ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሽ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን መካከል የተወሰኑትን በጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በኩል አነጋግሯል። ዘ-ሐበሻ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ እንደወረደ አስተናግዳዋለች፦
ስምሽ ማን ነው?
ፀጋ ኪዳኔ ገብረኪዳን
ምን እየጠበቅሽ ነው?
ዘመድ አለችኝ አዲስ አበባ የምትኖር፤ እስዋ እስክትመጣ እየጠበቅሁ ነው፡፡
ሳኡዲ ምን ያህል ጊዜ ቆየሽ?
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ነው ከሪያድ/ሞንፋ የመጣሁት፡፡ ከኢትዮጵያ ስሄድ በኮንትራት ቢሆንም በባህር ከሄዱት ስደተኞች የተለየ ክብር አላገኘሁም፡፡ ጭቅጭቅ፣ ስድብና ድብደባ ሲበዛብኝ ከተቀጠርኩበት ቤት በስምንተኛ ወሬ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ የሄድኩት ለአንድ ስራ ብቻ ተዋውዬ ነበር። የምተኛው ግን ከሁለት ሰዓት አይበልጥም ነበር፡፡ ሥራ ብቻ ነው 24 ሰዓት!
እስቲ ስለደረሰብሽ ችግር በዝርዝር ንገሪኝ..
በ700 ሪያድ ተቀጥሬ ነበር ከዚህ የሄድኩት፡፡ አሰሪዬ ቤት አራት ትላልቅ ወንድ ልጆች አሉዋት። የእህትዋ ልጆችም እዚያው ነው የሚኖሩት፡፡ ‹‹ወሲብ ካልፈፀምን..›› ብለው ያስቸግራሉ፡፡ በጣም ተሰቃየሁ፡፡ ከአቅሜ በላይ … ለህይወቴ በጣም አስፈሪ….ሲሆንብኝ ወጣሁ፡፡ ከአቅሜ በላይ ስትይ …
ልጆቹ ወሲብ ካልፈፀምን ብለው አሻፈረኝ ስላቸው፣ “በቢላ እናርድሻለን” እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ እምነቴን እንድቀይር ሁሉ ይፈልጋሉ። አፈር ድሜ በላሁ፡፡ ሰርቼ ለፍቼ … በዚያ ላይ ነፃነት አልነበረኝም፡፡ ወገቤ፣ ዓይኔ ታመመ፡፡ እነሱ እኮ ሃያ አራት ሰዓት እየበሉ እየጠጡ ነው፡፡ በዚያ ላይ በእጅሽ ላይ ስልክ ማየት አይፈልጉም፡፡ ሁሉ ነገር ሲያንገፈግፈኝ ሁለት ወር የሰራሁበትን ገንዘብ ጥዬ ወጣሁ፡፡ ከዛ ኤጀንሲው ለሌላ ሰው ሸጠኝ፤ በአስር ሺህ ሪያድ፡፡ እዚያም ግን አልተመቸኝም። ስራው ሃያ አራት ሰዓት ነበር፡፡ አምስት ሰው እንኳን የማይችለው ስራ ነበር፡፡ አንድ ኩንታል ሊጥ አብኩቼ፣ ለሱቅ የሚሸጡት ብስኩት ጠብሼ፣ ሰባት መቶ ሪያል ነበር የሚከፈለኝ፡፡ ሁለት ወር ሙሉ እንደምንም ድምጼን አጥፍቼ ሰራሁ… በእንቅልፍ እጦት ልወድቅ እየተንገታገትኩ፡፡ እፊታቸው ላይ ግን ደስተኛ እመስል ነበር፡፡ ሰውነቴ እየመነመነ መጣ፡፡ ይሄኔ ድጋሚ ለመጥፋት ተዘጋጀሁ፡፡
“ለሌላ ሰው ሸጠኝ” ያልሽው … ኢትዮጵያዊ ነው?
/እንባዋ እየፈሰሰ/አረብ ነው፡፡ ወደ ሳኡዲ ከላከኝ ኤጄንሲ ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ የረመዳን ጊዜ ደግሞ ሱቃቸው ወሰዱኝ፤ የአንድ ሰዓት መንገድ ተጉዞ ሌላ ቤት አላቸው፡፡ እዛ ይዘውኝ ሲሄዱ ስራ ይቀልልኛል ብዬ ነበር፡፡ … ግን የባሰ ሆነብኝ፡፡ ለካ ጓደኞቻችን ወደው አይደለም ራሳቸውን የሚያጠፉት፤ አብደው ጨርቃቸውን ጥለው በየጎዳውና የወጡትና መንገዱ የወደቁት … የወገብና የአእምሮ በሽተኞች የሆኑት? “ምነው እናቴ ስትወልጅኝ በመሃፀንሽ ውስጥ ደም ሆኜ በቀረሁ? እናቴ እባክሽ መልሰሽ ዋጪኝ” አልኩኝ፡፡ ራሴንና ቤተሰቤን ልረዳ ስንገታገት ከፊታቸው ድፍት ብል እኮ … እንደሰው ከቆጠሩኝ … ሬሳዬን ለእናቴ ይልኩላት ይሆናል፡፡ ያለዚያ ግን የሀገራቸው መንግስት አውጥቶ ይቀብረኛል፡፡ ከዚያ ሁሉ በፊት ጠፍቼ መውጣት እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ አንድ ቀን ረመዳን ካፈጠሩ በኋላ ቤተሰቡ ተሰብስቦ ሊዝናኑ ወጡ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ቶሎ ብዬ የሴትየዋን ሙሉ ልብስ ለብሼ፣ ሽፍንፍን ብዬ ወጣሁ፡፡
ሻንጣ ምናምን ሳትይዢ?
ባዶ እጄን ነው የወጣሁት፡፡ የሰራሁበት ገንዘብ እንኳን በእጄ የለም፡፡ በቃ ዝም ብዬ ወጣሁ፡፡ ፓኪስታናዊ የታክሲ ሾፌር አገኘሁ፡፡ ‹‹ምን ሆንሽ?›› ብሎ ሲጠይቀኝ በዝርዝር ነገርኩት፤ አዘነ፡፡ ‹‹ሪያድ የሀበሻ ሃገር ነው፤ ብዙ ኢትዮጵያዊ አለ›› ብሎ እዛ (በነፃ) ወሰደኝ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን አገኘሁ፡፡ እዚያ መኖር ጀመርሽ ማለት ነው?ሳያቸው በጣም ነው ያለቀስኩት፡፡ አገሬ የገባሁ ይመስል..መሬት ሁሉ ስሚያለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ በባህር (በህገወጥ መንገድ) የመጡ ሴቶች ነበሩ። ከእነሱ ጋር አንድ ቤት በስድስት መቶ ሪያድ ለስድስት ወር ተከራይተን አብረን እየኖርን እንሰራ ጀመር፡፡
ቤቱን ለስንት ተከራያችሁ?
አስር ነበርን፡፡ ሁለት ወር እንደሰራሁ ግን በአካባቢው ግጭት ተነሳ፡፡ እግሬ አውጪኝ ብለን በየፊናችን ተበታተንን፡፡
ምን ዓይነት ግጭት?
መንግስት የሌለበት አገር ይመስል ጐረምሶች በር እያንኳኩ በሽጉጥ፣ በካራ፣ ሰው መግደል ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ‹‹እጃችንን እንስጥ›› ብለን ተማከርን፡፡ ሌላው ችግር ፖሊስ፤ ትዳር መስርተው የሚኖሩትን የአበሻ ወንዶች እየወሰደ፣ ሴቶችን ለብቻቸው ይተዋቸው ነበር፡፡ በቤቱ ወንድ አለመኖሩን የተገነዘበ የአገሩ ዱርዬዎች (እንኳን ለአበሻው ለመንግስትም ልባቸው ያበጠ ነው) ሴትዋን ለአራትና ለአምስት እየሆኑ መድፈር ያዙ፡፡ ከእኛ ጎን የነበሩትን ሲያሰቃይዋቸው አይተናል፡፡ ወንዶቹን ፖሊስ ሲወስዳቸው ጎረምሶቹ ተከትለው ይገቡና ሴቶቹን መጫወቻ ያደርጓቸዋል/ለቅሶ/፡፡ አንድ ያየሁትን ልንገርሽ../ረጅም ትንፋሽ/ እነዚህ ጐረምሶች…ሶስት ሴቶች ያሉበት ክፍል ውስጥ ገብተው ለሰባት ደፈሯቸው፡፡ /ማውራት አልቻለችም፤ ሳግና እንባዋ እያቋረጣት/..ከሶስቱ አንዷ የሰባት ወር ነፍሰጡር ነበረች፤ ሲገናኝዋት ሞተች፡፡ አንዷን ደግሞ ለሰባት ደፈሯትና ገድለው ጥለዋት ሊወጡ ሲሉ ሽርጣ/ፖሊስ መጣ፡፡ ከፖሊስ ጋር ተኩስ ገጥመው እርስ በርስ ተገዳደሉ፡፡ የሀበሻ ወንድ ከእህቱ ወይንም ከሚስቱ ሊለዩት ሲመጡ አልለይም ይልና ይገደላል፤ ይደበደባል … በቃ እልቂት ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ ብለሽ ካራ ቆሬ እንደምትይው..ሪያድ ብለሽ ሞንፋ የሚባል አካባቢ በርካታ አበሾች ይኖራሉ፡፡ እኔ እንኳን የማውቀው … ከአምስት በላይ ሴቶች እንደተገደሉ ነው፡፡ መላ አካላቸውን ቆራርጠው ነው የጣሏቸው፡፡ ግን ይሄ ሁሉ መከራ ምን አድርገን ነው?
አንቺ እንዴት መጣሽ ወደ አገርሽ?
እጄን ሰጠኋ፡፡ አሰሪዬ ‹‹የት ልትሄጂ ነው?›› ብላ ስትጠይቀኝ፡፡ ‹‹አንድ ጓደኛዬ ልትወልድ ነውና ልጠይቃት ..›› ብዬ የሰራሁበትንም ሳልቀበል ወጣሁ፡፡ ምክንያቱም ብትገለኝስ ብዬ ፈራሁ፡፡ አብዛኛው አበሻ ከስራ ወደቤቱ ሲሄድ እየተያዘ ነው የሚመጣው፡፡ የሰራበትን የለፋበትን ሳይዝ ባዶ እጁን፡፡ እና እኛም ነገሩ ስላስፈራን እጃችንን ሰጠን። በቃ እኔም ወደ እዚህ መጣሁ፡፡
ዛሬ ላይ ሆነሽ ስታስቢው ወደዛ በመሄድሽ ምን ይሰማሻል?
መጀመሪያ ከዚህ ስሄድ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፤ የራሴንና የቤተሰቤን ህይወት ላሻሽል እንደሆነ ተስፋ በማድረግ፡፡ ከዛ በኋላ ግን ከስራው ብዛት የተነሳ ከጥቅም ውጪ ልሆን ነው ብዬ እጅግ አምርሬ አለቅስ ነበር፡፡ በጣም ስጋት ያዘኝ፡፡ ግን ከሞት ተርፌ ወደዚህ ስመጣ አምላኬን አመሰገንኩ፡፡
ቤተሰብሽ መምጣትሽን አውቀዋል?
አላወቁም፡፡ ምን እያሰቡ ይሆን? ይሄን ሁሉ ነገር እየሰሙ፡፡ እናቴ መንገድ መንገድ እያየች ይሆናል፡፡ ደሞ ከእኛ አካባቢ ልጆች ብዙ የሞቱ አሉ፡፡..አሁን እኔ ራሴ የሁለት ሰው መርዶ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ እናቴም ሰው ሲመጣ ‹‹ልጄን አይታችኋል?›› ትል ይሆናል፡፡ እኔስ መጣሁ..በረሃ ላይ ተደፍተው ለመምጣት ወረፋ እየተጠባበቁ ያሉ ህጻናትና ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ እዚህ የመጣነው እኮ ግማሽ አንሞላም፡፡ በሳኡዲ የኢትዮጵያውያን እንባ ያሳዝንሻል፡፡ ብዙዎቹ በሃዘን ላይ ናቸው፤ ድረሱላቸው፡፡
↧
“ነብሰ ጡሯን አስገድደው ሲደፍሯት ሞተች..”–ፀጋ ኪዳኔ (ከሳዑዲ ተመላሽ ኢትዮጵያዊት –ቃለምልልስ)
↧