(ዘ-ሐበሻ) “ሸማመተው” በሚለው የሙዚቃ አልበሟ ባሳየችው ብቃት በተለይም በቀጣይነት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ላይ ነብስ ሊዘሩበት ይችላሉ የሚል ግምት ከሚሰጣቸው አርቲስቶች ውስጥ ገብታ የነበረችው ድምፃዊት ሚካያ በኃይሉ በ37 ዓመቷ ከዚህ ዓለም ተለየች። የቀብር ሥነስርዓቷም ዛሬ በለብይ መካነ መቃብር መፈጸሙን ከአዲስ አበባ የመጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
ላለፉት 3 ሳምንታት ያህል ለጊዜው ምንነቱ ባልተገለጸ ሕመም ስትሰቃይ እንደነበር የደረሰን መረጃ አመልክቶ ትናንት ማምሻውን ግን ህመሙ አላላውስ ሲላት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቤተሰቦቿ አማካኝነት ብትወሰድም ሕይወቷ ሊተርፍ እንዳልቻለ ተገልጿል።
አንድ ሙሉ የሙዚቃ አልበም እንዲሁም ነጠላ ዜማዎችን በመልቀቅ ታዋቂነትን ያተረፈችው ሚካያ ትምህርቷን የተከታተለቸው በቤተልሔም አንደኛ ደረጃ እና በአብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝታ ሁለተኛዋን ዲግሪ ለመጨረስ ጥቂት በቀራት ሰዓት ሞት እንደቀደማት በሕይወት ታሪኳ ላይ ተቀምጧል።
ድምጻዊት ሚካያ በኃይሉ በአፍሪካ ኮራ የሙዚቃ አዋርድ ላይ ተሳትፋ፤ በተሳተፈችበት ምድብ በ2010 ዓ.ም ከምርጥ 20 ድምፃውያን መካከል አንዷ ሆና በመመረጥ እስከ ውድድሩ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ ደርሳ እንደነበር ይታወሳል።
የአንዲት ሴት ልጅ እናት የሆነችው ድምጻዊት ሚካያ ወዳጅ ዘመዶቿ በተገኙበት ዛሬ በለቡ መካነ መቃብር፤ የቀብር ሥነ ስር ዓቷ ተፈጽሟል። ዘ-ሐበሻ በድምፃዊቷ ሞት የተሰማውን ሐዘን ትገልጻለች።