Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ዛሬ ከወደ ባህርዳር እውነት ተገለፀች |ከዘመድኩን በቀለ

$
0
0

“መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።”
የዮሐንስ ወንጌል 10፣11

“ጥልም በመስቀሉ ተገደለ”።
“ኤፌ 2፣16″።

በአባቶቻችን ዝምታ ተስፋ የቆረጥነው የእኛን አንገት ቀና ያደርጉ ፣ የህዝቡንም እንባ የጠረጉ ፣ የመረጣቸውና ለተለየ ክብርና አገልግሎትም የጠራቸውን ቅዱስ እግዚአብሔርንም ያስከበሩ ደገኛ አባት በባህርዳር ከተማ ላይ በመስቀሉ አደባባይ ዛሬ ተገልጠዋል ።

ዛሬ በባህርዳር ከተማ ላይ የቅድስት ተዋህዶ የእምዬ ኦርቶዶክስ ድምጽ ከፍ ብሎ ተሰምቷል ።
14502816_1836993936535481_7906889427951457037_n
የብዙ ሺህ ህጻናትን አንገት በመቅላት የሚታወቀውን ጨካኙን ሔሮድስን እንደገሰጸው እንደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የለ ድምጽ በባህር ዳር ተሰምቷል ።

የአባቶቼን ርስት አልለቅም በማለቱ ምክንያት ብቻ በወይን እርሻው ውስጥ በባለ ጊዜዎቹ ንጉሥ አክአብና ንግሥት ኤልዛቤል በሰማሪያ በግፍ የተገደለውን የምስኪኑን ናቡቴ ደም ህዝቡም እግዚአብሔርም እንዲመለከቱትና ፍርዱን እንዲሰጡት በመገዘት ጭምር ስለ ምስኪኑ ናቡቴ እንደ ጮኸው እንደ ነብየ እግዚአብሔር ኤልያስ ያለ ድምጽ ዛሬ በባህርዳር ተሰምቷል ።

ኢትዮጵያ እንደ አቡነ ጴጥሮስና እንደ አቡነ ሚካኤል ያለ ጨካኞችን ፣ ገዳዮችን የሚገስጽ ፣ እንደ አቡነ ጎርጎርጎሪዮስ ቀዳማዊ አይነት ገዢዎችን የሚጋፈጥና የሚሟገት አባቶችን ነበር ያጣችው ።

ዛሬ ግን ያን የፍርሃት ሰንሰለት የሚበጣጥስ ድምጽ ከባህርዳር ተሰምቷል ። ደፋሮችን ፣ ገዳዮችን ፣ እና ጨፍጫፊዎችን ከመፍራት የተነሣ የሃይማኖት አባቶች ዝም ቢሉ እንደ ነብዩ ኢሳይያስ በእግዚአብሔር መቀጣት ይመጣል ብለው የተረዱ አባት በዚህ ዘመን ተገኝተዋል ።

ዛሬ ከወራት በፊት መንግስትን ጥያቄ ለመጠየቅ ወጥተው ብዙዎች አካላቸውን እና ህይወታቸውን ባጡበት በአዲስ አበባው የመስቀል አደባባይ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ በብዙ ሺህ ወታደሮች ታጅበው በመምጣት በዓሉን ለማክበር በብዛት በአደባባዩ ለተገኙት የፌደራል ፖሊስ አባላት የ5 ዓመቱን የመንግስት ዕቅድና የልማት ስትራቴጂ እንደ አንድ ካድሬ ሲያቀነቅኑ ቢያመሹበትም ፤ በባህርዳር ግን አዲስ ታሪክ ተመዝግቧል ።

እኚህ ሰው በቀደመ የምንኩስና ስማቸው አባ ቃለ ጽድቅ ይሰኛሉ ። በመርካቶ የሚገኘው የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ያደረጉ ፣ ኋላም ለማእረገ ጵጵስና ደርሰው አቡነ አብርሃም ተብለው ከተሾሙ በኋላ በሰሜን አሜሪካና ከዚያም ተመልሰው በምስራቅ ሐረርጌ አሁን ደግሞ የምእራብ ጎጃም ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን እያገለገሉ ያሉ አባት ናቸው ።

ዛሬ በባህር ዳር ህዝበ ክርስቲያኑ መግደል የማይሰለቻቸውና የሰው ደም በአደባባይ ሲፈስ የሚያረካቸው የአግአዚ ጦር የሰውን መሰባሰብ አይቶ ደግሞ እንደለመደው በስናይፐር ንጹሐን ዜጎችን እንዳይለቅመን በማለት ብዙዎች ከቤታቸው ቀርተዋል ። ነገር ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ግን የመጣው ይምጣ ብለው በቆራጥነት ወደ መስቀል አደባባይ ሄደው ነበር ።

በእለቱ የሚፈጸመው የጸሎትና የዝማሬ መርሀግብሮች ከተፈጸሙ በኋላ ግን ለቃለ ምዕዳኑና ለቡራኬው ወደ ዓውደ ምህረቱ የቀረቡት አባት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ አቡነ አብርሃም ነበሩ ።

ብፁዕነታቸው የክርስቶስን መስቀል በቀኝ እጃቸው ይዘው በትከሻቸው ስናይፐርና መትረየስ በያዙት ወታደሮች ፊት ቆመው እንዲህ አሉ ።

👉ሁል ጊዜ ችግር የሚፈጠር በመሪው እንጅ በተመሪው አይደለም፡፡ ሕዝብ መቼም ቢሆን ተሳስቶ አያውቅም፡፡ሕዝብ መቼም የችግር መንስዔ ሆኖ አያውቅም ። ቤተ ክርስቲያንም እንደዚያው። ሁሌም የችግር መንስኤ የሀገሪቱ መሪዎች ናቸው ። መንግስት ለህዝብ ጩኸት መልስ አይሠጥም… መንግስት አዎንታዊ መፍትሄ እስካልሠጠ ድረስ ደግሞ ህዝብ ጩኸቱን አያቆምም.።

👉 የህዝቡ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡

👉ወታደር ከዚህ በኋላ የሰላምን ምላጭ እንጅ የመሳሪያን ምላጭ መሳብህን አቁም፡፡

👉በስደት ያለው ወገናችን ወደ ሀገሩ መመለስ አለብት፡፡ ስደት ይብቃ

👉 ”..እናንተ ጋዜጠኞች ደግሞ ሁሌም ቃለመጠይቅ ታደርጉልናላችሁ፤ መርጣችሁ ምታስተላልፉት ግን እኛን ከህዝቡ ጋር የሚያጋጭ ነገር ነው። ህዝቡ የሃይማኖት አባት የለንም ብሎ እንዲያስብና ተስፋ እንዲቆርጥብን ከሆነ የምትፈልጉት ወደፊት እንድትቀርፁን ምንፈቅድላችሁ አይመስለኝም ። ለዛሬ ግን ችግር የለውም ነፃ ናችሁ።

👉ያለ በደላቸው የታሠሩት ወንድሞቻችን መፈታት አለባቸው፡፡

👉ጠላትን እንዳላንበረከኩ አባቶቻችን ፤ዛሬ ለምን እርስ በእርስ ተከፋፈልን?

👉 የተሸከምነው መሳሪያ ከክርስቶስ መስቀል አይበልጥም፡፡

👉ወታደሮችና ድንበር ጠባቂዎች ሆይ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ስለእናንተ ስለምትጸልይ የሷ ልጆች ናችሁና ደም አታፍሱ፡፡

እውነት ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘወትር በቅዳሴዋ የሀገር ድንበር ለሚጠብቁ ወታደሮች ትጸልያለች ። የዘመናችን ወታደር ጠላት የሚመጣበትን ድንበር መጠበቁን ትቶ በከተማ የሚጸልይለትን ስንቅ የሚያቀብለውን ደሞዝም የሚከፍለውን ባዶ እጁን ያለ ወገኑን በአደባባይ የሚገድል ሆነ እንጂ ።

ይህን ሁሉ በህዝቡ ጆሮ አፍስሰው ከጨረሱም በኋላ ህዝቡ ወደ ቤቱ ሳይገባ እኔ ወደ ማረፊያዬ አልሄድም በማለት በመጨረሻ ህዝቡ ሁሉ ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ ወደ መንበረ ጵጵስናቸው ሄደዋል ።

ለማንኛውም ዛሬ ቅድስት ቤተክርስቲያን ደስ ብሎአታል ። ነገ የሚፈጠረው ባይታወቅም ለዛሬ ብፁዕነታቸው በሰላም በዓሉ ፍጻሜ እንዲያገኝ አድርገዋል ።

በነገራችን ላይ በቅርቡ ሌላም የምስራች ይኖረናል ። የግብጽ መንግስት በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ መከራ በማብዛቱ ምክንያት ሁሉን ጥለው አቡነ ሺኖዳ ወደ ገዳም እንደ ተሰደዱት ሁሉ በቅርቡም ይህን ታሪክ ለመድገምና ቀሪ ዘመናቸውንም በዚያ ለማሳለፍ የወሰኑ ሊቀ ጳጳስ መኖራቸው መረጃው ደርሶኛል ።

ሰላም ለኢትዮጵያ ሰላም ለሀገራችን !!

ዘመድኩን በቀለ ነኝ
መስከረም 16/2009 ዓም


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>