Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ማንዴላ፡ ጀግና አይሞትም –ከዳንኤል ክብረት (ዲ/ን)

$
0
0

አንዳንዱ የሞተበት ቀን የድል ቀን ተብሎ ይከበርበታል፤ ሕዝብ የመሞቻውን ቀን የሚናፍቁለት ሰውም አለ፡፡ አንዳንዱ እንኳን ተወለደ ሳይባልለት እንኳን ሞተ ይባልለታል፡፡ አንዳንዱ እንዲሞት ይጸለይለታል፤ ሌላው እድሜው እንዲያጥር ይረገማል፡፡ ከዚህ የተለየ ነው ማንዴላ፡፡
ሚሊየኖች እንዳይሞት የሚጸልዩለት፤ ሚሊየኖች እንዲኖር የሚመኙለት፤ ሚሊየኖች ከእድሜያቸው ተቀንሶ ቢሰጠው የሚፈቅዱለት፤ ሚሊየኖች እነርሱ ሞተው ሊያኖሩት የሚሹት፤ ሚሊየኖች በየቀኑ የጤናውን ሁኔታ ከራሳቸው ጤና በላይ የሚከታተሉለት ሰው ነው ማንዴላ፡፡
mandela
አፍሪካ አያሌ መሪዎችን በቅርብ ዘመናችን አስተናግዳለች፡፡ አያሌ የነጻነት ታጋዮችን አይታለች፡፡ እንደማንዴላ ታሥረው የታገሉ ነበሩ፡፡ እንደ ማንዴላ ድርጅት አቋቁመው የተዋጉ ነበሩ፤ እንደ ማንዴላ ሕዝባቸውን ለነጻነት ያበቁ ነበሩ፤ እንደ ማንዴላም ከነጻነት በኋላ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የሆኑም ነበሩ፤ እንደ ማንዴላ ከሀገር ተሰደው የኖሩ ነበሩ፤ ታድያ ማንዴላን ምን ልዩ አደረገው?
ማንዴላ የታገለው ለፍትሐዊነት ነው፡፡ ደጋግሞ ይናገር እንደ ነበረው ‹‹እኛ የታገልነው የነጭ የበላይነትን በጥቁር የበላይነት ለመተካት አይደለም፤ የታገልነው ነጮች፣ ጥቁሮችና ሌሎች በእኩልነት የሚኖሩባትን ደቡብ አፍሪካ ለመመሥረት ነው›› ይል ነበር፡፡ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ከነጻነት ትግል በኋላ ጭቆና አልቀረም፡፡ ነገር ግን ነጭ ጨቋኞች በጥቁር ጨቋኞች ተተክተዋል፡፡ በነጮች ተይዞ የነበረው የገዥነት ቦታ ለሥልጣን በበቁት ታጋዮች ፓርቲዎችና ጎሳዎች ተተካ፡፡ የነጻነት ተዋጊዎች የፍትሕና እኩልነት አስፋኞች ሳይሆኑ አዳዲሶቹ ገዥ መደቦች ሆነው ብቅ አሉ፡፡ በነጮች ተይዞ የነበረውን ሀብት ነጻ አውጭ ግንባሮችና ፓርቲዎች ወረሱት፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ በትግሉ ጨቋኞችን በሌሎች ጨቋኞች ተካቸው እንጂ ፍትሕና እኩልነትን ለማግኘት አልታደለም፡፡

ማንዴላ ይህንን ነበር የተዋጋው፡፡ እንደተመረጠ ብዙዎች የነጮች መሬት ተቀምቶ ለጥቁሮች እንዲሰጥ፣ ነጮች ከሀገሪቱ እንዲባረሩ ይፈልጉ ነበር፡፡ እርሱ ግን አላደረገም፡፡ ‹መሬቱ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲዳረስ እንጂ መሬት አልባ ነጮች የመፍጠር ዕቅድ የለንም› አለ፡፡ ጥቁሮች ይበልጥ ነጻ የሚወጡት የበለጸገች ደቡብ አፍሪካ ስትኖር እንጂ በደኸየች ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አይደለም ብሎ አመነ፡፡ ለዚህ ደግሞ የብዙ ዘመን ሀብትና ልምድ ያላቸው ነጮች ወሳኞች መሆናቸውን ተገነዘበ፡፡ ለዚህም ነበር በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ያየነው ምስቅልቅል በደቡብ አፍሪካ ያልተከሰተው፡፡
ማንዴላ የዕርቅና የፍቅር ሰው ነበር፡፡ በነጮችና በጥቁሮች መካከል ለዘመናት በአፓርታይድ የተፈጠረውን መከፋፈል፣ መጠላላትና መገፋፋት በዕርቅና በይቅር ባይነት እንጂ በመሣሪያና በበቀል ሊጠፋ እንደማይችል የተረዳ መሪ ነው፡፡ አፓርታይድ ሲገረሰስ የይቅርታ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ ነባር የሕዝብ ለሕዝብ ችግሮች በተቻለ መጠን በይቅርታና በዕርቅ እንዲወገዱ ሠርቷል፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች ከነጻነት በፊት የነበሩ ገዥዎችና አበሮቻቸው ወደ እሥር ቤት ሲወረወሩና ወደ ውጭ ሲሰደዱ፤ በደቡብ አፍሪካ ግን የከፋ ወንጀል ካልፈጸሙና ይቅርታ ለመጠየቅም ከፈቀዱ ችግሩን በዕርቅና በይቅርታ ለመፍታት ተችሏል፡፡ በዚህም ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ ብቻ ሳይሆን ሀገርን አፍርሶ ከመሥራት አባዜ ነጻ እንድትወጣ አድርጓታል፡፡

ማንዴላ ለሰዎች ልጆች ሁሉ የቆመ መሪ ነበረ፡፡ ከዊኒ ማንዴላ ጋር ያፋታቸው ዋነኛው ምክንያት ዊኒ ማንዴላ በነጻነት ትግሉ ወቅት ‹ለነጻነት ትግሉ› ሲባል ፈጽመውታል የተባለው ኢ ሰብኣዊ ድርጊት በእርቅና ይቅርታ ኮሚሽኑ መጋለጡ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ለነጻነት ትግሉ ሲባል ቢደረግም፣ ምን እንኳን ዊኒ ማንዴላ ቢሆኑም ማንዴላ ግን ሊታገሡት አልቻሉም፡፡ የነጻነት ታጋይ ድርጅቱ ኤ ኤን ሲ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ የፈጸማቸው ኢሰብአዊ ድርጊቶች ካሉ ይቅርታ የመጠየቅ ግዴታ አለበት ብለው የሚያምኑት ማንዴላ በዚህ ምክንያት ከዊኒ ጋር ተለያይተዋል፡፡ ከነጻነት በኋላ አያሌ የነጻነት ታጋይ ድርጅቶች በትጥቅ ትግላቸው ወቅት የፈጸሙት ኢሰብአዊ ድርጊት፣ ወንጀልና ግፍ ተሠውሮ እንዲቀር ሲደረግ ማንዴላ ግን ኤ ኤን ሲ ይቅርታ እንዲጠይቅ አድርገዋል፡፡
ማንዴላ ሰላማዊ መንገድን ብቻ ይመርጥ የነበረ መሪ ነበር፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ምንም እንኳን የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረውን ኤ ኤን ሲ የመራ ቢሆንም ሰላማዊ የትግል መንገድ ከማንኛውም የትግል መንገድ ሁሉ ቅድሚያ እንዲያገኝ ሲታገል የኖረ ሰው ነው፡፡ ይህ ትግሉ ከአፓርታይድ መሪዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በኤ ኤን ሲ ውስጥ ከነበሩ ሌሎች አመራሮች ጋርም ጭምር ነበር፡፡ የጠመንጃ ትግል ለሰላማዊ ትግል፣ ለድርድርና ለውይይት የተዘጋውን በር ማስከፈቻ እንጂ ሰላማዊ መንግሥት የመመሥረቻ መንገድ አይደለም ብሎ ያምን ነበር፡፡ በአፓርታይድ የመጨረሻዎቹ ዘመናት እነ ፒተር ቦታ ከኤ ኤን ሲ መሪዎች ጋር ለመደራደር ያቀረቡትን ጥያቄ አንዳንድ የድርጅቱ አመራሮች አልቀበል ሲሉ ‹እኔ ብቻዬንም ቢሆን እደራደራለሁ› እስከ ማለት አቋም ወስዶ ነበር፡፡ ከአፓርታይድ ጋር የሚደረገው ትግል በጠመንጃ አሸናፊነት ሳይሆን በሃሳብ አሸናፊነት መጠናቀቅ አለበት የሚል አቋም ነበረው፡፡

Mandela
በደቡብ አፍሪካ ሁሉንም ያሳተፈ የመጀመሪያ ምርጫ በተደረገ ጊዜ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ሕገ መንግሥቱን ብቻውን ለማጽደቅ የሚያስችለውን ድምጽ አላገኘም ነበር፡፡ ይሄንን አጋጣሚ ማንዴላ በደስታ ነበር የገለጠው ‹‹ሁሉንም ሕዝብ የሚመራ ሕገ መንግሥት ብቻችንን ማጽደቅ የለብንም፤ ይህ አጋጣሚ መልካም ነው፤ ከሌሎቹ ጋር ተማክረን፣ ተደራድረንና ተስማምተን እንድናጸድቅ ያደርገናል› ብሎ ነበር፡፡
ማንዴላ ሥልጣን መያዝን ብቻ ሳይሆን መልቀቅንም ያስተማረ ሰው ነው፡፡ ማንዴላ ደቡብ አፍሪካን ለአንድ ዙር ብቻ ነው የመራው፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ዘመናት በሚደረጉ ምርጫዎችም የማሸነፍ ዕድል ነበረው፡፡ ነገር ግን በቃኝ አለ፡፡ እየተወደደ፤ እየተመሰገነና እየተከበረ በቃኝ አለ፡፡ በደቡብ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ብሎም በመላው ዓለም ‹አይከን› የመሆንን ጸጋ ተጎናጸፈ፡፡ የነጻነት፣ የጽናትና የትዕግሥት፣ የሰላምና የዕርቅ፣ የይቅር ባይነትና ከጥላቻ ውጭ የሆነ ፖለቲካ ‹አየከን› ሆነ ማንዴላ፡፡ በመላው ዓለም ሕዝብ ልብ ውስጥ ማንም ሊነቅለው የማይችል ዛፍ፣ ማንም ሊያፈርሰው የማይችል ሐውልት ሆነ ማንዴላ፡፡
ለዚህ ይመስለኛል ማንዴላን ዓለም በሙሉ የሳሳለት፤ ለጤናውም ሆነ ለእድሜው የጸለየለት፤ የተጨነቀለትና ልቡን ከልቡ ጋር ያስተባበረለት፡፡ እንደ እርሱ ዓይነት ሰዎች እንደ ሄሊኮሜት በዘመናት አንድ ጊዜ ብቅ የሚሉ ናቸው፡፡ ተወደው ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ፣ ተወደውም ከሥልጣን የሚወርዱ፤ ተወደውም ያለ ሥልጣን የሚኖሩ፡፡ እንደ ማንዴላ ዓይነት ሰው እንኳን ሌላው የአፍሪካ ሀገር ራሱ ኤ ኤን ሲም ዳግም ሊያገኝ አልቻለም፡፡ መከፋፈል ዕጣ ፈንታ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
መሪነትና ባለ ሥልጣንነት ምን ያህል እንደሚለያዩ ማንዴላ አንድ ማሳያ ናቸው፡፡ ማንዴላ ባለ ሥልጣን አልነበሩም፤ መሪ እንጂ፡፡ ባለ ሥልጣን በሰው ገንዘብ ውስጥ እንጂ በሰው ልብ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ባለ ሥልጣን ይፈራል እንጂ አይከበርም፤ ባለ ሥልጣን ቢሮ አለው እንጂ ሀገር የለውም፤ ባለ ሥልጣን የሚላላኩት ሠራተኞች እንጂ የሚጸልዩለት ወገኖች የሉትም፡፡ ባለ ሥልጣን የሚያዘው ሰው እንጂ የሚያፈቅረው ሰው አያገኝም፤ ባለ ሥልጣን ፊርማውን የሚፈልግ እንጂ እድሜውን የሚፈልግ የለም፤ ባለ ሥልጣን ብዙ ገንዘብ እንጂ ብዙ ልቦች አያገኝም፤ ባለ ሥልጣን ከሥልጣን ወዲህ እንጂ ከሞት ወዲያ ተዝካር የለውም፡፡

ማንዴላ ከሞት በኋላም ይኖራል፡፡ በብዙ ልቦች ውስጥ ይኖራል፡፡ መቃብር እርሱን ሊያስረሳ አይቻለውም፡፡ እርሱ ከመቃብር በላይ የሆነ ተግባር አለውና፡፡ ማንዴላ የአንድ ሀገር መሆኑ ቀርቶ የዓለም ሆኗል፡፡ መሬት ላይ የሚቆም ሐውልት አያስፈልገውም፤ እርሱ በሕዝቦች ልብ ውስጥ የማይፈርስ ሐውልት በሕይወት እያለ ሠርቷልና፡፡ ብዙ ባለ ሥልጣናት በሕይወት እያሉ በሰው ልብ ውስጥ ሐውልት መሥራት ስለማይችሉ፣ ከሞቱ በኋላ የድንጋይ ሐውልት ይሠራላቸዋል፡፡ ነገር ግን ሐውልታቸው መልእክት አልባ ሐውልት ይሆናል፡፡ እንደ ማንዴላ ያሉ መሪዎች በመሬት ላይ ሐውልት ሲተከልላቸው ደረቅ ሐውልት አይሆንም፤ መልእክት ያለው ሐውልት እንጂ፡፡
ማንዴላ አይሞትም፤ ጀግና አይሞትምና፤ የማንዴላ አይረሳም፤ ሕዝብ ልብ ውስጥ የገባ ሰው አይረሳምና፤ ማንዴላ አያልፍም፣ በጎ ሥራ አያልፍምና፡፡

(ዲ/ን ዳን ኤል ክብረት ይህን ጽሁፍ የጻፈው ማንዴላ በጣም በታመሙበት ወቅት እንደነበር ለማስታወስ እንወዳለን)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>