Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የተከለከለ ~~ ፍቅር –ሲፈቀር –ይገርም … እኮ! ምን ልበል ታዲያ -. ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 11.12.2013

ፍቅር የትውልድ ዋዜማ ነው።

የመንፈስ ማዕቀብ ሲነሳ የነፃነት ፈል ችግኝ ይበቅላል በዚህ ልጀምረው ….

4568ፍቅር ምንድን ነው? ማድመጥ። ፍቅር ዜማ – ጹዑም! ፍቅር የመንፈስ ጥንግ ሽብሻባ። ፍቅር የስሜት ቃናዊ መዝሙር። ፍቅር የአኃቲነት ብርቅ ወረብ። ፍቅር የመስጠት ለጋስ ፏፏቴ። ፍቅር የታሪክ ማውጫ ፍትኃ – ነገሥት። ፍቅር የውስጥነት ፍውሰት – ድህነት! ፍቅር ጣዕም ንጥር – መረቅ! ፍቅር ብጡል* ክብረት። ፍቅር ምህረት። ፍቅር ይቅርታ። ፍቅር ረቂቅ። ፍቅር ቀጥታ። ፍቅር መሆን። ፍቅር ኃብታም ነው ዲታ። ፍቅር ምህረት ነው ዘንባባ! ፍቅር ወድ ነው ስጦታ። ፍቅር ሩህሩህ ነው ርግብ። ፍቅር ፈውስ የራህብ። ፍቅር ጻድቅ የመስቀል ወተት። ፍቅር የመስዋዕትነት ጤና አዳም። ፍቅርን ሲሰጡ ሊፈቀሩ የሚችሉ ፍጡራን ፍቅርን ሲከለከሉ ደግሞ ማመጻቸው አይቀሬ ነው!  ይፈነዳል።

ዋ!

እናት ከሁሉም በላይ ትውደዳለች። እናት የመጀመሪያዋ የህይወት ትምህርት ቤት ናት። እናት መቅድመ የቤተሰብ አሰተዳዳሪ፤ የተፈጥሮ ሙሁራ ሊቀ-ሊቃውንት የርህርህና መግቢያም።  እናት ደግሞ ሴት ናት። እኔ በዓለም ደረጃ የፍቅር ምልክት ወይንም ዓርማ ሊሆን የሚጋባው ልብ ሳይሆን እናት ነው መሆን ያለበት። ስለምን? እናት ልልጇ የምትሰጠው ፍቅር የማያብል ነውና። እውነተኛ የፍቅር ተፈጥሮ የሚገኘው ከስፖርት ማልያና ከእናት ብቻ ነው። እናት የሥነ ፍጥረት ሙሉዑ አጀንዳ ናት! እናት የመንፈስ ቋንቋ ናት!  ዬዓለም ተወዳጁ ሥም እማማ!

 

እስኪ ወፍ ካወጣን አብረን … ወደ ተለምኩት ብያለሁ፤ ቀልቤን ወደ ገዛው፤ ሩኼን ወደ ዳኘው። ጉዞ በጋራ መልካም ነው። ኑሮም በወል ጣዕሜ ነው። … ሴት እህት ስትሆን ትፈቀራለች። ሴት አክት ስትሆን ትጠጋላች። ሴት ሚስት ስትሆን እንደ ነፍስ ትታያለች። ሴት ጓደኛ ስትሆን ትታመናለች። ሴት እናት ስትሆን የጸጋ ስግደት ይሰገድላታል። ሴት ይሁን ይሁን … አሜን አሜን … ስትል ….. ሰጥ ለበጥ ብላ ስትገዛና ስትረገጥ …. ስትመች ትመረቃለች ….

 

እኔ እንደማስበው በእምነቴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አምስቱ አዕማደ ሚስጢራት ላይ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልዑቅ ነገረ ሳይመር መቅረቱ በጣም ይጎረብጠኛል። እንደሚገባኝ ከሆነ ግን የተዋህዶ ልጆች ለቅድስት እናታችን ባለን ፍጹም ልዩ ፍቅርና ስስት ከጸጋ ስግደት ይልቅ የአምልኮ ስግደት ይገባታል ብለን እንዳንሟገት ብልሆቹ አቨው አስበውበት፤ ምንአልባትም መንፈስ ቅዱስም አቀብሏቸው ወይንም ሚስጢር ገልጦላቸው ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም ከመንፈሳዊ ዓለም ወጥተን ወደ ገኃዱ ዓለም ስንመጣ … በፖለቲካ አስተሳሰብ ሴት ላቅ ስትል ግን „ጉልበታምንት“ ይለጠፍላታል። በጠራ ቋንቋ „ጉልበታም“ ትባላለች። ገና ሳትታወቅ እፍታ መስመር ላይ እኮ ነው …. ልደቷን ሳታከብር የምትገፋው – ገምድልንት* የተከለከለ ፍቅር ይሏችኋል ይህ ነው። ቁስለት!

 

ሴት ረድ ስትሆን ትወደዳላች። ሴት ሎሌ ስትሆን ትደነቃለች። ሴት የቤት ውስጥ ሰራተኛ ስትሆን ስንዱ ትባላለች። ሴት ጠቅልል ጠቅለል አድርጋ ስታጎርስ የራህብ ደራሽ ትባላለች። ሴት ጓዳ ጉድ … ጉድ ስትል ዓይን አብሮ ይዞራል። መንፈስም አብሮ ይንከራተታል። ልብም ዳንኪራውን ያስነካዋል ስሜትም አብሮ ይከትማል። ፍቅሬ ወ/ሮዬ ትባላለች። ዓለም የፈጠረው ቄንጠኛ የዘነጠ ሥያሜ ሁሉ ይሰጣታል። ሴት እንግዳ ስታስተናግድ ትመሰገናለች። ሴት ልጅ ስትሰጥ በዓይኔ ላይ ፍሰሺ ትባላላች። ሴት ስልጣን ልትጋራ ብቅ ስትል ግን „ኃይለኛ“ ተብላ ትኮረኮማለች ወይንም ትባረራለች። ሌላ ድልዝ ይፈልግላታል። ሌላ የሰብዕናዋ ድክምት ቁፋሮ ይጀመራል።  የተከለከለ ፍቅር … ጎባጣ

 

ሴት ገንዘብ ያዥ ስትሆን ትመረጣለች። ሴት ገንዘብ ስትሰበስብ ታማኝነቷ ይሰበክላታል። ሴት እልፍኝ ስታሰናዳ ትሞካሻለች። ሴት ስነጥፍ ወይንም ስነጠፍ እንደ ብርቅ ትታያለች። ሴት ቅራኔ ውስጥ ገብታ ስተቀረቀር ይጨበጨብላታል። ሴት መድረክ ላይ ወጥታ አቅም ባላው ብቃት በፍፁም ታማኝነትና ግልጽነት እኩል ስትመጥን አቅሟን ለአደባባይ ስታበቃ ግን በግሳፄ ትባረራለች ….. ድገም ሳትል ከቢጫው ቀዩ ካርድ ቀድሞ ያለ ማስጠንቀቂያ ከጨዋታ ውጪ ትሆናለች። ነዳላ ገጠመኝ። የአንተ ያለህ ….

 

ሴት ስትለብስ ትፈቀራለች። ሴት ስተሸቀረቀር እንጉርጉሮው ላቅ – መጠቅ ይላላታል። ሴት የተፈጥሮን ፍቅር ስትመግብ ንቢት ተብላ ትሞገሳለች – ትመገባለች – ትጎረሳለችም። ሴት ሽክ ብላ ከጎን ስትጓዝና ግብዣ ላይ እኩል ስትቀመጥ አጃችን* ይሞላል ልጎዝጎዝልሽ ነው። ሴት ገብያ ወጥታ ቀጨር መጨሬውን ስትሸማምት አበጀሽ ትባላለች። ሴት ኮስሜቲክስ ስትገዛዛ ውዳሴ ይነጠፍላታል።  ሴት ወንበርን ልትጋራ ጥንካሬዋን ስታስመከር ግን ትገፈተራለች …. ቆመጥ ይዘጋጅላታል ….. የተከለከለ ፍቅርነቀዝ!

 

ሴት ቤት ስትውል፤ እንደ እመቤት ትታያለች፤ ጨዋ የተረጋጋ መንፈስ የረበባት እዬተባለ ይሰበክላታል። – ደስታ ነዋ ስታፎከፉክ። ሴት አንገቷን ደፍታ መከራን ስትቀበል ቅኔ ይዘረፍላታል። ሴት የልጆች አሳዳጊ ብቻ ስትሆን ትበረታታለች – ትሸለማለች። ሴት በማይታዩ ሩትን /ጥቃቅን/ ተግባራት ስትሰማራ ማን እንደ አንቺ ትባላለች። ሴት አንደበቷ ታስሮ የሳሎን ጌጥ ብቻ ስትሆን ማለፊያ ይባልላታል። ሴት ግን ኃላፊነትን እኩል ለመጋራት ጠበቅ ጠንከር ብላ ብቅ ስትል ጦር ይሰበቅባታል።  ያደገ ወይንም ያልተነካ ድንግል ወጥ ሃሳብ ወይንም ግኝት ወይንም ላቅ ያለነ የቀደመ ግንዛቤ  ስታፈልቅማ እሷንማ በሽታሽቶሽ* መውቃት።የተከለከለ ፍቅር …. ምግለት!

 

ሴት ስትጋግር … ስትሰራ …. ስታጥብ … ልብስ ስትተኩስ፤ ስታረግዝ …. ስታጠባ …. ከሚፈለገው ቦታ ላይ ተገኝታለችና ይዘፈንላታል። ከዚህ አለፍ ብላ የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ስታነሳ ግን ትወረወራለች …. እውነት ለመናገር በዘመናችን ያሉ ሴቶች እንኳን ጥቃ ሊቆምላቸው፤ እንክብካቤ ሊያገኙ ቀርቶ ገፍተው የሚወጡት በጣም ጥቂቶች ለምነው ለመታገል እንኳን ፈቃድ አያገኙም በወንድ ትምክህተኞች …. ዛሬም ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ካላው ኮረብታ ላይ እንዳሉ አሉ እነ ተባዕት …. ከእነ- የወንድ የበላይነት ተጫኝ ስሜታቸው ጋር ተጋብተው። ስለ ሴቶች ብዕራቸው በተቆርቋሪነት የሚቃኙት ከአንድ ለእናቱ  ሙሁር ከፕ/ አለማዬሁ ገ/ማርያም በስተቀር …. ፕሮፌሰሩ ከክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ጋር በመገናኘታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐሴትም አድምጠናል። ረስተውንም አያውቁም – ቅርባችን። ስለ ሴቶችን በሚያጠቃው የካንሰር በሽታ በተቆርቆሪነት የጻፉት ልብን የሚነካ ነበር። እውነት ልዩ አብነት ናቸው – ለእኔ። ድህነቴ እንጅ ለእሳቸው የምስጋና ቀን ባዘጋጅ ዕድለኛ በሆንኩ ነበር።

 

በፍጹም ሁኔታ የነፃነት ትግሉ ሆነ፤ ነገ የሚታሰበው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረቱና እርገቱ ከሴቶች ውጪ ሊታሰብም ሊሳካም እንደማይችል በጣም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የነፃነት ትግሉ የሴቶችን ሙሉዑ ተዋፆ በአጽህኖት፤ በተደሞና በአርምሞ ይጠይቃል። መደመጥ አለበት። አጥበቆ! አኔም የጥቃቱ ማዕደኛ በመሆኔ …. በልበ ሙለነት እጥፋለሁ … እንዲህና እንዲያ … ትርፉ ትራፊና ፍርፋሪ ካልሆነ ….

 

ይህቺ ለመላሾ እነ ተባዕት „ ቦታ አካፍለናል“ የሚሏት …. ልጥፍ ሽፋን ልግጫ ለማንም አይበጅም - ነገንም አያበጅ። የዶደመ …. መንገድ ነው። የነፃነት ትግሉ ሙሉዑነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሴቶችን የመጠነ፤ ያስተዋለ፤ ያደመጠ፤ ያከበረ ተሳትፎ በቅንነት ተግባር ላይ ዛሬውኑ ሲያውል ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ካላት ያልተነካ ቅምጥ ዕምቅ ኃይል በላይ የሴቶች ሃብት እስከ ዛሬ ድረስ ሥራ ላይ አልዋለም። … ነገም ከፍቶት ይታዬኛል።

 

እርግጥ ማሳሳቻ አስፓልት አለ። „የሴቶች መምሪያ ከፍተናል … ጉዳያቸውን የሚከታተል መዋቅር ዘርግተናል“ … ይህ የሴቶችን ብቃት የሚያቀጭጭ አፋኝ የማስመሰያ ጅራፍ ነው። በአንድ ወቅት ፕ/ መራራ ጉዴናን አበክሬ እጠይቃቸው ስለ ነበር ንገሩልኝ የሴቶች መምሪያ በድርጅቴ መጀመሬን አሉ። የዛሬ 14 ዓመት መሆኑ ነው። አሁንም እሳቸው ከያዟት ቁልፍ ቦታ ግን ፈቀቅ አላሉም። ጨምድደው ጉብ ብለው ይለፉንም ዘግተው አሉ እንደ አገዱ። ይህ ትልቅ ግድፈት ነው። የእኔ ሙግት የነበረው በ2ኛው  የኢተፖድህ ጉባዔ ከዬትኛውም አባል ድርጅት አንድም የአንስት ውክል አካል ልትገኝ ደረጃዋ ባለመፍቀዱ ነበር – አበክሬ እናገር የነበረው።

 

ዘግይቶ የዛሬ ዓራት ዓመት ገደማ መደረክ ሲቋቋም አዬነው በመላጣ – ጎብጦ የሴቶችን እኩልነት በባዶ ቃላት ተለብጦ። ያው ቢገላበጡም ጃኬቱም ቢቀያዬር የተባዕት ክምር። የድርጀታቸውም አቅም … የወንዶች ብቻ – ቁልቁል። ይህ ለናሙና እንጂ በሽታው ሁሉንም ያካልላል። ከእከሌ ድርጀት እከሌ ይሻላል ብዬ ውዳሴ ባቀርብ የሴትነቴ ክብር ይዘቅጣል። ሴትነቴ ካለይግባኝ ዘቅዝቆ ይሰቅለኛል። ተፈጥሮም ፊቷን ታዞርብኛለች። አምላኬም ከልቡ ያዝንብኛል። ሃቁን ለከንቱ ውዳሴ ብሸብብ።*

 

በማናቸውም ዘርፈ እኔ ነኝ ባለ ወሳኝ ኃላፊነት ሁሉ ሴቶች ጉልበታም አቅም አላቸው። ለዛ የሚመጥን ቦታቸውን አትጋፉ ነው መሰረታዊ ትግሉ። አጽህኖታዊ መጠዬቁም። እድሉን ያገኙ ሴቶች ተዝርክርኮ ሳይሆን አምሮና ሰምሮ፤ በጥራትና በጥንቃቄ እንዲሁም በስልትና በብልኃት ሁለመናው ያምርበታል። ሴቶች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚተጉት …. በእናትነታቸው ፍጹም የማይታይ ሰማያዊ ጸጋ አስውበው ነው። ምቹ ሁኔታ  ካገኙ፤ በቂ እንክብካቤና ጥበቃ ለመክሊታቸው ከተደረገ …. ማን ችሏቸው። ያኮራሉ! ተወዳዳሪም የላቸውም። ሚስጢር ይመሰጠራል። ትርጉምም ይነበባል። ተፈጥሮም ይዘክራል። የሰብዕዊ መብት አከባበርም ጽኑ ባለሟል ሲገኝ በደስታ ይፍለቀለቃል። እኔ እላለሁ ሴቶች የተፈጥሮ ድንጋጌ ናቸውና።

 

አውሮፓ ያላችሁ ሁሉ እንደምትከታተሉት አውሮፓ በኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ተሰቅዞ ሲባትልና ሲብተለተል የመፍትሄው ጭንቅላት የተገኘው አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ ማለቴ ነው ከጀርመን ነበር። የጀርመኗ መሪ ጠ/ሚ ወ/ሮ አንጅላ ሜርክል ቀጥ አድርገው በማያዝ ማገር ሆነው አውሮፓን ከውርዴት ዘመኑንም ከጥፋት ታድገውታል። ጠ/ሚር ሜርክል ፓን አውሮፓኒስት ናቸው። በተግባር የከበሩ የመጀመሪያዋ የጀርመን ተወዳጅ ሴት መሪ ናቸው። እርግጥ ከዚህ ጋር ያሉ ከፈረንሳይ ጋር የተሳሰረ ትብትብ ቢሮክራሲን  ዘልዬ …

 

ለናሙና …. የእንግሊዟ ታችር፤ ንግስት ኤልሳቢጥም፤ ተፍርተው በአጭሩ ተቀጩ እንጂ ልዕልት ዲያናም አሳይተዋል አስመስክረዋል … ያን ጉልበታም ተዝቆ የማያልቅ ብቃት …. ከብልህነት ጋር። ይህ በኒውዘላንድ፤ በአውስትራልያ፤ በፊላንድና በብራዚልም ተመሳጥሯል። ሲዊዘርላንድ በሰባት ሰዎች ትመራለች። አራቱ ሴቶች ናቸው። ያውም ቁልፍ ቁልፍ ቦታ የያዙ … በጀርመን ካለፈው ወራት ሀገራዊ ምርጫ በኋላ ያለውን ሽግሽግ አልተከታተልኩትም እንጂ ቀደም ባለው ጊዜ በርካታ ሴት ሚ/ራት ነበሩ …. የእውነት አባዛኞቹ ሴቶች በማለት ብቻ የሰከሩ አይደሉም። እናታዊ ሥነ -ምግባራቸው አይፈቅድላቸውምና! ይልቁንም በመሆን የበለጸጉ እንጂ …..

 

በዓለም በፈጠራ፤ በሳይንስና ምርምር፤ በሰብዕዊ ተግባር፤ እንዲሁም በሥነ – ጥበብ የበርካታ ምርጥ ዕንቁ ሴቶችንመዋዕለ ተጋድሎ፤ የያዘው የኖቤል ተሸላሚ ሴቶችን አስኪ ገድሉን ጎብኘት አድርጉት ….  እኔ በመንፈሴ እማማ ዊኒን፤ ሜርክልን እያጨሁ ነው። ብቁ ናቸዋ። በዬዓመቱ ከሲኤንኤን ጀግኖች ሴቶችም እኩላዊ ብቃታቸውን ለአደባባይ አብቅተዋል። እርግጥ እዬታፈኑ፤ ሳይታዩ እንዲጠፉ እዬታደመባቸው፤ እንዲከስሙ የተዘመተባቸው፤ እንዲሁም አስታዋሽና ጠበቃ ያጡት ሚሊዮኖች የነጻነት ሴት አርበኛ፤ የሥነ ተፈጥሮ ሁነኛ፤ የሥነ ጥበብ እማ ወራ … የፈጣራ ቀንዲል ዕልፍ ናቸው። የዓለም ብቁ ዜጎች ሴቶች መሆናቸው ምንም ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። በአግባቡ ተከታታይና ባለቤት ቢኖረውማ …. በቁጥር ይበልጡም ነበር – በሁሉም ዘርፍ።

 

ለሁላችንም የሚጠቅም ስለሆነ ደግሜ በመፃፌ እንደማላሰላችሁ በማሰብ በዘመነ ክሊንተን ያን የዓለም ስሜትን የሳበ የፕ/ ቢል ክሊንተን ተብዕታዊ ቅብጠት ብልኋ ባለቤታቸው እመቤት ሄነሪ ክሊንተን የሆነውን እንዳልሆነ አድርገው ትቢያ አልበሰውታል። በወቅቱ አንድ የፕሬስ ሰው እንዲህ ሲል ጠይቋቸው ነበር … „የሚባለውን አልሰማሽንም? … አላነበብሽውንም?“ ሲል ብልኋ እመቤት ግን መንፈሱ እንዲህ ነበር „ እናቴ ከልጅነቴ ጀምሮ ያስተማረችኝ ሰው የሚለኝን ከሰማሁ የምሰራው የሰወችን እንጂ የእኔን እንዳልሆን ነግራኛለች፤ አስተምራኛለች። መርሄ ይህ ነው። እኔ የኔን ሥራ እሰራለሁ ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን ይሰሩ“ ነበር ያሉት። ሰማዬ ሰማዬት የዘለቅ ዕጹብ መልስ ነበር። በዚህም ትዳራቸውን ከነዙፋኑ ሀገራቸውን ከነአልማዙ እስከብረዋል። አንስትን የወከለ ማለፊያ ብቃት!

 

ከዚህም በኋላ በዘመነ ፕ/ባራክ ኦባማ የውጭ ጉዳይ ሚር/ ሆነው እጅግ ውስብሰብና ፈታኝ በሆኑ መሰናክሎች ሁሉ በማለፍ የሴቶችን የመወስን አቅም በተግባር አሳብበውታል አሁንም የፕ/ ባራክ ኦባማ ባለቤት ቀዳማይ እመቤት ሚሻዬል ኦባማ ሁለገብ ንብ በመሆን ባለቤታቸውን ለሁለተኛ ጊዜ የሥልጣን ባለቤትነት አብቅተዋል … ለዚህም ደረጃ ያበቋቸው ቀዳማይ እመቤት ወ/ሮ ሚሻዬል ናቸው። ነገም ለፕሪዚዳንትንት እራሳቸውን ችለው ሊወዳደሩ ይችላሉ። ተወዳጅም ናቸው – ወ/ሮ ሚሻዬል። ወንድሞቼ ሆይ! የነፃነት ትግሉ መሪ አባ ወራዎች ሆይ! ዓይን ካላችሁ ከዚህ ሀቅ ጋር የመንፈሳችሁ ብሌን ይታረቅ ዘንድ ብዕሬ በጽሞና ያሳስባችኋል … በአክብሮት – በትሁት መንፈስ።

 

በአፍሪካ ታሪክ ጉልበታሙ የፕ/ ማንዴላ ተገዳሎ የምዕተ ዓመቱ ታላቅ መዘክር ነው። ሚሊዮን ሰማዕት ሴቶች ታድመውበታል። በፆታዊ ችግር አፓርታይድ ያሴረውን መረብ ዝለሉትና ክብርት የነፃነት ብቁ አርበኛ እማማ ዊኒ ማንዴላ ባላቤቷ እስር ቤት በነበሩበት ጊዜ የነፃነት ትግሉን በግንባር በመምራት፤ ልጆቿን በማሳደግ፤ ለትዳር አጋራ አጥር ቅጥር በመሆን የጽናት ወተት ነበረች። ይህን ከባለቤቷ ጋር ትጻጻፍ ከነበረው የነፃነት ትግሉ ዋነኛ ትምህርት ቤት ዝክረ ደብዳቤዎች ማገናዘብ ይቻላል። ህያው ምስክር ነውና። ሁሉም ፍጡር እናቱን የሚወድበት ሚስጢር በሀገር ጉዳይ ላይ ቢውለው ምንያህል ፈውስ በነበረ – ለመለውዓለም። የ ዓለም ዝበርቅ አስፈሪ ውጣ ውረድ ፍቺ ያለው ከሴቶች ነበር … ባሊህ አጣ እንጂ …

 

በእኛዋ እናት ሀገርም … በቀደመው በዘመን ንግስት ዘውዲቱ የመቻልን ተፈጥሮ፤  ከእቴጌ ምንትዋብ የተግባር ሚስትነትና አርበኝነትን፤  ከከዕቴጌ ጣይቱ ብልህነት – ፖለቲካ መሪነትና አማካሪነት – ጠበብትነትና ጀግንነትን ጠብተን አድገናል። በዘመናችንም … ሳራ ግዛውና ሺብሬ በሰማዕትንተ፤  አያልነሽ – አለምዘውድ፤  ብርቱካን ሜዲቄሳ፤ ሰርካለም ፋሲል፤  ርዕዮት ዓለሙ፤ በላይነሽን ስንቶቹን የነፃነት አርበኞች እናት ሀገራችን አፍርታለች። መሬታች መሃን አይደለም። ተሳትፎውን በጉልበት ያነጠፈው* ያንጠፈጠፈውም የወንድ በላይነት ብቻ  ነው። አሁንም  በአንድነት ወ/ት ወይንሸት የምትሰጠውን ቃለ ምልልስ አኑትና አጣጥሙት …. ያው ታች ስለሆነች ቅጥቀጣው ያልፋታል ብዬም አስባለሁ … ቀና ካላች ግን ቅንጧን ነው … በለመደ እጅ … እህህህህህ!

 

እኔ … በአጽህኖት እናገራለሁ። የፖለቲካ መሪዎቻችን የውስጥ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። በፍጥነት። በንግግራቸው ውስጥ እንኳን ብጣቂ እርስት አልተሰጠነም። እንኳንስ በፍላጎታቸው ልብ። በራዕያቸው አንጎልም የለንም። አብሰንት ነን።  ምንአልባት ትዝ የምንላቸው የራባቸው ጊዜ ይሆናል። ለነገሩ ነጭ ሀገር ፋስት ፉድም አለ … ዘመኑ ተለውጦ እራስም ይጋገራል … ሀገር ቤትም ተለምዷል አሉ … የጓዳ ነገር። እንዲሁም በዬአጋጣሚው የሚሾሟቸው አብዛኞቹ የበታች ገዢዎቻችንም ለውጡ ገፍቶ እንዲያነጥራቸው እንሻለን። አቅም በመበተንም አንቱ ናቸውና! ይደግም። የበታቾቻቸው አቅም በመበተን አንቱ ናቸውና!

 

የበላዮች የበታቾቸውን የሚከታተሉበት መስመር ቢኖር መልካም ነው። የጉሮሮ አጥንቶች እነሱ ናቸው። የፓለቲካ አመራር ልም ነው። ጣጣውን የጨረሰ ለስምሪት የበቃ ንጥር ቅቤም፤ ለስምሪትም ስንዱ። እኔ የማዬው ዘመንተኛው ፖለቲካ ግን ሽርክትና ግርድፍ ሆኖ ነው። አብሶ አጋርን በመገፍተር እረገድ ከንፍሮ የወጣ አንድም መሪ አልገጠመኝም። ቆሞ ስለ አርበኛ አንስት የሚመሰክር ዓይናችን አላዬም …. እንደናፈቃቸው ይቅር ዓይነት ነው ነገሩ …

 

እርግጥ ነው ሥር ላይ ያለው ተግባርን የሚያደምጡት፤ ከበታቾቻቸው ለዛውም ስታስቲክሱን በሩቁ ነው። ያው ወያኔ ባላው የተዛነፈ ዳታ ይወነጀላል። የኛም እኮ ያው ነው። ከታች ወደ ላይ የሚተላለፈው ቁጥር ተብዬ። የበቃ ፍጽምና ያለው ተሳትፎ …  ለማዬት ወረድ ይበሉ። ሰፊ መድረክ ይክፈቱ። የትችት አንባ ይወጁ። እንዲያድጉ እንዲመነደጉ ከፈለጉ። … በራስ አነሳሽነት የሚደረገው የፈጠራ ተሳትፎም እምብዛም ነው። ሁልጊዜ ከላይ የተንጠለጠለ መና ይጠበቃል። የማኒፌስቶውን ጭብጥ ይዞ ጭብጥን በጭብጥ አፋጭቶና አታግሎ የነጠረውን የፓርቲያቸውን አቋም አሸናፊ ለማድረግ ፈጠራ ከአቅም ጋር ይጠይቃል። ማረር!

 

ያው ቁንጮቹ የሚሉትን በተገኘው አጋጣሚ የጎረሱትን እዬፈቱ ሲደግሙና ሲሰልሱ ዓመት ይዞ እስከ ዓመት ከዛው ለዛው ሲዳክሩ ነው የሚታዩት። ተመስገን ነው ዛሬ እድሜ ለኢሳት በተለያዬ መድረኮች መሰናዶ ከሊቃኖች አዳዲስ ነገር ስንቅ ስለሚገኝ ተሽሎ ሊሆን ይችላል። ግን የራስ ጌታ ለመሆን ማንበብ መልካም ነገር ነው። የዬትም ሀገር ነፃነት ትግሎች ለድል እርከን ያደረሱት አጋራቸውን በበሰለ ህሊና ባሊህ ብለው ነው።  … እርግጥ ላይኞቹ ሴቶች ማለት ሲጀመሩ የታችኞች ቅጂውን እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋቡታልና እባካችሁ ላይኖቹ ጀመሩት …. ግን በተለበጠ መልኩ ሳይሆን ቁምነገር ባለው ዕውነት – ከልብም። ዝም ብሎ ከሆነ ልጥፍ ይሆንና የተላመጠ አገዳ ይሆናል ምኖታችን።

እኛ እንላላን። እኔና ትዳሬ ብዕሬ …. ተከታታይ የሆነ አቅም ያለው የመንፈስ ጥሪት ለመገንባት ይሞክሩ ፖለቲከኞቻችን ….፤ ሙሁሮቻችን። የሴቶችንም ነገረ ሚስጢር አክለው …. የሃይማኖት አባቶቻችን ሲያሰተምሩን „ነገረ መለኮትን“ ነጥለው ሳይሆን „ከነገረ ማርያም“ ተነስተውአስቀድመው እነሱ በቅድሰት ድንግል ፍቅር ቅጥል እያሉ ነው። የእናታቸው ፍቅር ግብግብ እያደረጋቸው ነው። እኛም እንደ እነሱ ሆነን እናታችን የማናሰነካው – ተከተል አባትህን ሆኖ ነው። የድንግል ነገር የሁለመናችን ገዢ የሆነውም በዚህው ቅኝት ተቀረጽን ስለሆን። ማለት ለተዋህዶ አማንያን። አሳምረው ጠረቡን። መንፈሳችን በቅዱስ መንፈስ ገሩት ነው። ያኑርልን ሊቀ – ሊቃውንቱን። የቅድስትን የመንፈስ ድንግልና ፍቅር በማያልቅ ወተት አጥብተው አሳድገውናልና። በሥጋዊ ፍቅርም ቢሆን ፍቅር ድብን አድርጎት እያለቀሰ ከልቡ የሚያዜም ከልብ ጠብ ይላል … በስተቀር ድው የለ ትም  ….

 

ይህ ትግል የሚባለው ጀግና … አርበኛና ሰማዕት …. ድሆኖው* ጉድሎበታል፤ ጎታው* ተራቁቶበታል ታላቅ ነገር ቅናዊ ዕይታ፤ ሥልጣንን የማጋራት ግልጽነት፤ ኃላፊነትን በቅመም የመመጠን ሥልጡን ዕይታ። ትርጉም ያለው ተግባራዊ እርምጃ ከኢትዮጵያዊነት መሪዎች በአጽህኖት ይጠበቃል።  እኩላዊ መስመር ሳይፈጠር አሯል። አይታይም። የመከነ ጉድ ነው …. በዬትኛውም ሁኔታ በቦታው የሌለ ነገር ቢኖር ሴቶችን  በአክብሮት እኩል ለማሳተፍ ያለው ፈቃደኝነት ልሙጥ መሆኑ ነው ድርቅ የተጫወተበት፤ ዝናብ ሲሄድበት የከረመ አለት የመሰለ ለዛ የለሽ ጉድ። በጣም በረቂቅ ሁኔታ በሴቶች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ዘመንና ጊዜ ይፈታዋል የሚል ግምት የለኝም። የተሳሳረ ድንቡልቡል ነገር ነው። በሩ ተቀርቀሯል። ጭላንጭል መተንፈሿ ቧንቧው የታነቀ ነው ….  ለዛውም እኮ ቆርጠው የሚወጡት ጥቂት ሆነው እነሱን እንኳን በአግባቡ ለመያዝ ምንም …. ታውቃላችሁ?! ምንም ነው 00000 በቅናሴ ያለ … ተቋም ቢኖር …. የሴቶች የእኩልነት የተሳትፎ መድረክ ድርሻ ምክነት።

 

ህይወት ካለሴቶች ኮረኮንች — አመዳም — ቡላ —- የፋደሰ —- ቀዝቃዛ — የነፈዘ —– ነው የተፈቀፈቀ። …. የትግሉም ዕጣ ፈንታው ይህ እንዲሆን ተገምድሎበታል። ይፍታህ በሉት! ነይልኝ — ነይልኝ — „የህይወቴ ህይወት“ ለዚህ ብቻ  … ። ትውልድን በአዲስ የተሳትፎ ፖለቲካዊ ባህል ለመገንባት ዳገት። ታሪካዊ ድርሻን ለመወጣት ክትከታ። የምንፈለገው ለአጃቢነት ወይንም ጥላ ለመያዝ ወይንም ለዘበኝነት ብቻ። ደንበር ሰበር ለሆነ ለሚመጥን የሥልጣን ክፍፍል ወይንም ተደማጭነት ማነቆ – እገዳ – ክልከላ … ሰባራ ጉድ፤ …. ጨምዳዳ ….. ዕጣ። የተሸበሸበ … ራዕይ። ሽራፊ …. ህልም። ያመለ … ነገ። የሻገተ … ተስፋ። ያልተጠረገው መንገድ ረቂቅ ሚስጢር ይህን ይመስላል። መፍትሄው ለዛሬ አዲስ መኃንዲሶች፤ እራሳቸውን የዘለሉ ሙሴዎች ያስፈልጉታል … ይመስለኛል።

 

እናሳርገው። ….. የምቀኝነት በሽታ ያለባቸው ድውያን በዬአጋጣሚው ያፈኑት ነገር መተንፈሻ ከሌለው አጉል ቦታ ይፈስና ብዙ መስመሮችን ይበርዛል። „ልብ ያለው ሸብ“ ብለናል … ከብሂሉ ጋር እርገት ይሁን። እኔ ምን እንደሚናፍቀኝ ታውቃላችሁ ዓይነታ የወጣለት መሪ … ደፈር ብሎ ስለ ሴቶች …. ጥብቅና አጋፋሪ የሚሆን ሊጋባ። የነፃነት እልፍኝ አስከልካይ ሀቀኛ ዓራት ዓይናማ። ሴቶች ብዙ አላቸዋ። ያጡት ያላቸውን የሚያቀኑበት ገብያ ብቻ ነው ….. ግጥም ታውቃላችሁ … ቅኔዊ። እንደ ግጥም የልብን ድርስ የሚያደርጉ ምርጥ ፉጡራን ናቸው አብዛኞቹ ሴቶች። እርዳታቸው – ፈጣን፤ ምክራቸው የልብ አድርስ፤ ጽናታቸው ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ፤ ፍቅራቸው የትውልድ ዋዜማ፤ ሥልታቸው ሥልጡን፤ ብልህነታቸው ተጨባጭን የዋጠ። ጉዟቸው ደፋር።

 

ሳልሄድበት የማልፈልገው ጥምዝ መንገድ ደግሞ ሌላው አጋር ለአጋር መገፋፋቱ ነው። ይህ ደግሞ ለአንስት የእኩልነት አንባ የከፋው ዕጣ ነውና ለአጋራችን እኛው አጋር በመሆን ጥጓ እንሁን። ብቃቷን ለመመስከር አንደበታችን እንፍታው፤ ለሴት እህታችን ብቃት ዋቢ እንሁንላት። ለሴት እህታችን ተጋድሎ ቀድመን እንገኝላት – ከጎኗ።  ለዘንካታ ትዕግስት ሞንሟና ምስጋና እንሆ!

 

ሴቶች የነፃነት ትግሉ ዓርማ ናቸው!

ሴቶች ለነጻነት ቅኔ ናቸው!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

መፍቻ

 

  • አጃ የልብ መደረስ፤ ከጠበቁት በላይ መርካት።
  • ቅንጧን … ቅንድቧን …
  • ብጡል የተለዬ … የተመረጥ …
  • መገምደል … ፍትህን የጣሰ ፍርድ።
  • ያነጠፈው …. ያደረቀው … ምደረበዳ ያደረገው …. ድርቅ ያስመታው … ለዘር ያላበቃው ….
  • ሽታሽቶ  …. እያረፉ፤ በፈረቃ በድርብ …. ማድቀቅ …. ማጥቃት ….
  • መሸበብ … መሸፈን … መጋረድ … እንዳይታይ ማገድ …
  • ድሆኖ … ከጭቃ የሚሰራ መሰል ግጣም ያለው የእንጀራ መያዣ … ሌማት፤ ወይንም ጥራር እንደማለት
  • ጎታ … ከጭቃ የሚሳራ ትልቅ የ እህል መያዣ … እንደ በርሚል ….

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>