Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

‹‹ጎልጎታ››፡- ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር . . . !!!

$
0
0

Gologotaበፍቅር ለይኩን፡፡

ለዚህ መጣጥፌ የመረጥኩት የእውቁ ሠዓሊና ባለ ቅኔ የገብረ ክርስቶስ ደስታን ‹‹ጎልጎታ›› በሚል ርዕስ የተጠበበትን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሥነ ስቅለት አስደናቂና ዘመን አይሽሬ (classical) ሥራውን ነው፡፡ የዚህን ገጣሚና ሰዓሊ፣ እጅግ ተወዳጅና ተደናቂው የሆነውን ‹‹የጎልጎታን›› ስነ ስቅለት፣ ፍቅርን ተጠበበትን ድንቅ ሥራውን ፅንሰትና ውልደት ታሪክ በአጭሩ ላውጋችኹ፡፡

ገጣሚና ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ስሙ ጎልቶ ከሚጠቀሱ የስነ ጥበብ ሰዎች ዘንድ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ እውቅና ታላቅ ሰው ነው፡፡ ገ/ክርስቶስ ዘመናዊ የስዕል ሙያን በአገር ውስጥና በአውሮፓ ከተማረ በኋላ በአገሩ እምብዛም አልቆየም ነበር፡፡ በአገራችን በተከሰተው የ1966ቱ አብዮትና ከነደደው የነውጥና የለውጥ እሳት የተነሣ እንደ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ወገኖቹ የእርሱም ዕጣ ፈንታ ስደት ሆኖ ነበር፡፡
ገ/ክርስቶስ በትምህርትና በስደት ሕይወት ለረጅም ዓመታት በባሕረ ማዶ በቆየባቸው ጊዜያት ውስጥ አውሮፓውያኑ ወይም በአጠቃላይ ነጮች ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ያላቸው ዘረኝነት፣ ንቀትና ጥላቻ በእጅጉ ያብሰለስለውና እረፍት ይነሳው ነበር፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምድር ተምሳሌት፣ በዓለማችን ታሪክ ታይቶና፣ ተሰምቶ በማይታወቅ ጀግንነትና ወኔ ኢትዮጵያውያን፣ አባቶቹ ወራሪውን የኢጣሊያንን ቅኝ ገዢ ኃይል በዓድዋ ጦር ግንባር በአኩሪ ጀግንነት አሳፍረው የመለሱ ኃያላን መሆናቸውን አሳምሮ ለሚያውቀው ገ/ክርስቶስ ይህ የአውሮፓውኑ ትምክህትና ንቀት ከመገረምም በላይ ሆኖበት ነበር፡፡

በዚህ የአገሩ ታሪክም በእጅጉ የሚኮራውና በዓለም ታሪክ አንጸባራቂ የሆነ የጥቁር ሕዝቦችን ነፃነት ድል፣ ፋና ወጊን ታሪክ በደማቸው ከፃፉ፣ የነፃነት ምድር ከሆነችው ከኢትዮጵያ ለተሰደደው፣ ለነፃነቱና ለክብሩ ቀናዒ ለሆነው ገ/ክርስቶስ ደስታ፤ አውሮፓውያኑ በጥቁሮች ወገኖቹ ላይ ያንጸባርቁት የነበረው ንቀትና ጥላቻ ፈፅሞ ሊቀበለው የማይችልና ሊቋቋመው ያቃተው ፈታኝ ገጠመኙ ነበር፡፡

ገ/ክርስቶስ በዚህ እጅግ በከፋውና ክፉኛ ቅሬታ ስላሳደረበት የአውሮፓውያኑ ዘረኝነት፣ የስደትና የብቸኝነት ዘመኑ፣ በእናት ምድሩ ናፍቆትና ትዝታ ነጋ ጠባ እንደ ሽንብራ እየተንገረገበ በጻፈው ‹‹አገሬ›› በሚለው ግጥሙ፣ አገሩ ኢትዮጵያ የሺሕ ዘመናት የስልጣኔ፣ የታሪክና የቅርስ ባለቤት፣ እንዲሁም የጥቁሮች ሕዝቦችና የሰው ልጆች ሁሉ ነፃነትና ሰብአዊ ክብር ተምሳሌትና መገለጫ አገር መሆኗን እንዲህ በሚል ስንኝ ነበር፤ አገሩን ከነፍሱ በፈለቀች ቅኔው የገለጻት፡-
… አገሬ ዓርማ ነው የነጻነት ዋንጫ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ።
እሾህ ነው አገሬ፣
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ።
… አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት።
ለምለም ነው አገሬ፣
ውበት ነው አገሬ፣
ገነት ነው አገሬ።
… ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ።
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ።
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ …፡፡
~ገብረክርስቶስ ደስታ፡፡
በዚህ ግጥም ውስጥ ገ/ክርስቶስ ለእናት ምድሩ ያለውን ፍቅሩን፣ ሰቀቀኑን፣ ናፍቆቱንና ትዝታውን ነፍስን በሚያማልል፣ አጥንት ድረስ ዘልቆ ሊሰማ በሚችል ስዕላዊ ቋንቋ የአገር ፍቅር ህመሙን፣ ስቃዩን፣ ጩኸቱንና ሰቀቀኑን እንዲህ ባለ ሕብረ ዜማ፣ ልዩ ቋንቋ ከነፍስያው ጋር እያወጋ፣ እንዲህ ለእኛም ህመሙን፣ የአገር ፍቅር ትዝታውንና ናፍቆቱን በሚጥም ዜማና ቋንቋ አካፍሎናል፡፡

አውሮፓውያኑ ዘንድ ‹‹ጥቁር በምንም ዓይነት ከነጮች ጋር በእኩልነት እንዲመደብ የሚያስችለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ስብእና የለውም፡፡›› በሚለው እሳቤያቸው ከአፍሪካ የጀግኖች ምድር ከሆነችው ከኢትዮጵያ ለሄደው ገ/ክርስቶስ የስነ ልቦና ቀውስ አሳድሮበት ነበር፡፡ ከዛም አልፎ ‹‹እግዚአብሔር ነጭ ወይም አውሮፓዊ›› እንደሆነ በድፍረት በሚሰብኩበት በዛ በባዕድ ምድር ያ የጥበብ ምርኮኛ ኢትዮጵያዊ በእጅጉ ልቡ ተነክቶ፣ ነፍሱም ክፉኛ አዝናበት ነበር፡፡

እናም ይህ የጥቁር ምድር፣ አፈር ትሩፋት የሆነው ጥበበኛው ገ/ክርስቶስ ከእኛ በላይ ክርስቲያን ለአሣር በሚሉትና ይህን የአውሮፓውያኑን መርዘኛ፣ ዘረኛ አስተሳሰብና ምልከታ፣ ጥልቅና ምጡቅ በሆነ የጥበብ ሥራው ሊሞግታቸው፣ ሊያሳፍራቸው ከነፍሱና ከመንፈሱ ጋር ተማከረ፡፡

ከልጅነቱ ጀምሮ ከታወቁት የቅኔ መምህርና የተዋሕዶ ሊቅ ከሆኑት ከአባቱ ከአለቃ ደስታ ነገዎ ዘንድ ፊደል ቆጥሮ፣ ዳዊት ደግሞ፣ ዜማ ተምሮ፣ በዘመኑ የነበሩትን የአባቱን ዘመነኞች ሊቃውንት ቅኔና የመንፈሳዊን ዓለም ረቂቅ የሆነ ትንታኔና ትርጓሜ የሆነ ጥልቅ እውቀት ጠዋት ማታ እየሰማ ላደገው ለገ/ክርስቶስ፣ መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር በምን መንገድ፣ በምን ጥበብ የአውሮፓዊነት ወይም የነጭነት ቆዳን ወይም መልክን እንደተጎናጸፈ ፈፅሞ ግራ ነበር ያጋባው፡፡

እናም ይህ እውቀት የሥጋ፣ ይኽ ድንቁርናም ከክፉው፣ የዚህ ጥበባቸው ምንጩም አጋንት- የሐሰት አባት ዲያቢሎስ መሆኑን ሊነግራቸው ሠዓሊው ቀለሙን በጠበጠ፣ ብሩሹን ወደረ፣ ሸራውንም ወጠረ፡፡ የአውሮፓውያኑን የዘርኝነት እኩይ አስተሳሰብ፣ ከሰው ዘር አልፎ እግዚአብሔርን ሳይቀር እንኳን ነጭና ዘረኛ ያደረጉበትን ከንቱ የሆነውን ትምክህታቸውንና ድንቁርናቸውን የእንቧይ ካብ መሆኑን በግልፅ ሊነግራቸው ቆርጦ ገ/ክርስቶስ ቀለሙን ከሸራው አዋኻደ፡፡

እናም ጥበበኛው በስዕሉ ዓለምን ያስደመመ ድንቅ የፍቅርን ቅኔን በብሩሹ ተቀኘ፡፡ ባለ ቅኔውና ሰዓሊው ገ/ክርስቶስ ይህን ‹‹ጎልጎታ›› ብሎ የሰየመውን ቆዳ አምላኪዎቹን፣ አውሮፓውያኑን ሣይቀር በእጅጉ ያስደመመውን ይህን ታላቁን የጥበብ ሥራውን በቅዱስ ቅናት፣ ከፍቅርና ከእውነት በመነጨ እውቀት ተነሳስቶ ነበር የሳለው፡፡ በዚህም ድንቅ የጥበብ ሥራው ገ/ክርስቶስ አውሮፓውያኑን ዘረኞችና ትምክህተኞች እንዲህ ሲል በጥበብ ሥራው ሞገታቸው፣ አሳፈራቸውም፡-

እናንተ እናመልከዋለን የምትሉት እግዚአብሔር ግን ነጭም ጥቁር ወይም ቢጫም አይደለም፡፡ አፍሪካዊም አውሮፓዊም ወይም አሜሪካዊ አይደለም፡፡ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ፣ የጥበብ ሁሉ መዝገብ፣ የፍቅር ምንጭ የሆነ- የፍቅር አምላክ ነው!! እናም እርሱን የዘር፣ የጎሳ፣ የነገድ፣ የቋንቋ፣ የቆዳ የቀለም ድንበር ፈፅሞ የማይለየው፣ የማይገድበው ሁለተናው ፍቅር የሆነ፣ በፍቅር የተጥለቀለቀ፣ በፍቅር ስለ ፍቅር የቆሰለ፣ በፍቅር ስለ ፍቅር በደም የተነከረ፣ ደምግባቱና ውበቱ ደም የጎረፈበት፣ በደም የተረጨ፣ በደም የታተመ፣ በደም የተጥለቀለቀ፣ ሞትን በሞት የረታ ሕያው፣ ዘላለማዊ ፍ-ቅ-ር ነው!!

ይህ ተአምረኛ የሆነው የገ/ክርስቶስ ‹‹ጎልጎታ›› የጥበብ ሥራው፡- የህማም ሰው፣ እንወደው ዘንድ ደምግባት የሌለውን፣ ውበት የራቀውን፣ የተናቀውን፣ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ መተላለፍ ቆሰለውን፣ ስለ በደላችንም የደቀቀውን፣ ስለ እኛ ብርቱ ህመምን የታመመውን፣ በጌተ ሰማኒ የደም ላብ ያላበውን፣ ስለ ክፋታችን የተጨነቀውን፣ በቀራኒዮ አደባባይ የተቸነከረውን፣ ክርስቶስ ኢየሱስን በደም ገለጸው፡፡

የእሾኽ አክሊልን የደፋው ራሱ፣ በሚስማር የተቸነከሩት ቅዱሳን እጆቹና እግሮቹ፣ በጦር የተዋጋው ጎኑ፣ በሮማውያኑ ጅራፍ የተተለተለው ጀርባውና የቆሰለው መላው አካላቱ፣ ፍቅርንና ምሕረትን በደም ጅረት፣ ለአዳም ልጆች ሁሉ የሚያውጁ፣ ዘላለማዊ የሆኑ የፍቅር ሕያው ማህተሞች መሆናቸውን በይፋ ገለጸላቸው፡፡

እርሱ ኢየሱስ መቼም መቼም የማይደበዝዝ፣ የማይነጥፍ፣ የማይደርቅ ሕያው የፍቅር ደም ጅረት፣ የዘላለም ሕይወት ምንጭ፣ የደም መሥዋዕት፣ ረቂቅ ውበትን የተጎናጸፈ ቅዱስ መሥዋዕት መሆኑን ጠቢቡ በብሩሹ በቀይ ቀለም፣ በደም ቋንቋ ገለጸልን፣ ተቀኘልንም፡፡

የዚህ ትንግርተኛ የጥበብ ሰው የገ/ክርስቶስ ዘመን አይሽሬ ሥራው በሸራ ሰሌዳ፣ በብሩሽ ቀለም፣ በደም ቋንቋ፣ እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ፡- በቀራኒዮ ባፈሰሰው በክቡር ደሙ ፈሳሽነት ለሰማያዊው አባቱ ሰዎችን ሁሉ ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋም ሁሉ፣ ከወገንም ሁሉ፣ ከሕዝብም ሁሉ የዋጀ ሕያውና ዘላለማዊ ፍቅር መሆኑ ነገረን፣ አወጀልን፡፡

በእርግጥም እርሱ ሕዝብን ከአሕዛብ፣ አይሁዳውያንን ከግሪክ፣ ነጩን ከጥቁሩ፣ ኢትጵያውኑን ከአውሮፓዊው ጋር አንድ ያደረገ ፍ-ቅ-ር . . . የፍቅር አምላክ፣ ንጹሕ፣ መዓዛው የተወደደ፣ ሽታው ያማረ የፍቅር መሥዋዕት ነው!!

ስለዚህም ይህ ፍቅር አለ ጥበበኛው ገ/ክርስቶስ፣ ይህ ፍ-ቅ-ር ዘር፣ ጎሳ፣ ቀለም፣ ዜግነት ሳይል ሁሉንም በእኩልነት የሚያፈቅር እንጂ እናንተ እንደምታስቡት እግዚአብሔር ነጭ፣ ፈጣሪ አውሮፓዊ ወይም አሜሪካዊ አሊያም አፍሪካዊ አይደለም …፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ፍቅርም እግዚአብሔር ነው እንጂ፡፡ ‹‹በጎልጎታ›› ድንቅ የጥበብ ሥራው ገብሬ ኢየሱስ የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ በደም የታታመ፣ በደም የተዋበ፣ ፍጹም ፍ-ቅ-ር፣ ሕያው ፍ-ቅ-ር፣ በፍቅር ስለ ፍቅር የተሠዋ የመሥዋዕት በግ ነው እንጂ፤

ሲል ገ/ክርስቶስ ይህን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን የቀራኒዮውን ፍቅሩን ‹‹ጎልጎታ›› ብሎ በሰየመው የጥበብ ሥራው በደም ቀለም፣ በደም ጎርፍ፣ በደም ብሩሽ ፅልመት በዋጠው በመሰለው ሸራው ላይ በብሩሹ ፍቅርን በደም ጎርፍ፣ ፍቅርን በደም አበላ እንዲህ ተጠበበት፣ እንዲህ ተደመመበት፣ እንዲህ ተቀኘበት፡፡

‹‹ጎልጎታ›› የገብረ ክርስቶስ ዘመን አይሽሬ (Classical) የሆነች በብዙዎች ነፍስ፣ አጥንትና ጅማት ድረስ ዘልቃ፣ የፍቅርን ብርቱ፣ ኃይልና ጽናት የምትገልጽ ሥራው እንደሆነች በርካታ አድናቂዎቹ ይመሰክራሉ፡፡ በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት (Ethiopian Studies Journal) ላይ የገ/ክርስቶስ የጥበብ ልጁና የሙያው ባልደረባ የሆነው አቶ እሸቱ ጥሩነህ ስለ ገብሬ ታሪክና ስለ ‹‹ጎልጎታ›› ድንቅዬ የጥበበብ ሥራው ባቀረበው የጥናት ጽሑፉ እንዲህ ነበር ያለው፡-

… ይህ የገ/ክርስቶስ ደስታ የሥነ ሥቅለት ስዕላዊ ድርሰት የፍቅርን፣ የመሥዋዕትነትን፣ የቤዛነትን፣ የሕያውነትና የዘላለማዊነትን፣ እንዲሁም የነፃነትንና ሰላምን ምንነት ባጫሩ በሕብረ ቀለማት የቃኘበትና የተቀኘበት ነው፡፡ መስቀሉ እውነታዊ ነው፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ ግን ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ሥዕሉ እስከተሠራበት እስከዚያን ጊዜ ድረስ ብዙ ሠዓሊዎች አካሉን ወይም ስጋውን አልፎም እውነታዊ ምስሉን ከነስቃዩ ይስላሉ እንጂ፣ እንደ ገብረ ክርስቶስ ክቡር ደሙን፣ ንጹሕ መሥዋዕትነቱን በቀይ ሕብረ ቀለም ብቻ ተምሳሌት አድርገውና ወሰነው የሠሩ የሉም … ፡፡

ይህን በሚመለከት ይላል አቶ እሸቱ ጥሩነህ፣ ‹‹የገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ አጭር ትውስታና ጨረፍታዊ ዕይታ›› በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባቀረበው በዚሁ ጥናቱ፣ ይህን በሚመለከት የጀርመን አገር ጓደኛው የነበረው ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል ይለናል፡-

ሰዓሊ ተብሎ የጎልጎታን ተራራ ያልወጣ፣ የቀራኒዮን ትልቁን ትራጀዲ ያላየ የለም፤ ግን የገብረ ክርስቶስ ሥነ-ስቅለት ለብቻው ነው፡፡ ቀለም ተናጋሪው ነው፣ የሚታየው ንጹሕ ደም ብቻ ነው፡፡ ግራና ቀኝ የነበሩት (የተሰቀሉት) እነ ፋይታዊ ቦታ የላቸውም ተዘንግተዋል፡፡ ወይም ሠዓሊው ሊያያቸው አልፈለገም፣ ይገርማል፡፡ ጥበብ ከንጹሕነት ከጽርየት ከርቀት ብቻ እንጂ ከሌላ ጋር ግንኙነት የሌላት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡

ዛሬም ድረስ የገ/ክርስቶስ የፍቅር፣ የናፍቆት፣ የነፍሱ ስቃይና ጣር የሆነችው ‹‹ጎልጎታ›› የፍቅር ሕያው መዝገብ፣ የጥበብ ቁንጮ ሥራ ሆና በዚህ ክብሯ፣ ማዕረጓና ሕያውነቷ ዘልቃለች፡፡ ፍቅርን በመሥዋዕትነት፣ ፍቅርን በእውነት፣ ፍቅርን በደም እየተረከች፣ በደም እየሞሸረች፣ በእሾኽ አክሊል፣ በደም እያነገሠች፣ በጦርና በችንካር በደም እያስዋበች፣ በደም እየተረከች… ፡፡

ይህ የገ/ክርስቶስ ዘመን አይሽሬ የሆነ የጥበብ ሥራው ለበርካታ ዓመታት በስደት ከቆየበት ከወደ አውሮፓ መጥቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጀርመን መንግሥት እርዳታ በስሙ በተቋቋመው የስነ ጥበብ መዘክር ውስጥ ይገኛል፡፡ ገና ወደዚህ ቤተ መዘክሩ አዳራሽ ውስጥ ስትገቡ ዓይናችሁ ፊት ለፊት በሚታየው በዚህ ትንግርተኛ የገብሬ ጥበብ ሥራ ‹‹ጎልጎታ›› ላይ ዓይናችሁ ተተከሎ ይቀራል፡፡ በዛ ፅልመት በዋጠው በሚመስለው ሸራ ላይ በተረጨው ደም ውስጥ የሰው ልጆች ሁሉ የመውደቅና የመነሳት ታሪክ፣ ጅማሬና ፍፃሜው በደም ቋንቋ፣ በደም ቀለም፣ በደም ብሩሽ በጉልህ ደምቆ ይታያል፡፡

ያን መሳጭ፣ ያን ምሥጢረኛ፣ ያን ትንግርተኛ፣ ያን ነፍስን፣ አጥንትንና ጅማትን ዘልቆ በሚመትር ልዩ ኃይልንና ጥበብን በተቸረው ‹‹በጎልጎታ›› ድንቅ የጥበብ ሥራ ላይ መላ አካላታችን በአጠቃላይ ለቅጽበት ዓይን ሆኖ ፈዞ፣ ደንግዞና ተውጦ ይቀራል፡፡ እናም ከቤተልሔም ግርግም እስከ ጎልጎታ-ቀራኒዮ የፍቅር ኃይል፣ የፍቅር ቤዛነት፣ የፍቅር ጥበብ፣ የፍቅር ትሕትና፣ የፍቅር ትዕግሥት፣ የፍቅር ጽናት፣ የፍቅር ኤልሻዳይነት፣ ፍቅር ሕያውነት… ቃላት ሊገልጹት በማይቻላቸው በደም ቋንቋ፣ በደም ቀለም ፍቅርን ያሳያችኋል፡፡ ፍ-ቅ-ር በለሆሳስ፣ መንፈሳዊ በሆነ ሰማያዊ ቋንቋ ያናግረችኋል፣ ያወራችኋል፡፡

በዚህ በእጅጉ አስገራሚ፣ አስደናቂና አስደማሚ በሆነው የጥበብ ሥራው ገ/ክርስቶስ ፍ-ቅ-ር-ን በጥበብ ቋንቋ፣ በረቂቅ ክህሎት፣ ልዩ በሆነ ኃይል ትላንትና፣ ዛሬ፣ ነገም እስከ ዘላለምም ሲያውጅ ታዩታላችኹ፣ ትሰሙታላችኹ፣ ሊያውም በለሆሳስ በሆነ የነፍስ ጩኸት፣ የነፍስ ድምፅ፣ የነፍስ ቋንቋ!!

በገ/ክርስቶስ ‹‹ጎልጎታ›› ሥራ ላይ ይህን እውነት፣ ይህን በደም የተከፈለ፣ በደም የጸና የእግዚአብሔር ፍቅር ምሕረትን፣ ይቅርታን፣ በጎነትን፣ ቸርነትን፣ ርኅራኄን፣ ፍትሕን፣ እውነትን፣ ፍርድን፣ ጽድቅንና በረከትን የተሞላ እንደሆነ በጎልጎታ ተራራ በቀራኒዮ ላይ ተገልጦ ለሁሉ ታይቷል፡፡

 ይህ ፍቅር አሳልፎ ሊሰጠው በ30 ብር የተዋዋለውን ይሁዳን ‹‹ሰላም ለአንተ ይሁን ወዳጄ ሆይ!›› ብሎ በፍቅርና በርኅራኄ መንፈስ ተቀብሎ የሳመ ነው፣
 ይህ ፍቅር የከሐዲውን የደቀ መዝሙሩን እግር በፍቅርና በትሕትና ዝቅ ብሎ ያጠበ፣ ከከበረ ማዕዱም ያለየው ልዩ ፍ-ቅ-ር ነው፣
 ይህ ፍቅር ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ የካደውን የጴጥሮስን በዕንባ ጅረት፣ በንስሐ፣ በጸጸት ወደራሱ፣ ወደ ፍቅሩ መንግሥት የመለሰ ነው፣
 ይህ ፍቅር ለጠላቶቹ፣ ለሚሳለቁበትና ለሚወጉት ሁሉ ‹‹አባት ሆይ የሚሰሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው!›› ብሎ ምሕረትንና ይቅርታን የማለደ ነው፣
 ይህ ፍቅር ከእናታችንና ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ፣ በዘላለማዊ ፍቅሩና ቸርነቱ ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን በእኛ በኃጢአተኞቹ ፈጽሞ ያላፈረብንና ያልተጸየፈን ነው፣
 ይህ ፍቅር ሰማይ፣ ሰማይ ሰማያትን በልዩ ብርሃን ያስዋበ የብርሃን ጎርፍ፣ የብርሃን ጎህ ምንጭ፣ ዘላለማዊና የማይጠፋ ፋና ነው፣
 ይህ ፍቅር በአፉ እስትንፋስ ምድርንና ሞላዋን፣ ባሕርንና ውቅያኖሶችን በውስጣቸው የሚኖሩትን ፍጥረታት ሁሉ በሕይወት ብርሃን ያስጌጠ፣ ውብ፣ ድንቅ ተዋዳጅ፣ አባትና አምላክ ነው፣
 በዚህ ፍቅር መጽሐፍ እንደሚል ሕያዋን ነን፣ ሕያው ሆነንም እንቀሳቀሳለን፣ ይህ ፍቅር ሕይወትን፣ ጸጋንና ሰላምን ሰጥቶናል፣

ይህ ፍቅር ሰላምን፣ ጽድቅን፣ ፍትህን፣ ፍርድንና ፍጹም ደስታን ለምድሪቱ ያጎናጸፈና ዘላለማዊ ሕይወትንና ነፃነትን ያቀዳጀን ነው፡፡ ለዚህም ነው በፋሲካው፣ በትንሣኤው ክብረ በዓል እኩለ ሌሊት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት አባቶችና ሊቃውንቱ በቤተ መቅደሱ በማሕሌታቸውና በወረባቸው፡- ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፈሲካ፣ ታሕፂባ በደም ክርስቶስ፡፡›› እያሉ ይህን ታላቅ የፍቅር ድል የምስራች ዜማ ለምድሪቱና ለፍጥረት ሁሉ በታላቅ ድምጽ ደግመው ደጋግመው በታላቅ ድምፅ የሚያሰሙት፡፡

‹‹ምድር ንጹሕ፣ ክቡር በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ታጥባና ነጽታ በሐሴትና ፍጹም በሆነ ሰማያዊ ደስታ ፋሲካን ታከብረው›› ዘንድ ልዩ በሆነ ሰማያዊ ዜማ ፍቅርን የምስራች በሚል ውብ ሰማያዊ ዜማ ሰላምንና ሕይወትን የሚያውጁት፡፡ የዚህ አምላክ ፍቅሩና ቸርነቱ በእጅጉ ያስደነቀው የቤተ ክርስቲያን አባትና ሊቅ የሆነው ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው እንዲህ እንዳመሰጠረ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡-

‹‹ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው፣ ይህን ያህል ሰው ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር የአምላክን ልጅ ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም ድረስ አደረሰው፡፡›› በማለት የእግዚአብሔር ሰውን ፈጽሞ ስለመውደድ፣ የመሞቱ ምስጢር ከዘላለማዊውና ሕያው ከሆነ ፍቅሩ የተነሳ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለትና ትንሣኤ በዓልም ከዚሁ ጥልቅና መንፈሳዊ ከሆነ ፍቅርና ምሕረት ጋር ተያይዞ እንደሚከበር የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ አንድ ያነጋገርኳቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባት እንደነገሩኝ የዘንድሮ ፋሲካ በዓል ለየት ያለ ነው አሉኝ፡፡ እንዴት አልኳቸውም መልሼ፣ ሲመልሱልኝም፡-

የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል ልዩ የሚያደርገው በእግዚአብሔር የተሰጠንን ነጻነታችንና ምድራችንን በአውሮፓውያኑ ወራሪ ኃይሎች፣ በፋሽስት ኢጣሊያን ኃይል ተነጥቀን ሳለ በእግዚአብሔር ፈቃድና ኃይል፣ በአባቶቻችን ጸሎትና በዐርበኞቻችን ተጋድሎ ነጻነታችን የተመለሰበትን ቀን የምንዘክርበት ቀንም ጭምር ስለሆነ በዓሉ እጥፍ ድርብ ነው ሲሉ ነግረውኛል፡፡

በዕለተ ስቅለትም ሆነ በፋሲካ በዓላችን የምንዘክረው የታረደው የፋሲካው ቅዱስ በግ፣ የቀራኒዮው ባለውለታችን፣ የትንሣኤው ጌታ፣ ፍቅር የሆነው የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ፣ ነፍስና ሥጋችንን እንዲገዛው ስንፈቅድለት ከወዳጆቻችን ሁሉ አልፎ ለሚጠሉንና ለጠላቶቻችን ሁሉ የሚተርፈረፍ ፍቅር በውስጣችን ይበዛልናል፡፡ ሕግ ሁሉ በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ይጠቃለላሉ እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፡-

‹‹እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹምም አሳብህ፣ በፍጹም ኃይልህ ወደድ፡፡ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ወደድ፡፡›› ፍቅሩ ለእግዚእ በመባል የሚጠራው በጌታ መስቀል ስር በዛች አስጨናቂ የጣር ሰዓት የተገኘውና በዚህም ድንግል ማርያምን የፍቅር ስጦታ ልዩና ዘላለማዊ እናት አድርጎ ለመቀበል የታደለው ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ፡- ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፣ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል፡፡›› ይለናል፡፡ በእውነተኛ ፍቅር እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በመካከላችን ይሆናል፤ ከክርስቶስ ኢየሱስ የተሰጠችን ፊተኛይቱ ትዕዛዝም ይህች ናት፡- ‹‹እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ!!››

መልካም የስቅለትና የፋሲካ በዓል ለሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ!
ሰላም! ሻሎም!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>