Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የፓትርያርኩ ልዩ ጸኃፊ፣ ወይንስ የህውኃት ጉዳይ አስፈጻሚ (ይገረም አለሙ)

$
0
0

ይገረም አለሙ
“በርግጠኝነት ሁልግዜም ችግር የመሪ እንጂ የህዝብ አይደለም፤” አቡነ አብርሀም
“ለጠፋው ህይወት መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም” አባ ሰረቀብርሀን
“በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፡፡እኩሌቶቹም ለክብር እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፡፡እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ ለክብርም የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል፡፡” (ጢሞቲዎስ 2፣2፣20)
መስከረም 16 ቀን 2009 ዓም በእለተ ደመራ ምሽት የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛውን ፕሮግራም እያዳመጥኩ ነው፡፡ በዜና መጽሄት ክፍለ ጊዜ የአዲስ አበባው ዘጋቢ እስክንድር ፍሬው በስብሰባ መሀል ነው ያነጋገርኩዋቸው ካላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ልዩ ጸሀፊ አባ ሰረቀ ብርሀን ወልደ ስላሴ ጋር ያደረገው አጭር ቃለ ምልልስ ቀረበ፡፡ እስክንድር በኦሮምያና በአማራ የተገደሉ ወጣቶችን ጉዳይ አንስቶ ቤተ ክህነት ምን አለች ምንስ አደረገች በማለት ላነሳቸው ጥያቄዎች በልዩ ጸሀፊው የተሰጠው ምላሽ እንደ ሰው የሚያሳዝን፣ እንደ ዜጋ የሚያበሳጭ፣ እንደ ኦርቶዶክስ አማኝ የሚያሳፍር ነበር፡፡

aba-sereke-brehan
አማርኛ ከእንግሊዘኛ እየደባለቁ የሚናገሩት አባ ሰረቀ ብርሀን አንደበታቸው ፈጽሞ የሀይማኖት አባት አይመስልም፡፡ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጀምሮ የተለያዩ ባለሥልጣኖች ጥፋቱ የእኛ የእኛ ነው በማለት ለማታላያም ቢሆን አምነው ለዚህም ጥልቅ ተሀድሶ ያስፈልገናል በማለት እየተውተረተሩ ባለበት በዚህ ወቅት እኝህ የጳጳሳችን ልዩ ጸሀፊ ግን ከጳጳሱ ቄሱ አንዲሉ ሆነው “ለጠፋው ህይወት መንግስትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም” በማለት በተከላካይነት ቆሙ፡፡ በዛች አጭር ቃለ ምልልስ በተናገሩት ከመንግስት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ብሰው የተገኙት አባ ሰረቀ ብርሀን “እየወረወረ በድንጋይ የሚገልም እየተኮሰ የሚገልም..” በማለት የመንግሥትን ግድያ ልክ አንደ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩ ዶር አዲሱ ተመጣጣኝ ሊያደርጉት ዳዳቸው፡፡ ይህን ሰምቶ የማይናደድ ሰው፣ የማያፍር የእምነቱ ተከታይ ይኖራል፡፡ ነደድሁ አፈርሁ፡፡
አባ ሰረቀ ንግግራቸውም ሆነ የቃላት አጠቃቀማቸው የሀይማኖት ሰው ሳይሆን የፖለቲካ ሰው የሚያስመስላቸው፤ ቅላጼአቸው ደግሞ የትግረኛ ነውና ግብራቸውን በማይገልጽ መጠሪያ የፓትርያርኩ ልዩ ጸሀፊ ከሚባሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የህውኃት ጉዳይ ፈጻሚ ቢባሉ የሚገልጻቸው ይመስለኛል፡፡
በሰማሁት ነድጄ በሀይማኖቴ አፍሬ እንዳይነጋ የለም ለሊቱ ነጋ፡፡ ማርፈጃው ላይ ወደ ማህበራዊ ድረ ገጽ ጎራ ስል ንዴቴን የሚያበርድ ብቻ ሳይሆን በሀሴት የሚሞላ፤ ሀፍረቴን የሚከላ ብቻ ሳይሆን በኦርቶዶክስ እምነቴ ይበልጥ እንድኮራ ያደረገኝ ንግግር አገኘሁ፡፡ ንግግሩ የተደረገው በባህር ዳር መስቀል አደባባይ የደመራ ክብረ በአል ላይ ሲሆን ተናጋሪው የአካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሀም ናቸው፡፡ ያገኘሁት ንግግር ከመጀመሪያው የማይጀምር ቢሆንም ከጀመረበት አንስቶ ያለው ግን እውነተኛ የሀይማኖት አባት መሆናቸውን ያረጋገጠ ንግግር ነው፡፡ ሙሉ ንግግራቸው በጽሁፍም በድምጽም ከተቻለ በምስል ጭምር ቢገኝ ለአሁኑ አስተማሪ ለታሪክም ቅርስ ነው፡፡
ለመንግሥት ጥብቅ መልእክት፣ ለእምነቱ ልጆቻቸው አባታዊ ምክር ባስተላለፉበት ንግግራቸው “ የምናገረው ሀይማኖት ነው፤በፖለቲካ ከተረጎመው የራሱ ጉዳይ ነው” በማለት እውነቱን በድፍረት የገለጹት አቡነ አብርሀም “በርግጠኝነት ሁልግዜም ችግር የመሪ እንጂ የህዝብ አይደለም” በማለት የመንግሥት ሰዎችን መክረዋል ፣አስጠንቅቀዋል፡ጋዜጠኞችንም ወቅሰዋል፡፡ የአቡነ አብርሀምን ይህን ንግግር እያዳመጣችሁ አለያም ይህችን ከመሀል መዝዤ የጠቀስኳትን ችግር የመሪ አንጂ የህዝብ አይደለም የምትለዋን እያብላላችሁ የአባ ሰረቀ ብርሀንን “እየወረወረ በድንጋይ የሚገልም እየተኮሰ የሚገልም..” የሚለውን አገላላጽ አስቡት አነጻጻሩት፡፡ መኩሪያና ማፈሪያ በአንድ ቤት፡፡
በመግቢያ ላይ የጠቀስኩት {በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፡፡እኩሌቶቹም ለክብር እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፡፡እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ ለክብርም የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል፡፡} (ጢሞቲዎስ 2፣2፣20) የሚለው በስማቸው ሳይሆን በግብራቸው በያዙት የሀላፊነት ቦታ ሳይሆን በፍሬቸው ለተለዩት ለእነዚህ ሁለት አባቶች ጥሩ ገላጭ ሀይለ ቃል ይመስለኛል፡፡
የሚሊዮኖች የእምነት ቤት የሆነችው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ አንደ አቡነ አብርሀም ያሉ ወርቆችንና ብሮችን፣ አንደ እነ አባ ሰረቀ ብርሀን ያሉ የእንጨትና የሸክላ ስሪቶችን የያዘች ለመሆኗ አይደለም በምእምኑ ከእምነቱ ውጪ ላሉትም በግልጽ የሚታይና የሚታወቅ ነው፡፡
የእንጨትና የሸክላ ስሪቶቹ ያለ ቦታቸው መግባታቸው፣ ያለ ደረጃቸው መቀመጣቸው፣ ለምን እንዴት በምን ምክንያትና በማን አንደሆነ የተሰወረ ባለመሆኑ ወርቅ እንዲሆኑ ማድረግም ሆነ ከማይገባቸው ቦታ ማንሳት የማይቻል ስለሆነ የሚቻለውና መሆንም ያለበት “አንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ” የሚለውን የቅዱስ መጽኃፍ ቃል መፈጸም ነው፡፡
ከብረው ለሚያስከብሩን፣ በእውነተኛ አባትነት በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ቃልና መንገድ ለሚመሩንና ለሚያስታርቁን የአባትነት አክብሮት መስጠት፣ቃላቸውን መስማት ምክራቸውን መቀበል መሪነታቸውን መከተል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያሉትን ደግሞ አታውቁንም አናውቃችሁም ማለት ያስፈልጋል፡፡ አቅሙ ካለና ሁኔታው ከፈቀደም ከወርቆቹና ከብሮቹ ጋር በመተባበር ቤታችንን ከሸክላና ከእንጨት ማጽዳት፡፡ ቤተ መቀደሴን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት አይደል ያለው ጌታ እየሱስ፡፡
እነዚህ አለቦታቸው ገብተው የተቀመጡ መንፈሳዊውን ሥልጣን ለአለማዊ ተግባር የሚያውሉ ከእውነተኞቹ አባቶች እየቀደሙ በተገኘው መድረክ ሁሉ እየታደሙ ምእምኑን የሚያሳቱ ናቸውና፤ በዮሐንስ መልእክት (1፣3፣17) “እንግዲህ እናንተ ወዳጆች ሆይ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ በአመጸኞች ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት አንዳትወድቁ ተጠንቀቁ”፡ተብሎ እንደተጻፈው ሰዎቹን ለይቶ ማወቅ፣አውቆም መጠንነቅ የምእምኑ ተግባር ይሆናል፡፡
“ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን በገበያም ሰላምታን፣ በምኩራብም የከበሬታን ወንበር፣ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ” ( የማርቆስ ወንጌል 12፣38/39)
ረዣም እድሜ ከጤና ጋር ለእውነተኛዎቹ የሀይማኖት አባቶች


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>