Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የሳዑዲ ጉዳይ፡ እድለኛው አስከሬን የሃገሩን አፈር ቀመሰ

$
0
0

ነብዩ ሲራክ (ከሳዑዲ አረቢያ)

ወላጅ እናት ወዳጅ ዘመድ ጓደኞች አስከሬኑን በክብር ተቀብለው ፣ አልቅሰው ተላቅሰው በቀጨኔ መድሐኒአለም ጓሮ የትናንቱን ህያው ካሱ በጋሻው ወንድሜነህ የሃገሩን አፈር ዛሬ አቃመሱት: ( እህትና ሚስት እዚህ ጅዳ በሃዘን ተቆርፍደው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዳያለቅሱ እየተሳቀቁ ከእናት ጋር በስልክ ተላቅሰው አይወጣ የለም ፣ እርማቸውን አወጡ::

kassu begashaw አብሮ አደጎቹ እህቱና ውድ ባለቤቱ “ማሙሽ “እያሉ የሚያቀማጥሉት ወንድም ለሃገሩ መሬት በወላጅ ዘመድ አዝማድ ተለቅሶለት በወግ ማዕረግ የሃገሩን አፈር የቀመሰ እድለኛ ነው ። ማንነታቸው ሳይታወቅ ቀባሪ ፈላጊ አጥተው ወይ ሞቱ ተብሎ ወላጅ ዘመድ አዝማድ የሌላቸው አስከሬኖችን እጣ ፈንታ ትናንት የአስከሬኑ ሃላፊ አጫውቶኛልና ወደ ሃገሩ ገብቶ በወግ በማዕረግ ለተቀበረው ማሙሽ ሳይሆን ለራሴ እና ለቀረነው ማዘኑ ይቀለኛል …

ማሙሽ በሽዎች የምንቆጠር ለፍቶ አዳሪ ፣ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ዜጎች ሁሉ ምሳሌ ነው ! ማሙሽ ከብዙዎች ጥቂት እድለኞች የሚሆነው ያሰበው ተሳክቶለት ሳይሆን በርሃ ላይ ያለ ቀባሪ አሸዋ በልቶት ባለመቅረቱ ሲሆን ብዙ ሳይታወቁ የጠፉትን እንድናዘክርና የስደትን አስከፊነት የሚያስረዳን ጥሩ ምሳሌ ነው ! ዛሬ ማሙሽ አይሰማም፣ አያይም ፣ አይናገርም … እድለኛው አስከሬን የሃገሩነወ መሬት ቀምሷል … ትዝታው ግን በቤተሰብ በወዳጅ ዘመዶቹ ዘንድ እስከወዲያኛው ይታወሳል!

ከልጅነት እስከ እውቀት አብሮ ያደገው ወዳጀ ፍጹም ከሃዘን ተነስቶ በጻፈው መልዕክቱ “የተሸኘውን አስከሬን ተቀብለን አፈር አለበስነው !” ብሎ የጻፋትን ልብ የምትነካ ማስታወሻ ከዚህች አጭር መግቢያ ጋራ የማሙሽን ፎቶ አጅቤ ላጋራችሁ ግድ አለኝ

” የተሸኘውን አስከሬን ተቀብለን አፈር አለበስነው++++++

•••••••• ሞት ክፉ ነው! በጣም ክፉ! የክፉዎች ሁሉ ክፉ!

•••••••የዛሬን አያድርገውና አብሮ አደግ ጓዴ የራሱንና የእናቱን እንዲሁም የእህቶቹን ህይወት እለውጣለሁ ብሎ ነበር ከሀገሩ የተሰደደው። በልቡም ትልቅ የመሆን ተስፋን ሰንቆ ነገውን በብርሐን ሊሞላ አስቦ ነበር ከቤት አወጣጡ። ግና የሃሳቡን ሳይሞላ፤ የልቡን ሳያደርስ ሞት ቀደመው።
••••••••• አዎ ደግሜ እናገራለሁ ሞት ክፉ አረመኔ ነው!
ሲመጣ ዱካው የማይሰማ፤ ሲሄድ ጥላው ከሰው ልብ አልፎ በሀገር ላይ ሁላ የሚያጠላ የሆነ መዐት ነገር። ሞት የአንድን ሰው ህይወት ነጥቆ ሲሄድ ብዙዎች በህይወት ያሉትን ደግሞ ቅስም የሚሰብር፤ ልብ የሚያደማ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የክፋት ሀይልን የተላበሰ ደመኛ ነው።
•••••••••• ዛሬ ይህ ክፉ፥ እጣውን በጓዴ ላይ ጣለና ለፍቶ አዳሪውን፣ እናቱን ወዳጁን የእህቶቹ መከታውን ከቤተሰቡ ነጥሎ ከጓደኞቹ ለይቶ ወሰደው።
•••••••••የወዳጄ ሞት ልቤን ክፉኛ አሳዝኖታል።

ግን•••ግን ሐዘን እኔን ጓደኛውን እንዲህ ያሳመመኝ ያቺ የወለደችው እናቱን እንዴት አርጓት ይሆን?

አብሬው አንድ ሰፈር ስለተወለድኩ የጓዴ ሀዘን እንዲህ አንጀቴን የበላው••• አብረው በአንድ ቤት ተወልደው ያደጉት እህቶቹን የወንድማቸው ሀዘን እንዴት አርጓቸው ይሆን?

•••••አምላክ ሆይ ከሰፊው እጅህ ላይ ብዙ ፀጋዎች እንዳሉ አውቃለሁና እባክህ ለእናቱና ለቤተሰቦቹ ይህንን ከባድ የሀዘን ወቅት ያልፉት ዘንድ ከልባቸው ላይ መፅናናትና መቻልን አኑርልኝ።

++ማሙሽዬ አምላክ ነፍስህን በገነት ያኑራት++

አብሮ አደግህ
ፍጹም አረፋይኔ ” አዎ ሌላ ምን ይባላል ። ሞት ክፉ ነገር ነው!
ለመላ ወዳጅ ዘመድ እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጣችሁ!

ነቢዩ ሲራክ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>