ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደዘገበው ‹‹የፍቅር ጉዞ›› ኮንሰርት ቢሰረዝም ለቴዲ አፍሮ 4.5 ሚሊየን ብር ሄኒከን ቢራ ይከፍላል። የጋዜጣው ዘገባ እንደወረደ ይኸው፦
በደሌ ለኮንሰርቶቹ 25 ሚ.ብር መድቦ ነበር ኮንሰርቶቹ ቢሰረዙም ውዝግቡ አልተቋጨም የቴዲ ደጋፊዎች የአፀፋ ዘመቻ ጀምረዋል
አለማቀፉ የኔዘርላንድ ኩባንያ ሄኒከን ከሚያስተዳድረው በደሌ ቢራ ጋር በመሆን በበርካታ ከተሞች ሊካሄዱ የነበሩ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርቶች ቢሰረዙም፣ ቴዲ አፍሮ በውላቸው መሰረት 4.5 ሚ. ብር እንደሚከፈለው ምንጮች ገለፁ፡፡ እስካሁን በአገር ውስጥ ከተካሄዱ ኮንሰርቶች በላቀና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በድሬዳዋ ተጀምሮ በርካታ ከተሞችን እንዲያዳርስ ታስቦ የተፈረመው የቴዲ አፍሮና የበደሌ ቢራ ስምምነት፤ በኢንተርኔት በተካሄደ የተቃውሞ ዘመቻ ታውኮ ነው ሳምንት ሳይሞላው የፈረሰው፡፡ ከ20ሺ በላይ ሰዎች በኢንተርኔት በተሰባሰበ ድምጽ ለተካሄደው የተቃውሞ ዘመቻና ውዝግብ እንደመነሻ ሆኖ የሚጠቀሰው ዐረፍተ ነገር “የአፄ ምኒልክ ጦርነቶች ቅዱስ ናቸው” የሚል አባባል ሲሆን፤ ቴዲ አፍሮ የኔ አባባል አይደለም በማለት ማስተባበሉ ይታወሳል፡፡ በምኒልክ ጦርነት ብዙ ሰው አልቋል በሚል የገፋው ተቃውሞ፤ በደሌ ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ጋር እንዳይተባበር ለሄኒከን ኩባንያ ጥያቄውን በማቅረብ እንዲሰረዝ አድርጓል፡፡
የቀድሞ የአገሪቱ ነገሥታትን በተመለከተ፣ በተለይም በአፄ ምኒልክ ዙሪያ ከየአቅጣጫው “መልካም ወይም መጥፎ ናቸው” የሚባሉ የንጉሱ ድርጊቶች እየተጠቀሱ በተደጋጋሚ የፖለቲካ ጭቅጭቆች፤ መነሳታቸው አዲስ አይደለም፤ በአንድ በኩል ምኒልክ ለአገሪቱ ነፃነት፣ አንድነትና ሥልጣኔ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ስልጣናቸውን ለማስፋፋት ባካሄዱት ጦርነት ግፍ ተፈጽሟል፤ ብዙ ህዝብ አልቋል ብለው የሚያወግዙም ጥቂት አይደሉም፡፡ በመሃል ደግሞ፣ በታሪክ የተከሰቱ ነገሮችን ወደኋላ ተመልሶ መለወጥ እንደማይቻል የሚገልፁ ወገኖች፤ መጥፎ ነገሮችን እያስተካከልን መልካም ነገሮች ላይ አተኩረን እየወረስን ማሳደግ አለብን በማለት ለማስታረቅ የሚሞክሩ አሉ፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎችና ብሔረሰቦች የፈለቁ ጀግኖች ከአፄ ምኒልክ ጋር ለአገራቸው ነፃነትና ስልጣኔ ተጣጥረዋል በማለት ከአስታራቂዎቹ ወገን የተሰለፈው ቴዲ አፍሮ፤ የምኒልክን መቶኛ ሙት ዓመት በማስመልከት ለ“እንቁ” መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ ካለፈው ዘመን የሚወረሱ መልካም ታሪኮችን ጠቅሶ፣ የስህተቶችና የጥፋቶች መድሃኒት ፍቅር ነው በማለት የዘረዘራቸው ሃሳቦች ታትመው ወጥተዋል፡፡
“የአፄ ምኒልክ ጦርነቶች ቅዱስ ናቸው” የሚል ሃሳብ ግን እንዳልተናገረና በመጽሔቱ እንዳልታተመ በመጥቀስ ያስተባበለው ቴዲ አፍሮ፤ በኢንተርኔት የተሰራጨው አባባል እኔን አይወክልም ማለቱ ይታወሳል፡፡ የበደሌ ቢራ ባለቤት የሆነው የአለማችን ታዋቂ ቢራ አምራች ኩባንያ ሄኒከን፤ የበደሌ ቢራ ፋብሪካ እና የቴዲ አፍሮ ስምምነት እንዲሰረዝ የወሰነው፤ እንደብዙዎች ኩባንያዎች ሁሉ አደባባይ በወጣ ውስብስብ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ መዘፈቅ ባለመፈለጉ እንደሆነ ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ እነዚሁ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለፁት፤ በደሌ ቢራ “የፍቅር ጉዞ” በሚል ስያሜ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በበርካታ ከተሞች በተከታታይ ለሚካሄዱ ኮንሰርቶች 25ሚ. ብር ገደማ መድቦ ነበር፡፡ በደሌ 4.5 ሚ. ብር ለቴዲ አፍሮ ለመክፈል ተስማምቶ ውል ሲፈራረም 1.5 ሚ ብር የመጀመሪያ ክፍያ እንደፈፀመ የገለፁት እነዚሁ ምንጮች፤ በተለያዩ ከተሞች የሚቀርቡት ኮንሰርቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ድምቀትን የተላበሱ ለማድረግ ከ20 ሚ. ብር በላይ ወጪ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ነበር ብለዋል፡፡ በደሌ ቢራ በራሱ መሪነት በሚያዘጋጃቸው ኮንሰርቶች ላይ፣ ከትኬት ሽያጭ የሚሰበሰበውን ገቢ ለበጐ አድራጐት ድርጅቶች ለመለገስ ሃሳብ እንደነበረውም ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡
በደሌ ከኮንሰርቶቹ ዝግጅት ራሱን ለማግለል ሲወስን፣ ቀደም ሲል የተፈራረመውን ውል በሚመለከት ከቴዲ አፍሮ ጋር ተደራድሮ የውል ማፍረሻ ስምምነት መፈራረሙንም ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡ የስምምነት ማፍረሻ ስምምነቱንና የክፍያውን መጠን በተመለከተ በደሌ እና ቴዲ አፍሮ ዝርዝር መግለጫ ካለመስጠታቸውም ባሻገር፣ ከሁሉም ወገኖች መረጃ ለማግኘት የተደረጉ ሙከራዎች አልተሳኩም። በድርድር የተቋጩ ጉዳዮች ላይ ተዋዋይ ወገኖች ጉዳዩን በተናጠል በይፋ ላለመግለጽ መስማማታቸው የተለመደ እንደሆነ ምንጮቹ ጠቅሰው፤ በደሌ የመጀመሪያ ክፍያውን ጨምሮ ለቴዲ አፍሮ 4.5 ሚ. ብር የሚከፍል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ብለዋል፡፡ በኢንተርኔት ሲካሄድ የነበረው ዘመቻ፣ የበደሌ እና የቴዲ አፍሮ የስምምነት ውል ከፈረሰ በኋላ ቢረግብም፤ ያንን ተከትለው የመጡ ሌሎች ዘመቻዎች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመቃወም የተጀመረው ዘመቻ፣ በተቃራኒ ኮንሰርቱን በመደገፍ ከተፈጠረው ሌላ ዘመቻ ጋር እንካ ሰላንቲያው ቀጥሏል፡፡ በቅርብ ጊዜ የሚካሄድ ኮንሰርት ባለመኖሩ ጭቅጭቁና ዘመቻው ምን ያህል የፌስቡክ ዕድምተኞችን ሳያሰለች ሊቀጥል እንደሚችል ገና አልታወቀም፡፡