![አቶ አሰፋ ጫቦ]()
አቶ አሰፋ ጫቦ
አስፋ ጫቦ Dallas Texas USA
መንደርደሪያ
የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ በሚያዝያ ወር 2008 በዋሺንግቶን ዲሲ (Washington,D.C) አከባቢ የ ት ዝ ታ ፈ ለ ግ መጽሐፌን ለማስመረቅ በተዘጋጁት ሁለት መድረኮች የታዘብኩትን ለማካፈል ነው::
ከሚያዚያ 14 እስከ ሚያዚዝያ 24,2008 Washington,D.C አካባቢ በተለይም ሲልቨር ስፕሪንግ (Silver Spring) ሰነበትኩ። የጉዞዬ ዋና ምክንያት የ ት ዝ ታ ፈ ለ ግ የተባለ የስብስብ ስራዬ ወደ መጽሐፍነት ስለተሸጋገረ አደባባይ ለማውጣት ነበር። ማስመርቅ ልንልም የምንችል ይመስለኛል። እዚህ አሜሪካ Book Signing Event ይሉታል።
ሁለት ወዳጆቼ መድረኩን አዘጋጁት። ሚያዝያ 16, 2008 አርታ አሌ ሆቴል ያሬድ ጥበቡ ወዳጆቹን ጋብዞ ያዘጋጀው ነበር። ሌሌዉ ሚያዝያ 21 2008 ታዋቂዋና የማከብራት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ያዘጋጀችው ነው።
ያሬድ ያዘጋጀው መድረክ ላይ ቡዙ ገጠመኞችም ነበሩ። የሆቴሉ ስም ራሱ፤አርታ አሌ ሆቴል፤ ለኔ ታሪካዊ ነው:: ከአፋር መሬት ከርሰ-ምድር የሚንተከተከው እሳተ ጎሞራ ስፍራ ስም ነው።የጓደኛዬ ልጅ፤ዶሊ፤ሀች-አምና ጎብኝታው ያነሳችውንና የተነሳችበትን ምስል Facebook ላይ ለጥፋ አየሁት:: ፈረንጅ ጎብኝዎች የለጠፉትን ከማየት በላይ አላጤንኩትም ነበር።ከኔ (ከኛ?) ይበልጥ ፈረንጅ ያውቀዋል እንደማለት ይመስለኛል።እዚህ አሜሪካ ታዲያ የሆቴል ስም ሆኖ ብቀ አለ::
አራት በር ያለው ዘመናይ ምግብ ቤት ነው። ይበልጥ የገረመኝ ባለቤቱ፤ዶክተር ሰለሞን፤ ሐኪም ነው።ስለደነቀኝም ምክንያት ፈልጌ ደጋግሜ አነጋገርኩት።አለባባሱ፣አነጋገሩ፤የቃላቶቹና ሐሳቦቹም ምርጫ ፤አገለለጹ (Body Language) ጭምር የአሜሪካን ዘመናይ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አይነት ሆነብኝ። ለመሆኑ ስንቶቻችን እንሆን ተፈጥሮ በለገሰን ስጦታ ሳንሰማራ ቀርተን እንዲህ ጓደኛ ወይም የሰፈራችን ልጆች በሔዱበት ፈለግ የተከተልነው? አሰኜኝ። በኔና በዶክተር ሰለሞን ዘመን ዝንባሌህ/ተሰጥኦህ እንዲህ ነውና የህንን ወይም ያኛውን ብታጠናው/ብትማረው ይሻላል የሚል አልነበረም። የአሁንን አላውቀውምና የምለው ብዙም የለኝም።
የአሁን ትምህርት፤ ትንሽ በፍንጭ ብቻ እንደማገኘውና እንደምሰማው ምኑም ምኑም የሚጥም አልመስለኝም።ከሹሞቻችን የአንዳንዶቹ ያልላመ ሽርከት ትምህርት ከወፍጮ ቤት (Degree Mills) የመጣ ነው እየተባለ አበበ ገላውና ሌሎችም በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ ሲያቀርቡም አያለህ።”ከመጠምጠም መማር ይቅደም!” (እዚህ ከመሿሿም በፊት ልንለው እንችላለን) የሚባለው ለዚህ ይመስለኛል። ቾኩሎ አጉል ይጠመጥምና “ገብርኤል ፈጣሪዬ!” ሲል እጅ ከፍንጅ ይያዛል:: እዚያ ሌላ ምክንያት ፈልጌ ሌላ ቀን ብመልስበት የሚሻል ይመስለኛል።
አንድ ልረሳው የነበረው ነገር!! በስራ ምክንያት ከመሔዱ በስተቀር ዶክተር ሰለሞን አፋር አይደለም።ይህ ደሞ በመጠኑም ቢሆን ሰፋ ያለ ስዕል መሳል የመቻልን አዝማሚያ የሚጠቁም ይመስለኛል።በተለይም ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሆቴሉ፤የንግድ ድርጀቱ፤የመንግስት መስሪያ ቤት ስሞች፤በተለየም የኢትዮጵያ ፓሊስና ወታደር ማዕረግ ከኢትዮጵያ ተፋቶ የእንግሊዝና የአሜሪካ ስም በሆነበት ዘመን መሆኑ የበለጠ ክብደት የሚሰጠው ይመስለኛል።
ት ዝ ብ ቱ
መጽሐፉ ምረቃ ላይ ንግግር፣መግለጫ ልንለውም የምንችል ይመስለኛል፤አደረኩ። መጽሐፉ ስብስብና 28 ምእራፎች አሉት። ዝርዝሩ ውስጥ አለገባሁም። አብነት ይኖራቸዋል ያልኩትን ጥቂቶች አነሳሁ።ከዚያ በፊት ግን መጽሐፉ የተዘርጋበበት ንፍቀ-ክበበ፤ትልቅ ምስል፤(Vista,Big Picture) ለማሳየት ሞከርኩ። መጽሐፉ ውስጥ ያሉት ምናልባት ካንድ ሁለት በስተቀር መድረኳ ኢትዮጵያ ነች። ስለዚህ ከኢትዮጵያ፣ማለትም ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር አዛምጄ ለማቅረብ ሞከርኩ።በዚህ አጭር ጊዜ፤በዚች በአንድ መጽሐፍ ሰበብ የኢትዮጵያን ታሪክ መዳሰስ እኔም ሆንኩ ማንም ሊያደርገው የሚችል አይመስለኝም። የኢትዮጵያን ህዝቦች ታሪክ ትልቁን ምስል በዚህ በተነሳው ጉዳይ ዙሪያ ለመሳል ሙከራ ነበር። ቢቻል ታሪኳን የምናይበት ሰፋ ያለ ትልቅ መንጽር ለመስራት ሙከራ መሆኑ ነው።
እዚህ ላይ አንድ የግርጌ ማስታወሻ (foot note) የሚሉትን አይነት ነገር ማለት እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ ታሪክ ስል እኔ ታሪክ ነው የምለውን አይደለም። በተቻለ መጠን ተጽፎ፤ተመዝግቦ፤ዛሬ ምድሪቱ ላይ ባሉት ሕዝቦችዋ ላይ የሚነጸባረቀውን እውነት ነው።ሕዝቦችዋ ደግሞ የብዙ ዘመናት አነባበሮ ናቸው:።ግምቴናምኞቴን አይደለም። ለፖለቲካ ፋይዳ ተብሎበግምት፣ተጣሞም፣ተንሸዋሮም ሲቀረብ አይና ወይ ይደነቀኛል፤አንዳንዴ ያስደነግጠኛል። መጽናኛዬ ግን “ይኸ ሀላፊና ረጋፊ ስለሆነ ትግስትና ጊዜም ስጠው!” የሚለው ነው። አጋጣሚው ሲገኝ ደግሞ አውራ ጎዳናው በዚህ በኩል ነው ብዬ ከመጠቆምም ወደኋላ አልልም።ወደኋላ አለማለት ነው!! ሆኖም ያኛው ወገን የሚለው ውስጥምኮ አንዳንድ እውነት አይጠፋም ማለቱ ጥሩ ነው። በር አለመዝጋት!አለመቀርቀር! ለማለት ነው። የእውነቱ ብቸኛ ባሌቤት (Monopoly) ያለው የለም!
ሁለቱም አውዶች ላይ በአካል ቋንቋ (Body Language) ሆነ በቃላት የተገለጠው ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ነበር ለማለት የምችል ይመስለኛል::በጥሞናና በተመስጦ የማዳመጥ ነገር በእያንዳንዱ ፊት አያለሁ::አነባለህ! ቆሜስለምናገር፤ተቀመጠው ስለሚያዳምጡ፣ ለማስታዋል ከሁሉም የተሻለ እድል ነበረኝ። በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ኦርቶዶክሶቹ “አልዕሉ አልባቢክሙ ሀበ እግዚአብሔር….” የሚሉት አለ።ልቡናችህን አንቅታችህ/አንግሳችህ አድምጡ ለማለት ይመስለኛል። ያንን ያየሁ ይመስለኛል!
ጣይቱ ማእከል የማደርገውን ገለጻ ጨርሼ ቁጭ ስል አጠገቤ የነበረው አያሌው ከበደ “ጋሽ አስፋ ሰውኮ ቆሞ ያጨብጭባል!” ሲለኝ አፍሬና ደንግጬ ተነሳህ። ፈርንጆቹ Standing Oviation የሚሉት ነው።ከዚያም ወደጥያቄና መልስ ወይ፤ወደ አስተያየት መስጠት ተኬደ።
በጥያቄና መልሱ ወቅት ሁለት ነገሮች/ ነጥቦች ጎልተው የወጡ ይመስለኛል። አንደኛው፤ ከጥያቄ ይልቅ የአስተያየቱ አይነነት ተቀራራቢነት ነበረ።”…ዛሬ የነገረከኝ አዲስ ነገር የለዉም!ያው የማውቀውን ወይም አውቃለሁ የምለውን የአገሬን ታሪክ ነው። አንተ፤እንዲህ አቀራርበህ፤ፈተህ፣አቃለህ ተርጉመህ ስትነገርኝ እንዴት አባቴ ሆኜ ነው እኔ እንዲህ ሳላይ የቀረሁት!” የሚል ነው። ቃል በቃልም ባይሆን መንፈሱ የኸው ነበር።እንዲያ ተከፍቶ ሳይታይ በባከነ ጊዜ/ ዘመን መቆጨትያለበት መስሎ ታየኝ።ሁለተኛው ክፍልደግሞ “ነገም ይነጋል!መንገድም፣ አማራጭ መንገድም ሞልቷል። ያንን የመፈለግ እንጅ አለቀ-ደቀቀ የሚያሰኝ ነገር የለም!” የሚል ነበር። በተስፋና በይቻላል መልክ መመልከት ልንለው የምንችል ይመስለኛል። Posetive Thinking የሚሉት። “ጥሩ ተመኝ ጥሩ እንድታገኝ”እንዲሉ።
የሰው ስብጥር ራሱ ገረመኝ። በእድሜ ከ50 በላይ የምንሆነው እኔን ጨምሮ 10% ብንሆን ነው። በአብዛኛው ምሁር፤ሊቀ ሊቃውንት ሊባል የሚችለው ስብጥር መስለኝ።ይህን ያውቅኩት ያሬድ ጥበቡ ያዘጋጀው መድረክ ላይ ነበር:: መጽሐፉን ለገዙት ፊርማና ትንሽ አስተያየት መጻፍ እንደጀመርኩ ነበር። “ለአቶ” ብዬ ስጀመር ያሬድ ” አሴ! ምን ነካህ? እሱኮ ዶከተር ነው !”አንድ ሁለቴ ሲለኝ “ማእረግህን ምን ልበል?” ማለት ጀመርኩ። እንደገመትኩትኩት አንድ አስሩ ያክል በየመስካቸው ዶክቶሮች ነበሩ።
ሌላው የማውቀው የሚያውቀኝ ብዙ ሰው አገኘሁ። ማእከላዊ የማውቀውን ምስማኩ አስራትንና መስፍን ቡልቻን አገኘሁት። መስፍንን ረስቼው ኖሮ ደጋግሞ “ጋሽ አስፋ ምን ነካህ ?!መስፍን ቡልቻኮ ነኝ!” አለኝ። ለካስ አንዴ የጻፍኩት መጻጽፍ ላይ መስፍን ቡልቻንና ሳምሶን ሙላትን አንስቼ ነበር። ቀና ብሩህ የመርካቶ ንጋዴ ልጆች ነበሩ። ሳምሶንን የዛሬ ስንትስ አመት Cambridge, Massachussettes አገኘሁት። የኮከበ ጽባህ ልጆችን ከኔ ቀደም ሲል የነበረውን ኢሳይያስንም ጭምር አገኘሁት። አንድ የአርባ ምንጭ ልጅም አገኘሁትና “ስለ አርባምንጭ አልጻፍኩም ይቅርታ ስለጋሞና ስለጨንቻ ጽፌአለሁና በዚያ ተካካስ!” አልኩት።
ጣይቱ ማእከል ሌላው የደነቀኝ፤በተለምዶ በየወሩ የግጥም ንባብ አለና የዚያን ማታ የተነበበው ነበር። ገጣሚዎቹች ወጣት ልጆች ነበሩ። ግጥማቸው ምራቁን አጣጥሞ የዋጠ፤ክንፍ ያለው፤ወደላይ ወደሕዋው የነጠቀ ፤የመጎርጎር፤ እግር ያለው፤ ስንጥሮ ወደ እመቀ እመቃት ወርዶ ጉዳችንንና ለእልናችንን የሚያበስር ነበር።
ከሁሉም በላይ የጀነራል መርዕድ ንጉሴን ልጆች አስተዋይንና እህቱን አገኘኋቸህ። አስተዋይ መርዕድ ከኔ ጋር ማእከላዊእ፣ታች ግቢ፣7 ቁጥር፤ ጨለማ ቤት አብሮኝ ታስሮ ነበር። የትዝታ ፈለግ ከተዘከረላቸው ሰዎች አንዱ ጀነራል መርዕድ ንጉሴ ነበሩ። ትንሽ ተላቀስን!! የልባችን ሳይደርስ በሰው ብዛት ተለያየን።የእለቱ ሙሽራ አየነትም ስለነበርኩ ያንንም ይሕንንም ሳነጋገር በቂ ጊዜ አለነበረኝም። ለዚያውም ከአደራሹ ሰአት እላፊ ደርሷልና ውጡ ተበለን ነበር የተለያየነው።
ያንለት ማታ ኩኩ ሰብስቤም አገኘኋት። በዝና እንጅ አንተዋወቅም። የመጣሁ ሰሞን ወንድምዋ DC ምን የመስለ ምሳ ፖቶማክ (Potomac) ወንዝ ዳርቻ ጋብዞኝ ነበር። ኩኩን በቅርበት የተዋወውኩት ራት ላይ ነበር።
ራት-ምሳ ግብዣ እንደልብ ነበር። 10ሩን ቀን መኝታዬ ጋ የምደረሰው ሁሌም ከዘጠኝ ሰአት በኋላ ነበር። አንዱን ምሸት፤ በማላውቀው ከተማ፤ዝናብ እየጣለ፤በማላውቃት፤በማታውቀኝ ሴት መሪነት (GPS) ወደቤት ሲሐድ ፖሊስ አስቆመኝ።መኪናዬ (የተከራየሁት) የተሰመረለትን ስቶ ሳይዋዥቅ የቀረ አይመስለኝም: እነደተለመደው መንጃ ፈቃድ ጠይቆኝ “ስትጠጣ ነበር?!” አለኝ። “አዎን!” አለኩት “ምን?!” ሲለኝ “ውሐ!” አለኩት። እውነቴን ነበር። ያን ያህል የምውደው ዊስኪ Johny Walker ጭመር ጣእሙ ጠፍቶብኝ መጠጣት ካቆመኩ ዘመን የለውም። ፖሊሱ ታዲያ ጢም ብሎ ሰክሮ የንገዳገዳል።ጨንቻ “ድንቄም! ዋሪቴም! ዋኬኔም!” የምሉትን አስታወሰኝ። ዋሪቴ ማን እንደሆነች አላውቅም። ወደዶርዜ መሔጃው ላይ፤ከመሪጌታ ብቃለ ከበበው ቤት ዝቅ በሎ፣ጋሽ ጣሴ ዋኬኔ እነደነበረ አውቃለሁ። “ድንቄም ሕግ ማስከበር!” ለማለት ነው።
ብቻ ራት ለመብላት ሔድንና ኩኩም መጣች።”አንተ ከበዛ ወርቅ አስፋው በስተቀረ ለመሆኑ ሌላ አርቲስት ታውቃለህ?” ብላ ጀመረች። የበዛወርቅን የ ት ዝ ታ “እስላም ክርሲቲያኑን እንዲህ ያዋሐደው፤ማቱቡ ነውከጥንት አብሮ የገመደው!”የሚለውን ደጋግሜ አንስቸው ኖሯል።” የአንችንም ዘፈን በጣም እወደዋለሁ!” አልኳት። “መች በአደባባይ መሰከረክ!?” አለችኝ። “እንዲያውም ከአርቲሲስቶቹ ሁሉ የምትቀረብኝ አንች ነሽ!” አልኳት። “ለምን?” ብትለኝ “አንቺም እኔም የጨንቻ ልጆች ነንና!” አለኳት። አባትዋ፤ደጃዝማች ስበስቤ ሽብሩ፤እኔ ልጅ ሳለሁ የጋሞ ጉፋ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ነበሩና አንድ ክረምት ልጆቻቸው ጭምር መጥተው ማየቴን ነገርኳት። ተማመንና ሁለትየጨንቻ ልጆች ተባብለን ተዛመድን። ኩኩ ሰብስቤ፤የተዝናናች፣እንደልብዋ የምትናገር፣የምትጫወት፣የምትጫወተውን የምታውቅ(small Talk)፣ነጻ የሚሏት አይነት (Cosmopolitan) አርስቲስት ሁና አገኘኋት።አነጎራጎረችልንም!
ቀኑ አርብ ምሸት፤የኦርቶዶክሶቹ ስቅለት ለት ነበር። የገረመኝ አንድ እኔ ያለሁበት ማእድ ሲቀረ የተረፈው የጾም ራት ነበር።ያልጠበኩት ስለነበር ገረመኝ። ከዚህ ትምህርቱ፤ለኔ፤ሌላውን በራሳችን መመዘኛ ብቻ አለመለካቱ ጥሩ መሆኑን ነበር።
ሌላ ከእለቱ ቅኝት፤ማለትም ከመጽሐፉ መረቃ ጋር የማይሔድም ገጥሞኝ ነበር። ያንን የመጨረሻው ጠያቂ ሆኖ የመጣው በዕዉቀቱ ሥዩም ነበር። “ኢ.ጭ.አ.ት(የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) የሚባል የደርግ ዘመን የፖለቲካ ድርጀት ሊቀ መንበር ነበርክና ስለዚያ አስርዳን” አለ። አንድምታዉ “ጠባብ ብሔርተኛ ሆነህ ደግሞ ስለኢትዮጵያ ታወራለህ!” እንደማለት መሰለኝ።
መጀመሪያ የመጣለኝ Non Sequitur[1] ነው። Non Sequitur ማለት” ይህ ከዚያኛውአይከተልም!” እንደማለት ነው። የህግ ባለሙያን ነኝ።በዚህም ላይ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ አመት ይሁን ሁለተኛ ተማሪ ሳለሁ ፈልስፍና 101 የሚባለውንም ወስጃለሁ። ይህ 101 ደግሞ ሎጂክ (Logic) የሚሉት ነው። በዕውቀቱ ደግሞ ዩኒቨርስቲም ተምሯል። ያ 101 አሁን መኖር አለመኖሩን አላውቅም። ብቻ ሰለኢ.ጭ.አ.ት አስረዳሁ! “ለመሆኑ ከዚህ ጋር እንዴትአገናኜኸው?”አላልኩም። ያተገቢው መልስ የነበር ይመስለኛል ።
በእውቀቱን አምና ዲስ የሔድኩ ጊዜ ከሌሎች “ጋሽ አስፋ ያንተን ጽሁፍ እያነበብን ነው ያደግነው!” ከሚሉት ብዙ ወጣት ምሁራን ጋር አግንቼው ነበር። እንዲያውም ያንተ ጽሁፍ ስበስብ በሙሉ አለኝ ብሎኝ ይህ መጽሐፍ የማድረጉ ሀሳብ የመነጨው ከበውቀቱ ነበር። ኢትዮጵያ ሲመለስ እንዲተባበሩት የልጄንና የእህቴንም ስልክ ቁጥር ሰጠሁት። ከዚያ በFacebookና በemail ብለው- ብለው ጠፋ! ጠፋ! የሰጠኝ ስልክ አንዴ ስደውል አንድ ሰው ጸያፍ መልስ ሰጠኝና ተውኩት።አሁን እነደገና አሜሪካ መጣ ሲሉ ጊዜ ስልክ ቁጥሩን ፈልጌ ስደውል ዘጋብኝ። ለካ መጽሀፍ ሊያሳትም ኖሯል።
አሁን ሳየው ለካ በዕውቀቱ እኔ “ማነው ነፍጠኛ ?”በሚል የጻፍኩትንና በቃለ መጠይቅም የሰጠሁትን ቃል በቃል ጠቅሶ ለአጼ ምንሊክ መልሶ ማቋቋሚያ (Rehabilitation) በሚመስል ተጠቀመበት። መጀመርያ፤ነገር የኔ “ማነው ነፍጠኛ?”መንፈስ ማንንም መልሶ ለማቋቋም ሳይሆን ታሪክ በተገቢ መልኩ እንዲታይ ነበር። ምንሊክም ሆነ ማንም እውነተኛና ታሪክ ነጋሪ እንጅ መልሶ ማቋቋምን የሚፈልጉ አይመስለኝም።በዚህ ላይ ከእገሌ ውሰደኩ ማለት ስነምግባር ብቻ ሳይሆን ሕግም ነው። እኔ ሕግ ትምህርት ቤት የዚህ ፕላጄሪሲም(Plagerisim) የሚባለው ለ4 አመት ዳኛ ነበርኩ። “ከእገሌ ወሰደኩ” ሳይል ፤የግርጌ ማስተዋወሻ (footnote)ሳይለጥፍ የሚጽፍ ተማሪ ለመቅጣታት የተቋቋመ Honer Court ይባል ነበር።
ይህ ደግሞ ሌላ አስታውሰኝ። የት ዝ ታ ፈለግ ውስጥ የኔይቱ ጀገና የሚል ስለዘውዲቱ አስማረ የተጻፈ አለ። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “የኔ ጀግና!” በሚል መጽሀፍ ጽፏል ተባልኩና ያ መጽሐፍ ስሞኑን ሊመጣልኝ ነው።”ከአሰፋ አገኘሁ” አይልም ። ሕጉ ይቅርና ከእገሌ ውሰድኩ ነውርነት የለውም። ወጥ ሐሳብ ያለን ጥቂቶች ነን።አብዛኛዎቻችን ሌላው ከተናገረውና ከጻፈው እያዳብረን ነው።
በዕውቀቱ ሥዩም የትና የት ሊደርስ የሚችል ጸሐፊ፤ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነው። ግጥሞቹ፤ቢያንስ እኔ ያነበብኳቸው፣የመጠቁና ፍልስፍና የሚሞክራቸው ናቸው። በእውቀቱ እንዲባክንብን አልፈልግም። ተስፋዬ ገብረአብ ምን የመስለ፤የትና የት ይድርሳል ያልኩት ደራሲ ባከነበን። አልባሌ፤አላፊ ጠፊ፤ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የባከነብን ይመስለኛል።ለዚህ መድኅኒቱ ለጥበቡና ለራስ ታማኝ መሆን ነው።ለነዚህ ታመኝ የሆነ ዝንተ አለም ታማኝ ሁኖ ይኖራል።
ትምሕርቱ
እኔ ከዚህ መጽሐፍ ምርቃ ዘላቂ ትምህርት ያገኘሁ ይመስለኛል።ነገር ዓለሙ ሁሉ ሰበብ-አስባብ ይፈልጋል ልንልም የምንችል ይመስለኛል። በዚህ በሳይንሱ ክሪቲካል ማስ (Critical Mass)የሚሉት አይነት መሆኑ ነው። “ሰኔና ሰኞ!” ሲገናኝ እንደማለት ነው ። በክርቲካል ማስ ወሐ ሲፈላ ይተናል። ሲቀዘቅዝ ደግሞ ወደበርዶነት ይለወጣል። ያንን ሲያሞቁት ወይም ሲያቀዘቅዙት ደግሞ ውሀ ይሆናል። የኔ አንዲት ስብስብ መጽሐፍ ያንን ያክል” ሰኔና ሰኞ “ሆናለች ለማለት አይደለም። ለማለት የፈለኩት አንዳች ነገር ሊሆን ወይም ላይሆን ሰበብ አስባብ ይፈለጋል ለማለት ነው። ከዚህም ተነስቼ የ ት ዝ ታ ፈ ለ ግ ሰበብ አስባቡ ሆና ያው ውስጣችን የታመቀንና ሊወጣ ምክንያት ሲሻ የነበረውን አውጣችው ወይም ለመውጣቱ ምክንያት ሆነች ለማለት ነው።
ለዚህ እስቲ ሁለት አባባሎችን እንውስደ። አንደኛው “ጠርጥር ገንነፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር”ና ሌላው “ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ!” የሚሉትን። ይህንን በዘመናይ ቋንቋ Negative versus Posetive thinking ብለን ልናይ እንችላለን። ነገርን በቀና መንፈስና አጣሞ በመትርጎም ውስጥ ያለ ልዩነት መሆኑ ነው።
በዚህ “ገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር!” ላይ June 26,2016 አንድ በኔ ላይ የደረስ ምሳሌ ልስጥ።አንድ ሰው፤እዚህ ስሙን መጥራት የማልፈለገው፤ Facebook ላይ “ወዳጅ ልሁን “ብሎ ጠይቆኝ “እንኳን ደህና መጣህ!” ብዬ ተቀበልኩት። ቀጥሎ “ጤንነትህ?” ሲለኝ “እዚህ አሁን በጋና ወበቅም አለው” አልኩኝ። “ለመሆኑ የት ነው ያለኸው?” አለኝ.” Dallas Texas USA” አልኩት። “አሜሪካ ነው?” አለኝ::”.USA አሜሪካ ማለት ነው” አልኩኝ። “USA አሜሪካ መሆኑን ከአንተ በፊት አውቃለሁ!” አለኝ። በኔ ግምት ይህ “ገንፎ ውስጥ አይጠፋም ስንጥር” ሳይሆን ገንፎው ውስጥ ስንጠር ጨምሮ “ይኸው ስንጥር አለበት!” ብሎ ማስረጃ ለማቅረብ እንደመሞከር ነው። አንዳንዱ የፖሊቲካ አስተያየት ሳዳምጠው የዚህ ጣእም/ ምሬት/ሬት ያለው ስለሆነ ይሰውረን ነው። እኔ ይህንን ግለሰብ ከውዳጆች አንባ ሰርዠው ተገላገልኩ። ይሰውረን ማለት ነው የሚበጀው።
ገልጠን ብናየው
ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝን ለማስረዳተ ከፍ ብዬ አንስቼ የነበረውን እዚህእንዳለ እደግመዋለሁ:-
እዚህ ላይ አንድ የግርጌ ማስታወሻ(footnote ) የሚሉትን አይነት ነገር ማለት እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ ታሪክ ስል እኔ ታሪክ ነው የምለውን አይደለም። በተቻለ መጠን ተጽፎ፤ተመዝግቦ፤ዛሬ ምድሪቱ ላይ ባሉት ሕዝቦችዋ ላይ የሚነጸባረቀውን እውነት ነው።ሕዝቦችዋ ደግሞ የብዙ ዘመናት አነባበሮ ናቸው:: ግምቴና ምኞቴን አይደለም። ለፖለቲካ ፋይዳ ተብሎ በግምት፣ተጣሞም ፣ተንሸዋሮም ሲቀረብ አይና ወይ ይደነቀኛል፤አንዳንዴ ያስደነግጠኛል። መጽናኛዬ ግን “ይኸ ሀላፊና ረጋፊ ስለሆነ ትግስትና ጊዜም ስጠው!” የሚለው ነው። አጋጣሚው ሲገኝ ደግሞ አውራ ጎዳናው በዚህ በኩል ነው ብዬ ከመጠቆምም ወደኋላ አልልም።ወደኋላ አለማለት ነው!! ሆኖም ያኛው ወገን የሚለው ውስጥምኮ አንዳንድ እውነት አይጠፋም ማለቱ ጥሩ ነው። በር አለመዝጋት!አለመቀርቀር! ለማለት ነው። የእውነቱ ብቸኛ ባሌቤት(Monopoly) ያለው የለም!
ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንግግር፣ንትርክ፣ጭቅጭቅ፣ዉዝግብ ውስጥ በአብዛኛው ይህንን የማየው ይመስለኛል። ጤነኛናውን በሽተኛ ነህ ብለው ነገሩት። ጉንፋን የያዘው፣በነጭ ሽንኩርት፤ በጦስኝ፤ግፋ ቢልም አስፕሪን ወስዶ እንዳይድን ካንሰር ይዞሐል አሉት።ካንስረ ደጎሞ ቀዶ ጥገናን የሚጠይቅ በሽታ ነው።ብአብዛኛው ቀሳፊ በሽታም ነው። ነገሩ ያለው መጀመሪያውን ታመሐል ያለው ሐኪም የህክምና፤የሕመም አይነት የመለየት፣የመቻል ባለሙያ አለመሆኑን የመረዳት ጉዳይ ነው። ግፋ ቢል የዚህ በዘር ከፋፍለህ ግዛው የቅርብ ምንጩ የሙሶሊኒ የጣሊያን የምስራቅ አፍሪቃ ግዛት (Africa Orientale Italiana መሆኑ የመረዳትና የማስረዳት ጉዳይ ነው። ጉንፋንና ካንሰርን ለይቶ የመረዳት ጉዳይ ነው።
ታዲያ በዚህ በየድህረገጹ በተለይም የአማራና ለኦሮሞ መብትና ግዴታ እንታገላለን የሚሉት የሚገርመው ክርክራቸውና አስተያይታቸው ከኢትዮጵያ የተፋታ መሆኑ ነው። ኦሮሞ ከራያና አዘቦ ጀምሮ ያሌለበት ክፍለ ሐገር የለም። ኦሮሞ በኢትዩጵያ በሕዝብ ቁጥር አንደኛው ነው።በምራጫ እንኳን ቢከድ አብላጫው ኦሮሞ ስለሆነ የኦሮሞ መንግስት ነው የሚሆነው። ከዘመን መሣሳፍንት ጀምሮ፤ ልጅ እያሱን፣ንግስት ዘውዲቱን፤ኃይለ ሥላሴ፣ጀነራል ተፈሪ በንቲንና መንግስቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ መሪዎቻችን ኦሮሞዎች ነበሩ።ከ108 የደርግ አባላቱ ውስጥ ግማሽ ያክሉ ኦሮሞዎች ነበሩ። ከወያኔ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንቶችና ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን የሚያስተዳድሩት ከንቲባዎቹ ኦሮሞች ናቸው። ያም ሆኖ በክርክራቸው፤ሙግታቸው፤ጭቅጭቃቸው ውስጥ የኢትዮጵያን ስም አይጠሩም። ይህ እንዲህ ከፍተው ሲያዩት ግራ የሚያገባ ነው። ወይም አዲሱ የወያኔ ክትባት፤ ካንሰር ታመሐል የሚለው እውነቱን ፍቆታል ማለት ነው። ዛሬ የመንግስት መሪዎችም የኢትዮጵያን ስም አይጠሩም። “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! የሚለውን የምሰማው የሸገርን 102.1 FM ራዲዮ ስከፍት ብቻ ነው።ሰንጥር ገንፎ ውስጥ ጨምሮ “ይኸውና!” ማለት መስሎ ይታየኛል።
ሌላው የፖለቲካ ሊቃውንት ነን የሚሉ ሁሉ ሲናገሩም ሲጽፉም የሚክድዱት የ17ቱን አመት የደርግ ታሪክ ነው። የማያከራክረው ግፉና ጭካኔው ላይ ያቶኩሩና ሌላውን ይክዱታል። ብዙዎች ደግሞ የራሳቸውን ጉድ ለመሸፈን ደርግን መሽሎኪያ ቀዳዳ (Escape Goat)ሲያደርጉት ይታያሉ።ደርግ የሰራቸው ዘለዓአለማዊና ታሪካዊ ድርግቶች አሉ።ኢትዮጵያን ሬፑብሊክ አድርጓል። በሐይማኖት እኩልነት የእስልምና ተከታዮችን በአላት ብሔራዊ በአል አድርጎታል።ብየካቲት 25,1967 የገጠር መሬት አዋጅ ሕዝቡን ፤በተለይም የደቡብ ኢትዮጵያን ህዝብ ከዘመናት ጢሰኝነት፤ገባርነት ገላግሏል። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ደግሞ አብዛኛው ኦሮሞ ማለት ነው።የካቲት 25,1967 የምኒልክን የአስገባሪነት ቀነበር ደመሰሰ(Null and Void) ማለት ነው:: እርግጥ የሚቀጥል የመብት ፤የነፃነት የብሔረሰብ ጥያቄዎች አሉ። ያንን የምንጀምረዎ ከባዶ፤ከዜሮ ሳይሆን ደርግ ባጎነጸፈን ድል ላይ ተመስርተን ነው። 17 አመት የኢዮጵያን፤ያንድ ሀገርን ታሪክ መካድና “አላየሁም! አልስማሁም!” ማለት ለፖለቲክ ንግድ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።የጤናም አይመስለኝም!
ሕዝቡ ግን እውነቱን ያውቃል።አንድ ማስረጃ ልጥቀስ።ሶማሌ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ሚሊሽያ የሆነው የኢትዮጵያ ገበሬ “ተነስ!” ሲባል ራሱ ገንፍሎ፤ፈንቅሎ ነበር ከዳር እስከዳር የወጣው። ” ለዛሬ ይበቃልና ወደቤታቸሁ ተመለሱ!” ሲባሉ “አንመለስም!” ብለው ያለቀሱ እንደነበሩ የዐይን ምስክር ነበርኩኝ። ከዚህ አንዱ አርባምንጭ ላይ ከጎፋ አውራጃ፤ከባንካ ማስኬቶ ወረዳ የመጡ ሁለት እደሜያቸው 20 ውስጥ ይሆኑ ሴቶችን አርባ ምንጭ ላይ “ተመለሱ!!” አልኳቸው።ልንጓጉዘው ከምንችለው በላይ ስለመጣብንና ምናልባትም ሴቶችን ማስተናገጃ አልተዘጋጀም ይሆናል በሚል ግምትም ጭምር ነበር። አለቀሱ! “አስፋ አትዘምቱም ብሎናል!” ብለው የደርግ አባል ለነበረው በንጉሴ ወልዴ ላይ ከሰሱኝ። ዘመቱ! “ነጻ ያወጣንን አብዮት ጠላት አይቀምንም!” ነበር መልእክቱ:
ያለፈ ዘመን ቁስል፤ የሻረ ቁስል መርቁዟል ያሉ፤የአገራቸውን ስም በአደባባይ መጥራት ያልፈለጉ፤”የጋራ ቤታቸውን” የካዱ የት እንደደርሱ የትላንትናዋ ዩጎዝላቢያ፤የዛሬይቱ ብጥቅጣቂ ወይም ወደዚያ በማምራት ያልቸውን ሶሪያን ልብ ይሏል።ትምህርቱ ከታሪክ መጽሐፍት ሳይሆን ፊት ለፊታችን ተገትሯል! ተውጥሯል! ተሰትሯል!
ሲጠቃለል
የትዝታ ፈለግ ከጠበኩት በላይና ውጭ ሔዶብኛል።ምን ጠብቀህ ነበር ብባል መልስ የለኝም።መጀመሪያ በመጽፍሐ መልክ መታተሙ ራሱ የኔ ሐሳብ አልነበረም።” የአንተን ጽሁፍ እያነበብን ነው ያደግነው” በሚሉ ወጣቶች አነሳኝነት ነበር።እዚህ አሜሪካ በምረቃው ላይ የሆነውን ለመግለጽ ሞክሪያለሁ።በስልክ፤ በFacebook, በemail በMessenger የደረሰኝ መልዕከት ቁጥር ስፍር ያለውም።መልእከቱ ከመላው አለም ነው ለማለት እችላለሁ።ከኢትዮጵያ፣ከጨንቻ ጀምሮ ደሴ፤ባህር ዳር ጎንደር፤መቀሌ ይገኙበታል።ይበልጥ የደነቀኝ የአቦቦነሽ አበራ ነው። አቦነሽ አሁን የተዘጋው የኢትዮጲ መጽሔት አባልና አዘጋጅም የነበረች ነች::Facebook ላይ ነው የተዋወቀነው።በስደት ናይሮቢ፤ኬኒያነውያለችው።መጽሐፉንይዛየተነሳችውንፎቶግራፍ ለጠፍችው።መልዕክቱ”መጽሐፉን በቁጥጥር ስር አዉለነዋል!” ይላል። በስልክ “እንዴት አገኜሽው?” አልኳት። “ተከራይቼ ነው!” አለችኝ።
የት ዝ ታ ፈ ለ ግ ውስጥ ሰዎች፤አነባቢዎቹ ምን አዩበት? ምን ታየበት? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ጥሩ ይመስለኛል። በኔ ግምት መጀመሪያ ነገር የት ዝ ታ ፈ ለ ግ ውስጥ የተወሳሰበ ነገር የለበትም። ይህም ማለት ሰው፤አንባቢው፣ያልተወሳሰበ ነገር ይወዳል ማለት ነው።ቀላሉን ነገር አወሳስበውው ለማቅረብ የሚሞክሩ ጸሐፊዎችም ተናጋሪዎችም አሉ። እርግጠኛ ምክንያታቸውም ባላውቀውም “ነገሩ እንዲህ እንደምታስቡት ቀላል እንዳይመስላችህ!” የሚል አንድምታ ለማስተላለፍ ይመስለኛል። በዚያውም “እኔ ሆኜ ነው እንዲህ ያፍታታሁላችህ እንጂ እንዲህ ቀላል እንዳይመላችህ!” ለማለትም ጭምር ይመስለኛል። አውቂ ነኝም ለማለትና ከሌላው “ተራ ሰው” ተለይቶና ገንጥል ብሎ፣ጎልቶ፣ፍክቶ ለመታየትም ይመስለኛል።
በኔ አስተያየት የ ት ዝ ታ ፈ ለ ግ እሽጉን ከፍቶ ለማየት መሞከሩ ይመስለኛል ተነባቢነት ያስገኘለት።”ገልጠን ብናየው!” እንደማለት ነው። ወይም በአሉ ግርማ “መጋረጃው ተቀዶ መቅደሱ ታዬ!” እንዳለው መሆኑ ነው።በአጭሩ እሽጉን ከፍቶ፣ ሳጥኑ፣ፓኮው ውስጥ ምን ምን እንዳለ የመመርመር ጉዳይ ነው።መጀመሪያውኑ ሳጥኑን የቆለፈው፤እሽጉን ያሸገው አላዋቂም ሊሆን ይችላል ብሎ የመጠርጠር ጉዳይም ሊኖር ይችላል::ይገባልም!! አብሮ መታሸግ፤መቆለፍ ያሌለባቸው አብረው ከታሸጉ” አጥፊና ጠፊም!”ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህም ላይ ለስንት ዘመንስ ይታሸጋል የሚሉትም አለ። ማንኛናውም እሽግ ዘመኑ ያልፍበትና(Expire Date) ካልታደስ ሊቃጠል ወይም ጎጅም ሊሆነ ይችላል። ከሁሉም በላይ እሽጉ ውስጥት የተበላሽ፤የበሰበሰ ፤ጠረኑን የለጠ፣ሊወገድ የሚገባውም ሊኖር ይችላል ብሎ መፈተሹ ጉዳት ያለበት አይመስለኝም።
ከዚህ ጋር የሚያያዝ እሽጉ እንዳይከፈትና ውስጡ እንዳይታይ የሚፈልጉ “የፖለቲካ ድርጅቶችና “የፖለቲካ “ጠበብቶች” ብዛት እነደ አሸን የፈላ ይመስለኛል።የተገነቡት መስረቱ የጠና መሠረት ላይ ስለአልሆነ፣የእምቧይ ካብ ወይም የተልባ ክምርነትም ሰስለማይጡ ነካ ሲያደርጉት መነሸራተቱ ስለማይቀር፣ይህንንም ስለሚያቁት “ዕውነት ለምኔ!”ይሆኑና “አትንገሩን! አትደርሱብን!”
የሚሉትም አላቸው። የፖለቲካ የንግድ ኩባናያ መሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ማንናቸውም ህዝብ፣ እውነቱ ሲነገረው ያውቃል። ራሱ ከሚያውቀውም ጋር ያነጣጥትርና “ይህ እውነት ነው!” ይላል። ያንን ካላለም “እውነት ይመስለኛል!”ይላል። ካልሆነ ደግሞ “አልገባኝም! ሆኖምአልጣመኝም!”ይላል።የትዝታ ፈለግ ይህንን መሠረታዊ ነገር ይጫረ ይመስለኛል።
ከሁሉም በላይ ግን ወዳጆቼ፤ዘመዶቼ፤ልጆቼ፤ከሁሉም በላይ የልጅ ልጆች ወደውታልና ከዚህ በላይ ጸጋ ያለ አይመስለኝም ። እመቤት አስፋ እንደምትነገረኝ ልጆችዋ መጽሐፉን ታቀፈው ነው ያደሩት። የወንድሜ ልጅ፤ግርማ ሐብተ ገብርኤል ከአርባ ምንጭ “አሴ አለቀስኩ!” አለ።በኩራት መሆኑ ነው።
በኦርቶዶክሶቹ ሕማማት ሔጄ በፋሲካ ማግስት ሰኞ ወደመጣሁበት ተመልስኩ።የመጀመሪያው መድረክ ሕማማት ዋዜማ፤ሁለተኞናው አርብ የስቅለት ለት ነበር። ከሁለት ቀን በኋላ ትንሳዔ ሆነና ተፈሰከ! ፋሲካ ሆነ! “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ!”እንዲሉ::የፋሲካ ምን የመስለ ምሳ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮጋዜጠኛው አሉላ ቤት የህ ቀረሸ የማይባል ምሳ ተጋበዝኩ።
ትንሳኤም ተከበረ!!
የኢትዮጵያን ትንሳኤ እመኛለሁ!!
ኢትዮጵያ በነፃነትዋ ለዘለዐለም ትኑር!!
[1] Non Sequitur | Definition of Non Sequitur by Merriam-Webstera statement that is not connected in a logical or clear way to anything said before it.