በአበራ ሽፈራው /ጀርመን/
በአረቡ ዓለም ከፍተኛ ተሰሚነትና የመላው ዓለም አይን ሁሉ በተለየ መልኩ በሚያያት ሳውዲአረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ግፍና መከራ ለትውልድ የማይረሳ ክፉ ታሪክ ጥሎብናል ፤ ዛሬም ሰቆቃው ቀጥሏል፡፡
ድረሱልን የሚለው የወንድሞቻችንና በተለይም የእህቶቻችን ጩኸት በእየቀኑ ከዚህች የሳውዲ አረቢያ ከተማዎች ለብዙሃን መገናኛዎች እየጎረፈ ይገናል። አልታደልንምና የእኛዎቹ ጉልበተኛ መሪዎች ይህንን እኩይ የሳውዲ አረቢያን ተግባር ከመኮነን ይልቅ በአገር ውስጥ ሌላ ተጨማሪ ሃዘንን የሚፈጥሩ የቃላት፣ የዱላንና የእስርን ጉዳይ በግልና በጅምላ ተያይዞታል ።
ሳውዲዎች እየጎዱንም ያሉት በብሄራችን አይደለም፣ በቋንቋችንም አይደለም፣ በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ ነው ። ዛሬ ወደአይምሮአችን እንመለስ፤ ለማሰብ እንነሳ፤ በቋንቋችንና በብሄራችን እየከፋፈለ በግልና በቡድን የሚያጠቃን ህወሃት ብቻ ነው፤ አሁንም ትንሽ ቆም ብለን እናስብ።
የኢትዮጵያ ሳይሆን የጥቂት ጎጠኛና ጉልበተኛ ቡድን ብዝበዛናንና ጭቆናን ለመጠበቅ ሲባል በኢትዮጵያ ህዝብ ደምና ላብ ከሽጉጥ እስከ ተዋጊ አይሮፕላን የታጠቀው ወታደራዊ ሃይልና የፌደራል ፖሊስ በሚል የሚጠራው ኃይል ከቆመጥ እስከ ካራቴ ሲያልፍም በጥይት በራሱ ወገን ላይ ድብደባንና ግድያን ሲያደርስ መመልከት በአገሩ ያልተከበረ ህዝብ እንዴት በውጭዎች ይከበራል? እጣ ፋንታችንም በአገራችን ውርደት፤በውጭ ሃገራትም ውርደት ሆኗል።
ከሳውዲዎች ጋር የሰው ዝውውር/Human Trafficking/ና የንግድ ትሥሥርን የፈጠሩት ህወሃቶች በወኪላቸው ሺህ መሐመድ አላሙዲን እና በሌሎች የህወሃት የንግድ ሰዎችና በኢትዮጵያውያን ስም በአረቡ አገራት ኢንባሲዎችና ቆንስላዎች በተቀመጡ የህወሓት ወኪሎች አማካኝነት የሰውን ዝውውርን በንግድ ትርፍነት ይዘው የሚጠቀሙበት መሆኑና ለዚህም በማስረጃነት በዚሁ የድለላ ሥራ የተሰማሩት ብዙዎቹ የህወሃት ሰዎች መሆናቸውና በሃዋላ መልክ በእነዚሁ ጭቁን እህቶቻችን የሚላኩትንም ገንዘቦች ዝውውር የሚፈጸመው በነዚሁ ሰዎች መሆኑ ፤ በቅርቡም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እህቶቻችንን በተመሳሳይ መልክ ለመላክ ተዘጋጅተው የነበሩ መሆኑ፤ ከዚህም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችንና ልዩ ልዩ የንግድ ተቋማትን የያዙት የሳውዲ ሰዎች ዛሬ ህወሃትን ባይተማመኑና በህወሃት አንባገነንዊ ሥርዓት ሥር መውደቃችንን ባያውቁ ኖሮ እንዲህ ባልተጠቃን ነበር ።
እነዚህ ሃገራችንንና ህዝባችንን የሚበዘብዙና የሚያዋርዱ ኃይሎች ይባስ ብለው በአገራችን ተቃውሞ እንዳይደረግ ለመከላከል መዘጋጀታቸውና ህዝቡን በዱላ መደብደባቸው፣ ማሰራቸውና መቀጥቀታቸው ቢያሳዝንም ዛሬ ወደአይምሮአችን እንድንመለስና ህወሃት ከዚህ በላይ ምን እስኪያደርገን እንደምንጠብቅ እንድናስብ ይጠበቅብናል።ግልጽ የአገራችንና የህዝባችን ጠላቶች ህወሓቶች መሆናቸውን ያለፉት 22 ዓመታት የህወሃት ድርጊቶች ምስክሮቻችን ናቸው ።
ለእውነቱ ከሆነ በዓለም ሁሉ ሁሌም በተቃውሞ ሰልፍ እንታወቃለን። አሁን ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍና መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገው ሰልፍ ተገቢና መቀጠል እንዳለበትና ሰልፎቹም ግቦቻቸውን ሊመቱ በሚችሉበት ሁኔታና በተጠና መልኩ መቀጠል እንዳለባቸው ግን አምናለሁ። አዋጩ መንገድ ግን ለዘለቄታው ማሰብና ተግባራዊ እንቅስቃሴን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው አለም መፍጠርና ለተግባራዊነቱ ለመነሳት መመካከር ይመስለኛል፤ ደግሞም ነው ብዮም አምናለሁ፤ የተጀመሩም ካሉ እንዲበረታቱ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል ።
በህወሓቶች መሰሪ ተንኮል መለያየትን በህዝቦች መካከል በመፍጠር በፍጹም አምባገነናዊ ሥርዓት እንድንተዳደር የተደረግንበትን የህወሃቶችን እኩይ ተግባርን አሁንም ለመቀልበስ እንድንችል ወደአይምሮአችን እንመለስ።
የሃገሬ ወጣቶች ፣ የተማራችሁ ኢትዮጵያውያን፣ ገበሬው፣ ሰራተኛው፣የሃይማኖት ተቋማትም ሁሉ ለእውነት ልትነሱና ፍትህን ልትናገሩ፣ ሁላችን እውነትን ልንጋፈጥና ለእውነት መስዋዕት ልንሆን፤ በወደፊትም የአገራችን እጣፋንታ ላይ ልንነሳና ይገባናል።
የኢትዮጵያ ወታደሮችና ፖሊሶች እየተባላችሁ ለጥቂት የህወሃት በዝባዥና ዘረና ኋይሎች በመሳሪያነት የምታገለግሉ የኢትዮጵያ ልጆች ለህዝባችሁ ወገንተኝነታችሁን ለማሳየት ወደአይምሮአችሁ ተመለሱ ፤ ተገቢውን ተቃውሞ በማሰማት ባለታሪክ እንድትሆኑና ለዚህም መልስ ለመስጠት ከወገኖቻችሁ ጋር እንድታብሩ እመክራለሁ። ካልሆነም ግን ጊዜ ሊፋረዳችሁ ከፊታችን ቀርቧል።
በልዩ ልዩ የኢሕአዴግ ፓርቲዎች ውስጥ ሆናችሁ በህወሃት በዝባዦች ውክልናን ተቀብላችሁ፤ህዝቡን ለመጨቆን እንደመሳሪያነት የምታገለግሉና የምታሰቃዩ፤ ወደአይምሮአችሁ ተመለሱ ወደህዝቡም ትግል ተቀላቀሉ፤ የሰውም የአምላክም ፍርድ ከፊታችሁ መጥቷል አመናችሁም ጠላችሁም የህዝቡ እንባ ለፍርድ ወጥቷል።
በልዩ ልዩ ሃገራት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ኢትዮጵያን ወክላችሁ በስራላይ ያላችሁና ይህንን የኢትዮያውያንን መከራ አይናችሁ እያየ እንዳላየ የምትሆኑ ሁሉ አሁን ከኢትዮጵያውያን ትግል ጎን ለመሰለፍና ለመወሰን ወደአይምሮአችሁ ተመለሱ። ብዙዎቻችሁ የህዝባችንን፣ የአገራችንንና የወገኖቻችንን ጥቅምና ተስፋዎች ለህወሃት አሳልፋችሁ በመስጠት ሁሌም ህዝብን እንደበደላችሁ የሚሰማችሁ ፤ የህዝቡ መከራ የሚያንቀጠቅጣችሁ ሁሉ ዛሬ ወስኑ፣ አቅዱ፣ ተግብሩ፤ በቃ! ከህወሃት እኩይ ተግባር ተባባሪነት እራሳችሁን እግልሉ ። ሰውም አምላክም ይቅር ይላችኋል፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ለይቅርታ የተዘጋጀ ነውና ቁረጡ። ቸር ይግጠመን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
aberashiferaw.wordpress.com