Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“‘አማራ ኬላ’የሚባሉ አምስት ቦታዎች አሉ፣ የአማራ ተወላጆች በነዚህ ኬላዎች አያልፉም”–ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል

$
0
0

(የፎቶ ምንጭ፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

(የፎቶ ምንጭ፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

(ዘ-ሐበሻ) በክልሎች ስለሚፈናቀሉ አማሮች ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት? በሚል በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል “አሁን ቤንች ማጂ ዞን ብትሄጂ አሠቃቂ ነገሮች አሉ፡፡ እኔ አሁን ጉዳዩን እንዲያጣሩ የላኳቸው፣ የአማራ ተወላጆች አይደሉም፡፡ ለምን ብትይ “አማራ ኬላ” የሚባሉ አምስት ቦታዎች አሉ፣ የአማራ ተወላጆች በነዚህ ኬላዎች አያልፉም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን እንዲያጣሩልኝ የደቡብ ሠዎች ነው የላኩት፡፡ መረጃ የደረሠኝም በደቡብ ተወላጆች በኩል ብቻ ነው፡፡ አማራ ቢሄድ በመታወቂያው ይያዛል፡፡” በማለት አጋለጡ።
አዲስ አበባ ላይ ታትሞ ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ሰፊ ቃለምልልስ ያደረጉት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል “አምስቱም ኬላዎች ላይ ፖሊስ ቆሞ ይጠብቃል፡፡ምን ምን የሚባሉ ኬላዎች?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “አሁን ዝርዝሩን አምጡልኝ አላልኩም ግን እነዚህ ኬላዎች አሉ፡፡ በእያንዳንዱ ኬላም ጠባቂ ሚሊሻዎች ቆመዋል፡፡ አንዳንድ አማራ ወደዛ የቢዝነስ ሥራ ኖሮት ለማለፍ ቢፈልግ “ አንድ ሺ ብር ክፈል” እንደሚባልም ደርሠንበታል፤ ጉቦ ነው እንጂ መቸስ ደረሠኝ አይሠጠውም እኮ፡፡ ህዝቡ ተስፋ ቆርጧል፣ ሠልችቶታል፣ ከኢህአዴግ ጥሩ ነገር አይጠብቅም ብለውኛል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
“ከእንግዲህ ወዲህ ይሄ ህዝብ ወያኔ እድል ይሠጠኛል ብሎ እንደማይጠብቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡” ያሉት ኢንጂነር ኃይሉ “የቀረው ሆ ብሎ መብቴን አስከብራለሁ ብሎ ሲነሣ፣ ያን ጊዜ ማን መልስ እንደሚሠጥ አናውቅም፡፡ በቃ ይሄው ነው፡፡” ብለዋል። በተለይም በተቃዋሚ ድርጅቶች መብዛት ዙሪያ ሰፊ ገለጻ የሰጡት ኢንጂነሩ “ይህን ሁሉ ፖለቲካ ፓርቲ የሚያራባው ማን ይመስልሻል፡፡ ዘጠና እና ዘጠና አምስት ፓርቲ አለ እኮ ነው የሚባለው፡፡ ለምሣሌ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲ ሲመሰረት ሌላ አራት ይፈጠራል። ማን ነው የሚፈጥራቸው ካልሽ ራሱ ወያኔ ነው የሚፈጥራቸው፤ ደሞዝ እየከፈለ የሚያኖራቸው ፓርቲዎች አሉ አይደለም እንዴ፡፡” በማለት ከመንግስት ደመወዝ የሚቆረጥላቸው በተቃዋሚ ፓርቲ ስም የተመዘገቡ ድርጅቶች እንዳሉ አጋልጠዋል።
በቃለ ምልልሳቸው “እውነት ለመናገር ቅንጅትን ወያኔ ራሱ ነው ያፈራረሠው፡፡” ያሉት ኢንጂነሩ “አሁንም እያፈረሠ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፓርቲ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ አስርና አስራ አምስት ያህል ሠላዮች አሠማርቷል፡፡ እኛም ወስጥ ተሠማርተው ስራቸውን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ የእኛ ጥፋት ምኑ ላይ መሠለሽ፣ ዴሞክራሲ ብለን ስለተነሣን በየአካባቢው ያለው ሁኔታ ዴሞክራቲክ ነው በሚል ራስን በሚደልል ሁኔታ ግልፅ ሆንን እና ምስጢር የሚባል ነገር መያዝ አልቻልንም፡፡ በፊት ለፊት ስንሠራ ስለነበር ለወያኔ ተመቸነው፡፡” በማለት አብራርተዋል።
በቅርብ ቀን “ህይወቴና የፖለቲካ እርምጃዬ” በሚል መጽሐፋቸውን ሊያወጡ በዝግጅት ላይ ያሉት እንጂነር ኃይሉ “መፅሀፉ ስለቅንጅት መፍረስ፣ በአጠቃላይ ስለ ፖለቲካው ሁኔታ የሚዳስስ እንደመሆኑ፣ ከመነሻው ጠቅላላ ሂደቱን ይተነትናል፡፡ መጀመሪያውኑ ቅንጅትን ስንመሠርት አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን ሳላስተውል ቀርቼ አልነበረም። ነገር ግን “ግዴለም አብረን ስንሠራ ቀስ በቀስ ይስተካከላል” በሚል አምኜ አብሬ ተጉዣለሁ። ያንን ጉዳይ አሁን ላይ ሆኜ ወደ ኋላ ሳየው “ለምን ሳናጣራ ሄድን” ብዬ እጠይቅና እቆጫለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ግዜው አይፈቅድም ነበር፡፡ ህዝብ ከእኛ ብዙ ይጠብቅ ነበር፡፡ የጋዜጦችም ግፊት ከፍተኛ ነበር፡፡ የዛን ጊዜ ወደ ኋላ ብንል ኖሮ “መኢአድ እንደልማዱ ቅንጅት አንፈጥርም ብሎ ነገር አበላሸ” ይባላል በሚል ነው የቀጠልነው፡፡ ምክንያቱም መኢአድ ባይኖር ቅንጅት አይፈጠርም ነበር፡፡ ይሄ ግልፅ ነው።” ሲሉ ስለመጽሐፋቸው ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።

Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>