Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አቡነ ማቲያስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከብዝበዛ በማዳን ታሪክ እንዲሠሩ ተጠየቁ

$
0
0

ሰንደቅ ጋዜጣ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው፦

‹‹ዐይናችን፣ ጆሯችንና ልባችን የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና በሚወስነው የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ተግባራዊነት ላይ ነው፤ የቤተ ክርስቲያናችን ትንሣኤ ደርሷል ብለን እናምናለን፡፡›› /ምእመናን/

‹‹ከእውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቷ ጥቅም ወዲያና ወዲህ አልልም፤ አትጠራጠሩ! ሕጉ የጠራ ኾኖ በትክክሉ ይወጣል፤ ቤተ ክርስቲያናችን ወደቀደመ ክብሯ ትመለሳለች፡፡›› /ፓትርያርኩ/

‹‹የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ከመሠረታዊው ተልእኮው ጋራ ያልተቀናጀ ከመኾኑም በላይ በወገንተኝነትና በሙስና የሚፈጸሙ የተለያዩ የሥነ ምግባር ብልሽቶች በስፋት የሚንጸባረቁበት ኾኖ ይስተዋላል፡፡ ይህን ከቤተ ክርስቲያኒቷ ክብርና ቅድስና ጋራ የማይጣጣም ሒደት ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ርምጃ ሊወስድበት ይገባል፡፡ አስፈላጊው እርማት በወቅቱ ሳይደረግ በመቅረቱ፣ ምእመናኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ላይ እምነት ማጣትን እያሳደረ ኹኔታውም እየተባባሰ ሲሔድ ይታያል፡፡ ስለዚህ ታሪክ እንዳይፈርድብን ካህናቱንና ምእመናኑን በማስተባበር አስቸኳይ የእርምት ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ይኾናል፡፡››

“እንደ አቡነ ጳውሎስ ነጭ ልብስ አልለብስም” – አቡነ ማቲያስ (ሙሉ ቃለ ምልልሱን ያድምጡ)
ይህ ጥቅስ አቡነ ማትያስ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾነው ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያቸውን የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሁለተኛ ዓመታዊ ስብሰባ ግንቦት 22 ቀን 2006 ዓ.ም. በንግግር ሲከፍቱ ካሰሙት ቃል የተወሰደ ነው፡፡
ፓትርያርኩ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም ለመጠበቅና የቀደመ ክብሯን ለመመለስ›› ሥር ነቀል የለውጥ ርምጃዎች እንደሚወስዱ ባስታወቁበት በዚያ የመክፈቻ ንግግራቸው÷ የቅ/ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ብልሹ አሠራርን ለማረምና ለማስወገድ፣ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ለማዋቀርና ለፋይናንስ አያያዙ ዘመናዊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አደረጃጀት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሦስት መሠረታዊ ርምጃዎችን እንደሚወስድ አመልክተው ነበር፡፡

አቡነ ማትያስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጤናማ ሒደት የሚወስኑ ናቸው ባሏቸው ሦስቱ መሠረታዊ ርምጃዎች ጋራ በተለይም ልዩ ሀገረ ስብከታቸው በኾነው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እየገዘፈና እየተመሰቃቀለ የመጣውን የመልካም አስተዳደር ዕጦትም በአደረጃጀቱና አሠራር ለውጥ ማስተካከል አስፈላጊ መኾኑን አሥምረውበት ነበር፡፡

ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ግልጽ የአስተዳደር ሥርዐት የሚሰፍንበትን የለውጥ መሠረት በአስቸኳይ ማስቀመጥና አቅጣጫውን መቀየስ ‹‹በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በመጪው ትውልድ ፊት›› ኹልጊዜ በሚዛን እየተመዘነ እንደሚኖር መዘንጋት እንደሌለበት ፓትርያርኩ ያሳሰቡት ለቅ/ሲኖዶሱ አባላት ጭምር ነበር፡፡

በስብሰባው መጨረሻ ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ለብዙኃን መገናኛ ግልጽ የተደረገው የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ መግለጫ÷ በየቀኑ በለውጥ ጎዳና ከሚራመደው ዓለም በተሻለና በበለጠ መንፈሳዊና አእምሯዊ ጥበብ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመምራት፣ ለማስተማርና ለማገልገል ዕንቅፋት የኾኑ ችግሮችን በመለየት ዓበይት ውሳኔዎች መተላለፋቸው የተነገረበት ነበር፡፡ ከእነርሱም መካከል፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኃይል አመዳደብ የሕግ የበላይነትን አክብሮ የሚሠራበት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ በቋሚ ሲኖዶሱና በፓትርያርኩ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግበት የሚያመለክተው ይገኝበታል፡፡

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በሞዴልነት የሚጠቀስበት ነው የተባለው የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናትም በፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያ በተሰጠውና በሀ/ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው በምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ በተሾሙት አቡነ እስጢፋኖስ የቅርብ ክትትል በተደረገለት የባለሞያ ቡድን ተካሒዷል፡፡ 13 ጥራዞችና ከአንድ ሺሕ በላይ አጠቃላይ ገጾች ያሉት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ፣ በጥቅምት ወር በተካሔደው የቅ/ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ሙሉ ይዘቱን በሚወክል ስላይድ ቀርቦ መገምገሙ ተገልጧል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው በግምገማው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ተልእኮ ለኾኑት ክህነታዊና የስብከተ ወንጌል ተግባራት ቅድሚያ በመስጠት÷ ሥራና ሠራተኛን እንዲገናኝ፣ ደመወዝና ሞያ በሐቅ እንዲነጻጸር፣ ተቀባይነትና ተአማኒነት ያለው የገንዘብ ፍሰት እንዲኖርና የራስ አገዝ የልማት እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ያስችላል ለተባለው የመዋቅርና አሠራር ጥናት ተግባራዊነት አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ ጥናቱ ወደታች ወርዶ በማኅበረ ካህናት፣ በማኅበረ ምእመናንና በሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ውይይት ዳብሮ፣ በውይይቱ በተገኘው ግብአት ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም ዓይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል ነው ምልዓተ ጉባኤው የሰጠው አቅጣጫ፡፡

ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ገዳማትና አድባራት የተውጣጡና ከፓትርያርኩ ጋራ የተነጋገሩ ምእመናን ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ ያላቸውን ድጋፍና ለተግባራዊነቱም የሚኖራቸውን አጋርነት ገልጸዋል፡፡ ሀ/ስብከቱ ከኅዳር 14 – ታኅሣሥ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ቁጥራቸው ከ2700 በላይ የኾኑ አለቆችን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችን፣ ካህናትን፣ ሊቃውንትን፣ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችንና ምእመናንን በአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ሰነዱ ላይ ማወያየቱን የገለጹት ምእመናኑ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ስምና ዝና ወደ ቀደመ የክብር ቦታው ለመመለስ የሚያስችል ነው ያሉት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱ በቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት በውይይቱ በተሰበሰበው ግብአት ተስተካክሎና በቋሚ ሲኖዶሱ ጸድቆ ተግባር ላይ እንዲውል ጠይቀዋል፡፡
ማንኛውም ለውጥ በተለይም የሥራ አመራር ለውጥ የራሱ ተግዳሮቶች እንዳሉት የተናገሩት ከደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የመጡት የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ዮናስ፣ በአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱ ጥቂቶች የሚያሰሙት ተቃውሞ መታየት ያለበት በትግበራ ሒደት በሚቋቋመው የቅሬታ ኮሚቴ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ በለውጥ ሥራ አመራር ከተለመደው በተለየ ከትግበራ በፊት በመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ የጎደለው እንዲሟላ፣ የጠመመው እንዲቃና ቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድል መስጠቷን ሰበብ አስባብ እየፈለጉና ምክንያት እየለጠፉ ለውጠን ለማሰናከል የሚሞክሩ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ተቃዋሞው ለውጡን ከራስ ጥቅም አንጻር ብቻ ከመመልከት የሚመነጭ መኾኑን ያብራሩት አቶ ዮናስ፣ ‹‹የእኛን ልብስ ለብሰው እኛን መስለው የገቡ ተቃዋሚዎች እኛ ለልጆቻችን ለማስተላለፍ የምንፈልጋትን ቤተ ክርስቲያን አይወክሉም፤›› ብለዋል፤ በተቃዋሚዎቹ ግፊት የአደረጃጀትና አሠራር ጥናቱ በዐዲስ መልክ ለመገምገም የተላለፈው ውሳኔም በጥንቃቄና በጥልቀት እንዲታይ ፓትርያርኩን አደራ ብለዋል፡፡
የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ ወጣቶችም ሽማግሌዎችም ወይዛዝርትም የሚስማሙበትና በቤተ ክርስቲያኒቱ የተንሰራፋውን የአስተዳደር ብልሽትና የገንዘብ ብዝበዛ እንደሚያስቆም ጽኑ እምነት እንዳላቸው የገለጹት ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ ከበደ ሙላት ከመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የመጡ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ ዐዋዲ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1965 ዓ.ም. ሲረቀቅ ከአርቃቂዎቹ አንዱ እንደነበሩ የተናገሩት አዛውንቱ ምእመን አቶ ከበደ፣ ‹‹ዛሬ ያ ቃለ ዐዋዲና እኔ አርጅተናል፤ ጊዜው የሚጠይቀው አዲስ መዋቅር ያስፈልገናል፤ አዲስ መዋቅር ባለመኖሩ ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ብዙ ጉዳት እየደረሰ ሲያንገበግበን ኖሯል፤›› በማለት የተሰማቸውን ቁጭት ገልጸዋል፡፡

የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ የተረቀቀው አዲስ መዋቅር በሚያስፈልግበት ወቅት መኾኑን የጠቀሱት አቶ ከበደ፣ በአስተዳደር ብልሽቱ ራሳቸውን ያበለጸጉ አካላት በለውጡ በሚቋረጥባቸው ሕገ ወጥ ጥቅም ክፉ ወሬ ማስወራታቸው አስገራሚ አይደለም ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹እንኳንስ ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግሥትም ቢኾን ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ነገር ሲነሣ ኹሉም እልል ብሎ አይቀበልም›› ያሉት አቶ ከበደ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ምዕራፍ ውስጥ ለስምዎም ለታሪክዎም ብቅ ብሎ የሚታይ ነው›› ያሉትን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ፓትርያርኩ ደፍረው እንዲያስፈጽሙትና ቤተ ክርስቲያኒቷን ከብዝበዛ በማዳን ታሪክ እንዲሠሩ ተማፅነዋቸዋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ነው አደራ የጣለብዎት፤ ሕዝቡም አደራ ጥሎብዎታል፤ ያንን ሕዝቡ የጣለብዎትን አደራ ከፍጻሜ ለማድረስ ብርታቱን ይስጥዎት፡፡››
የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ በሕይወት ያሉትም የሌሉትም በርካታ ምእመናን የጸሎትና እንባ ውጤት ነው ለማለት እንደሚደፍሩ የተናገሩት ወ/ሮ ቅድስት የተባሉ ምእመንት፣ በመንፈሳዊውም በሥጋዊውም ስለት በተሳሉ ባለሞያዎች የተዘጋጀ ነው ባሉት ጥናት ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን ትንሣኤ ደርሷል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡ በጥናቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር በሚገባ ማወቃቸውን ያስረዱት ወ/ሮ ቅድስት÷ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምእመኑ ዐይን፣ ጆሮና ልብ ለቤተ ክርስቲያን ህልውናና የቀረው ሕዝቧ እንዳይበተን ወሳኝ ነው ባሉት የጥናቱ ተግባራዊነት ላይ መኾኑን ገልጸዋል፤ ያለአንዳች ተቃውሞም በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲኾንም ፓትርያርኩን ጠይቀዋል፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ምእመናኑ ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ ተግባራዊነት ያላቸውን ስጋት በመግለጻቸው ደስ መሰኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አንድ የተወሰነ ቡድኑ ያጠናው የሕግ ረቂቅ ከቤተ ክርስቲያን ባህልና ቋንቋ አንጻር እንዲታይ መደረጉ ሕጉ የበለጠ እንዲጠራና እንዲጠነክር ያደርገዋል እንጂ እንደማያዳክመው በማረጋገጥ የዘመኑ ምሁራንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያሉበት ኮሚቴ ዳግመኛ እንዲያየው መሠየሙን ለምእመናኑ አስታውቀዋል፡፡ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ ከቀረበው ይዘት ተዳክሞና የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም የሚጎዳ ኾኖ ቢመጣ እንደማይቀበሉትም ለምእመናኑ በተደጋጋሚ ቃል ገብተዋል፡፡

‹‹ከዚኽም ከዚያም ይምጣ፤ ኹሉም የሚናገረውን አዳምጣለኹ፤ ኹሉም የሚናገረውን እያስተናገድኹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅም ግን ወዲያና ወዲህ አልልም፤›› ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ፍላጎታቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ ትክክለኛ መሥመሯን እንድትይዝ፣ ወደ ጥንቱ ቅድስናዋና ንጽሕናዋ እንድትመለስ በመኾኑ የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናቱ ከደረሰበት ወደ ኋላ የሚመለስበት ምንም ምክንያት እንደማይኖርና ወደኋላ መመለስ ዘበት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አትጠራጠሩ! ምሁራኑም ይዩት፤ ሊቃውንቱም ይዩት፤ ሕጉ የጠራ ኾኖ በትክክሉ ይወጣል፤ ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ቀደመ ክብሯ ትመለሳለች፤›› በማለት ለተግባራዊነቱ የምእመናኑን ድጋፍና እገዛ ጠይቀዋል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>