ናትናኤል ካብቲመር ኦስሎ ኖርዌይ 5 ጥር 2006
መቼም በኢትዮጲያ ብጥብጥና ሁከት የሚባለውን አባባል የማያቅ አለ ለማለት ያሰቸግራል። ምክንያቱም የመብትና የፍትህ ጥያቄ በተነሳ ቁጥር የህወሃት መንግስት “ ብጥብጥና ሁከት ሊያሰነሱ ሲሉ” ማለቱ የተለመደ ነው። ምንም አይነት መብትን የተመለክቱ ጥያቄዎች በድርጅት ወይም በግለሰብ በተነሱ ቁጥር “ብጥብጥና ሁከት” ሊያስነሱ ሲሉ ይባልና እስር ቤት ይወረወራሉ። እዚህጋ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነገር ይታያል። በኢትዮጲያ መብት ማለት ምንድነው? አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የመብት ጥያቄዎቹን ለመንግስት እንዴት ነው ማቅረብ ያለበት? ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ግን አንድ መራራ እውነት አለ እሱም መብት ማለት በኢትዮጲያ መንግስት መጥኖና ለክቶ ለራሱ በሚስማማ መልኩ ለማህበረሰቡ መብቶች ብሎ የተዋቸው ናቸው። መብት ሲባል በወያኔ ካድሬ አመለካከት ያው ሁሌ ንፅፅሩ ከዛ ከፈረደበት ደርግ ነው “በደርግ ጊዜ ሰአት እላፊ ነበር አሁን ግን የለም” ፣ “በደርግ ጊዜ ብሄራዊ ውትድርና ነበር አሁን ግን የለም” ስለዚህ ወያኔ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው እንባላለን።
ብጥብጥና ሁከት ምን ማለት እንደሆነ ሁላችንም ጠንቅቀን እናውቃለን ነገር ግን በአሁኑ ሰኣት በየእስር ቤቱ እየማቀቁ የሚገኙት ወጣቶች የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ነው እንጂ በጥብጠው እንዳልሆን ለማንም ግልፅ ነው። ደሞ ሌሎች አባባሎች አሉ “የተወሰኑ” ፣ “አንዳንድ” የሚባሉ ለምሳሌ ባለፈው ምስኪኖቹ የኢትዮጲያ መምህራን ደሞዝን አስመልክቶ ላነሱት ጨዋነት የተሞላው የመብት ጥያቄ ሟቹ አቶ መለስ “አንዳንድ ብቃት ያነሳቸው መምህራን ብጥብጥና ሁከት ሊያስነሱ ሲሉ” ብለው በአነስተኛ ገቢ በኑሮ ውድነት የሚሰቃዩትን ምስኪን የኢትዮጲያ መምህራን በሃዘን አንገታቸውን አስደፏቸው። እብሪት ከተሞላው ስድብና ማስፈራሪያ ውጪ ላነሱት ጥያቄ በአግባቡ እንኳን ማብራሪያ አልተሰጣቸውም።
የኢትዮጲያ ሙስሊም ማህበረሰብም ከህፃን እስከ ሽማግሌ እምነታቸውን አስመልክቶ ላነሱት ጨዋ የመብት ጥያቄ “አንዳንድ ብጥብጥና ሁከት ፈጣሪዎች” እየተባለ ይዘገባል። ባለፈው የብራዚል ማህበረሰብ ላነሳው የመብት ጥያቄ ፕሬዝዳንቷ ዲልማ ሩሴፍ የተናገሩት ንግግር እጅግ ያስቀናል “መብታችሁን ለማስከበር በመነሳታቹ ኮራሁባቹ” ነበር ያሏቸው። አንድ ነገር እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው በወያኔ አገዛዝ ይህንን በፍፁም አንሰማም። ለምን? የኢትዮጲያ ህዝብ በጥባጭ ስለሆነ? ወይም መንግስትን አጉል ጥያቄ ስለሚጠይቅ? አይደለም። ህወሃት ራሱ የሰራውና እየሰራ ያለው ኢሰባዊ የሆን ግፍና የመብት ረገጣ ስለሚያስበረግገው ሰው ሲሰብሰብ አይወድም። እጅግ በሚያስገርም መልኩ በቅርቡ የሳውዲ መንግስት በኢትዮጲያዊያን ላይ ያደረሰውን አስከፊ ግፍና የመብት ረገጣ ለመቃወም የወጣውን ህዝብ እንኳን “ብጥብጥና ሁከት” ሊያስነሱ ተብሎ እየተደበደቡ ተበተኑ። ኧረ ሌላም ብዙ አይተናል።
ነፃና ዲሞክራሲያዊ መንግስትማ የህዝቡን የመብት ጥያቄ እንዴት እንደሚመልስ እናያለን። እንደውም የኢትዮጲያ ህዝብ ሲበዛ የዋህ ነው ባለፈው ውጥንቅጡ በወጣውና መላቅጡ በጠፋው የኢትዮጲያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የተነሳ ተሰደው በሳውዲ ሲሰቃዩ ቆይተው ወደሃገራቸው ከተመለሱት ስደተኞችጋ አንድ ሁለት ፎቶ ስለተነሱ ብቻ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን የሚያደንቁም ተነስተው ነበር። ምን ስላደረጉ? ምንም። እንደው ህዝባችን ትንሽ ሲያረጉለት ወዲያው ለምስጋና አንገቱን ስለሚያጎነብስ ነው እንጂ። ይህን የመሰለ የዋህ ምስኪን ህዝብ በዘርፈብዙ ችግር ሲሰቃይ ማየት እጅግ ያበሳጫል።
ለምሳሌ የመብት ጥያቄ ማንሳት “ብጥብጥ” መባሉ ቀርቶ ለማንኛውም ኢትዮጲያዊ ተፈቀደ እንበልና ምስኪኑ የኢትዮጲያ ህዝብም “ኧረ ተው ከዚህ ሀገር ንቀለኝ” እያለ አማልክትን ከማስቸገር መብቱን ለማስከበር ቢነሳ ምን ያህሉ የሃገራችን ህዝብ የመብት ጥያቄ እንደሚያነሳ ሁላችንም መገመት አያቅተንም።
አንዳንዴ ሳስበው መንግስት ዝም ሲባል የተወደደ ይመስለዋል መሰለኝ ምናልባትም አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ቦታ የሚሰሩ ካድሬዎች የህዝቡን ሮሮ ትተው “ህዝቡ ለመንግስት ፍቅር አለው” ብለው ሪፖርት ስለሚያቀርቡ ይሆናል። እውነታው ቢገለፅ ግን ሪፖርታቸው የሚሆነው “መንግስት ሆይ ህዝቦችህ ይወዱሃል የምንልህ እኛ ነን እንጂ እነሱስ ሞትህን ይመኛሉ” ነበር።
ታስታውሱ እንደሆን አቶ መለስ “ይህ ማዕበል” ብለው አለወትሮአቸው ድምፃቸውን ሞቅ አርገው የተናገሩት መንግስታቸው የተወደደ መስሏቸው ነበር ወዲያው በነጋታው መልሱን አገኙት እንጂ። ግን እንዴት እንደዛ አሰቡ? በትክክል ቁጥሩን የማያውቁትን ህዝብ ፣ መንግስት በስርአቱ መዝግቦ ያልያዘውን ህዝብ ፣ በኑሮ ውድነት ፣ በነፃነት እጦት እያሰቃዩት ያለውን ህዝብ እንዴት ይወደኛል ብለው አሰቡ። ያስገርማል።
ወደዋናው ሃሳቤ ስመለስ ማንኛውም የሰው ልጅ መብቱን መጠየቅ ማስከበር አለበት ማንኛውም ኢትዮጲያዊም እንድዚሁ። ይህን ስል ግን የግድ መስቀል አደባባይ መሰብሰብ ላይቻል ይችላል ቢሆን ጥሩ ነበር ነገር ግን ሁሉም ኢትዮጲያዊ በሚኖርበት ፣ በሚሰራበት ፣ በሚማርበት ፣ አገልግሎት በሚያገኝበት ቦታ መብቱን ማስከበር አለበት። ባገኘው አጋጣሚ እምቢ ማለት አለበት።