Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ይድረስ ለጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም

$
0
0

ከወልደ ቴዎፍሎስ (ኦታዋ፡ ካናዳ)
tewoflos2013@gmail.com
“የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”
ትንቢተ ኢዩኤል 2፡32፤ ሮሜ 10፡13.

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት እና የደርግ ሊቀመንበር ጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡ ባሉበት በሐራሬ ዝምቧብዌ ለጤናዎ እንደምን ከረሙ? መቼም “ጓድ” ብዬ ስጠራዎ ደስታ እንጂ ቅሬት እንደማይሰማዎ እርግጠኛ ነኝ፤ ይህን መጠሪያ ስለሚወዱት፡ የትግል አጋርዎችዎን ብቻ ሳይሆን ውድ ባለቤትዎንም “ጓድ” ብለው ለመጥራት ወደኋላ አላሉምና (ትግላችን፤ “ምስጋና” ገጽ ፭)።
mengistu hailemariam
“ትግላችን፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ” የተሰኘው መጽሐፍዎ ለህትመት ከበቃ ዓመት ከመንፈቅ ቢሆነውም፡ ሰሞኑን እጄ ገብቶ አነበብኩት። እኔ ያነበብኩት ለአምስተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም. የታተመውን ሲሆን፡ መጽሐፉ ብዙ ጥያቄዎችን ቢፈጥርብኝም ርዕሴ እንደሚያመለክተው በመረጥኩት ጉዳይ ላይ ብቻ ይህን አጭር ጦማር ልጽፍልዎ ወደድሁ።

የተወለድኩት እርስዎ እና መሰሎችዎ በኢትዮጵያ የፊውዳሉን ሥርዓት በገረሰሳችሁበት ዓመት ነው። ስለዚህ በዕድሜ አሳምረው አባቴ መሆን ይችላሉ። እንዲያውም ከመጽሐፍዎ ስለእርስዎ ዕድሜ እንደተረዳሁት ከወላጅ አባቴ በ5 ዓመት ይበልጣሉ። “ውሃ ሽቅብ አይፈስም” እንዲሉ ኢትዮጵያዊው ጨዋ ባህላችን እንዳስተማረን ልጆች በአባቶቻቸው ላይ ሂስ (ነቀፋ) መሰንዘር ባይችሉም፡ እንደ አንድ የ72 ዓመት (ካልተሳሳትኩ) ኢትዮጵያዊ አዛውንት እርስዎን በማክበር፡ ከይቅርታ ጋር መጠነኛ ምክር ልለግስዎ ወደድሁ። መቼም “በአብዮቱ ፍንዳታ ወቅት የተወለደ ልጅ እንዴት እኔን ይመክራል?”፤ “ወይኔ መንግሥቱ ተደፈርኩ!” በማለት ዘራፍ እንደማይሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህን አነስተኛ ጦማር ለተለያዩ ድህረ ገጾች ለመላክ ስላሰብኩም፡ መጣጥፌን አንብበው በጽሑፍ መልስ ቢሰጡኝ ደስ ይለኛል።
ይህ ጦማር የመጽሐፍዎ አጠቃላይ ቅኝት (Book Review) ወይም ግምገማ ስላልሆነ፡ በመጽሐፉ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ላይ አስተያየት አልሰጥም። ነገር ግን ወደፊት በሚያዘጋጇቸው ተከታታይ ቅጾች ላይ ያካትቷቸው ዘንድ፡ የተወሰኑ ነጥቦችን ልጠቁም፤
- እስካሁን ድረስ የብዙ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ የሆነው፡ 60ዎቹ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዘግናኝ በሆነ መልኩ ያለፍርድ የተገደሉበትን ሁኔታ መጽሐፍዎ በዝርዝር አይዳስስም። አንባቢዎችዎን ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ ከሌ/ጄነራል አማን ሚካኤል አንዶም አሟሟት ጋር በማያያዝ ይህን ዐቢይ ጉዳይ በአንድ ፓራግራፍ ብቻ ነው ያለፉት (ትግላችን፡ ገጽ 219)።

- ስለ ብ/ጄነራል ተፈሪ ባንቲ ግድያ በመጽሐፍዎ ምንም ነገር አልነገሩንም። ገጽ 253 ላይ ግን፡ ስለ እኚሁ ጄነራል ማንነት በቅጽ 2 እንደሚጽፉ ስላሳወቁን ይህን በተስፋ እንጠብቃለን።

- ስለ አፄ ኃይለሥላሴ እና ስለ ሌ/ኮሎኔል አጥናፉ አባተ አሟሟት (ግድያ) የተረኩት ትረካ፡ በወቅቱ በሕይወት የነበሩ እና እውነታውን የሚያውቁ ኢትዮጵያውያንን ቀርቶ ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ የተወለድኩትን እና ስለወቅቱ ቀውጢ ሁኔታ ምንም የማላውቀውን እኔን እንኳ አላሳመነኝም። በመካከላችሁ በነበረው የሥልጣን ፉክክር ምክንያት ኮሎኔል አጥናፉን ከጄነራል ተፈሪ ባንቲ ጋር የእርስዎ ከሳሽ (ገጽ 246) እንዲሁም መስከረም 13/1969 ዓ.ም. የተሞከረብዎ ግድያ “ፈጣሪ፤ መሪ እና ተጠርጣሪ” (ገጽ 250) አድርገው ያስቡ ስለነበር፡ ኮሎኔል አጥናፉ በተወሰደባቸው አብዮታዊ እርምጃ የእርስዎ እጅ ወይም ግፊት የለበትም ብሎ ማሰብ ጥበብ የጎደለው የዋህነት ይመስለኛል። የአፄ ኃይለሥላሴ እና የጄነራል ተፈሪ ባንቲ ህልፈተ ሕይወት ጉዳይም እንዲሁ።

ሞት ይርሳኝ፡ የተነሳሁበትን ጉዳይ ረሳሁት እንዴ? አይ አልረሳሁትም፤ ጥቆማዬ አላልቅ ብሎኝ ነው እንጂ። ከላይ ያነሳኋቸውን ነጥቦች አብዛኞቹ የመጽሐፍዎ አንባቢዎች ይጋሩታል ብዬ አስባለሁ። አሁን ደግሞ የጦማሬ ርዕስ ወደሚያጠነጥንበት ጉዳይ ከመግባቴ በፊት በቅጽ 2 መጽሐፍዎ እንዲመልሱልኝ የምፈልጋቸውን የግሌን ጥያቄዎች ላቅርብ፤

- እርስዎ እና ባልደረቦችዎ የተከተላችሁት የኮሚኒስት ሥርዓት፡ በእግዚአብሔር ሕልውና በማያምኑ ሰዎች (atheists) የሚመራ ስለሆነ አንድ ሰፊ ሕዝብን ለማስተዳደር የሕዝቡን የእምነት ተቋማት በመቆጣጠር ላይ ያተኩራል። ይህ አባባል የራሽያ ኮሚኒስት ሥርዓት በራሽያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፤ እርስዎ የመሩት ተመሳሳይ ሥርዓት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ባደረሷቸው ተጽዕኖዎች ይረጋገጣል። ታዲያ በቅጽ 1 መጽሐፍዎ፡ ደርግ የኢትዮጵያ መኩሪያ ከሆነችው ከጥንታዊቷ እና የአገሪቱ ብሔራዊት ቤተክርስቲያን ተብላ ልትጠራ ከሚገባት (ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን) ጋር ስለነበረው ግንኙነት ምንም ነገር ያልነገሩን ለምንድን ነው?
- በወቅቱ የነበሩት የቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በመጽሐፍዎ ያነሷቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ጸሎተ ፍትሐት ጉዳይ ላይ ብቻ ነው (ገጽ 271)። እባክዎን የተከበሩ ኮሎኔል መንግሥቱ፡ በሞቴ ልበልዎና ፓትርያርክ ቴዎፍሎስን ማን እንደገደላቸው በክፍል 2 መጽሐፍዎ ይንገሩን።
- አያይዘው ደግሞ፡ ከፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ግድያ በኋላ እርሳቸውን የተኳቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ-ሃይማኖት እንዴት እንደተሾሙ በዚሁ በቅጽ 2 ቢያብራሩልን ምስጋናዬ የላቀ ነው። መቼም ጓድ ሊቀመንበር፡ “እኔ ስለ ቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርኮች የማውቀው ነገር የለም” የሚሉ ከሆነ፡ አኔም ሆንኩ ሌሎች አንባቢዎች በጣም ነው የምንታዘብዎ።

ቅጽ አንድን ሳነብ፡ ከ50 እና ከ30 ዓመታት በፊት የተፈጸሙ ነገሮችን በዝርዝር የማስታወስ ችሎታዎን በጣም አድንቄያለሁ። እርስዎ የ20 ዓመት ወጣት መኰንን ሳሉ ስለገጠምዎት ጉዳዮችም ሆነ የፊውዳሉን ሥርዓት በገረሰሳችሁበት ጊዜ (ያኔ እርስዎ የ34 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ) ስለተፈጠሩ ሁኔታዎች ያወጉን በሚገርም መልኩ ጠለቅ ካሉ መረጃዎች ጋር ነው። ጉዳዮቹ የተፈጸሙባቸውን ቦታዎች ከረጅም ዓመታት በኋላ እንኳን ቢሆን በፍጹም አልረሱም፤ በአካባቢዎ የነበሩትን ጓዶች ደግሞ፡ ከነማዕረጋቸው እና የአባት ስሞቻቸው ጭምር ላፍታ እንኳ አልዘነጓቸውም። ታዲያ በተፈጥሮ ስለተለገሱት ንቃተ ኅሊናም ሆነ የማስታወስ ከፍተኛ ችሎታ “የፍጥረታት ፈጣሪ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን” ብል በአባባሌ አይስማሙም?

መቼም የ72 ዓመት አረጋዊ ሆነው “የምን እግዚአብሔር አመጣህብኝ?” እንደማይሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ተስፋ እና ምኞት አይከለከልም፡ አይደል? “ኢትዮጵያ ትቅደም” የምትለዋን መፈክር በጥቁር ሰሌዳ ላይ ለደርጉ አባላት ከጻፉበት ጊዜ ጀምሮ፡ እንደ ታላቁ ኢታዮጵያዊ ጀግና አፄ ቴዎድሮስ እስከመጨረሻዋ ጥይት ሳይዋጉ ወደ ሐራሬ እስከኮበለሉበት ግንቦት 1983 ዓ.ም. ድረስ የእግዚአብሔርን ስም በስህተት እንኳ ሲጠሩ አልሰማንም። እኔ እና የእኔ ትውልድ ያደግነው የሚያንባርቅ እና እሳት የሚተፋ የሚመስል ድምጽዎን በሬድዮ እየሰማን ሲሆን፡ ክርስትናን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የተቀበለች የታላቂቱ ኢትዮጵያ ርዕሰ-ብሔር እንደመሆንዎ የልዑል እግዚአብሔርን ስም በንግግርዎ መሀል ሲጠቅሱ ለመስማት አልታደልንም። የዚህ ምክንያቱ፡ ለቆሙለት የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮት (አመለካከት) ታማኝ ለመሆን ብለው ነው ወይስ ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔር “እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” (መዝሙረ ዳዊት 67፡31) ከተባለላት ከኢትዮጵያችን የተማሩት ምንም ነገር ስላልነበር?

ወላጅ አባትዎ አቶ ኃ/ማርያም (ይቅርታ ሌላ የማዕረግ ስም ካላቸው) ስለፈጣሪ ምንም ነገር ሳይነግርዎ ነው ያሳደጉዎት ብዬ ላስብ አልችልም። ለመሆኑ እርስዎ በልጅነትዎ ፊደል ሲቆጥሩም ሆነ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ዳዊት ሲደግሙ (እንደደገሙ በመገመት ነው) የተማሩት የዳዊት መዝሙር ስለ እግዚአብሔር ምን እንደሚል አስበው ያውቃሉ? ወይስ ይኸው የዳዊት መዝሙር “ይብል አብድ በልቡ አልቦ እግዚአብሔር – ሰነፍ በልቡ ‘እግዚአብሔር የለም’ ይላል” ስለሚል (መዝ ፲፫፡ ፩) በልብዎ ‘እግዚአብሔር የለም’ እያሉ አድገው፡ ወታደራዊ ሳይንስ በሚማሩበት ጊዜ ይህን አመለካከትዎን አጸኑት? የደርግ ቁንጮ ለመሆን በቅተው “ጓድ ሊቀመንበር” ከተባሉ በኋላ ደግሞ በእግዚአብሔር መኖር እንደማያምኑ በተግባር አሳዩን። ይህንን የምለው፡ ሌላውን እንተወውና “እግዚአብሔር ያያል፤ ኃያሉ አምላክ ይፈርድብኛል” ብሎ የሚያስብ አንድ ግለሰብ፡ ቢያንስ ንፁህ ደም በግፍ ከማፍሰስ ይቆጠባል ብዬ ስለማምን ነው። ሌ/ኮሎኔል አጥናፉ አባተ እውነት በሆነው፡ ግን ለሞት ባበቃቸው ንግግራቸው እንዳሉት፡ እርስዎ እና መሰሎችዎ “ከአገራችን ባህል፤ [ሃ]ይማኖትና ታሪክ ጋር ፈፅሞ የማይገጥምና የማይስማማ የሶሻሊስት ሥርዓት እንከተላለን [ብላችሁ] አገሪቱን የጦርነት አውድማ [አደረጋችኋት]” (ትግላችን፡ ገጽ 254)። ተቆጡ እንዴ ጓድ ሊቀመንበር? ምን ይደረግ እንግዲህ፤ “እውነቱ ሲነገር ይጎዳል” ይባል የለ?

በቅጽ አንድ መጽሐፍዎ የኢትዮጵያን የቀድሞ አፄዎች ለአገሪቱ ካከናወኗቸው ዐበይት ተግባራት አንፃር ያወዳድሯቸው ነበር። አፄ ቴዎድሮስ የመሳፍንቱን “ከፋፍለህ ግዛ” ሥርዓት አስወግደው አንዲት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ባደረጉት ጥረት ማንም እንደማይስተካከላቸው፤ የአፄ ዮሐንስን መንፈሳዊ መሪነት፤ አፄ ምኒልክ ትምህርትን እና አንዳንድ ሳይንሳዊ ውጤቶችን ወደ አገሪቱ በማስገባት የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሐንዲስ ቢሆኑም የባሪያ ንግድን እና የገበሬውን ጭቆና ማስወገድ ስላለመቻላቸው፤ አፄ ኃይለሥላሴ ቀድመዋቸው ከነበሩት ነገሥታት በተለየ መልኩ የትምህርት እድል ስለገጠማቸው፡ ታላላቅ የፖለቲካ እመርታ የተሰኙ ሥራዎችን እንዳከናወኑ እና የእርሳቸው ዘመን ከደረሰበት የ እድገት ደረጃ አንፃር እርሳቸውን ከቀደምቶቻቸው አፄዎች ጋር ማወዳደር እንደማይቻል አስረድተውናል።

እስኪ እኔ ደግሞ በርእሴ ጉዳይ ላይ ብቻ እርስዎን ከመጨረሻው የዘውድ አገዛዝ መሪ (አፄ ኃይለሥላሴ) ጋር ለማወዳደር ልሞክር። አፄ ኃይለሥላሴ፡ እግዚአብሔርን የሚያውቁ እና የሚያምኑ መሪ እንደነበሩ ወደሌላ ዝርዝር ሳልገባ ከእርስዎ መጽሐፍ በመጥቀስ ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል። ከዙፋናቸው ካወረዳችኋቸው በኋላ ወደ ማረፊያ ክፍል ተወስደው፡ እርስዎ “የጎደለ ነገር ካለ ለማሟላት ዝግጁ ነን” ሲሏቸው “ምንም አይደል፤ እግዚአብሔር እንደፈቀደ እንኖራለን” እንዳሉ ነግረውናል (ትግላችን፡ ገጽ 189)። ይህ ሁሉ ለደህንነታቸው እንደተረገ ሲነገሯቸውም፡ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ባንጸባረቀ መልኩ “ለደህንነታችንም የሚያውቀው ሁሉን የሚችለው አንድ አምላክ ብቻ ነው” በማለት መለሱ (ትግላችን፡ ገጽ 189)። በዚሁ ገጽ ላይ ከክብራቸው በተዋረዱባት በዚያች ቀን መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው እንደነበርም ዘግበዋል። ከዚህ በመነሳት አፄ ኃይለሥላሴ እንደ ታላላቆቹ የአሜሪካ መሪዎች (አብርሐም ሊንከን እና ሩስቬልት) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነቡ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለሰው ዘር ያስተላለፈውን መልዕክት ከያዘው ከታላቁ የሕይወት መጽሐፍ ጋር የሚተዋወቁ መሪ እንደነበሩ ለመረዳት ይቻላል።

እርስዎ ግን 17ቱን የመሪነት ዘመንዎ በጦርነት ተወጥረው ስላሳለፉ እና ደግሞም ጊዜ ቢኖርዎት እንኳ ለማንበብ የሚመርጡት የኮሚኒዝም ፍልስፍና መጻሕፍትን ስለሆነ ቅዱሱን መጽሐፍ ያነበቡ አይመስለኝም። በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. አስቀድመው በተዋዋሉበት መንገድ ወደ ዝምቧብዌ ካመለጡ በኋላ ላለፉት 22 ዓመታት በፍጥረታት ፈጣሪ በሕያው እግዚአብሔር ላይ ያለዎት እምነት ምን እንደሆነ አይታወቅም። “ትግላችን…” የተሰኘው መጽሐፍዎ ግን በባዕድ አገር ሁሉንም ነገር በሰከነ መንፈስ ማሰብ በሚችሉበት ሁኔታ እየኖሩ እንኳን፡ የእምነት ሰው ወደመሆን እንዳልተቀየሩ በመጠኑም ቢሆን ያመለክታል። መጽሐፉን ከጥግ እስከ ጥግ ያነበበ ማንኛውም አንባቢ፡ አብዮታዊው እና ተራማጁ ጓድ መንግሥቱ በስደት አገርም ቢሆን ምንም አይነት የዓላማ እና የአመለካከት ለውጥ እንዳላደረጉ ይገነዘባል።

መጽሐፍዎ “አብዮት፤ አድኃሪ፤ ጭሰኛ፤ ጉልተኛ፤ ከበርቴ፤ ምንደኛ፤ ገንጣይ፤ አስገንጣይ፤ ወያኔ፤ ባንዳ፤ ሠራዊት፤ ብርጌድ፤ ጦርነት፤ እዝ፤ ጠገግ፤ ሜካናይዝድ ጦር ወዘተ.” በሚሉ አብዮታዊ እና ወታደራዊ ቃላት የተመላ ሲሆን፡ “እምነት፤ ተስፋ፤ ፍቅር፤ ይቅርታ፤ ምሕረት፤ ቸርነት፤ በጎነት” የተሰኙት ውብ ቃላት መጽሐፍዎ ውስጥ በመብራት ቢፈለጉ እንኳ ለማግኘት ያዳግታል። አማኝ ወደ መሆን እንዳልተቀየሩ ከሚጠቁሙት አገላለጾች መካከል፡ ገጽ 55 ላይ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን “የምድር ገነት” እያለ ይጠራት እንደነበር ገልጸው፡ በዚህ አጠራር ላይ ያለዎትን አመለካከት “ገነት የሚባል ነገር ካለ…” በማለት አሳይተዋል። ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ ቢኖርዎት ኖሮ፡ ሙሶሎኒ ምድረ ኢትዮጵያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመጀመሪያው መጽሐፍ (ኦሪት ዘፍጥረት 2፡8) “የኤደን ገነት” ተብሎ ከተጠቀሰው ቦታ ጋር እንዳነጻጸራት መግለጽ ይችሉ ነበር። ደግሞም ይኸው መጽሐፍ “የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል” (ኦ. ዘፍ 2፡13) ስለሚል የሙሶሎኒ ስያሜ ትርጉም ሊገባዎ ይችል ነበር። በሙሶሎኒ ስያሜ ላይ ከሰጡት አስተያየት የተረዳሁት ነገር ቢኖር፡ ገነት፤ ሲኦል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) የሚባሉ ነገሮች እንዳሉ አለማመንዎን ነው።

በእግዚአብሔር ህልውና እና ለሰው ዘሮች ባለው ጥባቆቱ (መግቦቱ) እስካሁን ድረስ እንደማያምኑ የተረዳሁበት ሌላው የመጽሐፍዎ ክፍል ደግሞ፡ መስከረም 13/1969 ዓ.ም. ከተደረገብዎ የግድያ ሙከራ የተረፉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፡ “ያንን ሁሉ ጥይት ሲያፈስብን እኛን ሊፈጀን ያልቻለው፡ አንደኛ የላንድሮቨሩ ተጠባባቂ ጎማ ከኋላ ከበሩ ጋር ተያይዞ የተቀመጠ በመሆኑ ስለተከላከለልን፤ ሁለተኛ አሉሚኒየም የሆነ ወፍራም የመኪናው ገላና እንዲሁም የመኪናው የኋላ መቀመጫ ጥቅልል ሽቦዎችና ስፖንጆቹ ጥይቶቹን ውጠው እየቀነሱና እያበ[ረ]ዱልን ነው” የሚለው ነው (ትግላችን፡ 7ጽ 248)። ይህ ሁሉ ዝባዝንኬ ውስጥ ከመግባት “እግዚአብሔር አትርፎን ነው” ቢሉ ምን ነበረበት? እዚህ ላይ መልስ ከሰጡኝ፡ እንዲመልሱልኝ የምፈልገውን አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ልጠይቅዎ፤ እርስዎም ሆኑ ባልደረቦችዎ የደርግ አባላት በሀልዎተ እግዚአብሔር የማታምኑ የሶሻሊዝም ፖለቲካዊ ርዕዮት ተከታዮች ሆናችሁ ሳለ፡ ላለመከዳዳት በገባችሁት ቃለ መሐላ ውስጥ ለምንድን ነው “በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ” የሚል ዐረፍተ ነገር የጨመራችሁት? (ትግላችን፡ ገጽ 171)።

የተከበሩ ኮሎኔል መንግሥቱ፡ ይቅርታው እና ምሕረቱ የበዛ ቸሩ እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሐ ስለሰጠዎ፡ በብዙ ጥይቶች መካከል አልፈው፤ ምድራዊ ፍርድንም አምልጠው እስካሁን በሕይወት ይገኛሉ። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በዘር ማጥፋት ወንጀል ከስሶ ስለፈረደብዎ፡ በመሪነት ዘመንዎ የሠሩትን ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያማከሩ የሠሩ ይመስል ፍርዱን በሕዝቡ ላይ የተፈረደ ነው በሚል መንፈስ፡ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘር አጥፊና የጦር ወንጀለኛ ተብሎ መፈረጁን በመስማቴ ለታሪክና ለሕዝቡ የተተወውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ እኔ እራሴ ለመጻፍ ተገደድኩ” ብለውናል (ትግላችን፡ ገጽ 5)። ፍርዱ አበሳጭቶዎት 500 ገጾችን የያዘ መጽሐፍ ስለጻፉ፡ እርስዎ ላይ ያደረሰውን አዎንታዊ ተጽዕኖ እረዳለሁ። ነገር ግን በሰከነ እና በተረጋጋ መንፈስ ማሰብ በሚችሉበት የኑሮ ሁኔታ እና የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው ሳለ፡ በመሪነት ዘመንዎ በፍጹም ስህተት ሰርቻለሁ ብለው አያምኑም። በመጽሐፍዎ የመጸጸትም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ የመጠይቅን ዝንባሌ አንድም ቦታ አላሳዩም። አቋምዎ አሁንም ‘አብዮት ልጇን ስለምትበላ የአብዮቱ ተጻራሪዎች እርምጃ ተወሰደባቸው (ተወገዱ)፤ እንዲሁም በወቅታዊው አጣብቂኝ እና አስገዳጅ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት እና ዕድገት ስንል አስፈላጊ ውሳኔዎችን ወሰንን’ የሚል ይመስላል።

ከሞት በኋላ ሕይወት (ያውም ዘለዓለማዊ) እንዳለ የሚያምኑ ከሆነ ግን፤ የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ጽዋቸው ሞልቶ በሞት እንደተጠሩ፡ እርስዎም አንድ ቀን ይጠሩና ነፍስዎ ወደ ፈጣሪዋ ልዑል እግዚአብሔር ትመለሳለች (መጽሐፈ መክብብ 12፡7)። “የእግዚአብሔር እስትንፋስ” በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን “ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለን” (2 ቆሮንቶስ 5፡10)። የነገሥታት ሁሉ ንጉሥ የሆነው ጌታም ለፍርድ ዳግም እንደሚመጣ እና ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው እንደሚከፍለው ነግሮናል (ራዕየ ዮሐንስ 22፡12)። በእግዚአብሔር የተወሰነልዎ የዕድሜ ገደብ አብቅቶ በአካለ ነፍስ በክርስቶስ ዙፋን ፊት ቆመው በሕይወት ዘመንዎ ስለሰሩት ነገር ሁሉ ከመጠየቅዎ በፊት፡ ቃሉ “ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ፤ ንስሐ ግባ፤ ያለበለዚያ ፈጥኜ እመጣብሀለሁ” (ራዕየ ዮሐንስ 2፡5) ይላልና ዛሬውኑ ከሕሊናዎ ጋር ተማክረው ወደ እግዚአብሔር ልብዎን ይመልሱ። “አባታችን ሆይ…” ብለን እንድንጠራው የፈቀደልን መሐሪው አምላክ፡ ልጆቹ በ11ኛው ሰዓት (የዕድሜያቸው መገባደጃ) ላይም ቢሆን በንስሐ ቢመለሱ በፍቅር ይቀበላቸዋልና “አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ” ይበሉት (መዝሙረ ዳዊት 50፡1)።

በምሕረቱ ባለጸጋ የሆነው እውነተኛው አምላክ፡ የእርሱን ምሕረት እና ይቅርታን ለማግኘት ከፈለግን መጀመሪያ ከወገኖቻችን ጋር ይቅር መባባል እንዳለብን ነገሮናልና (የማቴዎስ ወንጌል 5፡24፤ የማርቆስ ወንጌል 11፡25-26) በሥልጣን ዘመንዎ ለወታደሮችዎ ባስተላለፏቸው ቀጫጭን ትዕዛዞች አማካኝነት ልጆቻቸውን ወይም ወላጆቻቸውን በሞት በመቅጠፍ ለዓመታት ደም ዕንባ ያስነቧቸውን ኢትዮጵያውያን ወገኖች በሙሉ በግልጽ ይቅርታ ይጠይቁ። አለበለዚያ እውነተኛው ዳኛ እግዚአብሔር፡ ለመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ለቃየን እንደነገረው አሁንም “የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” ይላል (ኦ. ዘፍጥረት 4፡10)። ስለዚህ ከላይ የጠቀስኳቸውን የቃሉን መልእክታት በማስተዋል፡ የትዕቢት መንፈስ ቢጫንዎት እንኳ እንደምንም ይቃወሙት እና በትህትና ራስዎን ከኃያሉ አምላክ የጸጋ ዙፋን ሥር ይጣሉ። ምሕረቱን ይለምኑ፤ ቅዱስ የሆነውን ስሙንም ዘወትር ይጥሩት፡ መጽሐፍ እንደሚል “የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል[ና]።”


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>