(ሪፖርተር) የይድነቃቸው ተሰማ ሌጋሲ እንዲቀጥል የኢሕአዴግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ አቀረበ
ከሁለት ዓመታት ወዲህ እመርታን ያሳየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከአገር አልፎ በአህጉር እንዲሁም በዓለሙ መድረክ ትኩረት የሳበው ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ የአፍሪካን ዋንጫ መቀላቀሉ ብቻ አይደለም፡፡
በመጪው ሰኔ ብራዚል በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ከሚወክሉት አምስት አገሮች አንዱ ለመሆን ከተፋለሙት 10 ምርጥ ቡድኖች አንዱ መሆኑ ጭምር ነው፡፡ በወሳኙ ምዕራፍ በደርሶ መልስ ውጤት በናይጄሪያ 4ለ1 (2ለ1 እና 2ለ0) ቢረታም፣ በአጨዋወቱ ብዙኀኑን ሲያስደምምና ቁጭ ብድግ ሲያደርግ ከርሟል፡፡ ተልዕኮውን ባለፈው ቅዳሜ በናይጄሪያዋ ካላባራ ከተማ በመጫወት ያጠናቀቀው ብሔራዊ ቡድን አዲስ አበባ በተመለሰ በማግስቱ ኅዳር 9 ቀን ምሽት በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በተደረገ ልዩ ዝግጅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንንና ከፍተኛ ሹማምንት በተገኙበት የ2.7 ሚሊዮን ብር ሽልማት ለተጫዋቾቹና ለቡድኑ አባላት ተበርክቶለታል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ዋሊያዎቹን በማወደስ የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፣ በኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ስፖርትና ኦሊምፒክ መድረክ ሁነኛ ስፍራ የነበራቸው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የሄዱበትን ርቀት፣ ያሳለፉትን ሌጋሲ [ውርስ] ትውልዱ እንዲቀጥልበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከተጫዋቾቹና አሠልጣኞቹ ጋር ፎቶግራፍ የተነሱት ከቆሙት በስተግራ የስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አምበሳ እንየው፣ የኢሕአዴግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ ከኋላ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ፣ ከፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋር ተጨባብጠው፤