ትናንትና ዛሬ!
——————–
በሑመራ ከተማ ከሚገኘው አንድ ባንክ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለማጭበርበር ወይ ለመዝረፍ ሞክረዋል ወይ ወስደዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ለማእከላዊ ምርመራ ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸው ሰማሁ። የሑመራና አከባቢው ፖሊስ እንደሚለው ባንክ የዘረፉ ወይ ለመዝረፍ የሞከሩ ግለሰቦች የዴ.ም.ህ.ት ታጋዮች ናቸው (ይህ በመንግስት አካላት ለአከባቢው ህዝብ የተነገረ ነው)።
ከሑመራው ጉዳይ የተያያዘ ነው መሰለኝ እዚሁ መቐለም ባንኮችና የመንግስት መስራቤቶች (በተለይ የህወሓት ቢሮዎች) ሃያ አራት ሰዓት በፀጥታ አካላት እየተጠበቁ ነው። ከመከላከያ፣ ፖሊስና ደህንነት የተውጣጣ አንድ ግብረሃይል (Command Post) የመንግስት ተቋማትን (በተለይ ባንኮች) በተለየ ሁኔታ ጥበቃና ክትትል እያደረገ ይገኛል። ግብረሃይሉ የሚያግዙ አዲስ አበባ የሰለጠኑ ወደ አምስት መቶ የሚሆኑ ወጣት ሲቪል ፖሊሶች (ጀሮ ጠቢ) በዚሁ ወር በመቐለ ከተማ ተሰማርተዋል።
ፀጥታ ማስከበር መሞከራቸው ጥሩ ነው። ስለ ባንክ ዘረፋ ጉዳይ ስሰማ ግን አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ድሮ በደርግ ግዜ የህወሓት ታጋዮች በአክሱም ባንክ ሲዘርፉ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር። ህወሓቶች ስልጣን ከያዙ በኋላም ባንክን የዘረፉ ግለሰቦች ጀግኖች ተብለው እነሱን ለማወደስ ፊልም ተሰርቶላቸዋል። ላከናወኑት የዝርፍያ ተግባር ለማሞካሸት ቁልፍ ስልጣን ተሰጣቸው። እስካሁንም የኢትዮጵያ ገዢዎች ሁነው እያገለገሉ ነው።
ድሮ ባንክ የዘረፈ ተሸለመ፤ አሁን ባንክ የዘረፈ ወንጀለኛ ነው። ባንክ መዝረፍ አንድ ተግባር ነው፤ አንድም ወንጀል ነው አልያም ደግሞ ጀግንነት ነው። አሁን በሑመራ ባንክ ለመዝረፍ ሞክረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች (አድርገውት ከሆነ) ወንጀለኞች (ጥፋተኞች) ተብለው እንደሚፈረዱ ሳይታለም የተፈታ ነው።
በሕግ መሰረት ባንክ መዝረፍ ወንጀል ነው። ድሮ ህወሓቶች ባንክ ሲዘርፉም ተግባሩ ወንጀል ነበር። ግን ህወሓቶች ለዘረፉት ነገር ተጠያቂ አልሆኑም። እንዳውም ለነሱ ባንክ መዝረፋቸው የጀግንነት ተግባር ነበር። ራሳቸው ባንክ ዘርፈው የተሸለሙ ሰዎች አሁን ተመሳሳይ ተግባር ለፈፀሙ (ባንክ ለዘረፉ) ግለሰቦች የጥፋተኝነት ዉሳኔ ይሰጣሉ። ራሳቸው ባንክ ሲዘርፉ ጀግንነት ነው፤ ሌሎች ባንክ ሲዘርፉ ግን ወንጀል ነው።
ግን እንዴት ሆነ? በደርግ ግዜ ባንክ መዝረፍ ወንጀል ነበር። ግን ወንጀለኛ የሚኮነው ስትሸነፍ ነው። ህወሓቶች ባንክ ሲዘርፉ በደርግ ወታደሮች ቢያዙ ኖሮ ወንጀሎች ተብለው በህዝብ ፊት ይረሸኑ ነበር። ዉምብድና በራሱ ሕገወጥ ነበር። ለህወሓቶች ግን ዉምብድና ጀግንነት ነበር። አሁን ውንብድና ይሁን ባንክ መዝረፍ ወንጀል ነው። ህወሓቶች ግን ራሳቸው እንደ ጥሩ ነገር ቆጥረው ሲያደርጉት የነበረውን ተግባር እንዴት አሁን ሕገወጥ አደረጉት?
አዎ! ህወሓቶች ዉምብድና ሲሰሩ (ለምሳሌ ባንክ ሲዘርፉ) ወንጀለኞች ተብለው ከመያዝ ይልቅ ጀግኖች ተብለው የተሸለሙበት ምክንያት ስላሸነፉ ብቻ ነው። ህወሓቶች አሸንፈው ስልጣኑ ስለተቆጣጠሩት የሰሩት ጥፋት ሁሉ ወንጀል ሳይሆን ጀግንነት ሆነ። ህወሓቶች ቢሸነፉ ኖሮ ግን ተግባራቸው ጀግነንት ሳይሆን ዉርዴት ይሆን ነበር። ስለዚህ ወንጀለኝነት/ጀግንነት ከመሸነፍ/ማሸነፍ ግንኙነት አለው።
በቃ ከተሸነፍክ ወንጀለኛ ትሆናለህ። ካሸነክፍ ደግሞ ጥፋትህ ሁሉ እንደ ጀብድነት ይቆጠርልሃል። በሰው አገዛዝ ትልቁ ወንጀል መሸነፍ ነው። አንድ ወጣት እንውሰድ። ተርቧልና ከባንክ አንድ ሺ ብር ሰርቆ ጠፍቷል። በፖሊስ ከተያዘ በስርቅ ወንጀል ተከሶ ወህኒ ይወርዳል። ያ ልጅ አቅም አግኝቶ፣ የራሱ ፖሊስና ወታደር ይዞ ገዢውን ፓርቲ አሸንፎ ስልጣን ቢቆጣጠር ኖሮ ግን አንድ ሺ ብር ቀርቶ አንድ ሚልዮን ብር ቢያጭበረብር የማይጠየቅበት ሰፊ ዕድል አለው።
በመቐለ ከተማ አንድ በካድሬዎች የሚናፈስ ወሬ አለ። ከወራት በፊት በፊትዋ አስገራሚ ፅሑፍ የነበራት አንድ ዕብድ መሳይ ለማኝ ነበረች። አሁን አትታይም። አሁን እንደምንሰማው ከሆነ (ትክክል ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፣ ግን ‘ግርማይ ገብሩ’ የተባለ ጋዜጠኛም ስለሷ መፃፉ አስታውሳለሁ) ለማኟ በፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ዉላለች። ምክንያት: የዴምህት ሰላይ ሆና በመገኘቷ የሚል ነው።
ይህ የለማኟ ወሬ የድሮ የህወሓት ታሪክ ያስታውሰኛል። ህወሓቶች አንድ ጓዳቸው በውምብድና ወንጅል ተጠርጥሮ በደርጎች ተይዞ ይታሰራል። ጓዳቸውን ለማስፈታት የታሰረበት ቦታና ሌላ ተያያዥ መረጃዎች ማግኘት አስፈላጊ ነበርና ሰላይ ወደ ቦታው ላኩ። የተላከው ሰላይ ስዩም መስፍን ነበር። ስዩም ዕብድ ሁኖ ነበር የሚሰልለው። ዕብድ መስሎ ለመሰለል የተፈለገው የመንግስት የፀጥታ ሃይሎችን ለመሸወድ ነበር።
ይህን ጉዳይ (ዕብድ መስሎ መሰለይ) በህወሓቶች እንደ ጥሩ ስትራተጂ ተወስዶ ፊልም ተሰርቶበታል (‘ሙሴ’ ፊልም ይመለከቱ)። ብዙ ነገር ተብሎለታል። ስዩም ዕብድ መስሎ መሰለይ በመቻሉ ቆራጥና ጀግና ተብሏል። ምክንያቱም ህወሓቶች አሸንፈዋል። እንዳሁኗ ስዩም መስፍን በመንግስት (በደርግ) ፀጥታ ሃይሎች ቢያዝ ኖሮስ? ወንጀለኛ ተብሎ ይሰቃይ ነበር። ቶርቸር ይደረግ ነበር።
ያሁኗስ (አሁን የተያዘች ለማኝ)? በጠላት እጅ ወድቃለች። ስለዚህ ትሰቃያለች። ምክንያቱም ወንጀለኛ ናት። ምክንያቱም ለግዜው አላሸነፈችም። ምናልባት (እንደሚባለው የዴምህት ሰላይ ናት ብለን እናስብና) ዴምህቶች አሸንፈው ስልጣን ከተቆጣጠሩ ልጅቷ ‘ጀግና’ ተብላ ፊልምና ሐውልት ይሰራላት ይሆናል። አሁን በህወሓቶች ከተገደለችም ልክ እንደነ ‘አሞራ’ና ‘ቀሺ ገብሩ’ ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቶላት ታሪኳ ይተረክልን ይሆናል። ዴምህቶች ከተሸነፉ ግን ወንጀለኛ እንደተባለች ትቀራለች። ስሟም አይነሳም። ህወሓቶች ባያሸንፉ ኖሮ ስለ አሞራና ቀሺ ገብሩ ምንም ነገር አንሰማም ነበር። ተራ ወንበዴዎች እንደሆኑ ይቀሩ ነበር። ልጅቷ ሰላይ ናት የሚል ግምት የለኝም ምክንያቱም ሰላይ ብትሆን ኖሮ ቀልብ (ትኩረት) የሚስብ ነገር (የፊትዋ ፅሑፍ) አታረግም ነገር። ሰላይ ቀልብ የሚስብ ነገር ማድረግ የለበትም።
ህወሓቶች ‘ስዩም መስፍን ዕብድ መስሎ ለመሰለል የፈለገው ለዓላማ ነበር’ ይሉን ይሆናል። ዴምህቶችም ‘ለማኟ ዕብድ መስላ ለመሰለል የሞከረችው ዓላማ ስለሆነ ነው’ ሳይሉን አይቀሩም። ነጥቡ ግን ‘እርስበርሳችን መሰለል፣ መገዳደል ለምን አስፈለገ?’ የሚል ነው።
ጀግኖችን እናደንቃለን። ጀግና መሆን ግን ያስፈራናል። ጀግና ለመሆን ፈተናን ፊትለፊት መጋፈጥ ይኖርብናል። ከፈተና በመሸሽ ጀግንነት አይገኝም። ፈተና የጀግንነት መንገድ ነው። ጀግናን ማድነቅ ጀግና አያደርግም። ጀግና የሚያደርገን ፈተና ነው። ላብዛኛው አስፈሪ የሆነ ፈተና ለኛ የጀግንነት መለኪያችን ነው። ጀግኖችን የምናደንቅ ከሆነ ለምን ራሳችን ጀግና ለመሆን አንጥርም?
ዞሮዞሮ በሰው አገዛዝ ስርዓት ሕግ የሚወጣው ገዢው እንዲገለገልበት እንጂ ፍትሕ ለማስፈን አይደለም። ገዢዎች ህዝብን ለመጨቆን እንዲያገለግላቸው የራሳቸው ሕግ ያወጣሉ። ሕጉ እነሱን አይመለከትም። ገዢዎቹ ከሕግ በላይ ናቸውና። ገዢዎች ሕግ የሚያወጡት ተፎካካሪዎቻቸውን ለመቅጣት ነው።
አሁን የምንፈለገው የገዢዎች የራስ ሕግ ሳይሆን የህዝብ ሕግ ነው። በህዝብ ሕግ ሁሉም ሰው (ገዢም ተገዢም) እኩል ነው። የሕግ የበላይነት ይኖራል። ሰው በወንጀል የሚጠየቀው ጥፋት ሲሰራ እንጂ ሲሸነፍ ብቻ አይደለም። የሕግ የበላይነት ሲኖር ሁሉም (አሸናፊውም ተሸናፊውም) ከሕግ በታች ይሆናል፣ በሕግ ይጠየቃል። ገዢው ሰው ሳይሆን ሕጉ ይሆናል።
አሁን የስርዓት ለውጥ ያስፈልጋል። ሰዎች ሳይገድሉና ሳይገደሉ የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ የምናመጣበት መንገድ ማመቻቸት ይኖርብናል። ያሁኑ ባለስልጣናትም የማይሰደዱበት (የማይገደሉበት)፣ ከሀገር ዉጭ ያሉ (የሃይል መንገድ የመረጡ ሃይሎችም) በሰላም ወደ ሀገራቸው የሚገቡበት ሁኔታ የሚፈጠርበት ሀገራዊ መግባባትና ዕርቅ እንፈልጋለን። ስልጣን ለመያዝ ይሁን ስልጣን ለመልቀቅ የሞት ስጋት መኖር የለበትም።
ሰው ሳይሰደድና ሳያሳድድ፣ ሳይገድልና ሳይገደል የስልጣን ሽግግር የሚደረግበት የፖለቲካ መድረክ እንጠብቃለን። ስልጣን ለመያዝ ወይ በስልጣን ለመቆየት ደም መፋሰስ ይቁም።
አንዱአለም አራጌና አስተያየቶች!
——————————
ትናንት እንዲህ ፅፌ ነበር:
“ከትግራይ ሰዎች ባሰባሰብኩት መረጃ መሰረት ባሁኑ ሰዓት ክብርና አድናቆት የተቸረው የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ አንዱአለም አራጌ ነው። (በትግራይ ሰዎች የሚወደድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ: አንዱአለም)!”
ከተሰጡኝ አስተያየቶች በመነሳት አንድ ነገር ተገነዘብኩ፤ አንድም እኔ አማርኛ አልችልም (የፈለኩትን አልገለፅኩም) አልያም ደግሞ የትግራይ አንባቢዎቼ የአማርኛ ቋንቋ ችግር አለባቸው።
እኔ የፃፍኩት “ከትግራይ ሰዎች” የሚል ነው። እኔ እንደሚገባኝ “ከትግራይ ሰዎች” ማለት ትግርኛ የሚናገሩ ግለሰቦች ማለት እንጂ የትግራይ ህዝብ ወይም የመቀሌ ወይ የሌላ አከባቢ ኗሪዎች ማለት አይደለም። አንድ ሰውም ትግርኛ ተናጋሪ ከሆነ የትግራይ ሰው ነው፤ የትግራይ ህዝብ ግን አይወክልም። ስለዚህ “ከትግራይ ሰዎች” ብዬ ስል ያናገርኳቸው ሰዎች የትግራይ (ትግርኛ ተናጋሪ) ናቸው ለማለት ነው።
ሌላው ችግር የፈጠረው ሐረግ “ባሰባሰብኩት መረጃ” የሚል ነው። እዚህ ላይ መረጃ መሰብሰብና ጥናት ማካሄድ ይለያያሉ። መረጃ ሰበሰብኩ እንጂ ጥናት አላካሄድኩም። መረጃ ያሰባሰብኩት Informal በሆነ መንገድ ነው። ስለዚህ ለትግራይ ህዝብ ኮሽኔር (questionnaire) በመበተን የተሰበሰበ መረጃ አይደለም።
ሌላው ደግሞ “ከተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ነው” እንጂ ከአጠቃላይ ፖለቲከኞች አይደለም። አሁንም የትግራይ ሰዎች (ትግርኛ ተናጋሪ) እንደነገሩኝ ከሆነ ከተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች ተወዳጁ አንዱኣለም ነው።
መረጃ የሰጡኝ ሰዎች (አንደኛ) የትግራይ ሰዎች ናቸው፣ የሌሎች ክልሎች ግምት ዉስጥ አላስገባሁም። (ሁለተኛ) መረጃ የተቀበልኳቸው ሰዎች አንዱኣለምን በቅርበት የሚያውቁ ወይም በቂ መረጃ ያላቸው ናቸው። (ሦስተኛ) መረጃው የተሰበሰበው ስርዓት ባለው መደበኛ አሰራር አይደለም (Informal ነው)። በስተመጨረሻ አከባቢ ግን ሆን ብዬ ስለሱ መረጃ እያሰባሰብኩ ነበረ። (አራተኛ) መረጃ የሰጡ ሰዎች በፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ብቻ ናቸው (ከአምስት ሰዎች ዉጭ)።
በዚሁ መሰረት ከአርባ ሦስት ሰዎች (እኔ አርባ አራተኛ ነኝ) የሰበሰብኩት መረጃ ነው። እነኚህ ሁሉ ትግርኛ ተናጋሪ (የትግራይ ሰዎች) ብቻ ናቸው። አስራዘጠኙ የዓረና ትግራይ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣ አስራአንድ የህወሓት አባላት (አብዛኞቹ የደህንነት ሰዎች)፣ ሦስት የአንድነት ፓርቲ አባላት፣ አምስት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ያልሆኑ፣ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የነበሩ (አሁን ግን ያልሆኑ)፣ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ የፖለቲካ አቋማቸው በግልፅ ማወቅ አልቻልኩም።
ከነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ አንዱኣለም አራጌን ያደነቁበት ምክንያት (አንድ) በሚሰጠው በሳል ሓሳብ፣ (ሁለት) የጥላቻ ፖለቲካ ስለማያራምድ። በብዙዎቹ አገላለፅ አንዱአለም ምንም ዓይነት የብሄር (የጥላቻ) ፖለቲካ አያራምድም። በኢህአዴግ የታሰረውም በፖለቲካ ብቃቱ ምክንያት ገዢውን ፓርቲ ስላሰጋ ነው ሊሆን የሚችለው ብለዋል። ከሰዎቹ ስድስቱ ግን ስለ አንዱኣለም መጥፎም ጥሩም አልተናገሩም።
በዚህ መሰረት ነው አንዱኣለም አራጌ በትግራይ ሰዎች (ትግርኛ ተናጋሪ ግለሰቦች) ተወዳጁ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪ ነው ብዬ ለመፃፍ የተገደድኩት። አሁንም ልብ በሉ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ነው።
እኔም ስለ አንዱኣለም አራጌ መረጃ ያገኘሁት ከነዚህ ሰዎች ነው።