(ዘ-ሐበሻ፟) በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ከሚገኝበት ቦታ ዛሬ ተነሳ። ሐውልቱ በጊዜጣዊነት ያርፍበታል ወደተባለው ብሄራዊ ሙዚየም ቢዛወርም አሁንም ሕዝቡ በሐውልቱ መመለስ ላይ ጥርጣሬ እንዳለው እየገለጸ ይገኛል።
“የመንገድ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በማንኛውም ሃገር መሠራታቸው ይደገፋል። ሆኖም ግን በሚሰሩበት ጊዜ የእምነት ተቋማትንና እና ለሀገር እና ለህዝብ ትልቅ ውለታ የዋሉትን ለስማቸው መታሰቢያ የተሰየሙ ሃውልቶችን መነካት እንደሌለባቸው መታወቅ ነበረባቸው” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች “የአገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተ ክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ መታሰቢያቸውን በማንሳት በስመ የባቡር ፕሮጀክት ለዚች ሃገር የዋሉት ውለታ ፤ ለአርበኞች ያሳዩት ተጋድሎ ፤ ህዝቡ በእምነቱ አንድ በመሆን ጠላትን እንዴት መመከለት እንዳለበት ያስተላለፉት መልዕክት ከግምት ውስጥ ሳይገባ ለአንድም ቀን ከቦታው ማንሳት እምነቱንም ታሪክንም መዳፈር ነው።” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ለአንድ ዓመት ያህል ከቦታው ርቆ በብሄራዊ ሙዚየም ይቀመጥና ተመልሶ የነበረበት ቦታ ይቀመጣል ሲሉ የመንግስት ባለስልጣናት ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገ ባለው የቀላል ባቡር ግንባታ ፕሮጀክት ምክንያት ሐውልቱ የየሚያርፍበት ቦታ የሚቆፈር በመሆኑ በጊዜያዊነት ነው የሚነሳው ቢባልም ባለሙያዎች ሐውልቱ ሳይነካ ባቡር መስመሩን መዘርጋት ይቻል ነበር ማለታቸውን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች “በአሁኑ ጊዜ የሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የእምነት ተቋማትንና ታሪካዊ ሃውልቶችን በጥናት ወቅት ለምን ግምት ውስጥ አስገብተው እንደማይሰሩ አይገባንም። ባልጠፋ ቦታ ዋልድባ ላይ ስኳር ልማት ማቋቋም እና ባልጠፋ መንገድ ሃውልቶችን እያነሱ መንገድ መስራት የሃገሪቱን ታሪክ ጥላሸት ከመቀባት በላይ ሃገሪቱ አለኝ የምትላቸውን ቅርሶች ከማጥፋት የማይተናነስ ስራ ነው መስሎ የሚታየው” ይላሉ።
አቡነ ጴጥሮስን በጥቂቱ
(አንድ አድርገን ብሎግ በአንድ ወቅት እንደጻፈው)የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ከእርሷ ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልጽ ከተመረጡት አባቶች አንዱ በመሆን ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም. በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዓመት በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ”ተብለው ተሾሙ።በ1928 ዓ.ም. አረመኔው የኢጣልያ ፋሺስት በግፍ አገራችንን ለመውረር ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት በማለት ውቅያኖስ አቋርጦ በመምጣት ኢትዮጵያን ሲወርና ሕዝቧን፣ ሊቃውንቷን፣ ገዳማቷንና አድባራቷን በግፍ ሲጨፈጭፍ ያዩት ብፁዕነታቸው ወራሪውን ኃይል ከኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎት ሊዋጉት ቆረጡ። የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከአረመኔው ፋሺስት ጦር ጋር በመፋለም ላይ የነበረውን አርበኛ ለማበረታታት ወደ ማይጨው በሔዱ ጊዜ ብፁዕነታቸው ተከትለው ሔዱ። ከዚያ እንደ ተመለሱም በታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ተሰባስበው የቤተ ክርስቲያን አምላክ በኢትዮጵያውያን ላይ የመጣውን ችግር እንዲያስታግሥ በጸሎት እየተጉ ወደነበሩት አባቶችና አርበኞች በመሔድ ለአገርና ለነጻነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን በመስበክ ሁሉም እንዲጋደሉ ማሳሰብ እና ማትጋት ጀመሩ። ኋላም የገዳሙ መነኮሳትና የሰላሌ አርበኞች ይባሉ የነበሩት አርበኞች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተሳታፊ ሆኑ። ከዚያም አርበኞቹ የቻሉትን ሁሉ አድርገው ወደ ሰላሌ ሲመለሱ ብፁዕነታቸው አዲስ አበባ ቀሩ። ብዙም ሳይቆዩ በጠላት እጅ ተያዙ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስምንት ጥይት አሁን ሃውልታቸው ከሚገኝበት ቦታ ዝቅ ብሎ ባለው ቦታ ላይ ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡