በ1999 ዓ.ም ይመስለኛል አንድ የደቡብ አፍሪካ ምሁር የወያኔ-መሩ ኢሕአዴግና የሀገር ቤት ሰላማዊ ተቃዋሚወች ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወጥተው ታሪካዊት ሀገራቸውን ወደ ዴሞክራሲ: ሰላምና ብልጽግና እንዲያሸጋግሩ ሲያሳስቡ እንዲህ ብለው ነበር::
“ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሆነው በተመረጡ ጊዜ በሀገሪቱ በሚኖሩት ነጮች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በርካታ ሰዎች ጎትጉተው ነበር:: ማንዴላ ግን ‘የበደለን ስርአቱ እንጅ ሰዎች አይደሉም:: ያ አስከፊ ስርአት ተመልሶ እንዳይመጣ ሁላችንም ተረባርበን አርቀን ልንቀብረው ይገባል:: ደቡብ አፍሪካ ሰፊ ሀገር ናት: ለሁላችንም ትበቃናለች::’ በማለት ሀገራቸውን ከጥፋት በመታደግ በመላው አለም ለዘላለም የሚታወስ ታሪክ አስመዘገቡ::
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀርቶ ለመላው አለም ምሳሌ የምትሆን ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር ናት:: የአፍሪካ ሀገሮች እንደሀገር በማይታወቁበት ጊዜ ኢትዮጵያ በንግድ: በስልጣኔና በወታደራዊ ሀይሏ ታዋቂ ነበረች:: አሁን የሚታየው ሁኔታ መታረም አለበት:: መንግስትና ተቃዋሚወች በሀገራችሁ ጉዳይ ላይ ቁጭ ብላችሁ መነጋገር ይኖርባችኋል:: ሶማሌወች ‘ከቆመ ወጣት የተቀመጠ ሽማግሌ አሻግሮ(አርቆ) ማየት ይችላል’ ይላሉ:: አፍሪካውያን ከናንተ የረጅም ጊዜ ልምድና ተሞክሮ የምንማረው ብዙ ነገር አለ::”
ወያኔወች በጣሊያን ፉርኖና ካልቾ አድገው መንገድ በመምራትና በስለላ ሀገራቸውን የበደሉ የባንዳ ልጆች መሆናቸውን ዶ/ሩ አላወቁም:: የጣሊያንን ባህርይ ተላብሰው በዚያው በጣሊያን ስታይል ኢትዮጵያን በዘርና በቋንቋ ከፋፍለው እየገዙን ያሉ ጸረ-ሕዝብና ጸረ ሀገር መሆናቸውን አልተረዱም:: ስለሀገርና ስለአንድነት የሚያወራ ትምክህተኛ የሚባልበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ: ከአንድነት ይልቅ ልዩነት: ከሀገር በፊት ጎሳ ይቅደም የሚል መፈክር የሚያስተጋባ በስምም ሆነ በተግባር ኢትዮጵያን የማይወክል ቡድን ጥንታዊቷንና ታሪካዊቷን ሀገር በጉልበት እየገዛ እንደሆነ አልተገነዘቡም::
የወያኔን ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት በሚመች መልኩ ሀገራችን ኢትዮጵያ በክልሎች ተከፋፍላ በዜጎቿ መሀል የመጠፋፋት ፖለቲካ ሲቀነቀን ኖሯል:: በመንግሥት ደረጃ በሚካሄደው የጥላቻና የዘረኝነት ሰበካ ምክንያት ከትግራይ ክልል በስተቀር ደረጃው ይለያይ እንጅ ሁሉም ክልሎች ተጠቂ ሆነዋል:: ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ ግን ነገሮች ተገለባብጠው እንዲጠፋፉ ይቀሰቀሱ የነበሩት ጎሳወችና ሀይማኖቶች ግምባር ፈጥረው የጥፋት አራማጁን ኃይል ለጠፋው ጥፋት አንደኛ ደረጃ ተጠያቂ ያደረጉበት ሁኔታ እየታየ ነው:: አንዳንዴ ሌላውን ለማጥመድ በምትተበትበው ድር ራሷ ድር-አድሪ ሸረሪቷም ልትያዝ ትችላለች:: በወያኔወች ላይ የደረሰው ሁኔታ ይኸው ነው:: የዘር ፖለቲካ ይቅር የሚሉትን ሰዎች እያዋረዱ በሰላምና በፍቅር በአንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር የነበረውን አንድ ሕዝብ በቋንቋና በዘር ከፋፍለው ሲያናቁሩ የኖሩት ወያኔወች ችግሩ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደራሳቸውና ወርቅ ወደሚሉት ሕዝባቸው ፊቱን በማዞሩ በድንጋጤ መደናበር ይዘዋል:: አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየደከሙ እንደሆነ የሚደሰኩሩት ውሸት የማይሰለቻቸው እኒህ ወመኔወች እነርሱ ይጠሩበት የነበረውን ስም ለተቃዋሚወቻቸው አሻግረው በሀገራችን ዘር-ተኮር እልቂት ለመፍጠር እና የልማትና የአንድነት እቅዳቸውን ለማበላሸት “ጸረ-ሰላም ኃይሎች” የሚሏቸው ተቃዋሚወች እንቅልፍ አጥተው ለጥፋት እንደተሰለፉባቸው አድርገው ያለሀፍረት መተርተር ይዘዋል::
እውነታው ግን እኒህ የወያኔ እብዶች ከስህተታቸው ተምረው ሕዝብን ከሕዝብ የሚያቀራርብ ስራ እየሰሩ አለመሆኑ ነው:: ለችግሮች ትክክለኛ መፍትሄ ክመፈለግ ይልቅ ችግሩን ለማባባስ በእሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ መርጠው የትግራይ ሰዎችን በሙሉ አስታጥቀው ለጦርነት አዘጋጅተዋል:: ትግሬ የተባለን ሁሉ መሳሪያ ማስታጠቅና በወታደር ማስጠበቅ በምንም መለኪያ መፍትሄ ሊሆን አይችልም:: ለተቃውሞ የሚወጡትን ሰዎች በማሰርና በመግደል በግፍ ላይ ግፍ ይከምሩ ካልሆነ በስተቀር መፍትሄ ማምጣት አይቻልም:: እየተፈጠረ ያለውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የጥፋት ሀይሎች ሴራ አድርጎ ማውራትና ችግሩን ወደሌላ መግፋት ወይም በሀይል ለመፍታት መሞከር ዘላቂ ሰላም አያመጣም::
የትግራይ ሕዝብ በወያኔ ጊዜ የተፈጠረ አይደለም:: ወያኔ ከመፈጠሩ በፊት ከሌሎች ጎሳወች ጋር ችግሩንም ደስታውንም ተካፍሎ አብሮ የኖረ ሕዝብ ነው:: በተፈጥሮ አደጋም ይሁን በጦርነት ቢፈናቀል አቅም እንደፈቀደ የወገኖቹ ድጋፍ ተችሮት በየትኛውም ክልል ያለመሸማቀቅ ኖሯል:: በአሁኑ ጊዜ ግን ሁኔታው ተለውጦ በቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥርስ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ይታያል:: ይኸ ሀቅ ነው:: ቢያለባብሱት መፍትሄ አይሆንም:: የትግራይ ሕዝብ በሌሎች ክልሎች ተገልሎም: ተፈርቶም: ተጠልቶም: ኮሽ ባለ ቁጥር በፍርሀት እየባነነ የሚኖር ለጥቃት የተጋለጠ ሕዝብ ሆኗል:: ለምን? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መልሶች ሊኖሩ ይችላሉ:: ብዙወች የሚስማሙበት ግን ትግሬ የተባለ ሁሉ ሕወሀት ጥቅሜን የሚያስጠብቅልኝ ድርጅቴ ነው ብሎ ደግፎት ስለቆመ ነው የሚለው መልስ ነው:: ከኗሪው ጋር ተሰባጥረው በየክልሎች የሚኖሩት ትግሬወች ሴት-ወንድ: ትንሽ-ትልቅ ሳይል መሳሪያ ታጥቀው ለወያኔ መረጃ የሚያቀብሉ ሰላዮች እንደሆኑ ነው የሚታወቀው:: ከሀገር ውጪ የሚኖሩት በበኩላቸው የወያኔ ክንፍ በመሆን ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ እንጅ ሲቃወሙ አይታዩም:: በትግራይ የሚኖረው ሕዝብም ቢሆን የወያኔን ዕቅድ ለማስፈጸም ከመሰለፍ ውጪ በአጎራባች ክልሎች የሚኖረው ሕዝብ እየተፈናቀለ በምትኩ የትግራይ ተወላጆች በቦታው እንዲሰፍሩ ሲደረግ: ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉና በሕዝብና በሀገር ላይ በደል ሲፈጸም ድጋፍ እንጅ ተቃውሞ ሲያሰማ አልተደመጠም:: እንደ ፖለቲከኛ አንድን ሕዝብ በጅምላ በአንድ መልክ መፈረጅ ተገቢ ላይሆን ይችላል:: እውነታው ግን ይኸው ነው:: በተቃውሞው ጎራ ተሰልፈናል የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ራሳቸው ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ወደኋላ ሲንሸራተቱ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም:: ከሕዝብ ርቆ ወደወያኔ በመጠጋት የጥፋት ሀይልና ምሽግ ሆኖ እያገለገለ በመሆኑ ነው የትግራይ ሕዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያዊ የመገለል እጣ እየደረሰበት ያለው:: “የትግራይ ሕዝብ ከማንም ባላነሰ በወያኔ የተበደለ ሕዝብ ነው:: ተቃውሞውን እንዳያሰማ ከፍተኛ አፈና አለበት ገሌ መሌ” የሚለው ፍሬ ከርስኪ ወሬ አይሰራም:: ከሶማሌ እስከ ጋምቤላ ከጎንደር እስከ ሞያሌ ያለው ሕዝብ እየታገለ ያለው ከአፈና ነጻ ስለሆነ ወይም የተለዩ ምቹ የመታገያ መንገዶች ስላሉት አይደለም:: ከስራ መባረሩን: ዱላውን: እስሩን: ግድያውን ችሎ ነው እየጮኸ የተቃውሞ ድምጹን እያሰማ ያለው::
ከክልሉ ወጥቶ በሌሎች አካባቢወች ለሚኖረው ለተራው የትግራይ ሕዝብ የበፊቱ ኑሮ ይሻለዋል ወይስ የወያኔው ጊዜ? መሳሪያ ታጥቆ ወይም በወታደር ጥበቃ እየተደረገለት የሚኖር ሰው በነጻነት የሚኖር ሰው ነው ለማለት ይቻላል? እንዲህ ተሁኖ ኑሮስ ኑሮ ነው? በዚህ ሁኔታስ እስከመቸ መቀጠል ይቻላል? እኒህ ጥያቄወች በትግራይ ልጆች ምላሽ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጥያቄወች ናቸው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በዝባዥና ጨቋኝን እንጅ ሰላማዊ ወገኑን የሚጠላ ሕዝብ አይደለም:: የትግራይ ሕዝብ ሰልፉን አስተካክሎ ወያኔን ለመታገል መንቀሳቀስና መስዋእትነት መክፈል ሲጀምር ያን ጊዜ የጦርመሳሪያና ጠባቂ ታጣቂ ኃይል ሳያስፈልገው እንደማንኛውም ሰው በፈቀደው የሀገሪቱ ክልል ተዘዋውሮ ሰርቶ መኖር ይችላል::
የብሄር-ብሄረሰቦች መብት ተከብሮ ሁሉም ክልሎች በቋንቋቸው እየሰሩ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው ተብሎ የሚቀለድባት ኢትዮጵያ በወያኔወች መዳፍ ውስጥ ውላ እንደቆሎ እየታሸች ነው:: የወያኔወች ግፍ አንድ ሁለት ተብሎ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም:: ሌላው ቀርቶ ከትግራይ በስተቀር ሌሎች ክልሎች በራሳቸው ሰዎች እንዲተዳደሩ አልተፈቀደም:: ብሔር-ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መብቱ ቢሰጥ ኖሮ እነ በረከት ስምዖን: ህላዊ ዮሴፍ: ገነት ገ/እግዚአብሔር— የአማራ ክልል መስተዳድር ውስጥ ምን ይሰሩ ነበር? ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ ተዘዋውሮ የመኖርም ሆነ ሀብት የማፍራት መብቱ የተጠበቀ ነው በሚለው አረዳድ ከክልላቸው ወጥተው በሌሎች ክልሎች የሚኖሩትን ሰዎች በሀገር ልጅነታቸውና በሕገ-መንግሥቱ አግባብ ልክ ነው ብለን እንቀበል:: በስልጣን ላይ ተቀምጠው “ያዘው! ጣለው! ግረፈው!” እያሉ የሚቀልዱብንን በምን ስሌት ይሁን ብለን እንቀበላቸው? ትግራይ ውስጥ ከቀበሌ እስከክልል ድረስ ባሉት የፖለቲካ ስልጣኖች በአመራር ሰጭነት የተቀመጠ የአማራ: የኦሮሞ: የደቡብ:— ሰው አለ? ሌሎች ክልሎች ለምን ከክልላቸው ውጪ ባሉ ሰዎች እንዲተዳደሩ ይደረጋል? እነ አቶ በረከት: ወ/ሮ ገነት አማራ ክልል ምን ያደርጋሉ? ወርቅነህ ገበየሁ: አባዱላና ኩማ ደመቅሳ ኦሮሚያ ክልል ምን ይሰራሉ? ለመሆኑ በረከት ስምዖን ኢትዮጵያዊ ነው? ኢትዮጵያ እንደአሜሪካ በሀገሪቱ ውስጥ በመወለድ ዜግነት ትሰጣለች ወይስ ፎርማሊቲውን አሟልቶ ዜግነት እንዲሰጠው ማመልከቻ አቅርቦ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ ዜግነት ተሰጥቶት ነው? “አንችው ታመጭው አንችው ታሮጭው” እንደሚባለው የማንፈልገውን ዘረኝነት ከጫናችሁብን በኋላ ይሁን በቃ ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድራለን ብለን ስንል ፊልትሮው እንደተበላሸ መኪና ትንተፋተፋላችሁ::
ብአዴን ሲመሰረት የቀበሌወች: የመንግሥት መ/ቤቶችና ድርጅቶች ወኪሎች የተገኙበት ስብሰባ በየቀበሌው ተደርጎ ነበር:: በአንደኛው ቀበሌ ከተሰብሳቢወቹ መሀል ብዙ ትግሬወችን የተመለከቱ አንድ አማራ “የተሰበሰብነው የአማራ ድርጅት ለመመስረት ወኪል ለመምረጥ ነው ብላችሁናል:: ታዲያ ከእኛ መሀል ያሉት ትግሬወች ምን ያደርጋሉ?” ብለው ጠይቀው ነበር:: ከሕዝቡ መሀል ተመሳስለው ተቀምጠው የነበሩ አንድ የብአዴን አመራር አባል እመር ብለው ተነስተው “የሰውን ደም እየመረመርን ፖዘቲቭ ከሆነ አማራ ኔጌቲቭ ከሆነ ሌላ የሚል ቀልድ ለመጫወት አይደለም እዚህ የተሰበሰብነው” የሚል አስገራሚ መልስ ነበር የሰጡት::
ወ/ሮ ገነት ገ/ እግዚአብሔር የሚባሉ የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ከወያኔ ጋር በመተባበር ወጣቶችን እያስገደለች ነው ተብላ ስሟ ከብዙወች መሀል በመጠቀሱ የአማራው ክልል ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ አዝነው ለወ/ሮይቱ የሚከላከልና የሚያሞገስ ጽሁፍ በፌስቡክ ላይ ማስነበባቸውን ሰማን:: አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለወ/ሮዋ ብቻ ጠበቃ ሆነው የቆሙት በቀሪወቹ ላይ የተሰነዘረው ክስ ትክክል ነው ብለው ተቀብለውት ነው ወይስ ምን? ወ/ሮይቱ ተወልዳ ያደገችው ባ/ዳር ነው ይሉናል አቶ ንጉሱ:: ዶሮና ቆቅ ዝርያቸው አንድ ነው:: ነገር ግን በቤት ውስጥ የተፈለፈለች ቆቅ ዶሮ ልትሆን አትችልም:: የዘር ፖለቲካ ቀርቶ እንደሆነ ይነገረን:: የዘር ፖለቲካ ካልቀረ ግን ለማም ጠፋም ሁሉም በየራሱ ሰው ይተዳደር እንላለን:: የሆነው ሆኖ በአማራ ክልል አማራ ያልሆኑ ሰዎች በፖለቲካ አመራር ሰጭነት እንዲቀመጡ የተደረገው እነርሱን የሚተካ አማራ ማግኘት ስላልተቻለ ነው? በሌሎች ክልሎች ያለው ሁኔታስ ተመሳሳይ ነው ማለት ነው: ወይስ ምን?
አሁን ካለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን ስንገመግም የወያኔ የዘር ፖለቲካና የተዛባ አመራር መቋጫው እየቀረበ ይመስላል:: ብዙ ያስሄደናል ተብሎ የተጠረገው የከፋፍለህ ግዛው ጎዳና ሱር ኮንስትራክሽን እንደሰራው መንገድ እየፈራረሰ ነው:: ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ይጠቀሙበት የነበረው መላ ከሽፏል:: በብሔር-ብሔረሰቦች መሀል የዘሩት ቂምና ጥላቻ የፈለጉትን ያህል ምርት ሳያስገኝ ደርቋል:: በፍርሀት የተሸበበው ሕዝብ ልጓሙን አውልቆ ጥሎታል:: እስከ የልጅ ልጅ ድረስ በዙፋን ቁጭ ብለን እንድንገዛ ያስችለናል ብለው የቋጠሩት ሸር ተፈቷል:: ለጻድቃን የወረወሩት ጦር ወደሀጥአን ዞሯል:: ወያኔወች ግን አሁንም ቢሆን ከስህተታቸው ሊማሩ ባለመፍቀዳቸው ከራሳቸው አልፈው በደጋፊወቻቸው ላይ አደጋ ደቅነዋል:: በእርግጠኝነት ለመናገር ወያኔ መቸም እንዳያቀጠቅጥ ሆኖ ይቆረጣል:: የወያኔን ውድቀት ተከትሎ ዜጎች በነጻነት የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆናለች::
ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!