በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኮትዲቯር የአፍሪካ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ሻምፒዮን መሆኗን አረጋገጠች።
በሞሮኮ ማራኬች ከተማ አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረውን የአፍሪካ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ዋንጫ ኮትዲቯር በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሳችው ናይጄሪያን በመርታት ነው።
የዋንጫ ተፋላሚ የነበሩት ናይጄሪያውያን በፍፃሜው ጨዋታ መደበኛ ሰዓቱን አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ቢያጠናቅቁም በመለያ ምት አምስት ለ አራት ከመሸነፍ አልዳኑም።
ናይጄሪያ በፍፃሜው ጨዋታ ገና በ ስምንተኛ ደቂቃ መሪ ለመሆን የሚያስችላትን ግብ በ አይዙ ኦሚንጐ አማካኝነት ብታስቆጥርም የፊት መስመር ተጫዋቹ ቢል ዴዲአ ከአስራ ስምንተኛ ደቂቃ በኋላ ለኮትዲቯር የአቻነቷን ግብ ከመረብ አሳርፏል።
በጨዋታው አስራ ስድስተኛ ደቂቃ ላይ ኦሚጐ የተባለውን ተጫዋች በቀይ ካርድ ያጣችው ናይጄሪያ አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ በአቻ ውጤት ብታጠናቅቅም በመለያ ምት ያባከነችው አንድ ኳስ ዋንጫውን እንዳታገኝ አድርጓታል።
ኮትዲቯር ና ናይጄሪያ በምድብ ጨዋታ ተገናኝተው ኮትዲቯር አንድ ለ ዜሮ በሆነ ውጤት ማሸነፏ ይታመናል።
የደረጃ ጨዋታቸውን ያካሄዱት ቱኒዚያና አስተናጋጇ ሞሮኮ ሙሉውን የጨዋታ ጊዜ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተው በመለያ ምት ቱኒዚያ አስራ አንድ ለ አስር አሸንፋለች። በዚህም መሠረት ቱኒዚያ ሦስተኛ ሞሮኮ አራተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል።
በዚህ ሻምፒዮና ከአንድ እስከ አራት ባለው ደረጃ ውስጥ ያጠናቀቁት አራት አገሮች በመጪው ዓመት በሚካሄደው የዓለም ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናሉ።
በመጪው ዓመት የሚካሄደውን የዓለም ከአስራ ሰባት ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እንደምታዘጋጅ ይታወቃል።
↧
ኮትዲቯር ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ሻምፒዮን ሆነች
↧