Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ቢሞትም አይሞትም! (ግጥም ስለማንዴላ) –ከፋሲል ተካልኝ (አደሬ)

$
0
0

mandela

ቢቢሲ..አልጀዚሪያና ኤፒ የመሳሰሉ መገናኛ
ብዙኃን..በሰበር ዜናነት..የታላቁን የዓለማችን
ተምሳሌ – ተአርአያ የሆነውን የኔልሰን
ማንዴላን (የማዴባን) ዜና ዕረፍት እየዘገቡ ነው::

የዜናው እውነትነት ቢረጋገጥም..ቀደም ብዬ
በስንኞቼ..አጽንኦት ሰጥቼ እንደገለጽኩት..
የማዴባን ሕያውነት አይለውጥም::

ለማንኛውም..በሥጋዊ ዕረፍቱ የተሰማኝን ሐዘን በመግለጽ..ነፍስ ይማር እላለሁ::

የመታሰቢያ..ስንኞቹንም እነሆኝ ብያለሁ!!!

____ ቢሞትም አይሞትም ____

ከዳር እዳር ይናኝ..
ላለም ሁሉ ያስተጋባ
ስሙ የተቀደሰ ነው..
ለዘላለም ማዴባ!..ማዴባ!..

ማዴባ!..ማዴባ!..

ታቦት ተቀርጾ ለግብሩ..
ቢጠራ በቀንም ሆነ በሌት
ቢያሞጋግሱት ደጋግመው ቢቀኙለት..
ቢቆሙለት ቅኔ ማሕሌት

እማይበዛበት..
እማያንስበት..

ለሔደበት ፍኖተ-ነጻነት..
የመለኮታዊ ብርሐን ነጸብራቅ ነው!..
እሚያወጣ ተጭቆናዊ ቅሌት
ለቅኖች ሁሉ አብነት..
ለመላው ዘረ-አዳም ተምሳሌት::

ተሥጋዊ መሻቱ ‘ርቆ..ያለትዕቢት..ያለአመፃ..
በቅዱስ ውስጣዊ ሃይሉ..
የበደሉትን ይቅር ብሎ..በነጻ መንፈሱ ያነፃ

ተክፋታቸው እግረ-ሙቅ አላቆ..
በእርቀ-ሰላም በምህረትና በይቅርታ
የትም’ክታቸውን ሠንሰለት በጥሶ..
ያሰሩትን በትህትናው የፈታ
ለጨቁዋኞች ነጻ አውጪ ነው..
ለተጨቁዋኞችም እንደጌታ::

የተንኩዋሰሰው..
የዘረሰው መንፈስ..
ተዘር..ተቀለም ልቆ..በፅኑ መንፈስ ገዝፏል
ሕያው የሆነ ታሪኩን..በበጐ ምግባሩ ጽፏል

ምድረ-ደንብን ተቃርኖ..
ሕገ-ተፈጥሮን ተላልፏል
የዕድሜ ልክ ጽልመቱን እንኩዋ’..
በብሩህ ብርሐኑ ገፏል
ማዴባ ቢሞትም አይሞትም!..
ሞትን ቀድሞ አሸንፏል..
ተሚኖርበት በላይ ኖሮ..
ተሚሞትበትም ቀን አልፏል!!!

የቂም..የበቀል..የክፋት..
እሾህ እሾሁን ነቃቅሎ..
በእርቅና ሰላም ያስተቃቀፈ..
…ያበረከተ የፍቅር አበባ
ስለራሳችሁ ኑሮ ፀልዩ..
ቢሞትም እኮ አይሞትም!..
…ዘላለማዊ ነው ማዴባ::
* * *

___ፋሲል ተካልኝ አደሬ___


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles