አላውቅም ለማለት ይቸገራል፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ ሰዎች መራራት ሊሳናቸው፣ ራስ ወዳድ ሊሆኑ እና ልትጎዱ ትችላላች፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ‹‹የእኔ ጥፋት ነው›› የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ትክክል አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን እውነታው ምንድን ነው? አብዛኞቻችን ከምናስበው በላይ የፍቅር ህይወታችን ላይ የቁጥጥር ኃይል አለን፡፡ ምንም እንኳ ብዙ ጊዜ ብንዘነጋውም ሁላችንም አውቀንም ይሁን ሳናውቅ የምንኖርበትን ዓለም እንፈጥራለን፡፡ ራሳችንን ሁል ጊዜ በተጎጂ መነፅር ለመመልከት አልያም ዕቅድ ያለው እና የገዛ ህይወቱን እጣ ፈንታ መቆጣጠር የሚችል ሰው በሚል መነፅር ራሳችንን ለመመልከት መምረጥ እንችላለን፡፡ መቆጣጠር የማንችለው ነገር ላይ ሳይሆን መቆጣጠር የምንችለው ነገር ላይ ትኩረተ ብናደርግ የተሻለ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ሰዎች ስለ እኛ የሚሰማቸውን ስሜት መወሰን የምንችልበት አቅም አለን፡፡ ይህ አቅም ታዲያ አሉታዊ ስሜቶችንም ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ብቸኛ የሆነና የፍቅር አጋር በመፈለግ ላይ የሚገኝ ሰው ለራሱ ሊያቀርበው የሚገባው ጥያቄ ‹‹ብቸኛ ልሆን የቻልኩበት ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው?›› የሚል ነው፡፡

images
1. ማስተባበያዎች (Defenses)

ብዙ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ተጎድተው ያውቃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት መሽቶ በነጋ ቁጥር ውስጣችን ቅያ፣ ቁጣ እና ጥርጣሬ ያድጋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ማስተባበያዎችን አለልክ እንጠቀማለን፡፡ ይህ ሂደት የሚጀምረው በልጅነታችን ሊሆን ይችላል፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ሰዎች ስሜታችንን በመጉዳታቸው የተነሳ ራሳችንን ከጉዳት ለመከላከል ያስችላል ብለን ያሰብነውን በተለይ በተለይ ነፍስ ከአወቅን በኋላ ህይወታችንን አሉታዊ በሆነ መንገድ ሊጫን የሚችል ዓለምን የምንመለከትበት፣ ክፉ እና ደግ ነው የምንለውን ነገር የምንለይበት ማጣሪያ እናዘጋጃለን፡፡ እነዚህ ማጣሪያዎች ከልክ በላይ ራሳችንን ከጉዳት ለመከላከል ብቻ የምንተጋ፣ የትኛውንም ግንኙነት ለማስወገድ የምንጥር፣ ለማፍቀር ሳይሆን ለአለመጎዳት የምንሰራ ሰዎች ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡ ይህ ጠባይ በአዋቂነት ዘመናችን ራሳችንን ለፍቅር አጋር አሳልፈን ከመስጠት እንድንቆጠብ እና በቀላሉ በሰዎች ተስፋ የምንቆርጥ አይነት እንድንሆን ያደርጋል፡፡

ለምሳሌ፤ ፍቅር ተነፍጋችሁ ከሆነ ያደጋችሁት አዋቂ ስትሆኑ ሰዎች ፍቅራቸውን ሊገልፁላችሁ ሲሞክሩ ትጠራጠራላችሁ፡፡ እንደውም በምትኩ የልጅነት ህይወታችሁን መልሶ የሚደግም አይነት፤ ፍቅር የሌለበት፤ በቅናት፣ ጥርጣሬ እና ጥል የተሞላ ግንኙነት ልትመሰርቱ ሁሉ ትችላላችሁ፡፡ እንደ ወላጃችሁ ወይም አሳዳጊያችሁ ፍቅር መስጠት የማይችል ሰው ልታፈቅሩ ትችላላችሁ፡፡ ይሁን እንጂ ብቸኛ ልንሆን የቻልነው በዚህ በዚያ ምክንያት ነው እያልን ውጫዊ ነገሮችን ብቻ በመውቀስ ውስጣችን የሚገኙ እውነተኛ ምክንያቶችን ሳንመለከት እንቀራለን፡፡

sex2. ጤናማ ያልሆነ መሳሳብ

ቀደም ሲል ያነሳነው አይነት ማስተባበያ ውስጣችን ከኖረ አጋር ስንመርጥ የምንፈልገው አይነት ሰው ላንመርጥ እንችላለን፡፡ ይልቁንም እምብዛም ፍቅር የማይሰጠን እና በስሜት ሩቅ የሆነ ሰው ላይ እናተኩራለን፡፡ የሚቀርበንን ሳይሆን የሚርቀንን፤ የሚያከብረንን ሳይሆን የሚያጣጥለንን ሰው እናሳድዳለን፡፡ ይህ ሂደት በአመዛኙ ለእኛ የሚታይ ባለመሆኑ አልሰራ ላለው ግንኙነት ተወቃሽ የምናደርገው አጋራችንን ብቻ ይሆናል፡፡ እነዚህን መሰል ግንኙነቶች እየመሰረትን የምንገኘው በገዛ እጃችን መሆኑን መመልከት ስለሚከብደን በተደጋጋሚ በሚያጋጥመን መገፋት እንጎዳለን፡፡

ለምንድን ነው እንዲህ የምናደርገው?

ምክንያቶቹ ብዙ ጊዜ የተወሳሰቡ ሲሆኑ መሰረት የሚያደርጉት ውስጣችን በጥልቀት የተቀበረ ጥልቅ ወዳጅነትን የመፍራት አባዜ ላይ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ለእነሱ ያን ያህል ጎልቶ የማይታይ ነገር ግን በራሳቸው ዙሪያ ቀደም ሲል ያስቡ የነበሩትን ቁልፍ አስተሳሰቦች የሚያጠናክር ግንኙነት የመሳብ ተነሳሽነት ውስጣቸው አለ፡፡ በዚህ ምክንያት የልጅነታቸውን አሉታዊ ገፅታዎች መልሰው በአዋቂነታቸውም ዘመን ይደግሙታል፡፡

3. መቀራረብን መፍራት

ብዙዎቻችን አፍቃሪ አጋር እንደምንፈልግ እንናገራለን፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛ ፍቅር ወደ ህይወታችን ሲመጣ ያ ከልጅነት ጀምሮ ውስጣችን ያደገውን የፍቅር ቅዠት አልመስል ስለሚለው ልባችንን አንከፍትም፡፡
ቅርርብን መፍራት ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ አንድ ሰው ‹‹ከልክ በላይ ነው የሚወደኝ፤ ከእሱ/እሷ ጋር መሆን ይከብደኛል›› የሚል ማስተባበያ ነው፡፡ ይህ ምክንያት ከአንድ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመስረት በፍፁም ሊከለክል አይችልም፡፡ የሚወደንን ሰው በማብጠልጠል እና በመግፋት አጣን የምንለውን ፍቅር እውነትም እንዳጣን ለማረጋገጥ እንሞክራለን፡፡ እውነቱን ለመናገር ብዙ ሰዎች የሚመርጡት በተወሰነ መልኩ መቀራረብን ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳ የፍቅር አጋር እንደምንፈልግ ብንገልፅም ውስጣችንን ግን በዚህ መልኩ ልንዘጋው እንችላለን፡፡ ነገሩን በጥልቀት ስትመለከቱት እንፈልጋለን እንላለን እንጂ አንፈልግ ሁሉ ይሆናል፡፡

4. ሲበዛ መራጭ መሆን

ማስተባበያዎች ብዙ ጊዜ አለልክ መራጭ ያደርጉናል፡፡ ይህ በተለይ እውነት የሚሆነው በአንድ አጋጣሚ በጣም በምናወድሰው ሰው የተጎዳን እንደሆነ ነው፡፡ ብዙ ሴቶች ‹‹ጥሩ ወንድ እኮ የለም፤ ያሉት ጥቂቶችም ተይዘዋል›› ሲሉ ይደመጣል፡፡ ወንዶች በሌላ በኩል ‹‹ሴቶችን ማመን አይቻልም፤ ተጠቅመውብህ ዞር ይላሉ›› ይላሉ፡፡ እውነታን ያላገናዘበ ነገር ከሰዎች እንጠብቅና ገና ከመገናኘታችን ‹‹አይ ይሄ/ይቺ እንኳን ሊሆን/ልትሆን አትችልም›› የሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡ በአብጠልጣይ አይን ዓለምን የምንመለከት ከሆነ ወደ ፊት አብረውን ቢሆኑ አስደሳች ህይወት ለመምራት ሊረዱን ሁሉ የሚችሉ ብዙ ሰዎችን እናጣለን፡፡ ወደ ፊት ያ ሰው ምን ያህል ሊያስደስተን እንደሚችል ሳናውቅ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡

5. ዝቅተኛ በራስ መተማመን

አንዳንድ ሰዎች የፍቅር አጋር እንደሚፈልጉ ከልባቸው ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በበለጠ መልኩ የሚፈልጉት አይነት ሰው እነሱን እንደማይፈልጋቸው ያምናሉ፡፡ ሁላችንም ውስጣችን በጣም ወፍራም፣ መልከ ጥፉ፣ ልዩ እንደሆንን የሚነግረን ድምፅ ይኖር ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎችን የሚያርቅ ነገር እናደርጋለን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ዝቅተኛ በራስ መተማመን ውስጣቸው ሲነግስ ሌላው ቀርቶ ከቤት መውጣት ሁሉ ያስጠላቸዋል፡፡ አይን ለአይን መተያየት ይከብዳቸዋል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ሊወዱት ከሚችሉት ሰው ጋር ቢተዋወቁ እንኳ ‹‹ልትፈልገኝ ትችላላች/ሊፈልገኝ ይችላል›› ብለው ስለሚያስቡ ፍላጎታቸውን አይገልፁም ይልቁንም ሽሽት ውስጥ ይገባሉ፡፡

6. ፉክክርን መፍራት

ዝቅተኛ በራስ መተማመን ፉክክር እንድንፈራ ያደርጋል፡፡ በተለይ ከተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ራሳችንን ከሌሎች ጋር አወዳድሮ ዝቅ ዝቅ ማድረግ በጣም ቀላል ነው፡፡ እኛ ፍላጎት ያሳደርንበት ሰው ላይ ሌላ ሰው ፍላጎት እንዳሳደረ ስናውቅ እግሬ አውጪኝ ብለን እንሸሻለን፡፡ በተለይ ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድና ሰዎች ‹‹ቆመህ መቅረትህ/መቅረትሽ ነው›› ነው ትችት መሰንዘር ሲጀምሩ የመፎካከር መንፈስ ከውስጣችን ሙልጭ ብሎ ሊጠፋ ይችላል፡፡ መፎካከርን የምንፈራ ከሆነ ወጣ ብለን የሚመስለንን ሰው ለማግኘት ሙከራ አናደርግም፡፡ አንዳንዴ መሸነፍን ብቻ ሳይሆን ማሸነፍን ሁሉ እንፈራለን፡፡ እኛ አሸንፈን ልባችን የፈቀደውን ሰው ብናገኝ ሌላኛው ሰው ሊጎዳ ይችላል የሚል ፍርሃት ውስጥ እንገባለን፡፡ ቀላል እውነታ ግን ምንድነው? ፍቅርን አጋርን ማግኘት ፉክክር የሚጠይቅ ሂደት ነው፡፡

7. መገለል እና ልማድ

በተለይ ዕድሜ እየገፋ ሲመጣ ሰዎች የለመዱት ነገር ውስጥ ከልክ በላይ የመወሸቅ ፀባያቸው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ዘመናዊ ሴቶች በብዙ መልኩ ስኬታማ ናቸው፡፡ ይህ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዘመናዊ ወንዶች እና ሴቶች በሀብትም ይሁን በሌላ መልኩ ሊደላደሉ አንዳንዴ ከምቾት መጋረጃቸው ውስጥ ወጥተው ሰዎችን ለመተዋወቅም ሆነ ለመቀራረብ ይቸገራሉ፡፡ አደጋን ለመግፋት እና ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ ከረጅም የስራ ቀን በኋላ ብዙዎቻችን ወደ ቤታችን አምርተን ቢጃማ ለብሰን እረፍት ማድረግ እንጂ ወጣ ብሎ ሊያስፈራ የሚችለውን ሰዎችን የመተዋወቅ እና መቀራረብ ሂደት አንመርጥም፡፡

ቤት እንድንሄድ የሚያበረታታን አንድም ውስጣችን የሚገኘው ያ ድምፅ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ግድ የለም ብቻችሁን ብትኑ ይሻላል››፣ ‹‹ምን ጎደለባችሁ››፣ ‹‹እንደውም ልብስ ቀያይራችሁ ያንን የቴሌቪዥን መርሀግብር ተከታተሉ›› ወዘተ… ሊለን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ይኸው ድምፅ ኋላ መልሶ ‹‹ምን ነካችሁ! ዕድሜያችሁ እኮ ሄደ››፣ ‹‹ቆማችሁ መቅረታችሁ ነው››፣ ‹‹ብቻችሁን መሞታችሁ ነው›› ብሎ ሊረብሸን ይችላል፡፡
ስለዚህ እንደዚህ አይነት ልማድ ውስጥ ሰምጠን እንዳንቀር ወጣ ብሎ ሰዎች መተዋወቅ፣ የፍቅር አጋር እየፈለግን እንደሆነ ለጓደኞቻችን መናገር ወዘተ አስፈላጊ ነው፡፡

8. ህግ ማውጣት እና ማጥበቅ

ጊዜያቶች ሲሄዱ የተቃራኒ ፆታ ግንኙነትን የሚመለከቱ ህጎች ለራሳችን እናዘጋጃለን፡፡ በዚህ መሰረት በጎ ነው ብለን የምናስበውን ወረቀት ላይ እናሰፍራለን፡፡ ይሁን እንጂ ወረቀት ላይ ያማረ ነገር ተግባራዊ ሲሆን ላያምር ይችላል፡፡ ያለፈ ግንኙነታችንን መሰረት ያደረገ ህግ አውጥተን ለመኖር ስንሞክር አሳዛኝ አጋጣሚዎች ሊደጋገሙብን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ያማረ የሚሉት የፍቅር ህይወታቸው ሲፈርስ ‹‹ከዚህ በኋላ ከምወደው ሰው ጋር አብሬ መሆን የለብኝም›› የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡ በዚህ መሰረት ያን ያል ከማይወዱት ሰው ጋር ፍቅር ለመመስረት የሚያደርጉት ጥረት መጨረሻው ደስታ አልባ እየሆነ ይቸገራሉ፡፡

የፍቅር አጋር በምንፈልግበት ወቅት ልናደርግ የሚገባው ትልቁ ነገር ምን ጊዜም ልባችንን ክፍት ማድረግ ነው፡፡ እውነት ነው አንዳንዴ በዚህ ምክንያት ልንጎዳ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ላለመጎዳት በማሰብ ብቻ ልባችን ዝግ ሲሆን ደግሞ በአንፃሩ ወደፊት አብሮን ሊሆን የሚችልን ሰውል ናጣም እንችላለን፡፡
የፍቅር አጋርን የማገኘት ሂደት አልጋ በአልጋ የሆነ ጉዞ አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ሁልጊዜም በእኛ በኩል ያለውን ኃላፊነት መወጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ወደ ኋላ የሚጎትቱንን ውስጣችን የሚገኙ ልማዶች መዋጋት ያስፈልጋል፡፡ ራሳችንን እንዴትም ቢሆን ፍፁም ከአደጋ መከላከል አንችልም፡፡ ሁላችንም ደካማ ጎን ያለን ሲሆን እነዚህ ጎኖች ደግሞ በተለይ ሌላ ሰው እየቀረብን ስንሄድ መጉላታቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ ጥልቅ የፍቅር ግንኙነት መመስረት ትልቅ ጥረት የሚጤቅ ሲሆን ስኬቱም አስደሳች እና ‹‹እንኳንም ደከምኩ›› የሚያሰኝ በመሆኑ ውስጣችን የሚገኙ ጎታች አስተሳሰቦችን፣ ፍርሃቶችን፣ ልማዶችን መታገል እና መጣል አስፈላጊ የቤት ስራ ነው፡፡
Zehabesha.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>