Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ምትኩ አረፈ

$
0
0

(ዘ-ሐበሻ) አርብ ሴፕቴምበር 7 ቀን 2013 ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ቴዲ (ቴዎድሮስ) ምትኩ በሜሪላንድ ግዛት ሆስፒታል መግባቱ ተገለጸ በሚል ዘ-ሐበሻ ዘግባ ነበር። ይህ ዜና እንደተሰማም በርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አፍቃሪያን ይህን ዝነኛ አርቲስት ፈጣሪ ምህረቱን እንዲሰጠው ሲጸልዩ ቆይተው ድምጻዊው ከሆስፒታል ተሽሎት ወጣ።

ሆኖም ግን ዛሬ ጠዋት ዲሴምበር 22 ቀን 2013 ዓ.ም 4፡06 ላይ ኢትዮጵያውያንን ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሲያዝናና የነበረው ቴዎድሮስ ምትኩ ማረፉ ተሰምቷል። የድምጻዊው የቀብር ቦታ እና የፍትሃት ሁኔታው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ባይሰማም፤ የፊታችን ማክሰኞ ሊሆን ይችላል የሚል መረጃ ግን ለዘ-ሐበሻ ደርሷል። ሁኔታውን ተከታትለን እንዘግባለን።

ዝነኛው ቴዎድሮስ ምትኩ የጥላሁን ገሰሰ ባለቤት እህት ከሆነችው ወ/ሮ መአዛ በዙ ጋር ላለፉት 22 ዓመታት በትዳር ዓለም ቆይቷል።

ዘ-ሐበሻ በዚህ ታዋቂ የሳክስፎን ባለሙያ የተሰማትን ሃዘን እየገለጸች ታዋቂው ጸሐፊ ዳግላስ ጴጥሮስ እንደ አርቲስት ቴዎድሮስ ምትኩ ያሉ ዝነኞችን ለማስታወስ የጻፈውን ለግንዛቤ አስተናግዳለች።
ከዳግላስ ጴጥሮስ
የአንድ ጐልማሳ ዕድሜን ያህል ወደ ኋላ ዞር እንድንል የዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ትዝታ ይቀሰቅሳል – ከ1960ዎቹ ዓመታት በፊት፡፡ በእነዚያ ዓመታት ውስጥ በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ በድንቅ ባህልነቱ የሚጠቀስ አንድ ጥበብ በተለየ ሁኔታ አብቦ ነበር፡፡ ያውም የሙዚቃ ጥበብ፡፡
ይሁን እንጂ ይህን መሰሉ ባህል ከዘመን ዘመን የሚሸጋገር ፍሬ እንዳያፈራ «የሥርዓቶች ዋግ መትቶት» በአበባ ብቻ ሊቀር ግድ ሆኗል፡፡ በጭንገፋ ተመትቶ «ግባ መሬቱ» የተፈፀመው ይህ የጥበብ ቡቃያ ፍሬው ከትውልድ ትውልድ እንዳይተላለፍ በእሸትነቱ ስለ ተቀጨ እነሆ የዛሬው ጥበብ ነክ ችግራችን ገዝፎና ሥር ሰዶ «ለወይነዶ!» ቁጭት ዳርጎናል፡፡
ዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ምትኩ አረፈ
«ዛሬ» የሚለው ቃል በጽሑፌ ውስጥ መደጋገሙ አለብልሃት አይደለምና አንባብያን እንድትታገሱኝ በመቅድም አቤቱታ እማፀናለሁ፡፡
እናም የዛሬን አያድርገውና ለልዩ ልዩ ሕዝባዊ ክብረ በዓላት በመዲናችን አዲስ አበባና በዋና ዋና የሀገራችን ከተሞች በዓላቱን የሚያደምቁት የማርች ባንድ (በተለምዶ ማርሽ ባንድ የሚባለው) ሙዚቀኞች ከወታደራዊ ክፍሎች የተገኙት ብቻ አልነበሩም፡፡ ከእነርሱ ባልተናነሰ ደረጃ ያውም በተሟላ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተደራጅተውና ማራኪ የደንብ ልብስ ለብሰው ጥዑም ዜማቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡ የትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንዶች ያበቡበት ወቅት ነበር፡፡ ወጣትነት በለገሳቸው መለሎ ቁመት እየተውረገረጉ የተመልካችን ቀልብ ይስቡ የነበሩት እኒያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዳጊ የሙዚቃ ጠበብት ዘግይቶ በተፈጠረው ትውልድ ይዘነጉ ካልሆነ በስተቀር በታሪክ መዝገብ ውስጥ ግን ህያው እንደሆኑ መቆየታቸውን የሚደልዝ የተሟጋች ብዕር አይኖርም፡፡
ዳግማዊ ምኒልክን፣ ኰከበ ጽባሕን፣ የደሴው ወ/ሮ ስሂንና የናዝሬቱን አፄ ገላውዲዎስ ትምህርት ቤቶች ብቻ ለጊዜው በክብር ልዘክር፡፡ እነዚያ ትምህርት ቤቶች የነበራቸው የሙዚቃ ባንዶች (ኦርኬስትራና ማርቺንግ ባንድ) በወቅቱ ለተደረሰበት የሙዚቃ ዕድገት ከፍታ ብቻ ሳይሆን በእነዚያ የሙዚቃ ባንዶች ውስጥ ተፈጥረው፣ አድገውና በጥበቡ ተራቅቀው ከሙዚቃ ጋር ነፍስና ሥጋቸው እንደተቆራኘ የሚገኙ ባለሙያዎች ቁጥር ቀላል የሚሰኝ አይደለም፡፡ ሌሎቹን ጥበባት ወቅትና ጊዜ ሲፈቅድ አስታውሳቸዋለሁ፡፡
«ክርስቶስ ለሥጋው አደላ” እንዲሉ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዕውቀት የተጐነጨበትን የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ የሚያስታውሰው በትልቅ አክብሮት ነው፡፡ ልዩ ልዩ ክበረ በዓላት ሲመጡ አዲስ የሙዚቃ ቅንብር ለመፍጠር ቀን ከሌት ይደረግ የነበረው ኃላፊነት የተሞላበት የተማሪ ጓደኞቹ የሸብ ረብ ዝግጅት አስደናቂ የሚሰኝ ብቻ ሳይሆን ከግምት በላይ ሊነገርለት የሚገባ ነው፡፡ በወርቃማ ጐፈርና በቀይና ቢጫ ቀለማት የተዋበው የተማሪዎቹ የሙዚቃ ባንድ ገና የትምህርት ቤቱን በር አልፎ ወደ ዋናው የአራት ኪሎ አውራ ጐዳና ሲገባ በዕልልታ ይቀርብለት የነበረው የሕዝብ አቀባበል ወደር አልነበረውም፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንዶች ውስጥ ያገለግሉ የነበሩት የያን ጊዜዎቹ ተማሪዎች በኋለኞቹ የጉልምስና ዕድሜያቸው ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት የተጫወቱት ሚና እንዲህ በዋዛ በቀላል የሃሳብ ጥቅሻ የሚታለፍ ስላይደለ ጥቂቶቹን ብቻ ለአብነት በመጥቀስ ዝርዝሩን በይደር ማስተላለፉ ይበጃል፡፡

ወደ ኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት እስኪዛወር ድረስ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ማርቺንግ ባንድ ታንቡር መች የነበረው የሙዚቃው ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደና በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከከፍተኛ የሥራ መሪነት እስከ መምህርነት እያገለገለ የሚገኘው አቶ ሰሎሞን ሉሉን ብቻ ለአብነት አስታውሼ ልልፍ፡፡ አቶ ሰሎሞን ሉሉ አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር የዜማ ደራሲ እንደሆነም ማስታወሱ አስፈላጊ ነው፡፡
እኒህን መሰል ጐምቱ የሙዚቃ ጠበብት ተኰትኩተው ያደጉት በአንጋፋው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ ውስጥ ነው፡፡ እኒህንና ሌሎች በርካታ ወጣቶችን ሲያሰለጥኑ የነበሩት አቶ ዘውዱና አቶ መብራቱም የማይዘነጉ የጥበቡ ፊታውራሪዎች ነበሩ፡፡
የኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድም ልክ እንደ ትምህርት ቤቱ ስም ሁሉ በወቅቱ የፈካ አጥቢያ ኰከብ ነበር፡፡ በዚያ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ አድገው የወጡት ወጣቶችም በሀገራችን የሙዚቃና የቴአትር ጥበብ ላይ ያሳረፉት በጐ አሻራ ሊዘነጋ ከቶውንም አይችልም፡፡ ጥቂቱቹን ልዘክር፡፡ የትምህርት ቤቱ ዘንግ ወርዋሪ፣ ትራንፔት ተጫዋችና ድምፃዊ የነበረው ዓለሙ ገብረአብ እንዴት ይረሳል፡፡ ዓለሙ ገብረአብ ሕይወቱ እስካለፈ ጊዜ ድረስ የብሔራዊ ቴአትር ቤት ፈርጥ ተዋናይ ነበር፡፡
ዛሬ በውጭ ሀገራት ኑሮአቸውን የመሠረቱት ዝነኞቹ የሙዚቃ ባለሙያ ወንድማማቾቹ ተሾመ ምትኩና ቴዎድሮስ ምትኩ የኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ አባላት ነበሩ፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከዲሬክተርነት እስከ መምህርነት የዘለቀው አቶ ተክለ ዮሐንስ ዝቄ የዚሁ ትምህርት ቤት ፍሬ ነው፡፡ ታምራት ፈረንጅ፣ ተስፋዬ መኰንን፣ ታምራት ሎቴ፣ ሞገስ ሀብቴ ብዙዎቹ በሕይወት ባይኖሩም በተነደፉበት የሙዚቃ ፍቅር እስከ መጨረሻ የዘለቁት የኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ባንድ ከጥበቡ ፍቅር ጋር ስላቆራኛቸው ነበር፡፡ የእነዚህ ወጣቶች አሠልጣኝ የነበሩት አቶ ማሞ ደምሴና አቶ ጌታነህ ታደሰም አይዘነጉም፡፡ በምሥረታውና በማጠናከሩ ሂደት ላይ የጐላ ድርሻ የነበራቸው ዳኒሻዊውን ፓል ባንክ ሃንሰንን የመሳሰሉ የውጭ ሀገር መምህራንን ለጊዜው በማስታወስ ብቻ እናልፋቸዋለን፡፡
የዝነኛው የደሴው ወ/ሮ ስሂን ትምህርት ቤት የወጣቶች ፖለቲካዊና ሁለገብ ገናና ተሳትፎ በታሪክ የከበረ ቦታ እንዳለው አይደለም የሰው ምስክርነት ሣር ቅጠሉም ቢሆን እኔ ልናገር ብሎ ለዋቢነት መሽቀዳደሙ አይቀርም፡፡ በተለይ ግን የወ/ሮ ስሂን ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ በወቅቱ የነበሩትን ወታደራዊ የሙዚቃ ባንዶችን ብቃት በከፍተኛ ሁኔታ ይፈታተን እንደነበር ዕድሜውን የታደሉት ሁሉ የሚያስታውሱት ነው፡፡
የናዝሬቱ ዓፄ ገላውዲዎስ፣ የሐረሮቹ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት እና የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም የሙዚቃ ባንዶችም የነበራቸው ዝና እንዲሁ በጥቂት ቃላት እየታወሰ የሚታለፍ ባይሆንም ዝርዝሩን ለታሪክ ጸሐፍት በመተው ለዝክር ያህል ስማቸውን አስታውሰን እናልፋለን፡፡ የአዲስ አበባዎቹን መድኃኒዓለም ትምህርት ቤትና ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትን በተመለከተ ግን ንባቤና መረጃዬ ስላልዳበረ እንዲህ ነበሩ ለማለት ድፍረት አጥቻለሁ፡፡ እነዚህን ሁለት ትምህርት ቤቶች በተመለከተ አዋቂዎች ቢያስተምሩን ነበርኩበት ባዮች ቢያሳውቁን ለዕውቀታችን በእጅጉ ይጠቅመናል፤ ከስህተትም ይታደገናል፡፡ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤትን ካነሳሁ አይቀር ብዕረ መንገዴን በትምህርት ቤቱ ዋና መግቢያ ላይ ይነበብ የነበረውንና በፍፁም ከህሊናዬ ሊወጣ የማይችለውን ጥቅስ አስታውሼ ልለፍ፤ «ከዚህ ከማይሞተው የሰው ልጅ ማደጊያ ሥፍራ ግቡ» የሚለውን፡፡ ዛሬስ ያ ጥቅስ በቦታው ይገኝ ይሆን?
በውስን የጋዜጣ ገጽ ግዙፍ ሃሳቦችን ማስተናገድ ፈተናው የትዬለሌ መሆኑን አንባቢያን እንደሚረዱት ተስፋ በማድረግ ወደ ማጠቃለያው ሃሳብ ብዕሬን በፍጥነት ማንደርደሩን መርጫለሁ፡፡
ዛሬን ከቀዳሚ ዘመናት ጋር እያስተያዩ ይህ ጐደለ ይህ ሞላ ማለቱ አግባብ ባይሆንም ትናንትን ከዛሬ ጋር እያነፃፀሩ መልካሙን ማስታወሱ ግን ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ለምን ቢሉ፤ «ብልህ ከትናንት ይማራል፣ ሞኝ ግን ዕለት በዕለት ይሳሳታል» እንዲሉ መሆኑ ነው፡፡
ከላይ በተዘረዘሩት ትምህርት ቤቶች የሙዚቃ ባንድ ውስጥ አባላት የነበሩት ወጣት ተማሪዎች ትምህርት ቤታቸውን ከተሰናበቱ በኋላ ምን ሠሩ? ምን ፈፀሙ? ዛሬስ የት ናቸው? ተገቢ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በታዳጊነት ዕድሜ ከመደበኛው ትምህርታቸው ጐን ለጐን በሙዚቃ ፍቅር የወደቁት እኒያ ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሸናፊነት ተወጥተው በልዩ ልዩ ሙያቸው ለሀገራቸው ኩራት እንደነበሩና እንደሆኑ ሥራቸውና ስማቸው ምስክር ነው፡፡
ለአብነት ያህልም በዘመኑ ዝነኛ ባንድ የነበረውን «ሶል ኤኰስ» በመባል ይታወቅ የነበረውን ባንድ የመሠረቱት በኰከበ ጽባሕ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ የነበሩት ተስፋዬ (ሆዶ) መኰንን (ከበሮ መቺ)፣ ታምራት ፈረንጅ (ትራምፔት ተጫዋችና ድምፃዊ)፣ ተክለ ዮሐንስ ዝቄ (ትራምፔት)፣ ተሾመ ምትኩ (ጋራ ሥር ነው ቤትሽ፣ ሞት አደላድሎን፣ ሃሳቤን የመሳሰሉት ዝነኛ ዜማዎቹ ይጠቀሳሉ) እና ቴዎድሮስ ምትኩ (ሳክሲፎኒስት) የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ የኰከበ ጽባሕ ፍሬዎች ከሶል ኤኰስ በፊትም ዙላ ባንድን መሥርተው ነበር፡፡ «ሶል ኤኰስ» ባንድን ወደ «አይቤክስ ባንድ» ከዚያም «ሮሃ ባንድ» ወዘተ. እየተባለ የስም ሽግግር በሚደረግበት ጊዜ ሁሉ እነዚያ ወጣቶች በንቃት ተሳታፊ ነበሩ፡፡
በዚያ ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ የትምህርት ቤቶቹ የሙዚቃ ባንድ አባላት በሀገራችን የሙዚቃ ጥበብ ውስጥ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ዛሬም ድረስ የደበዘዘ አይደለም፡፡ እንዲያውም ብዙ ታላላቅ የጥበቡ ሰዎችን አሁን ድረስ ለደረሱበት ደረጃ መሠረት የሆናቸውን መደላድል ጥቀሱ ቢባሉ ያለጥርጥር ምሥጋና የሚያቀርቡት ላሳደጋቸው የየትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ባንድ እንደሆነ መገመት አይገድም፡፡
ይህ ታላቅ የጥበብ መክሊት በዛሬዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ አለወይ? ርግጥ የዕውቀትና የጥበብ ሁሉ መፍለቂያው ትምህርት ቤት መሆኑ መስካሪ አያሻውም፡፡ ግን ግን በየትምህርት ቤቱ ለዛሬውም ሆነ ለነገው ሙዚቃችን መሠረት ሊሆን የሚችል ሥራ እየተሠራ ነው? ከመደበኛው ሥርዓተ ትምህርት ጐን ለጎን ለሙዚቃ ጥበብ እየተሠጠ ያለው ትኩረት ምን ያህል ነው? የትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን «የተቀበረውን ውጤታማ መክሊት» ቆፍሮ ለማውጣት ምን እየሠራ ይሆን? ዳግማዊ ምኒልክ፣ ኰከበ ጽባሕ፣ ወ/ሮ ስሂን … ትምህርት ቤቶችስ «ነበር» ታሪካቸውን ማደስ አይገባቸውምን? የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወድቋል ወይም ተነስቷል እያልን መከራከራችን ብቻ በራሱ በቂ ይሆናልን? ምን ያህሉን መክሊቶቻችንስ አርቀን በመቆፈር ያለማስተዋል ቋጥኝ ጭነንባቸው ቀበርናቸው ይሆን? እንወያይበት፣ እንምከርበት፡፡ ከንባቤ ጎን ለጎን ለዚህ ጽሑፍ በቂ ግብዓት በመስጠት የተባበሩኝን አርቲስት እሸቱ ጥሩነህ፣ ደራሲና ሃያሲ አስፋው ዳምጤና አቶ ተክለዮሐንስ ዝቄን ክብረት ይስጥልኝ በማለት በአንባቢያን ስም የማመሰግነው በታላቅ አክብሮት ነው፡፡ ሰላም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>