ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው። ወደዚህ የአበው ማዕረግ ከመምጣታቸው በፊት በዋሺንግተን ዲሲ የቅ/ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን አቋቁመው ሲያገለግሉ ነበር። ማዕረግ ጵጵስናን ካገኙ በኋላ ወደ አገር ቤት ተጠርተው በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። ከዚያም የዲሲ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ወደ አገር ቤት ሲጠሩ ቦታውን ተረክበዋል። ርክክቡ በወቅቱ በፈጠራቸው የተለያዩ ችግሮች ምክንያት አለመግባባቶች ተፈጥረው ለረዥም ጊዜ አገልግሎቱ ተጎድቶ የቆየ ቢሆንም በስተመጨረሻ ችግሩ እልባት ሊያገኝ ችሏል። በወቅቱ በነበረው ጉዳይ ብዙዎቻችን በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል አካሔድ ባለመደሰታችን ተቃውሟችንን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ስንገልጽ ቆይተናል። ያን ጊዜ ተቃውሟችንን በግልጽ እንዳቀረበውነው ሁሉ አሁን ደግሞ በመፈጸም ላይ ባሉት ሕዝብን የማጽናናት፣ «አይዞህ፣ አለሁልህ» የማለት አባታዊ በጎ ተግባር ደስታችንን መግለጽ ይገባናል።
ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የአገራችንን ችግር በተመለከተ በቀጥታ መልእክት ማስተላለፍ ከጀመሩ መቆታቸውን በፌስቡክ ከሚሰራጩ መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል። ምእመኑ ጳጉሜን 1፣ 2 እና 3/2008 ዓ.ም በጾምና በጸሎት ተጸምዶ ወደ አምላኩ ምሕላና ልመና እንዲያቀርብ ከማሳሰባቸውም በላይ በሕዝባችን ላይ የሚፈጸመው ግድያ እንዲቆም በይፋ መጠየቃቸውን ከፌስቡክ ቪዲዮዎች መረዳት ይቻላል (Facebook: https://goo.gl/cLiG8v)። ልክ እንደ አቡነ አብርሃም ሁሉም፣ የደመራ ዕለት ባስተላለፉት አባታዊ ትምህርት አሁን ያለው የሕዝብ ሰቆቃ እንዲያበቃ ተግሳጽ እና መልእክት አስተላልፈዋል (Facebook: https://goo.gl/8TNqyr)። (Youtube: https://goo.gl/yZER86)::
እነዚህ ሁለት የብፁዕነታቸው መልእክቶች ተገቢውን ሽፋን ባለማግኘታቸው ሕዝቡ ሊሰማው ይገባ የነበረውን ማጽናኛ ተነፍጓል ባይ ነኝ። መልእክቱን በማስተላለፍ ሌሎች አባቶችም አርአያነቱን እንዲቀስሙ ማድረግ ያስፈልጋል። ሌሎቹ አባቶቻችን እየተናገሩ ነገር ግን ድምጽ ሊሆናቸው የሚችል ሰው በማጣት ታፍኖ የቀረውን መልእክታቸውን በማስተላለፍ በኩል ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንድንወጣ እለምናለሁ። ይኸው ነው።
Source:-adebabay.com