በፓትሪያርክነት ከተሾሙ በኋላ ለመጀምሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ የመጡት አቡነ ማቲያስ አብረዋቸው ከኢትዮጵያ ከመጡ አገልጋዮቻቸው መካከል አንዱ የሆነው ዲያቆን አሁን ደረሰ እዚሁ አሜሪካ ጠፍቶ መቅረቱን የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች ገለጹ።
የፓትሪያርኩ ልዩ ቪድዮ እና ፎቶ ግራፍ አንሺ እንደሆነ የሚነገረውና ለሳቸውም ከፍተኛ ቀረቤታ እንደነበረው የሚነገርለት ዲያቆን አሁን ደረሰ አቡነ ማቲያስ በሰሜን አሜሪካ ለ10 ቀናት ለጉብኝት በመጡበት ጊዜ ፓስፖርቱ እና ሁሉ መረጃዎቹ ተይዘውበት የነበረ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ ላለመመለስ እንደጠፋባቸው ተገልጿል።
ምንጮቻችን እንደሚሉት ዲያቆን አሁን ደረሰ አቡነ ማቲያስ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አብሯቸው ያልተመለሰ ሲሆን እስካሁን በምን ዓይነት ምክንያት ጥገኝነት ይጠይቅ አይጠይቅ የታወቀ ነገር የለም። ከፓትርያርኩ ጋር አብረው ከአዲስ አበባ የመጡት ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለሱ ድረስ ፓስፖርታቸው ተይዞባቸው እንደነበር የገለጹት ምንጮቹ ዲያቆን አሁንን በምን ምክንያት የሃገር ቤቱን ሲኖዶስ ጥሎ በአሜሪካ ሊቀር እንደቻለ ለማነጋገር እንደሚሞክሩ ቃል ገብተዋል።