Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

እስክንደር ነጋ አሸባሪ ከተባለ ጆን ኬሪና አል ባራዴየም አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው –ግርማ ካሳ

$
0
0

ግርማ ካሳ

Eskinder-Negaኢቲቪ በቅርቡ አንድ በአንድ በኩል አሳዛኝ በሌላ በኩል አስቂኝ ዶኪሚንተሪ ለተመልካቾቹ አቅርቧል። በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል። ለዛሬ፣ የፌዴራል ከፍተኛ አቃቤ ሕግ የሆኑት፣ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ አንጋፋዉ ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋን በተመለለተ፣ በተናገሩት ላይ ጥቂት ሃሳቦችን ለመገልጽ እወዳለሁ። ሰዉዬ ስለ ሕግ፣ ስለ ሕገ መንግስቱ እየደጋገሙ አውርተዋል። ማንም ሕገ መንግስቱን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት የገለጹት፣ አቃቤ ሕጉ፣ የአገሪቷ ሕግ ሲናድ ወንጀለኞችን ይዞ ለሕግ ከማቅረብ ወደኋላ እንደማይሉ አሳስበዋል። ማለፊያ ነዉ። ወንጀለኛ መያዝና መቀጣት አለበት። ሕግ መከበር አለበት። ይሄ ብዙ አያከራክረንም።

ነገር ግን «ሕግ፣ ሕግ» እየተባለን፣ ፍጹም ሕገ ወጥ የሆነ ተግባራት፣ ሕግ አስከባሪ ነን በሚሉ እየተፈጸመ መሆኑ ነዉ ብዙ እያከራከረን ያለው። ሕግ ሁላችንንም በእኩልነት የሚዳኝ መሆኑ ቀርቶ፣ ጥቂቶች እንደፈለጉ የሚገለባብጡት፣ የመጨቆኛ መሳሪያን በርት መሆኑ ነዉ እያሳሰብን ያለው። አቶ ብርሃኑ ስለ እስክንደር ነጋ ሲናገሩ የሚከተለዉን አሉ፡

«የእስክንድርንም ኬዝ ቢሆን፣ የ2004 አረብ ስፕሪንግ አይነት፣ ኢትዮያ ዉስጥ የአመጽ ጥሪ በማድረግ ከተንቀሳቀሱ ኃይሎች አንዱ እራሱ ነዉ። እርሱ በተለይም በየተኛዉ እርስ ላይ፣ በመጻፉ ምክንያት፣ አንድም ክስ አልቀረበበትም።የእስክንድር ጉዳይ ከፍሬደም ኦፍ ኤክስፕረሽን፣ ከመናገር ነጻነት ጋር፣ ከመናገር መብት ጋር የተያይዘ በፍጹም አይደለም። ቅድም እንዳልኩት፣ የአመጽ ጥሪ ማስተላለፉ ነዉ። የአምጽ ጥሪው ደግሞ የግንቦት ሰባት ተልእኮን ለማሳካት ነዉ። ከዚህ ጋር እስከ ፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ በጣም ሰፋ ይሉ ክርክሮችን በተደጋጋሚ አድርገናል።የአገሪቱ የመጨረሻ የሆነው ፌደራል ጠቅላ ፍርድ ቤት ፤ የጠፋተኝነት ዉሳኔ ሰጧል።»

በግብጽ የታየው፣ በኢትዮጵያም እንዲደገም እስክንደር ነጋ የሚፈልግ እንደነበረ ብዙም አያክራክረንም። በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በተደረገ ስብሰባ ላይ «እንችላለን! በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች እንደሚቻል አይተናል። ኢትዮጵያ ከእነሱ ቢያንስ ቢያንስ አታንስም። ታሪክ እንስራ!» ያለዉና ኢቲቪ ቀንጥቦ ያወጣዉ አባባል ትክክለኛ አባባል ነው። እስክንደር ነጋ፣ ይሄን አልክዳእም። ሊክድም አይችልም።

«እስክንደር፣ በግብጽ የተከሰተዉ በኢትዮጵያ እንዲከሰት መፈለጉና በዚያ ዙሪያ መንቀሳቀሱ በምን መስፈርትና ሚዛን ነዉ ሽብርተኘንት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ? » በሚለው ላይ ነዉ የመጀመሪያ ክርክራችን። በግብጽ የነበረው እንቅስቃሴ ፍጹም ሰላማዊ የነበረ እንቅስቃሴ ነዉ። ከዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች መካከል የነበሩ አንዱ ዶክርተር ሞሃመድ አል ባራዴ ይባላሉ። በተባበሩት መንግስታት የአለም አቀፍ ኑክሊያር ኤጀንሲ ሰብሳቢ ሆነው ለበርካታ አመት ያገለገሉ የተከበሩ ሰው ናቸው። እንደ ሳዳም ሁሴን የመሳሰሉ ሽብርተኛ መንግስታት ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች በማከማቸት ለአለም ስጋት እንዳይፈጥሩ የታገሉ የሰላም ሰዉ ናቸው። እኝህ ሰውና የሚመሪት ድርጅታቸው እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2005 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ታዲያ ሰላማዊ በሆነ መልኩ፣ አምባገነኑ የሙባረክ መንግስት ለሕዝብ ፍቃድ ተጠያቂ እንዲሆን፣ የስርዓት ለዉጥ እንዲመጣ፣ መታገላቸው እኝህ የሰላም የኖቤል ተሸላምዊ ሽብተኛ ያደርጋቸዋልን ?

ከሰባት ወራት በፊት ጆን ኬሪ፣ ሃርድ ቶክ ቢቢሲ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተው ነበር። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቴዎድሮስ አዳኖም በዚያ ነበሩ። ጆን ኬሪ ንግግራቸውን ሲጀመሩ የተናገሩትን ማንሳት እፈልጋለሁ። በግብጽ ስለነበረው ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ሽብርተኘንት ብሎ ስለሚጠራዉ፣ እንቅስቃሴ ሲናገሩ የሚከተለዉን ነበር ያሉት፡

«…the greatest concern has to be the lack of the fulfillment by governments in many countries, of the aspirations of people. Particularly the creation of jobs, and tሀ educational opportunities that are needed, for this modern world….In Egyopt, that was not a revolution that was moved by Islamism, or any ideology ….It was young people.. ..it was you ..people who came to the square , and twitted each other , texted each other , e-mail each other and brought people»

ጆን ኬሪ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ንደ ሽብርተኝነት የሚቆጥረዉን በግብጽ የታየውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደ ትልቅ ምሳሌ አጉልተው ሲናገሩ፣ እስክንደር ነጋና ሌሎች ከተናገሩት አባባሎች ጋር የሚስማማ ንግግር ሲናገሩ፣ የሕወሃት/ኢሕአዴጉ ዶር ቴዎዶርስ ቁጭ ብለው ያዳምጡ ነበር። ታዲያ ጆን ኬሪ፣ የግብጽን እንቅስቃሰ እበነደገፋቸው፣ ወጣቶች ከግብጽ ወጣቶች እንዲማሩ በማባረታታቸው ችብርተኛ ሆኖን ? ሌላ ሌላም ምሳሌዎች ማቅረብ ይቻላል።

በግብጽ የታየዉ «አምባገነኖች» እምቢ የማለት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የአለም አቀፍ ሕግን ያከበረ፣ በሰለጠነው አለም አድናቆትን ያተረፈ፣ የሕዝብ ጉልበት ታፎኖ እንጂ ከተነሳ ተአምር ሊያደርግ እንደሚቻል ያስተማረ ፣ ለአምባገነኖች ፍርሃትን የለቀቀ እንቅስቃሴ ነዉ። ሽብርተኝነት በፍጹም አይደለም።

እንግዲህ ሕወሃት/ኢሕአዴግ እስክንደርን ሽብርተኛ እያለ መጠራቱን ከቀጠለ ጂን ኬሪ፣ የስላም የኖቤል ተሸላሚ የሆኑትን ዶር መሃመድ አልባራዴን የመሳሰሉትን ሽብርተኛ እያለ እንደሆነ መቆጠር ይኖርበታል።

ሌላዉ ማንሳት የምፈልገው አቶ ብርሃኑ ከየት ዘለዉ እስክንደር ነጋን ከግንቦት ስባት ጋር እንዳገናኙት ነዉ። በግብጽ የነበረዉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነዉ። ግንቦት ሰባት «የሰላም እንቅስቃሴ አይሰራም» ብሎ ነፍጥ ጨብጫለሁ ያለ ደርጅት ነዉ። እንዴት ተደረጎ ነዉ በግብጽ የታየዉን መደገፍ፣ የግንቦት ሰባት አባል የሚያሰኘው ? እዚህ ላይ ሕወሃት/ኢሕአዴጎች እራሳቸው ያስገመቱ ይመስለኛል። ምን አለ ባይቀልዱብን ?

በመጨረሻ በትክክለኛ መንገድ ክርክሮች ተደረገዉ በርካታ መረጃዎች ቀርበው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የጥፋተኛ ዉሳኔ እንደሰጠ በመግለጽ አቶ ብርሃኑ፣ የሕግ ስርዓት እንዳለ፣ ለማሳየት ሞክረዋል። እስክንደር ነጋ ቦምብ አላፈነዳም። ቤቱ ተበርብሮ አንድም ጥፋተኝነቱን የሚገልጽ መረጃ አልተገኘም። ወንጀሉ እንደ ጆን ኬሪ፣ ሞሃመድ አልባራዴ የግብጽ ሕዝባዊ እንቅስቃሴን መደገፉ ፣ በሕዝብ ጉልበት ኃይል መተማመኑ ነዉ። ወንጀሉ አገሩን መዉደዱ ነዉ።

«እክንድር ሽብርተኛ መሆኑን የሚያመለከት መረጃ አላየሁምና ልፈታው ነው» ባሉ ጊዜ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አማረ አሞኜ ፣ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ተጠርተዉ መመሪያ እንደተሰጣቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አንድ ወቅት ዘግቦልን ነበር። ዳኛ አማረ፣ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው፣ ምንም እንኳን ጉዳዩን ሲያዳምጡ የነበሩ እርሳቸው ቢሆንም፣ ጉዳዪን ያላዳመጣ ሌላ ዳኛ (ወይንም ካድሬ) ተመድቦ ነዉ፣ የፖለቲካ ዉሳኔዉን በፍርድ ቤት ያነበበዉ። ሐቁ እንግዲህ ይሄ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሕግ ስርዓት የለም። የግብጽ አይነቱን እንቅስቃሴ፣ የሕዝቡ መነሳት ምን ጊዜም አምባገነኖችን የሚያስጨንቅ ስለሆነ፣ ክህደት፣ ሽብር፣ ወዘተረፈ እያሉ ማሰርና መግደል ልማዳቸው ነዉ። ነገር ግን ለጊዜ ያሸነፉ ሊመስላቸው ይችላል እንጂ ወዳቂዎች ናቸው። ይህ በነ እስክንደር ላይ የምናየው ድራማ አገዛዙ በራሱ የማይተማመን፣ የደነበረ መሆኑን ያሳየ ነው፡ በሚቆጣጠሩት ሜዲያ ጠዋትና ማታ መለፈፋቸውም የዉሸታቸውና የግፋቸውን መጠን አይቀንሰውም። ሕዝቡንም ማታለል አይችሉም። ሕዝቡ ያውቃል። ሕዝቡ እስክንደር ነጋ ማን እንደሆነ ያወቃል። እስክንደር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግና ነው። እርሱ ቃሊቲ የሚቆዩባቸው ቀናት በጨመሩ ቁጥር፣ እርሱ የበለጠ እየሸነፈ፣ እነርሱ ደግሞ እየመነመኑ ፣ ምናምንቴ እየሆኑ ነዉ። እርሱ በአለም አቀፍ መድረክ እየተከበረ፣ እነርሱ ደግሞ ሃፍረት እየተከናነቡ ነዉ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles