ከኢሳያስ ከበደ
በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ አፈ ቀላጤ የሆኑት አቶ ፀሐዬ ደባልቀው በአደባባይ ሲዋሹ እጅ ከፍንጅ ተያዙ። አቶ ጸሐዬ ደባልቀው በጠራራ ፀሐይ ሲዋሹ የተያዙበት መረጃ የወያኔን ላለፉት ሃያ ዓመታት ውሸት በይፋ ያጋለጠና ለስርዓቱም ክስረት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች እየተናገሩ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው – ሰሞኑን በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ስቃይ የተቆጡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሃገራትና ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ኢትዮጵያውያኑ ወያኔን የሚቃወሙ የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው እንደነበርም ይታወሳል። ታዲያ ከተደረጉት ሰልፎች መካከል አቶ ጸሐዬ ደባልቄ የተጋለጡበትና ለሥርዓቱም ኪሳራ ነው የተባለለት ጉዳይ በላስቬጋስ እና በዋሽንግተን ዲሲ የተደረጉ ሰልፎች ፎቶ ግራፎች ናቸው። አቶ ጸሐዬ ሃገር ቤት ቴክኖሎጂው ሁሉ በወያኔ አፈና ስለተዘጋ የኢትዮጵያ ህዝብ መረጃውን አያገኝም በሚል በፎቶ ሾፕ እና በቪድዮ ኤዲቲንግ የለመዱትን የውንጀላ ተግባር እዚህም እንዲያው መስሏቸው ትግራይ ኦንላይን በተሰኘ ዌብ ሳይት ላይ በላስ ቬጋስ ኢትዮጵያውያን ይዘውት የወጡትን መፈክር በፎቶ ሾፕ ቀይረው የኢሳያስ አፈወርቂ ፎቶ በማስገባት ሕዝቡን ለማሳሳት ከመሞከራቸውም በላይ የኢሳያስን ፎቶ ግራፍ ያልያዘ ልጅ እንደያዘ አስመስለው በመስራት በሕግ የሚያስጠይቅ የሚያዋርድ ሥራ ሰርተዋል። ይህ የሚያዋርድ ብቻ ሳይሆን በሳዑዲ ባለቁት እና እየተሰቃዩ ባሉት ዜጎች ላይም መቀለድም ጭምር ነው። በላስቬጋሱ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያዊው የያዘው መፈክር በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ መዘጋቱን የሚገልጸውን ደብዳቤ ሲሆን አቶ ጸሐዬ በኢሳያስ ፎቶ በመቀየር “ወያኔ በቃን” በሚል ተሰላፊው ኤርትራዊ ወይም የኤርትራ ደጋፊ ለማስመስል ሲሞክሩ ተዋርደዋል። ሌላው ውሸታቸው ይህን ፎቶ ልክ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ እንደተደረገ አድርገው ሲያቀርቡት ፎቶ ግራፉ ግን የተነሳው ላስቬጋስ ላይ መሆኑ በጠራራ ጸሐይ የወያኔን ውሸት አጋልጦ ስርዓቱን ሸንካላ የፕሮፓጋንዳ ባለሙያዎች እንዳሉት አሳይቶናል። ሁለቱንም ፎቶ ግራፎች ይመልከቱና በወያኔዎች ይሳቁባቸው፦