(ዘ-ሐበሻ) በ እስራኤል ሐገር የሚገኘው የኢትዮጵያን እናድን ማኅበር በቴላቪቭ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፃፈው ግልጽ ደብዳቤ በሳኡዲ አረቢያ የወገኖቻችንን እልቂት ለማስቆም 8 ጥያዊዎች በአስቸኳይ እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ። “የኢትዮጵያ መንግስት ፈጥኖ ለዜጐች ማድረግ የሚገባውን ህይወትን የማትረፍ ተግባር ባለማከናወኑ እስከዛሬ ከተገደሉና የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው በተጨማሪ ቁጥራቸው ከ35000 /ሠላሳ አምስት ሺህ/ በላይ የሚሆን በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ ወገኖቻችን ህይወታቸው ለአደጋ ተጋልጦ ይገኛል።” ሲል ለኢምባሲው ደብዳቤ የጻፈው ማህበሩ ደብዳቤውን ቀጥሎም “ስለሆነም አንድን ሃገር እመራለሁ የሚል መንግስት ቀዳሚ ተግባሩ የሀገርንና የሚመራውን ህዝብ ሁልንተናዊ ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ብሔራዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ እውነታ በመነሳት ከዚህ በታች ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች በአስቸኳይ ለኢትዮጵያ መንግስት በማሣወቅ ወገኖቻችን ከተደቀነባቸው የሞት አደጋ ይተርፉ ዘንድ ኤንባሲው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እንጠይቃለን።” ይላል።