ከይርጋ አበበ
አርሴን ቬንገር ቡድናቸው ማራኪ ጨዋታ ማሳየት ከቻለ ወይም የክለባቸው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ጤናማ ከሆነ ለዋንጫ ደንታ የላቸውም እየተባሉ ይተቻሉ። ለክለባቸው ውጤታማነት የሚያስፈልጉ ተጫዋቾችን ለመግዛት አይደፍሩም። በተቃራኒው ክለባቸው ውስጥ የሚገኙትንና ደህና ዋጋ እንደሚያስገኙ የሚያስቧቸውን ተጫዋቾች ወደ ገበያ ሲያቀርቡ ዓይናቸውን አያሹም ይባላሉ። «ቬንገር ዘጠኝ ዓመት ከዋንጫ ጋር መለያየቱ የማያስጨንቀው ሰው ነው» እያሉ የስፖርት ተንታኞች ያብጠለጥሏቸዋል።
ሆኖም አርሴን ቬንገር ለሚሰነ ዝርባቸው ትችት መልስ ለመስጠት የሚመስልና እጅግ ውድ ዋጋ የወጣበትን ተጫዋች ዘንድሮ እንዲገዛ አድርገዋል። አሠልጣኙ ዘንድሮ ድንገት ሳይጠበቁ ጀርመናዊውን የኳስ ሊቅ ሜሱት ኦዚልን በ42 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ክለባቸው አዘዋውረ ውታል። ለዚህ ጀርመናዊው ኮከብ ያወጡት ገንዘብ በፕሪሚየር ሊጉ ከተከናወኑ ዝውውሮች ሁሉ በትልቅነቱ ሁለተኛው ነው። ቬንገርም በድርጊታቸው ተኩራርተው «እኔ የክለቤን ደረጃ የሚመጥን ከሆነ ለምን መቶ ሚሊዮንስ አያወጣም» ሲሉ ተናገሩ።
ከኦዚል መፈረም በኋላ መነቃቃት ታይቶበት የነበረው ክለባቸው ግን ቀስ በቀስ መንሸራተት በመጀመሩ ክለባቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው አስበዋል። በተለይ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ያለባቸውን ክፍተት ለመድፈን ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በክለባቸው ኦፊሴላዊ ድረ-ገጽ አስታውቀዋል።
አርሴን ቬንገር በተለይ የግቡን መስመር ለማግኘት የተቸገረውን ኦሊቨር ዥሩን ለማገዝ የሚችል ሁነኛ ፊት አውራሪና ከጀርመናዊው መለሎ ፔር ሜርትሳከር ውጭ የሚተማመኑበት የኋላ መስመር ተጫዋች በቡድናቸው ውስጥ ባለመኖሩ እነዚህን ቦታዎች ለመድፈን እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል። ለመሆኑ የቬንገርን ዓይን ያንከራተቱት ከዋክብት እነማን ናቸው?
5. ላርስ ቤንደር
አርሰን ቬንገር በቡድናቸው ውስጥ ማቲው ፍላሚኒ በቦታው ቢኖርም ለተከላካዮቻቸው ተጨማሪ ሽፋን የሚሰጥላቸው የአማካይ መስመር ተጫዋች አስፈልጓቸዋል። ለዚህም ዓይናቸውን ያሳረፉበት በጀርመናዊው የባየር ሊቨርኩሰን ወጣት አማካይ ላርስ ቤንደር ላይ ነው። ቬንገር ለዚህ መስመር የሚሆነው ተጫዋች ምርጫ ላይ ላርስ ቤንደርን የመጀመሪያ ምርጫቸው ባያደርጉትም፤ እርሱንም ቢሆን ለማገኘት እስከመጨረሻው እንደሚታገሉ ይጠበቃል።
4. አሌክሳንደር ፓቶ
ኢማኑኤል አዲባዮርና ሮቢን ቫንፐርሲ አርሴናልን ከለቀቁ በኋላ አርሴን ቬንገር የክለባቸውን ደጋፊዎች አንጀት የሚያርስ አጥቂ በክለባቸው ማየት አልቻሉም። በቅርቡ የቫንፐርሲን ቦታ ይተካሉ ተብለው ወደ ክለቡ የተዘዋወሩት ጀርመናዊው ሉካስ ፖዶሊስኪና ፈረንሳዊው ኦሊቨር ዥሩ የታሰቡትን ያህል መሆን አልቻሉም።
በተለይ ሉካስ ፖዶሊስኪ በተደጋጋሚ ጉዳት የሚያጋጥመው ከመሆኑ አኳያ ኦሊቨር ዥሩን በብቸኝነት እንዲጠቀሙ ተገድደዋል። ሆኖም አርሰን ቬንገር ከሀገራቸው ልጅ የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ፍንጮች እየተነገረ ይገኛል። ለዚህም ይመስላል ለብራዚላዊው አሌክሳንደር ፓቶ ዝውውር በራቸውን ክፍት አድርገው የልጁን ወደ ለንደን ማምራት በጉጉት የሚጠባበቁት።
የቀድሞው የኤሲ ሚላን አጥቂ በአሁኑ ክለቡ ኮሮንቲያስ እያሳየ ያለውን ብቃት የተመለከቱት የአርሴናል ጎረቤቶች ቶተንሃም ሆትስፐርሶችም የልጁ ፈላጊ ሆነው መቅረባቸው ለአርሰን ቬንገር ዳገት ሳይሆንባቸው አይቀርም እየተባለ ነው።
የተጫዋቹን የአውሮፓ ኑሮ እንደገና ለማስጀመር የጓጉት አርሰን ቬንገር ግን ፈተናውን ተቋቁመው የክለባቸውን ማሊያ ያለብሱታል የሚሉ አስተያየቶችም መነገር ከጀመሩ ቆይተዋል።
3. ጁሊያን ድራክስለር
ወጣቱ የሻልካ 04 አማካይ መስመር ተጫዋች ድራክስለር ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተዘዋውሮ መጫወት ይፈልጋል።። አርሴናል ደግሞ የድራክስለር ፈላጊ መሆኑን ቬንገር ፍንጭ ሰጥተዋል። አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስፔናውያንና ፈረንሳውያን ተጫዋቾችን «በቃኝ» ያሉ የሚመስሉት አርሰን ቬንገር ፊታቸውን ወደ ጀርመናውያን ማዞራቸውን ተመልክተው የድራክስለር ማረፊያ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ፍላይ ኤምሬትስ መሆኑ አይቀርም እያሉ ነው።
የሻልካው መለሎ ተጫዋች ድራክስለር ቬንገር የሚፈልጉት ዓይነት ተጫዋች መሆኑና ወጣትነቱ ወደ ሰሜን ለንደን የሚያደርገው ጉዞ እንደሚሳካ የስፖርት ቤተሰቡ ከፍተኛ ግምት የሰጠው ትኩረት መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።
2. አይካይ ጎንዶጋን
የአርሰን ቬንገር የአማካይ መስመር ላይ ተመራጭ ተጫዋች ቢኖር ይህ የ23 ዓመት ጀርመናዊ ወጣት ነው። ቬንገር በአማካይ ተከላካይ ቦታ ከማቲው ፍላሚኒ ውጭ የክለባቸውን ማሊያ ለብሶ ሲጫወት ሊያዩት የሚፈልጉት ይህን የቦሩሲያ ዶርትሞንድ ተጫዋች ነው። ተጫዋቹን ለማግኘትም የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጎንዶጋን በማንቸስተር ዩናይትድ ሳይቀር ፈላጊው በዝቷል። ተጫዋቹን በእጃቸው ለማስገባት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው የተረዱት አርሴን ቬንገር ልጁን ለማማለል በክለባቸው ያሉትን ስድስት ጀርመናውያን እንደሚጠቀሙ ሲገለጽ፣ ለእናት ክለቡ ደግሞ አሳማኝ የዝውውር ሂሳብ ለመክፈል የሚያግዳቸው ምንም ምክንያት እንደሌለ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ።
አርሰን ቬንገር በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጫወት ፍላጎቱ ከፍተኛ የሆነውን ጎንዶጋንን ወደ ክለባቸው አዘዋውረው ከሀገሩ ልጆች ጋር ማጫወት ይችሉ እንደሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል።
ካሪም ቤንዜማ ፈረንሳዊ ነው። ይህ የሪያል ማድሪድ ግብ አነፍናፊ ተጫዋች የማይፈልገው ክለብ በምድረ አውሮፓ የለም። ቬንገርም የሀገራቸውን ልጅ በማድሪድ ያለውን ቆይታ እንዳልወደደው ተረድተዋል። በማድሪድ ያለው ቆይታ ቀስ በቀስ እየተነቃነቀ መምጣቱን ተከትሎ ተጫዋቹ የቤርናባውን መውጫ በሮች እየተመለከተ ይገኛል። አርሰን ቬንገርም ከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ መድበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እየዘገቡት ነው።
የኦሊቨር ዥሩ ግብ የማግባት ችግር እየተባባሰ መሄድ ተስፋ ያስቆረጣቸው ቬንገር ችግራቸውን እንዲያቃልላቸው የሀገራቸውን ልጅ ወደ ኢምሬትስ ማዘዋወር የመጀመሪያ ግባቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።