Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አንድነት ፓርቲን በተመለከተ መልስ ለኢሳቱ ፋሲል የኔአለም –ከግርማ ካሳ

$
0
0

የኢሳት ባልደረባ አቶ ፋሲል የኔአለም «የአንድነት ፓርቲ የመጪው ጊዜ ፈተና» በሚል ርእስ የጻፉትን ዘሃበሻ ድህረ ገጽ ላይ አነበብኩ። አቶ ፋሲል ጽሁፉን ያቀረቡት እንደ ግል አስተያየት እንደመሆኑ፣ ኢሳትን በዚህ ዉስጥ ጣልቃ አላስገባም። የአንድነት ፓርቲ አዲሱ ሊቀመንበር፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራዉ፣ አገር ዉስጥ ለሚታተመዉ ሪፖርተር ጋዜጣ ከሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የሚከተለዉን በመጥቀስ ነበር አቶ ፋሲል ጹሁፋቸውን የጀመሩት

«ከኢሕአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት እንዲኖረን እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የጥላቻ ፖለቲካ ማብቃት አለበት። ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የሚያያቸው እንደ ጠላት ከዚያም አልፎ እንደሽብርተኛ ነዉ። በእኛም በኩል ኢሕአዴግን የምናየው እንደ አዉሬ ነዉ። ምናልባትም የሰራዉን ሥራ ሁሉ ዋጋ ያለመስጠት አለ። አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካችን ኢሕአዴግን መቃወም ብቻ ሆኗል። ያ መቆም አለበት። ትልቁ ኳስ ያለው ኢሕአዴግ ዘንድ ነዉ። እኔ በበኩሌ ወደፊት በማደርገዉ እንቅስቃሴ ገንቢ ግንኙነት አድርገን ያለዉን የፖለቲካ ምህዳር ለሁላችንም አኩል መሆን አለበት» በማለት ነበር።

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም


«ይህ መንገድ (ኢንጂነር ግዛቸው በሪፖእርት የታናገሩት) ፣ ካልተሳሳትኩ ሶስተኛ መንገድ የሚባለዉና አቶ ልደቱ አያሌው የ1997 ምርጫ አጣብቂኝ በገባበት ወቅት አምጥተው የደነጎሩት፣ በሌላ አነጋገር መሃል ላይ መቆም የሚባለው የፖለቲካ አካሄድ ነዉ» ሲሉ የጻፉት አቶ ፋሲል፣ ከአገዛዙ ጋር እርቅና ሰላም ለመፍጠር ፍቃደኝነት መኖሩ፣ በአንዱዋለም አራጌና በናትናኤል መኮንን ላይ ተጽእኖ ሊያሳደር እንደሚችል ፣ የአንድነት ፓርቲም አደጋ ላይ እንደሚጥል የሚያመላክቱ ሃሳቦችን ለማሳየት የሞከሩ ይመስላል። የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤም፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራዉን ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጡ፣ ትክክል እንዳልሰራም አቶ ፋሲል ጠቆም ሳያደርጉንም አላለፉም።

እዚህ ጽሁፍ ላይ ስለ ኢንጂነር ግዛቸው ብዙ መጻፍ አልፈልግም። ኢንጂነሩን ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃቸዋል። አብዛኞቹ ወጣቶች በሆኑበት ፣ ከክልሎች ሁሉ በተወጣጡ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት የተመረጡም ናቸው። በዲሞክራሲ የማምን እንደመሆኔም፣ አገር ቤት፣ ፊት ለፊት አፈናን እየተጋፈጡ ያሉ፣ የአንድነት ፓርቲ አባላት «እነዚህ ናቸው የሚመሩን !» ብለው የመረጡትን እደግፋለሁ። እቀበላለሁም።

አሁን ግን ኢንጂነሩ ለሪፖርተር ሰጡ በተባሉት ሃሳቦች ላይ፣ አንዳንድ አስተያየቶችን እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ። አንድነት ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀመሮ፣ የአንድነት ፓርቲ፣ ከገዢዉ ፓርቲ ጋር፣ ችግሮችን በሰላምና በዉይይት ለመፍታት ሁልጊዜ ፍላጎት እንደነበረዉ፣ የአንድነትን እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉትና በሚገባ የሚያውቁት ነዉ። ገዢው ፓርቲ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጠ፣ ለዉይይት ፍቃደኛ አልሆነም እንጂ፣ አንድነት ሁልጊዜ ለዉይይት በሩን የከፈተ፣ ሰላማዊ ድርጅት ነዉ። ኢንጂነር ግዛቸው፣ የተናገሩት አዲስ አባባል አይደለም። አቶ ፋሲልንም ለምን እንዳስቆጣ አልገባኝም። የቀድሞ ሊቀመናብርት፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ዶር ነጋሶ ጊዳዳ ጠይቆ መረዳትም ይቻላል። (በነገራችን ላይ ኢንጂነር ግዛቸውን ከልደቱ አይሌው ፣ አንድነትን ከኢዴፓ ጋር የማገናኘቱ ነገር ትንሽ አስቆኛል። አቶ ልደቱ በቅርቡ በአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ዙሪያና ስለ ኤዴፓ ሶስተኛ መንገድ ወደፊት በሰፊዉ እመለስበታለሁ)

አቶ አንዱዋለምን በተመለከተ አንድ ነገር ላንሳ። ይህ ወጣት የዴሞክራሲ ታጋይ፣ የሰላም ሰው ነዉ። ብሄራዊ እርቅ በአገራችን እንዲመጣ የሚፈልግና የሚመኝ ነዉ። ኢንጂነር ግዛቸው የተናገሩትን እርሱም ቢሆን ይናገረዉ ነበር። አንዱዋለም ለአላማው የጸና ሰው እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ነገር ግን ለአላማ መጽናት ማለት በጥላቻ መሞላት ማለት አይደለም። የገዢዉን ፓርቲ ተግባራት እንጂ አንዱዋለም የሚጠላው፣ አሳሪዎቹን እንደ ጠላት የሚያይ አይደለም። ልብ ገዝተው ወደ ቀናዉ መንገድ ከመጡ ከምንም በላይ የሚያስደስተው ያ ነዉ። ለዚህም ነዉ ቀድሞ የሕወሃት ከፍተኛ አመራር የነበሩ እንደ አቶ ስዬ ያሉ ወገኖች፣ ወደ አንድነት እንዲመጡ ትልቅ አስተዋጾ ካደረጉ ወገኖች መካከል አንዱ የነበረዉ። አንዱዋለም፣ ሰላምና እርቅ እንደማይፈልግና ግትር እንደሆነ ተደረጎ መቅረቡ ትልቅ ስህተት ከመሆኑም ባሻገር፣ ዜጎች አንዱዋለም አራጌ ያልሆነዉ እንደሆነ አድርጎ እንዲያስቡ የሚያደርግ ጎጂ አቀራረብ ነዉ።

GizachewShiferawየአንድነት መሪዎች ከአንዱዋለም ጋር በቅርበት ይገናኛሉ። በአንድነት ዉስጥ ያለዉን ሁኔታም አንዱዋለም ያውቃል። እሥር ቤት ባሉ፣ በነአንዱዋለም እና በዉጭ ባሉት አንድነቶች መካከል ልዩነት የለም። አቶ ፋሲል የሚያስታወሱ ከሆነ ፣ በአዲስ አበባ፣ በቀበና አንድነት፣ በጠራዉ በመቶ ሺሆች በተገኙበት ሰልፍ ላይ፣ ከእሥር ቤት የመጡ የነአንዱዋለም ደብዳቤዎች ተነበዉ ነበር። የመንፈሰና የአላማ አንድነት በአንድነቶች ዉስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነዉ። ለዚህ ነዉ አቶ ፋሲል አንዱን የአንድነት አባል በአንድ ወገን፣ ሌላዉን በሌላ ወገን ማቅረባቸው ብዙ ያላስደሰተኝ።

ለሰላምና ለእርቅ በር መክፈት፣ ገዢውን ፓርቲ ለማነጋገር መፈለግ፣ ፍርሃት አይደለም፤ የሰለጠነ የፍቅር ፖለቲካ እንጂ። ስለፍርሃት ማወቅ ከተፈለገ፣ ያገር ቤቱን ትግል ሸሽተው፣ በዉጭ «ዘራፍ» የሚሉ፣ በእነ አቶ ፋሲልም ይደገፋሉ የሚባሉ፣ የአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን ማነጋገሩ መልካም ሊሆን ይችላል። ኢንጂነር ግዛቸው እዚያው አገዛዙ አፍንጫ ሥር ሆነው እየታገሉ ያሉ ናቸው። ዉጭ ሆነን እርሳቸውን «ፈሪ» ማለት፣ ትንሽ የሚያስተዛዝብ መሰለኝ።

የአንድነት ፓርቲ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራቶች በሶስት መስክ፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ዝግጅት ላይ እንዳለ በአንድነት ራዲዮ ኢንጂነር ግዛቸው ለማስረዳት ሞከረዋል። የመጀመሪያው የተበታተኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን አሰባብሶ ጠንካራ ተቃዋሚ መመስረት ነዉ። የሕዝቡ ጥያቄ «ተባበሩ ወይንም ተሰባባበሩ» የሚል ነዉ። የህዝብን ጥያቄም አክብሮ፣ በዚህም ረገድ ንግግሮች ከአረና ትግራይና እና ከመኢአድ ጋር እየተደረጉ ናቸው። ውይይቱ ተሳክቶ መልካም ዜና እንሰማለት የሚል ተስፋ አለኝ።

ሁለተኛዉ ወደ ሕዝቡ ወርዶ የፖለቲካ ሥራ መስራት ነዉ። ከሰኔ 2005 እስከ መስከረም 2006 ዓ.ም ተደረጎ በነበረዉ የሚሊየሞች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ወቅት፣ በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በመቀሌ፣ በአዲስ አበባ፣ በአዳም፣ በፍቼ፣ በባሌ/ሮቢ. በወላይታ ሶዳ፣ በአርባ ምንጭ ፣ በጂንካ …ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል። ሕዝቡ ድረስ ተኪዶ፣ በየበሩ እየተንኳኳ፣ ወረቀቶች እየታደሉ ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲነሳ የመቀስቀስ ሥራ ተሰርቷል። ያኔ የተደረገዉ አይነት እንቅስቃሴ፣ በስፋት ፣ በተጠናከረ መልኩ፣ የሚሊየነሞች ድምጽ ለነጻነት ክፍል ሁለት፣ ሶስት በሚል ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነዉ።

በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ፣ አገዛዙ ፍቃደኛ ከሆነ፣ ያሉትን የፖለቲካ ችግሮች በሰላምና በዉይይት መፍታት ነዉ። ኢንጂነር ግዛቸው «ኢሕአዴግ ፍቃደኛ ካልሆነ፣ እጆቻችንን አጣምረን እንቀመጣለን» አላሉም። የአንድነት ፓርቲም ከአገዛዙ መመሪያ የሚቀበል ድርጅት አይደለም። የትም ቦታ ቢኬድ፣ ችግሮችን በሰላም መፍታት ከተቻለ፣ ጭንቅላት ያለው ሰው ሁሉ፣ የሚመርጠው መንገድ ያ ነዉ። እንጂነሩ ግልጽ አድርገዉታል። «ኳሷ ኢሕአዴግ ሜዳ ላይ ናት» ነዉ ያሉት። ኢሕአዴግ በሩን ከዘጋ፣ ለውይይት ፍቃደኛ ካልሆነ፣ የታሰሩ የሕሊና እሥረኞችን ካልፈታ፣ ትግሉ አይቋረጥም። ነጻነቱን እና መብቱን ሕዝቡ በልመና የሚያገኘው አይደለም። ታግሎ እንጂ።

አቶ ፋሲል ስለ ምርጫ ስነ-ምግባር ኮድም አንስተዋል። የምርጫ ስነምግባር ኮዱን ካልፈረሙ ኢሕአዴግ ሊያነጋግራቸው እንደማይፈልግ የገለጹት አቶ ፋሲል፣ ኮዱን አንድነት መፈረም እንደሚኖርበትም ይናገራሉ። እዚህ ላይ ትክክል ናቸው። ገዢዉ ፓርቲ ከነአቦነግ ጋር ያለምንም ችግር ሲደራደር፣ ከነአንድነተኖች ጋር ግን የምርጫ ስነ ምግባር መግባር ኮዱን ፈርሙ የሚል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ በሩን መዝጋቱን እናውቃለን።የምርጫ ስነ መግባር ኮዱን አንድነት ከፈረመ ደግሞ፣ እንደ ፈሪና ደካም ተቆጥሮ፣ የአንድነት ተቀባይነቱ እንደሚያሽቆለቁል አቶ ፋሲል ለመግለጽ ሞክረዋል። በዚህ ከርሳቸው ጋር ልዩነት አለኝ።

ጋዜጠኛ ፋሲል ምን ያህል ስለ ምርጫ ስነ-ምግባር ኮዱ ፣ እውቀት እንዳላቸው፣ ምን ያህልም እንዳነበቡት አላዉቅም። ኮዱ የአገሪቷ ሕግ ሆኖ የወጣ፣ አንድነትም ሆነ አገር ዉስጥ ያሉ ድርጅቶች ሁሉ የሚቀበሉት ነዉ። በኮዱ ያሉ አንቀጾች ከአንድነት መርሆዎችና እሴቶች ጋር የሚቃረኑ አይደሉም። በመርህ ደረጃ፣ በኮዱ በተካተቱት፣ ያኔም የአንድነት ፓርቲ ችግር አለነበረዉም። በኮዱ ዙሪያ የተነሱ ዉዝግቦች፣ የስነ ምግባር ኮዱ መጥፎ ሆኖ ሳይሆን፣ በሌሎች ተጨማሪ ሁለት ሰነዶች ላይ ለምን ንግግር አልተደረገም በሚል ነበር። ሕግ ሆኖ የወጣው የስነ ምግባር ኮዱ፣ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የሚተነትን ነዉ። የምርጫ አስፈጻሚዉን (ምርጫ ቦርድ) እንዲሁም የምርጫ ታዛቢዎች ሊያደርጉት ስለሚገባዉ የሚተነትኑ ሌሎች ሁለት ሰነዶች ነበሩ። በነርሱ ላይም ስምምነት ለምን አልተደረገም የሚል ነበር ክርክሩ።

UDJአንድነት ያኔ በመድረክ ዉስጥ ሆኖ ነበር የሚደራደረዉ። መድረኩ፣ «ሶስቱንም ሰነዶች ተወያይተን በሶስቱም ላይ መፈረም ነው ያለብን» የሚል አቋም ያዘ። ከዚህም የተነሳ እራሱን ከድርድር አወጣ። ያ ዉሳኔ በኔ ግምት ስህተት ነበር። አንድነት የያኔዉን የመድረክ ስህተት መድገም ያለበትም አይመስለኝም። አንዱን ሰነድ ፈርሞ፤ በሌሎቹ ሁለት ላይ በሂደት መነጋገር ይቻላል ነበር እኮ። የአንድነት ፓርቲ በሕግ የወጣዉን እና የሚቀበለዉን የምርጫ ስነ-ምግባር ኮድ ቢፈርም፣ ከዚያም የተነሳ ከአገዛዙ ጋር የዉይይትን በር ማስከፈት ቢችል፣ ትልቅ ሥራ ነበር የሚሰራዉ። አንዳንዴ በትንሹም በትልቁም ማክረር ጥሩ አይመስለኝም። ከዋናዎቹና አብየት ከሆኑ ፕሮግራሞቻችን ጋር እስካልተጋጨ ድረስ፣ በሌሎች ማናቸዉም ጉዳዮች ዘንድ ፈረንጆች እንደሚሉት ፍሌክሲቢሊቲ ሊኖረን ይገባል።

በመጨረሻ ይሄን ብዬ ላጠቃል። የአንድነት ፓርቲ ይኸው ከተመሰረተ ጀምሮ ሶስት ጠቅላላ ጉባኤዎችን አድርጓል። በሶስቱ የተለያዩ ሊቀመናብርት ነዉ የተመረጡት። የግድ ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ የለበትም፤ በማናቸዉም ጊዜ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ኢንጂነር ግዛቸውን ከሃላፊነታቸው ሊያነሳ ይችላል። ፓርቲዉን በትክክል የማይመሩ ከሆነ፣ አብዛኛዉ የአንድነት አባል ሳይደግፍ፣ ድርጅቱን በአንድ አቅጣጫ ሊወስዱት አይችሉም። ተጠያቂ ናቸውና። በመሆኑም «ከአሁን ለአሁን እንዲህ ይሆናል» የሚል መሰረት የሌለው ዉዥንብሩ ዉስጥ ባንገባ ጥሩ ነዉ። አንድ ሰው ገና ሥራ ሳይጀምር ወደ ትችት መሮጡ አግባብነት ያለውም አይመስለኝም። የአንድነት ፓርቲ ላይ ከወዲሁ ከማሟረት፣ ከዳር ሆኖ ጠጠር ከመወርወር ፣ ፓርቲዉ አገር ቤት የሚያደርጋቸውን እንቅስቅሴዎች መደገፍ ፣ ፓርቲው ሥራዉን የማይሰራ ከሆነ ደግም፣ እንደደገፍነዉም ያኔ መተቸት የአባት ነዉ።

እንግዲህ እነዚህ ጥያቄዎች ለአቶ ፋሲልም ሆነ ለተቀረዉ ኢትዮጵያ መጠየቅ እፈልጋለሁ። በኢትዮጵያ ሕዝብ ጉልበት እና አቅም እንተማመናለን ወይ ? የኢትዮጵያን ሕዝብ ከላይ እስከ ታች ማደራጀቱ ዋና የፖለቲካ ተግባር ነዉ እንላለን ወይ ? በአዲስ አበባ እና ክልሎች ሰላማዊ ሰልፎች፣ ህዝባዊ ስብሰባዎች በስፋት እንዲደረጉ፣ ህዝቡ በራሱ እንዲተማመን የማድረግ ሥራ፣ እንዲሰራ፣ በ547 ወረዳዎች ጊዜና ጉልበታቸውን ሰጥተው፣ ለመታሰር፣ ለመገደል ዝግጁ የሆኑ፣ ሕዝቡን የሚያደራጁ ታጋዮች በስፋት እንዲሰማሩ፣ ሕዝቡ ያነባቸው ዘንድ ፣ ጋዜጦች፣ የቅሰቀሳ ወረቀቶች በስፋት እንዲሰራጩ እንፈልጋለን ወይ? መልሳችን አዎን ከሆነ፣ ታዲያ የዚህ ጥረት አካል መሆን አይጠበቅብንም?


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>