ከመምህር አብርሃ በላይ መቀሌ
መምህር ፍፁም ግርሙ የተባለ የዓረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ዛሬ በዓዲግራት ከተማ በፖሊስ ታስረዋል። መምህር ፍፁም የታሰረው ባለፉት ሁለት ቀናት በዓረና አባላት ላይ የተፈፀመው ደብዳብ አስተባባሪ የነበረች ትርሓስ የተባለች የህወሓት ካድሬ “እሱ ካልታሰረ ለራሴና ለልጆቼ ደህንነት እሰጋለሁ” የሚል አቤቱታ ለፖሊስ በማሰማቷ ነው።ትናንት ህወሓት ባደራጃቸው ዱርዬዎች፣ ሲቪል የለበሱ የፖሊስ አባላት፣ የከተማ አስተዳደር ባለስልጣናትና ሰላዮች መደብደባችን ይታወሳል። አቶ አስገደ ገብረስላሴ ሲታሰር ሌሎቻችን ደግሞ በፖሊስ ጣብያ ታግተን አምሽተናል። አቶ አስገደ ሌሊት ከእስር በዋስ ቢለቀቅም ፖሊስ በእሁዱ ስብሰባ ጥበቃ እንደማያደርግልን ስላሳወቀን የጠራነው ስብሰባ ሰርዘን ጉዳዩ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ዛሬ ጠዋት መቀሌ ገብተናል።
የዓዲግራት ተወላጆች የሆኑ አባላቶቻችን ግን ከሌላ ወረዳ በመጡ ቅጥረኞች “ከዓዲግራት ዉጥሉን” እያሉ ወደ ቤታችን ድንጋይ ሲወረዉሩ ዉለዋል። ድንጋይ ወርዋሪዎቹ የዓዲግራት ተወላጆች ሳይሆኑ በህወሓት አማካኝነት ከሌላ አከባቢ የመጡና የአከባቢው ሕብረተሰብ እያሰቃዩ ያሉ ናቸው። ቅጥረኞቹ ደብዳቢዎች ከዓዲግራት ህዝብ ጋር ሲጋጩ ነበር። የህወሓት ማፍያ ቡድን በሰለማዊ ዜጎች ላይ ድንጋይ በመወርወር የአምባገነንነት ሪከርድ ሰብሯል። ከዚህ በፊት አቶ አረጋዊ ገብረዮሃንስ የተባለ የዓረና አባል በባንዳዎቹ የህወሓት ቅጥረኞች መገደሉ ይታወሳል።
ዛሬ ከዓዲግራት ከተማ ህዝብ ባሰባሰብነው መረጃ መሰረት በህወሓት ተደራጅተው የዓረና አመራር አባላት እንዲደበድቡ ከተከፈላቸው ሰዎች አንድም የዓዲግራት ተወላጅ እንዳልነበረ ነው። የዓድግራት ኗሪዎች ህወሓት ማንነታቸው የማይታወቁ ዱርየዎች በመቅጠር የዓጋመ ህዝብን እንግዳ አክባሪነት ባህል ለማበላሸት መሞከሩ እጅግ አሳዝኗቸዋል። በመደብደባችን ክፉኛ ያለቀሱ እናቶች እንደነበሩም ለማወቅ ችለናል። እኛን ለማዳን ሲሉ ዱርየዎቹን ያባርሩ የነበሩ የዓዲግራት ወጣቶች ማምሻውን በፖሊስ መደብደባቸው ተሰምቷል።