በካታሎኒያ የሚታተሙት አራቱን ጋዜጦች ማንበብ ለኤስፓኞሉ አሰልጣኝ ሃቪዬር አጊሬ ደስታን አይሰጥም፡፡ በየዕለቱ ከቢሯቸው ተቀምጠው ጋዜጦቹን ሲያነቡ ይበሳጫሉ፡፡ ከገጽ ገጽ እያገላበጡ የሚያተርፉት ንዴትን ብቻ ነው፡፡ የአጊሬ ጥያቄ ሌላ ነው፡፡ በግዙፍ ክለብ ጥላስር ሆነው በጋዜጦች አለመታየታቸው አያሳምናቸውም፡፡ በባርሴሎና ከተማ ሁለተኛው ክለብ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ክለብ ደግሞ እጅግ ግዙፍ ነው፡፡ ሁሉም ስለኤፍሲ ባርሴሎና እንጂ ስለኤስፓኞል መፃፍ አይፈልግም፡፡ ዕለታዊዎቹ ጋዜጦች ለእግርኳስ ሰፊ ሽፋን ቢቸሩትም የሁሉም ገፅ ትኩረት ባርሴሎና እንጂ ኤስፓኞል አይደለም፡፡
‹‹የከተማው ሁለተኛው ክለብ እንሁን እንጂ በርካታ ጥሩ ጎኖች አሉን፡፡ ደጋፊዎቻችን እጅግ ስሜታዊ ናቸው፡፡ ስለ ብዙ ነገሮች ጠንካሮች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ባርሴሎናን በመጥላት…›› ይላሉ አጊሬ፡፡
በስፖርቱ ዓለም በአንድ ከተማ ሁለት ክለቦች መካከል የሚኖር ተፃራሪ ስሜትና ጥላቻ በተለመዱ የመደብ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የጂኦግራፊና በመሳሰሉት የተፈጠረ መሆኑ ተለምዷል፡፡ በባርሴሎና ከተማ ውስጥ በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለው መራርነት ግን ከነፃነት ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው፡፡ ካታሎኒያ ከስፔን የመገንጠል ስሜት የሚንቦገቦግባት ክልል መሆኗ ይታወቃል፡፡ ክልሉ ነፃ መንግስት ለመመስረት ላለው ፍላጎት ባርሴሎና የበኩሉን ድጋፍ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ ባርሳ የካታላን የነፃነት ንቅናቄ ምልክት ነው፡፡ ኤስፓኞል ደግሞ ከስፔን ጋር መቆየትን በሚመርጡ የአንድነት አቀንቃኞች ይደገፋል፡፡ ስለዚህ ለባርሴሎና ደጋፊዎች ኤስፓኞል ከሪያል ማድሪድም በላይ ባላንጣ ጠላታቸው ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ባርሴሎናን የደገፈው የ28 ዓመቱ አልበርት ሬይራ ‹‹ሪያል ማድሪድን ከምጠላበትም በላይ ኤስፓኞልን እጠላለሁ›› ይላል፡፡ ‹‹የኤስፓኞል ደጋፊዎች ከካታላንነታቸው ይልቅ ስፔናዊነት ይሰማቸዋል፡፡ አለመታደል ሆኖ ለዚህ ጉዳይ ፖለቲካ ትልቁን ሚና ይጫወታል›› በማለት እውነተኛውን ስሜቱን ይናገራል፡፡ ሬይራ አንገቱን በአዎንታ ይነቀንቅና ይቀጥላል፡፡ ‹‹እንደ እኔ ሀሳብ ኤስፓኞል ወደ ሌላ ሀገር መወሰድ አለበት››
ከክልሉ የመራቁ ነገር እንኳን የማይታሰብ ነው፡፡ ከሁለቱም ክለቦች የተውጣጡ ባለስልጣናት መራራውን ፖለቲካዊ ስሜት ለማርገብ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል፡፡ በተለይ የኤስፓኞል ባለስልጣናት ስለጉዳዩ ሲነሳ በቶሎ ስሜታቸው ይነካል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ዮአን ኮሌት ክለባቸው ከብሔርተኝነቱ ንቅናቄ ራሱን ያላራቀበት ጊዜ እንደነበር ያምናሉ፡፡ ሆኖም አሁንም ክለቡ በተቻለው ሁሉ ክፍት መሆኑን ይሟገታሉ፡፡
በዚሁ ስሜት የሚጦዘው ጠላትነት ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙም ይበልጥ ይባባሳል፡፡ በቅርቡ በካምፕ ኑ የሆነው ይኸው ነው፡፡ 22 ጊዜ ሊጉን ላሸነፈውና አራት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን ለሆነው ባርሴሎና ጨዋታው ታናሽ ወንድምንም ገጥሞ ማሸነፍ አስፈላጊ መሆኑን የሚገልፅ ነው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው የመጨረሻዎቹ 12 ጨዋታዎች ባርሴሎና ስምንት ጊዜ አሸንፏል፡፡ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡ እስከ ዛሬ በተደረጉት አጠቃላይ 191 ጨዋታዎች 43ቱ በባርሴሎና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የኑ ካምፑ ክለብ ውጤታማት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ሆኖም ለኤስፓኞል ባርሴሎና በፍፁም የበላይነት መጫወት ደርቢውን የበለጠ ትልቅ ያደርግላቸዋል፡፡ ዛሬ ኤስፓኞል በላሊጋው 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ሆኖም ከዚህ እጅግ ያነሰ የውጤታማነት ደረጃ ላይ ሳለ እንኳን ከባርሴሎና ጋር ተጫውቶ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መላው የውድድር ዘመኑን ምርጥ እና የማይረሳ ያደርግላቸዋል፡፡ ለምሳሌ በ2007 ኤስፓኞል በ11ኛ ደረጃ ላይ ጨረሰ፡፡ ሆኖም ደጋፊዎች ፍፁም የማይዘነጉት ዘመን ሆነ፡፡
ምክንያቱም በዚያ ዓመት በኑ ካምፕ በተደረገው ደርቢ ራኡል ታሙዶ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል ጨዋታው በ2-2 ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጓል፡፡ በአቻነቱ ውጤት ምክንያት ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ ጋር በእኩል ነጥብ ዓመቱን እንዲጨርስና እርስ በርስ ተገናኝቶ የተሻለ ውጤት በመያዝ ሪያል ማድሪድ የሊጋው ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ ለኤስፓኞል ከዚህ በላይ ደስታ ያለ አይመስልም፡፡ ታሙዶ ዕለቱን አይረሳትም፡፡ ደጋፊዎችም አጋጣሚዋን ሁል ጊዜም ያስታውሷታል፡፡ ጎሏም በመላው ስፔን ‹‹ታሙዶዞ›› ተብላ ትታወሳለች፡፡ ‹‹በሄድኩበት ሁሉ የማድሪድ ደጋፊዎች ያመሰግኑኛል›› ታሙዶ ይናገራል፡፡ ‹‹የባርሳ ደጋፊዎች ደግሞ…››
ለኤስፓኞል ያቺ አጋጣሚ ሁል ጊዜ የምትገኝ አይደለችም፡፡ በደርቢው ኤስፓኞል በአሸናፊነት የወጣበት የቅርብ ጊዜ አጋጣሚ ከተፈለገ በ2009 ይገኛል፡፡ ባርሳ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻዎቹ ዙሮች ድረስ መወዳደር የየዓመቱ ልማዱ ነው፡፡ ኤስፓኞል ግን ለዩሮፓ ሊግ እንኳን ለማለፍ አልቻለም፡፡ ራቅ ባለ ታሪክ ክለቡ ዛሬ ዩሮፓ ሊግ ተብሎ ለሚጠራው (የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ዋንጫ) ፍፃሜ የበቃው በ1988 እና በ2007 ነበር በሁለቱም ተሸነፈ እንጂ፡፡
የባርሴሎና ኃያልነት የሚያበቃ አይደለም፡፡ የኤስፓኞል ፕሬዝዳንት ኮሌት ጎረቤታቸውን ከግዙፉ ጭራቅ ጋር ይመስሉታል፡፡ ለክለባቸው ህይወት በሁሉ ረገድ ፈታኝ ነው፡፡ ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና የላሊጋውን የቴሌቪዥን ገቢ በተናጠል እየተደራደሩ ገበያቸውን ይሰበስባሉ፡፡ ከስፔን ሊግ ለተቀሩት ክለቦች የሚሰጠው ገንዘብ በአንፃራዊነት እጅግ ያነሰ በመሆኑ ሌሎቹን አቀጭጯል፡፡ ከሊጉ የቲቪ ገቢ ግማሹን ሁለቱ ግዙፋን ወደ ካዝናቸው ማስገባታቸው ብቻ ለኤስፓኞል መጥፎ አልሆነም፡፡ ባርሴሎና ከወጣት ተጨዋቾቻቸው ምርጦቹን እየመነተፈ ለራሱ የማድረጉ ችግርም አብሯቸው አለ፡፡ ‹‹የባርሳ ታላቅነት የካታላኒያን ስፖርት ጎድቶታል›› ይላሉ ኮሌት፡፡ ባርሴሎና በሁሉ ቦታ አለመጥፋቱ የደለበ የስፖንሰርሺፕ ገቢ ማግኘት እንኳን ለኤስፓኞል የሚቻል አይደለም፡፡ የማሊያ ሽያጭም እንዲሁ የተገደበ ነው፡፡ የባርሴሎና ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ሆዜ ማሪያ ጋይ ደ ሊባ በጣም ተወዳጅ የኤስፓኞል ማሊያ በጀርባው ላይ ምንም አይነት ስም ያልሰፈረበት፣ የደጋፊው ስም የተፃፈበት ወይም የዳኒ ያር ስም የሚነበብበት ብቻ ነው፡፡ (ያርኬ በ2009 በ26 ዓመቱ ሜዳ ላይ ወድቆ ህይወቱ ያለፈው ተጨዋች ነው)
የኤስፓኞል ደጋፊዎች በክለባቸው ለየት ያለ ባህሪይና ሁኔታ ይኮራሉ፡፡ ሜሲና ዣቪን መሆንን የሚመኙ ህፃናት በሞሉባት ከተማ ለኤስፓኞል ለመጫወት የሚፈልጉ ታዳጊዎችን ማግኘት እጅግ ያስቸግራል፡፡ ‹‹የኤስፓኞል ደጋፊ ከሆንክ የሆነ ስሜት ይኖርሃል›› ይላል የ13 ዓመቱ ሰርጂ ፊሸር፡፡ ‹‹ባርሳ ሁል ጊዜ ስለሚያሸንፍ ሁልጊዜ ደስታ ነው››
የኤስፓኞል ደጋፊዎች በአገሬ የጨዋታ ዘይቤም ደስተኞች ናቸው፡፡ ባርሴሎና በኳስ ቁጥጥርና ቅብብል ላይ ያተኮረ ጨዋታን ይወዳል፡፡ አገሬ ግን ቀጥተኛ ማጥቃትን ያማከለ አግሬሲቭ አጨዋወትን ይመርጣሉ፡፡ በተጨማሪም ክለቡ ልክ እንደ ጀርመን ስታዲየሞች ደጋፊዎች በስሜት የሚጮህበትን አዲስ የስታዲየም መቀመጫ ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ካደረገ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
የስታዲየሙን የስያሜ መብት መሸጥ ቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡ ስታዲየሙ 70 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ የኤስፓኞል ዓመታዊ በጀት 50 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ የባርሳ በጀት ግን ከዚህ በ10 እጥፍ ይበልጣል፡፡ ብራዚላዊውን ኔይማር ለማስፈረም ብቻ 57 ሚሊዮን ዩሮ አውጥቷል፡፡ ‹‹ለአንድ ተጨዋች 60 ቢሊዮን ዩሮ? እኛ ግን ለስምንት ተጨዋቾች 700 ሺ ዩሮ ብቻ አውጥተናል›› ይላሉ አሰልጣኝ አጊሬ፡፡ ‹‹ተጨዋቾችን ከየስርቻው ማግኘት ይኖርብናል››