“የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት” በሚል ርዕስ አቶ ዘውዴ ረታ ያሳተሙትን መጽሐፍ በጥሞና አንብቤዋለሁ። መጽሐፉ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የተፈጸሙትን እውነተኛ ታሪክ በሙሉ የካተተ ነው ባልልም፤በውስጡ ያሉት በርካታ ዘገባዎች ከዚህ በፊት በሌሎች መጽሐፎች ውስጥ ተጽፈው ያልነበሩ ናቸው። በተለይም ክቡር ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን፤ ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳን፤ ክቡራን አቶ አክሊሉ እና አቶ መኮንን ሀብተወልድን በተመለከተ የተጻፈው፤እነዚህን የኢትዮጵያ ብርቅ ልጆች ስም ህያው የሚያደርግ ስለሆነ ለደራሲው ያለኝን አድናቆት በከፍተኛ አክብሮት እገልጻለሁ፡፡
ይሁን እንጂ “ይድረስ ለአንባቢዎቼ” በሚለው ርእስ ስር ደራሲው በአቀረቡት ዘገባ ውስጥ “ይህ ጎድሏል፤ ይህ ቀርቷል የሚባሉ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ እና እንደሚኖሩ አውቃለሁ” ብለው አስተያየት እንድንሰጥ በር ከፍተዋል። እኔ ደግሞ “ጎድሏል፤ ቀርቷል” ከሚለው በተጨማሪ አቶ ዘውዴ ረታ የተሳሳቱትን ለማረም ይጠቅማቸዋል ብዬ ያሰብኩትን እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።
በመጀመሪያ የማነሳው “የቫቲካን አቋም በኢትዮጵያ ጉዳይ” ብለው ስለአቀረቡት ዘገባ ነው። በዚህ ርእስ ስር፤ እሳቸው የጻፉትን እዚህ ላይ ለመድገም አልፈልግም። ዋናው ቁም ነገር፤ “የቫቲካን አቋም በኢትዮጵያ ጉዳይ” የሚል ርእስ ሰጥተው ከጻፉ ዘንዳ፤ የቫቲካንን አቋም ይገልጻሉ ብዬ ስጠብቅ፤እሳቸው ሸወድ አድርገው ወደ ፒዮስ 11ኛ አሉባልታ ገብተዋል። ለምን ይህን ለማድረግ አንደፈለጉ ስላልገባኝ፤የእኔን እይታ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
አንድ የበላይ የሆነ የሃይማኖት አባት ወይም የአገር መሪ፤ከበታቹ ያሉት ሰዎች ለሚፈጽሙት ተግባራት ሁሉ ተወዳሽም፤ተወቃሽም እደንደሚሀን እሳቸው ሳያውቁ ይቀራሉ የሚል እምነት የለኝም። ይህ ሐቅ ተቀባይነት ያለው የአስተዳደር ጽንፈ ሐሳብ በመሆኑ፤የቫቲካን ካርዲናሎች (ጳጳሶች) በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸሙት በደል ዋና ተጠያቂ፡ የቫቲካን የበላይ መሪ ፒዩስ 11ኛ ናቸው፡፡ ይህን ሐቅ አቶ ዘውዴ ረታ መካድ አልነበረባቸውም። በፒዩስ 11ኛ ስር ያሉት ካርዲናሎች የፈጸሟቸውን ተግባራት አቶ ዘውዴ እንዲያስታውሱት፤ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡
- አቶ ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት” በሚል ረእስ በጻፉት መጽሐፍ ገጽ 301 ላይ “የሚላኖው ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ኢደልፎንስ ሹስተር፤የፋሸስት መንግሥት ደጋፊነታቸውን በግልጽ አስረድተዋል” ብለዋል። በመቀጠልም “- – - – የጣሊያን መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር የባርነትን አገዛዝ ሰንሰለት በመጣስ፤የካቶሊክን ተልዕኮ የተቀበለ ነው – - ” ብለው ከጻፉ በኋላ፤ፒዩስ 11ኛን ለመደገፍ የተነሱበትን ዓላማ ለማሳካት ሲሉ “የሚላኖ ሊቀ ጳጳስ በተናገሩት፤ፒዩስ 11ኛ እጅግ ማዘናቸውን ገልጠዋል” በማለት ነገሩን ለማርገብ ሞክረዋል። በትልቅ ሥልጣን ላይ ያለው ካርዲናል ኢደልፎንስ ሹስተር፤የኢትዮጵያን ነፃነት የሚያሳጣ እና ክብሯን የሚነካ ድርጊት በመፈፀሙ፤ቢያንስ አሰተዳደራዊ እርምጃ አለመውሰዳቸው ፒዩስ 11ኛ የድርጊቱ ተባባሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ፤እሳቸውን ከበደሉ ነፃ የሚያደርግ አይደለም።
ከዚህ ዝቅ ብሎ የሚታየው ፎተግራፍ የሚያሳየው “የሚላኖው ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ኢደልፎንስ” ሕዝብ በተሰበሰበበት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በር ላይ ቆሞ፤በልበ ሙሉነት የፋሸስትን መንግሥት የሚደግፍ ንግግር ሲያደርግ ነው። በዚህ ፎተግራፍ ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ካርዲናል ሹስተር የሚናገረውን የሚያዳምጡ ቢሆኑም፡አንድ ግርምት የፈጠረበት ሰው አፉን ይዞ እናያለን።
ፒዩስ 11ኛ “ፍትሐዊ ባልሆነ ጦርነት አናምንም” ከማለት ውጭ የኢትዮጵያን መብት ለማስጠበቅ ምን የተናገሩት ወይም የፈፀሙት ተግባር አለ?
ካርዲናል ሹስተር የፋሽስት ደጋፊነቱን ሲናገር
- የጣሊያን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ በሚሳፈርበት ወቅት፤ መድፎቹንና ሌሎች አውዳሚ መሣሪያዎቹን የባረከው፣ የቫቲካን ካርዲናል ፎቶግራፍ ከዚህ በታች ያለው ነው።
- የኒው ዮርክ ታይምስ እ.አ.አ. የካቲት 13 ቀን 1937 ባወጣው ህትመት “ዛሬ ማለዳ ላይ ጳጳሱ ለጣሊያን ንጉሥ እና ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት፣ ለቪክቶር ኢማኑኤል፣ ብለው ቅዱስ ቡራኪያቸውን በመስጠት፣ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ስላላት ሉዓላዊነት እውቅናቸውን ገልጸዋል” ብሏል። የእንግሊዝኛውን ጽሁፍ ከዚህ በታች አቀርባለሁ።
(Earlier today the Pontiff had given his recognition of Italian sovereignty over Ethiopia by bestowing benediction upon Victor Emmanuel as King of Italy and Emperor of Ethiopia)
- የፋሽስት ኢጣሊያ ወታደሮች መረብን ተሻግረው፣ ወደ መሐል አገር ለመገስገስ ሲሰለፉ ቡራኬ ሲሰጥ በፊልም የተቀዳው በእጄ ይገኛል።
- “እምነተ ቢስና የቀኖና አፈንጋጭ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ማካሄዴ፤የካቶሊክን እምነት ለማስፋፋት በር ስለሚከፍት፤ የተቀደሰ ጦርነት ነው በማለት የቶራኖ ሊቀ ጳጳስ ተናግሯል፡፡ “The war against Ethiopia should be considered as a holy war, a crusade to open Ethiopia, a country of infidels and Schismatics to the Expansion of the Catholic Faith.” (By OCP on Mach 12, 2010)
- የሚላኖው ሊቀ ጳጳስ ሹስተር ከተናገሩት ቀደም ሲል ከገለጽሁት በተጨማሪ “የጣሊያን ፋሽስት ባንዲራ፤በአሁኑ ጊዜ የክርስቶስን መስቀል በኢትዮጵያ ውስጥ በድል አድራጊነት ባሮችን ነፃ ለማውጣትና ለእኛም የሚስዮን ፕሮፓጋንዳ መንገድ እየከፈተ ነው” ብለዋል።
The Archbishop of Milan, cardinal Schuster, went farther and did all he could to bestow upon the Abyssinian War, the nature of a Holy Crusade. “The Italian (Fascist Flag) is at the moment bringing in triumph the Cross of Christ in Ethiopia to free the road for the emancipation of the slaves, opening it at the same time to our missionary propaganda.” (By T.L. Gardini, Towards New Italy.)
ከዚያ በኋላ የሚላኖው ራሱ ሊቀጳጳሱ አንድ ታንክ ላይ ዘልሎ ወጣና ረጋ ብሎ እዚያ የተሰበሰቡትን የፋሽስት ጀሌዎች ባረከ። የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ሳለቬሚኒ እንደገለጸው፣ ቢያንስ ሰባት ካርዲናሎች፣ 29 ሊቀ ጳጳሶች፣ 61 ጳጳሶች ወዲያውኑ ጦርነቱን ደግፈዋል። የቫቲካን ድጋፍ በዚህ ብቻ ሳያበቃ፣ በውጭ አገርም ጦርነቱን ደግፈዋል። በየአገሩ ያሉት የካቶሊክ ጋዜጦች በሙሉ እንደ እንግሊዝ አገርና አሜሪካም ያሉት ሳይቀሩ ኢጣሊያን ደግፈዋል።
- እ.አ.አ. በ1949 አቭሮ ማንሃታን በጻፈው መጽሀፍ እንደገለጸው “ፓዮስ 11ኛ ለሙሶሊኒ ትልቅ ክብር የሚሰጡ መሆናቸው ይታወቃል። በአጠቃላይ፣ የጣሊያን ቀሳውስት በሙሉ፣ የፋሽስቶቹ ወገን መሆናቸውን በቀላሉ ለመረዳት የሚቻለው፣ የፋሽዝም መርሆ፣ ብሄርተኛነት፣ ፈላጭ ቆራጭና ሕዝባዊነትን የሚቃወም አስተዳደር መሆኑ ነው” ይላል። በእንግሊዝኛው የተጻፈው እንዲህ ይላል።
(Pope Pius XI is credited with much admiration for Mussolini that the Italian Clergy as a whole are pro-Fascist is easy to understand, seing that Fascism is a nationalist, authoritarian, anti-Socialist Force”.) Avro Manhattan 1949.
ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ አቶ ዘውዴ ረታ ደግሞ “- – - የዓለም የካቶሊኮች አባት (ፓዮስ 11ኛ ማለታቸው ነው) ከፋሽስቱ ዲሬክተር መሪ ተጣልተው ከባድ ችግር ላይ ከመውደቅ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ዓይነት ፍትሕን የተመረኮዘ አስተያየት ከመስጠት ታግደው መኖር የሚሻል መሆኑ ታያቸው” ሲሉ መስክረዋል። ይሄ እንግዲህ አቶ ዘውዴ ረታ ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱላቸው የካቶሊኮች አባት፣ ፓዮስ 11ኛ፣ ለፍትሕ አለመቆማቸው በራሳቸው አንደበት ገለጹት። ሌላው የፒዩስ 11ኛ ጥፋት፣ የራሳቸው ካርዲናሎች ከፋሽስቱ መሪ ሙሶሊኒ ጎን ቁመው ወረራውን ከፍ ብዬ በማስረጃ እንዳቀረብኩት፣ የጦር መሣሪያዎች ሲባርኩና ፋሽስቶችንም ሲያወድሱ፣ እነዚህን የቫቲካን ባለሥልጣናት ላይ የመገሰጽም ይሁን የማገድ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነው።
ክቡራን አንባቢያን
ሌላም ላክልበት። ሙሶሊኒ እና ጭፍራዎቹ ኢትዮጵያን በመውረር የፈጸሙት በደል እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ለማስታወስ ያህል፣ ጥቂቶቹን ከዚህ በታች አቀርባለሁ።
|
2,000 |
|
525,000 |
|
275,000 |
|
78,500 |
|
24,000 |
|
17,800 |
|
35,000 |
|
300,000 |
|
5,000,000 |
|
7,000,000 |
|
1,000,000 |
|
700,000 |
ከላይ ከተዘረዘረው በተጨማሪ፤ለዚህ ሁሉ እልቂት መሪና ኃላፊ የሆነውን ጀነራል ግራዚያኒን ለመግደል ሞገስ አስገዶምና አብረሃ ደቦጭ ባደረጉት ሙከራ ሰበብ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እ.አ.አ. ከየካቲት 12 እስከ 15 1937 ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ 30,000 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በእነዚሁ ቀናት ውስጥ ሞገስ አስገዶምንና አብርሀም ደቦጭን ደብቀዋል በሚል ሰበብ ደብረሊባኖስ የነበሩትን ከ300 እስከ 500 የሚደርሱ መነኩሴዎችና ካሕናት ተረሽነዋል። አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል፣ ሕዝቡ ለፋሽስት መንግሥት እንዲገዛ ስበኩ ሲባሉ አሻፈረኝ በማለታቸው በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል።
ይህን ሁሉ የሰው እልቂት፣ እንዲሁም የንብረት መውደም የሚያውቁት የቫቲካኑ መሪ ፓዩስ 11ኛ በዝምታ ማለፋቸው ይታወቃል። አቶ ዘውዴ ረታ ይህን ሐቅ ወደ ጎን ትተው ፓዩስ 11ኛ የዓለም ነርሶችን ሲቀበሉ “በመንግሥታት ግንኙነት መሀከል የሚፈጠር ማናቸውም አለመግባባት – - – በሰላም መንገድ መፈታት ያለበት መሆኑን በጥብቅ ካሳሰቡ በኋላ – - -” በሚል ቃል ለማስረጃነት ለማቅረብ ሞክረዋል። ይህን መሰል አነጋገር፣ እንኳን በከፍተኛ ሥልጣን ያለ ሰው ይቅርና ማንም ተራ ሰው ሊናገረው የሚችል አባባል አለመሆኑን አቶ ዘውዴ ረታ የሚገነዘቡት ይመስለኛል። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥር ያሉት ጳጳሶች እና ካርዲናሎች ተጠሪነታቸው ለፓዩስ 11ኛ በመሆኑ እሳቸውን ከተወቃሽነት ሊያድናቸው አይችልም።
የዓለምን ሰላም ፈላጊ የሆኑ ሁሉ፣ የፋሽስቶች መሪና ጭፍሮቹ በኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግፍ አውግዘዋል። ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ፣ አቶ ዘውዴ ረታ የቫቲካኑን መሪ ፓዩስ 11ኛ ከደሙ ንጹህ ናቸው ብለው ለመደገፍ መነሳሳታቸው እጅግ የሚያሳዝን ጉዳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የናዚ መሪ የነበረው ሂትለር፣ አይሁዳውያንን በጨፈጨፈ ጊዜ ዝምታን መርጣ የነበረችው ቫቲካን፣ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ፣ ከአንዴም ሁለት ጊዜ፣ አይሁዳውያንን ይቅርታ ጠይቃለች። ፋሽስቶች በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸሙት ግፍ ግን ቫቲካን እስከ ዛሬ ምንም ዓይነት የመጸጸት እርምጃ አልወሰደችም። ስለዚህ፣ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉት ፓፓ ኢትዮጵያን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው የምንል ብዙ ኢትዮጵያውያን አለን።
ውድ አንባቢያን
ከዚህ ከፍ ብሎ የተጻፈው ቫቲካንን በተመለከተ ያለው ጉዳይ ብቻ ነው። “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በሚለው መጽሀፍ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ግድፈቶች ልጠቁማችሁ። አቶ ዘውዴ ረታ ስለ ሙሶሊኒ አስተዳደግ፣ ጠባይ እና ተግባራት ብዙ ብለዋል። ግን ይህ ትረካ እሳቸው ከሰጡት ርእስ አኳያ ሲታይ ምን ጠቀሜታ አለው? ይልቁንስ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለሊግ ኦፍ ኔሽንስ አቤት በማለት ከአገር ቢወጡም፣ ለረጅም ጊዜ እንግሊዝ አገር እንዲቆዩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ስላደረጉት አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሼቱ ጠባይና ተግባራት ቢጽፉ ጥሩ ነበር። ከሁሉም የሚገርመው የሲልቪያ ፓንክረስት በጥቂቱም ቢሆን መጻፋቸው ነው።
ሲልቪያ ፓንክረስት ስለ ኢትዮጵያ ልትጽፍ የቻለችው ከ1927 እስከ 1931 ዓ.ም. ድረስ በሎንዶን የኢትዮጵያ ሙሉ ባለ ሥልጣን ሚንስቴር በነበሩት አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ ድጋፍና ቡራኬ መሆኑን “የአዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሼቱ የሕይወት ታሪክ፣ ከታደለ ብጡል ክብረት” የሚባለውን መጽሐፍ ቢያነቡ ብዙ ጠቃሚ መረጃዎች ያገኙ ነበር።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንግሊዝ አገር ሲደርሱ፤ አንድም የእንግሊዝ መንግሥት ባለሥልጣን የክብር አቀባበል አላደረገላቸውም። ከመርከብ ከወረዱ በኋላ የተቀበሏቸው የአዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሸቱ የግል ወዳጆች ናቸው። ይህንን ሁኔታ የሚያሳየው ፎተግራፍ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መርከብ ውሰጥ ገብተው የተቀበላቸው አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እሸቱ መሆናቸውን የሚያሳየው ፎቶ
ከ1927 እስከ 1931 ዓ.ም. ድረስ በአወሮፓ፤ በአሜሪካ እና በሕንድ የብዙሃን መገናኛዎች፤ በጽሑፍ እና በአካል ተገኝተው፤ፋሽስት ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን በግፍ እንደወረረ፤ ሕዝቡን እንዳሰቃየና ንብረትን እንዳወደመ በሰፊው ገልፀዋል። እንኳን እሳቸው፤ ሕፃናት ልጆቸቸው ዳዊትና ዮሐንስ ሳይቀሩ በአደባባይ ላይ ቆመው ስለ ወረራው ያላቸውን ኀዘኔታ ገልጸዋል። አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ እንደ ዴል ቫዩ ያሉ ሰዎች በጦር ሜዳ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መልምለው ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል።
አቶ ዘውዴ ረታ ይህን ሁሉ ታሪክ አያውቁም ነበር ለማለት አልደፍርም። ሆን ብለው የሸሹት ጉዳይ ነውም አልልም። ግርምት እንደፈጠረብኝ ግን አልክድም።
የአዛዥ ሐኪም ወርቅነህ ወዳጆች ወደቡ ድረስ ሄደው ንጉሠ ነገሥቱን ሲቀበሉ
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና አዛዥ ሐኪም ወርቅነህ ስለ ሥራ ጉዳይ ሲወያዩ
ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት አንዳንድ ነገር ላክልበት፡፡
- በቅርቡ ከመገናኛ አውታሮች እንደ ተረዳነው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸመው ግፍ እና አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከሰላሳ ሺህ በላይ ሰዎች ላስገደለው ለጀነራል ግራዚያኒ፣ አፊሌ በሚባል ትንሽ ከተማ ውስጥ አንድ የመታሰቢያ ሙዚየምና ሐውልት ጭምር ተሠርቷል። ሐውልቱ በተመረቀ ዕለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካርዲናል በሥፍራው ተገኝተው ቡራኬ መስጠታቸውም ተነግሯል። ይህ ተግባር የሚጠቁመው፣ ዛሬም ቢሆን ቫቲካን ለፋሽስቶች እንጂ ለተበዳይዋ ኢትዮጵያ መብት አለመቆማቸውን ነው። ስለዚህ የአሁኑ የሮማ ጳጳስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ ነው።
- ለፋሽስቱ ጨፍጫፊ ጀነራል ግራዚያኒ አፊሌ ከተማ የቆመው ሐውልት እንዲፈርስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ጳጳስ የጣሊያንን መንግሥት መጠየቅ አለባቸው የሚል ጥያቄ ማቅረብ ተገቢ ነው።
- ኢጣልያ ሊቢያ ውስጥ ለፈጸመችው ግፍ ካሳ የከፈለች መሆኗ ይታወቃል። ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ውስጥ የፈጸመችው ሊቢያ ውስጥ ከፈጸመችው የማይተናነስ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ ካሳ እንድትከፍል መጠየቅም ትክክል ነው።
- አቶ ዘውዴ ረታ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሚለው መጽሀፍ ውስጥ ፒዩስ 11ኛን በመደገፍ ከጻፉት በተጨማሪ፣ ታኅሳሥ 7 ቀን 2005 በሪፖርተር ጋዜጣም አውጥተውታል። ይህን ለማድረግ የተነሱበት ዓላማ ባይገባኝም አካሄዳቸው፣ በስተጀርባው አንድ ድብቅ ዓላማ ያለው አስመስሎባቸዋል።
እንደ እኔ አስተሳሰብ፣ ይህ ድርጊታቸው ትክክል እንዳልነበረ አምነው በመቀበል፣ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ቢጠይቁ ጥሩ ነው እላለሁ።
ታደለ ብጡል ክብረት (ኢ/ር)
ሞባይል፡ 00911 23 24 43
ፖ.ሣ. ቁጥር 5510
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ