አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
አርብ ሐምሌ ፲ ፭ ቀን ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት
በሀገራችን ያለውን ፀረ-ኢትዮጵያ ወራሪ ቡድን ከሥልጣን ለማውረድና የፖለቲካ ሀቁን ለመቀየር፤ በትግሉ የተሰማራን ብዙ ድርጅቶችና ግለሰቦች አለን። እያንዳንዳችን ድርጅትም ሆነ ግለሰቦች፤ የየራሳችን የሆነ እምነትና ዓላማ ሰንቀናል። በጠላትነት ተጋርጦ ያለው፤ የአንድ አካባቢ ነፃ አውጪ ግንባር ሲሆን፤ ይህ ነፃ አውጪ፤ ከራሱ አካባቢው ወጥቶ፤ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ዘመቷል። እናም ሀገሪቱን ወሮ እየገዛ ያለ መንግሥት ነው። ይህ ወራሪ መንግሥት፤ ወገንተኛ ከመሆኑም በላይ፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ በጠላትነት ፈርጆ፤ በዘር ማጥፋት በሚያስወለጅል ደረጃ እየጨረሳቸው ነው። ታዲያ ተጋዮቹ በአንድነት ለመታገል አለመቻላችን፣ ትግሉን ወደፊት ካለ መግፋታችን በላይ፤ መታገል ለሚፈልገው ወገን ችግር ፈጥረናል።
ችግራችን ምንድን ነው? በግልጽ ብንነጋገር፤ ሕዝባዊ ትግል ሠልጥነው ሥራ የሚይዙበትና የሚፈለግ ሙያ አይደለም። ሕዝባዊ ትግል ፈልገውት የሚመጣና የሚወደድ ክስተት አይደለም። ሕዝባዊ ትግል፤ ግድ ብሎ በሕዝብ ላይ የሚጫን፤ ከይስሙኝ እባክዎ ልመና ቀጥሎ፣ የለም ይሄ መሆን የለበትም ብሎ ከመቃወም ቀጥሎ፣ ከእምቢዮ አሻፈረን ይሄ አይደረግም ጉርምርምታ ቀጥሎ፣ አይ አሁንስ በዛ ብሎ ከማንጓጠጥ ቀጥሎ፤ አንገቴንስ ተኝቼ አላሳርድም ብሎ ሕዝቡ ለሞትና ሽረት የሚነሳበት ጣጣ ነው። ሕዝባዊ ትግል፤ ሕይወት የሚጠፋበት፣ ንብረት የሚወድምበትና ሀገር የሚቆረቁዝበት ሀቅ ነው። በዚህ በከፍተኛ ደረጃ የተያዘ ትንቅንቅ፤ በስሌትና በዘዴ፤ ግብንና መስመርን በደንብ ለይቶ ባስቀመጠ ጎዳና መሄድ፤ ለስኬት ያበቃል። እናም ከፍተኛ ምርምርና እቅድ ግድ ይላል። በዘፈቀደ የሚኬድበት ጎዳና አይደለም።
በኛ በታጋዮቹ ዙሪያ ያለውን ስንመረምር፤ ለልዩነታችን ምክንያት የሆነው፤ የየድርጅቶቹ አፈጣጠር አይደለም። የየድርጅቶችም የትግል ዘመን ልዩነት አይደለም። የየድርጅቶችም የአባላት ብዛትና የንብረት ጥንካሬ አይደለም። የትግል ስልትም አይደለም። እኒህ ሁሉ ድርጅቶቹ በአንድ ተቀምጠው በውይይት ሊነጋገሩባቸው የሚችሏቸው ጉዳዮች ናቸው። ለኛ፤ የተለያዩ ድርጅቶች አብሮ ለመቀመጥ እንኳ ፈቃደኝነት አለመኖሩ፣ አብሮ ለመተባበር መቀራረብ መጥፋቱ፣ በትግል አንድነት ለመፍጠር አለመስማማቱ ምክንያት ብዬ የማቀርባቸው፤ ከላይ ከተዘረዘሩት የተለዩ፤ ሌላ ሶስት መሠረታዊ፤ ነገር ግን በግልጽ ያልታዩ ጉዳዮች አሉ። እኒህ የሚሽከረከሩት፤ ትግል ማስፈለጉንና አለማስፈለጉን በግልጽ ያስቀምጡልናልና ነው። እነሱም፤ የምንታገለው ማንን ነው? ታግለን እንዲከተል የምንፈልገው ግብ ምንድን ነው? እና ይሄንን ግብ በምን መንገድ ታግለን ልናገኘው እንችላለን? የሚሉት ላይ የምንሠጣቸው መልሶች ናቸው። በእነዚህ ላይ ስምምነት ካለን፤ በአንድነት መታገሉ የማያጠያይቅ ይሆናል።
ላስረዳ፤
በታጋዩ ክፍል ያለው የመጀመሪያው ችግር፤ “ማንን ነው የምንታገለው?” ባሁኑ ሰዓት ምን ዓይነት መንግሥት አለ? በሚለው ላይ፤ እያንዳንዱ ድርጅት ግልጽ የሆነ አቋም አለማስቀመጡ ነው። ይህ ማለት፤ አምባገነን፣ ወገንተኛ፣ ጠባብ፣ በማለት የምናልፈው አይደለም። ወይንም ደግሞ ይሄን የሚሠራ፣ ያንን የሚያደርግ ብለን በወንጀሉ ብዛት የምናስቀምጠው አይደለም። ይህ መንግሥት፤ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ የአስተዳደር መመሪያና የተግባር ታሪክ አለው። እናም ለጠቅላላ ሕይወቱ ባለቤት የሆነ ክፍል አለው። የዚህ ባለቤት ማነው? የትርታው እስተፋሽ ማነው? ተጠቃሚው ማነው? አራጋቢው ማነው? በመንግሥታዊ መዋቅሩ የተሰገሰገው ማነው? ማለት አለብን። ከዚህ ምንነቱ ተነስተን፤ ማንን ነው የምንታገለው በሚለው ላይ፤ ግልጽ የሆነ ዕይታ ይኖረናል።
እኛ የዚህን መንግሥት ምንነት ዕውቀታችን ጥልቀት የሌለውና ማስረጃ ቢስ ከሆነ፤ ምን ዓይነት ትግል እያካሄድን እንደሆን፤ ራሳችን አናውቀውም ማለት ነው። በተጨማሪም፤ በዚህ ላይ አንድ ዓይነት ግንዛቤ ከሌለን፤ ግባችን ብቻ ሳይሆን የተለያየ የሚሆነው፤ በመካከላችን አጥፊና ጠፊ አለ ማለት ነው። እስካሁን እንዳየነው፤ በትግል አዟሪት መጠመዳችን ነው። ይህ መንግሥት ይሄን አደረገ፣ ያን ጨመረ፣ እያልን ማላዘኑ በቂ አይደለም። ከዚህ ተነስተን ደግሞ፤ ይሄንና ያን እንዳያደርግ ይሁን! እያልን ልመና እንሄዳለን። ተከትሎም ይሄን ስላደረገ እንጣለው በሚል ያልተቀናጀ ርብርቦሽ ወደ ማድረጉ እያመራን ነው። ያ ሕዝባዊ ትግል ቀርቶ፤ በምንም መልኩ ትግል ተብሎ የሚፈረጅ አይደለም። ሩቅም አያስኬድም። ጠባብና የሥልጣን ሽኩቻ ሆኖ፤ አሁን ባለው የጠገበ ጅብ ቦታ፤ ሌላ የተራበ ጅብ ለመተካት የሚደረግ ሩጫ ይሆናል። አዎ! እስካሁን ያደረገው፣ አሁንም በማድረግ ላይ ያለውና ለመጪውም የሚያደርገው ግልጽ ነው። በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ግብ አለው። የግብ መንገድ አቅጣጫውን አሳምሮ ያውቃል። መንገዱን አበጅቷል። እያንዳንዱ የሚወስደው እርምጃ፤ ለሱ ዋና ግቤ ብሎ ከመጀመሪያው ለተነሳበት ዓላማና ለሚገነባው ሕንፃ፤ አንድ ጡቡ ነው። መንግሥታዊ መዋቅሩን እስከቻለ ድረስ ለጥጦ፤ አብዛኛውን ጊዜም ከልኩ በላይ፤ መጀመሪያ ለተነሳበት ዓላማ እየተጠቀመበት ነው። በሥልጣኑ ላይ የተቆናጠጡት ከሀገሪቱ ሀብት ጋር መተሳሰር፣ ራሳቸው ነጋዴዎች መሆናቸው፣ የትምህርቱ፣ የአስተዳደሩ፣ የጦር ሠራዊቱ፣ የደህንነቱ፣ የሃይማኖት ተቋማቱና የመሳሰሉት በመንግሥታዊ መዋቅሩ ያሉት ክፍሎች በሙሉ በዚሁ በሥልጣን ላይ ባለው አንድ ቡድን እጅ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ማገናዘብ አለብን። ስለዚህ ይሄን ቡድን ከሥሩ በአንድነት ፈትሾ በደንብ ማጥናቱ፤ ትክክለኛ ግብ ለመንደፍና ስኬቱ ያማረ የትግል መንገድ ለመቀየስ፤ የግድ አስፈላጊ ነው።
በተጨማሪ ደግሞ፤ ይህን ገዢ ቡድን፤ ከሕግ አንጻር መመልከት ነው። ምን ዓይነት ሕገ-መንግሥት አረቀቀ? በዚህ ሕገ-መንግሥት ላይ ምን ሀገር ጎጂ አንቀጾች ተካተዋል? በሕጉ ላይ የሠፈሩት ለሁሉም በእኩልነት ይሠራሉ ወይ? ከሕግ በላይ የሆነና በአንጻሩ ደግሞ ሕጉ የሚገዛው ክፍል አለ ወይ? ይኼን በዝርዝር እያንዳንዱ ድርጅት ማጥናትና ግንዛቤ መውሰድ አለበት። ምክንያቱም፤ እኒህ ተጨባጭ የሆኑ ግንዛቤዎች፤ ያለውን መንግሥት ተርጓሚና ገላጭ በመሆናቸው፤ የተለያየ ግንዛቤ ሊያስከትሉ አይችሉም። ይህ ወደ ገዢው ይመራናል። በርግጥ እዚህ ላይ ብዙ ተብሎ ተብሎ ያበቃና ያልተጠቀሰ ጉዳይ የሌለበት በመሆኑ፤ ልዩነት ሊኖር አይችልም። አማራውን ከደቡብ፣ ከምዕራብና ከምሥራቅ ኢትዮጵያ አፈናቅሏል፣ ንብረቱን አውድሟል፣ ገድሏል፤ አስገድሏል፤ እንደ እህልም አስበልቶታል። አኙዋኩን አውድሟል። ኦጋዴኑን ጨርሷል። ኦሮሞውን ፈጅቷል። በደቡብ የሚኖሩትን ርስ በርስ በማጋጨት ሰውን አፋጅቷል። በተቃራኒ ደግሞ ከመቅጽበት ከመሬት ተነስተው ቱጃር የሆኑ ግለሰቦች ተፈጥረዋል። ከየት የመጡ ናቸው? ከገዥው ቡድን ጋር ዝምድናቸው ምንድን ነው? በጽንሱ ላይ ከባድ ችግር ያለበት የክልሎች አመሠራረት፤ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ይህ ቡድን በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ አጫራሽና ሰላም ነፋጊ የሆነው እቅዱ፤ ይሄው ሀገሪቱን ለማፈራረስ መንገድ ከፍቶለታል። በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በሙያ ጣልቃ ገብቶ፤ ሰውን ከሰው በማቃቃር፤ ሀገራዊ አንድነቱን አፍርሷል። እዚህ ላይ፤ በግንዛቤ ደረጃም ሆነ በዝርዝሩ ልዩነት ሊኖር አይችልም።
ባጠቃላይ ሲታይ፤ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት አስተሳሳሪ የሆኑትን፤ ማዳበርና አስተካክሎ መቀጠል ሲገባው፤ እንዳለ በሙሉ እየበጣጠሳቸው ነው። የደርጋማውን መንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት ክፉ ተግባር በጥቅሉ ከመውረሱም በላይ፤ በከፋ መንገድ ቀጥሎበታል። አዲስ በጭንቅላቱ የያዛትን ኢትዮጵያ፤ የ“ትግል” ድርጅቶቹን ጠፍጥፎ እንደሠራቸው ሁሉ፤ ጨፍልቆ በአዲስ መልክ ሊሠራት ተነስቷል። ይህ ከተነሳበት ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያዊ የሆኑ ዕሴቶችን በማጥፋት፤ ለምሳሌ፤ አብሮ መኖር፣ በፈለጉት የኢትዮጵያ ምድር ሠርቶ ማደርና ሀብት ማፍራት፣ ማንም ኢትዮጵያዊ ከማንም ኢትዮጵያዊት ጋር ትዳር መመሥረትና ጎጆ ማበጀት፤ በሀገር ደረጃ፤ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ የተመሠረተ የግል አመለካከትን ተመርኩዞ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ፤ ከዚህ ወይንም ከዚያ ወገን የተወለደች በመሆኗ፣ አንዲት ኢትዮጵያዊት ከሌላዋ ኢትዮጵያዊት የተለየ ጥቅም ወይንም ጉዳት የማይደርስባት፤ ከመንግሥታዊ መዋቅሩ ሌላ፤ ዕለት በዕለት ለሚከሰቱ የኅብረተሰብ ግንኙነት ችግሮች፤ በአካባቢው ያሉ የራሱ የሕዝቡ የልምድ ማስተዳደሪያና ማስታረቂያዎችን መጠቀም፤ ያለ መንግሥት ተፅዕኖ በንግድና በትምህርት፣ በሕክምናና በሙያ ሥምሪት መሰማራት፤ የመሳሰሉትንና ሌሎችንም ጭምር። እዚህ ላይ፤ ኢትዮጵያዊነት ብየ ከላይ በዘረዘርኳቸው ላይ እንከን የለም ማለት አይደለም። ግንዛቤያችን መሆን ያለበት ግን፤ መስተካከል ያለበትን አስተካክለን ወደፊት መሄድ በሚለው ላይ ማተኮሩ፤ ለተከታታይ ትውልድ የተሠጠ ትውልዳዊ ግዴታ መሆኑን መቀበል ነው። ማንም ኅብረተሰብ የተሟላ አይደለም። ጊዜ እያስተካከለው የሚሄድ እውነታ ነው። አሁን ትክክል የምንለው ነገ ጉድለቱ ታይቶ፤ የበለጠ ተስተካክሎ ወደፊት ይኬዳል። ለዚህ ነው የኅብረተሰብ እድገት ተብሎ የሚጠናው። ከነበረው የሚከተለው ተምሮ፤ የተሻለ እንደሚያደርግ የተፈጥሮ ሕግ ነውና!
ሁለተኛው ደግሞ ሕዝባዊ ትግሉ ለድል ሲበቃ፤ ምን እንዲከተል እንፈልጋለን? የሚለውን አስመልክቶ ታጋይ ድርጅቶቹ ያላቸው አቋም ነው። ይህ ትግል ብዙ ክስተቶችን ያዘለ በመሆኑ፤ የትግል ግቡ ምን እንደሆነ ከወዲሁ ታጋዩ ክፍል መስማማት አለበት። እንዲያው በደፈናው “ይህ ቡድን ይውደቅ እንጂ፤ ሕዝቡ ይወስናል!” እያሉ መግፋት፤ በአንዳንዶቹ በኩል የዋህነት፣ በሌሎቹ ደግሞ ብልጣ ብልጥነትን ያነገበ ነው። ለዚህ ነው ልዩነቱ በግልጽ መሰመር ያለበት። ካሁኑ እኛ ተጠናክረን ለብቻችን ሥልጣኑን እንወስዳለን በሚል ስሌት፤ ለብቻቸው መታገልን የመረጡት፤ የራሳቸውን መሪዎች ለማንገስ እንጂ፤ የሕዝብ ትግል አልያዙም። ሁሉም ሊስማማበት የሚገባ በተጨባጭ ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ ተብሎ የተዘረዘረና ቅድም ተከተሉ የተነደፈ መርኀ-ግብር ሊቀመጥ ይገባል። ይህ አልተደረገም። “ይህ መንግሥት ይውደቅ እንጂ፤ ሠይጣንም ቢመጣ ከዚህ አይከፋም!” የሚሉ አሉ። “እቺን ዘፈን በፊት ስምተናታል!” የምንልም አለን። መጀመሪያ፤ ያረጀ ያፈጀው የአፄው መንግሥት እንዲወድቅ፣ ቀጥሎ ደግሞ የአረመኔው መንግሥቱ ኃይለማርያም ደርጋማ መንግሥት እንዲወድቅ፣ የተዘፈነ ነበር። አሁን አዙሪት ገብተን፤ የጅል ዘፈን መልሶ መልሶ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። ስምተነዋላ! አሁን ለብቻቸው የሚታገሉት ድርጅቶች በሙሉ፤ የየራሳቸውን ንጉሶች ለማንገስ ብቻ ነው እንጂ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እየታገሉ አይደለም። ሕዝባዊ ትግሉ ድል ሲመታ፤ ምን መከተል አለበት? ምን ዓይነት መንግሥት መቋቋም አለበት? የሚለው ላይ እያንዳንዱ ድርጅት ያለውን አቋም በግልጽ ማስቀመጥ አለበት። በዚህ ላይ የተለያዩ አቋሞች ይስተዋላሉ። ለዚህ መነሻው፤ ከላይ በቁጥር አንድ የተቀመጠው ጉዳይ ላይ ስምምነት አለመኖሩ ነው።
በሶስተኛ ደረጃ የቀረበው፤ ይሄን ሕዝቡ የሚፈልገውን ግብ ለማስገኘት፤ ምን ማድረግ አለብን? የሚውን ጥያቄ፤ እያንዳንዱ ድርጅት እንዴት እንደሚመልስ ከመረዳቱ ላይ ይሆናል። በመሠረቱ ሁሉም ድርጅቶች፤ ቢያንስ በማስተጋባት ደረጃ፤ በአንድነት መታገሉ ጥሩ ብቻ ሳይሆን፤ አስፈላጊ መሆኑን አሳውቀዋል። እንግዲህ ይህ የትግሉን የስልት ሂደት መተለሙ ላይ ሳይሆን፤ የትግሉን አጠቃላይ ሂደት ማስመሩ ላይ የሚያተኩር ነው። ሁሉም እንተባበር ይላል፤ ማንም ማንንም አያዳምጥም፤ የየራሱን “ጥሪ አደረግሁ!” ብሎ ከመደንፋት በስተቀር! ለዚህ ጥሪውም፤ ራሱ አጀንዳ አውጪ፣ ራሱ ማን እንደሚሰበሰብ ወሳኝ፣ ውጤቱን ከወዲሁ ራሱ አዋቂ የሆነበትን ሀቅ እያስነበቡን ነው። የሕዝባዊ ትግሉ መሠረት፤ የሕዝቡ በአንድነት መነሳት ነው። በሀገራችን ያለው ወራሪ መንግሥት ነው። ትግሉ የነፃነት ትግል ነው። ነፃነት የሁሉም ጥሪ ነው። እናም በአንድ ድርጅት ብቻ መጠቃለሉና በአንድነት መታገሉ ግዴታ ነው። ለምን? ምክንያቱ ግልጽ ነው። ለአንድ ዓላማና ግብ፤ ሁለት ወይንም ከዚያ በላይ ድርጅቶች አያስፈልጉም። የትግሉ ውጤት የሁላችን እንዲሆንና እውነትም ሕዝቡ ወሳኝ እንዲሆን፤ የትግሉ ባለቤትም ሕዝቡ መሆን አለበት። ይህ ማለት፤ እያንዳንዳችን በኢትዮጵያዊነታችን እኩል በግለሰብ መሰለፍ አለብን ማለት ነው። ለድሉ ብቻ ሳይሆን፤ መስዋዕትነቱን ለመክፈልም እኩል እንቀርባለን። “ሌሎቹ ዝም ሲሉ፤ እኔ ዝም ልል ነው ወይ?” ባዮች ተደምጠዋል። “ሌሎች አይረቡም!” ባዮችም ተደምጠዋል። እኒህ ከአንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ድርጅቶችም የተወረወሩ ናቸው። ይህ ሁሉ ተልካሻ ምክንያት ነው። ሕዝቡን ቀስቅሼ አታግላለሁ ባይ ደርጅት፤ ከጎኑ እንታገላለን ካሉ ድርጅቶች ጋር የማይተባበረው ለምንድን ነው? እንዴት ነው እኒህን ትቶ፤ ስለትግሉ ምንም ከማያውቁት ብዙ የሚጠብቀው? ትግል ማለት እኮ፤ ወዶ ገባውን ብቻ ሳይሆን፤ ያልተነሳውንና ምንም ያልገባውንም በዳር የሰፈረውንም ማስተማርና ከጎን ማሰለፍ ነው! በዚህ ላይ “እሺ ከኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ጋር እስማማለሁ!” ብሎ በግልጽ የቀረበና ይሄን በተግባር ያዋለ አንድም ድርጅት አላውቅም። ምን አልባት ዕውቀቴ አነስተኛ ሆኖ ሁሉንም ባለማረዳቴ፤ ተሳስቼ ይሆናል። ስህተቱ ከኔ ነውና አስረዱኝ፤ ለመማር ዝግጁ ነኝ። እኩል ሁላችን እንድንታገል የሚፈልግና፤ የራሱን የድርጅት አባላት በግለሰብ ደረጃ ለኢትዮጵያ እንዲታገሉ የሚያቀርብ ድርጅት ካለ፤ ያ ድርጅት ትልቅ ምስጋና ይግባው። በዚህ ሂደት ከፍ ያለ ሚና ይጫወት! እስኪ ውይይታችን እናጠቃል።
ማንን ነው የምንታገለው? የኛ ግብ ምንድን ነው? የትግል ሂደቱስ እንዴት ተተለመ? ወገን የምንለው ማንን ነው? የትግል ዕሴቶቻችን ምንድን ናቸው? በተለይም ከገዢው ቡድን አንጻር፤ የምንለይባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? እኒህ የተግባር ዝርዝሮች አይደሉም። እኒህ መሠረታዊ የሆኑ የሕዝባችንና የሀገራችን ምንነትና የፖለቲካ ግንዛቤያችን፤ ብሎም የትግሉን ዕሴቶች ወሳኝ ናቸው። የዚህን ገዢ ቡድን የፖለቲካ ፍልስፍና፣ የአስተዳደር መመሪያና ተግባር እንዴት ነው የምንረዳው? አማራጮች ብለን የምናስቀምጣቸው ምን ያህል ተጨባጭ ናቸው? በእነዚህ ላይ ውይይት ማድረግ አለብን።
ይህ በዚህ አንዳለ ግን፤ አንገብጋቢ ጉዳይ ከፊታችን ተጋርጧል። ይሄውም በጎንደር አሁን እየተካሄደ ያለው ዕልቂት ነው። ትናንት በአዲስ አበባ ዙሪያ የገዥው ቡድን አባላት ለዝርፊያ የክልሉን መሬት ሲያዘጋጁ፤ የተነሳባቸውን ተቃውሞ ለጊዜው ለማብረድ እንዳደርጉት፤ የወልቃይትን ጥያቄ ለጊዜው ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ ሊመልሱት አይችሉም። ካልተገደዱ በስተቀር! ሕዝቡን ማደንዘዣ የሚሆን መውጫ በር የላቸውም። የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን “ሰርዘነዋል!” እንዳሉት፤ “ወልቃይትን መልሰን ለአማራዎቹ ሠጥተናል!” አይሉም። ሕዝቡ ደግሞ ማንነቱን ተነጥቆ “ልኖር አልፈልግም!” ብሎ ተነስቷል። ስለዚህ በጎንደር የተከሰተው መነሳሳት፤ ለወራሪው ውድቀት፤ ወሳኝ ደውል ነው። መቀመጫው የሆነውን መሬቱን ከሥሩ የሚንድ ነው። ካለ ወራሪው መጥፋት፤ መብረጃ የለውም። ሕዝቡን እንደለመደው ቢገድልም፤ ጎንደር መልስ መሥጠት ጀምሯል። ከሱም ወገን መገደሉ ተጀምሯል። አሁን የትግሬው ገዥ ቡድን በቁጥጥሩ ሥር ያዋላቸውን ተወካዮች፤ ሕዝቡ “ካልተመለሱ ወዮ!” ብሏል። ወራሪው የሚሠጠው መልስ ግልጽ ነው። አቤቱታ አቅራቢ የእስልምና ተከታዮችን ተወካዮች፤ ይኼው እስከዛሬ እንዳሰረ ሁሉ፤ እኒህንም አይለቅም። ባህሪው አይፈቅድለትም። ነገ ይገድላቸዋል። ታዲያ የሚከተለው ተጨማሪ ግድያ መሆኑን ለማወቅ ጠንቋይ አያስፈልገንም።
በቦታው ታጋዮች አሉ። በቦታው ታጋዮችን የሚመራ አካል አለ። በቦታው የተዘረጋ የትግል መንገድ አለ። “እኔ ካልመራሁት አይሆንም!” ካላልን በስተቀር፤ ይሄን መከተሉ የኛ ግዴታ ነው። በቦታው ያለውን አመራርም ሆነ ታጋይ ክፍል ማጠናከሩና መርዳቱ የኛ ፈንታ ነው። አሁን በማውገዝና መግለጫ በማውጣት መወሰን የለብንም። ጎንደር የተሰናዳለትን ግድያና ጭፍጨፋ ለመቋቋም፤ አሁን እርሻው አረም መንቀል በሚሻበት ወቅት፤ ሕዝቡ ጦሩን አንግቦ ተነስቷል። ዘመድ ስንቅ በማቀበል ተልዕኮ ላይ ነው። ይህ ሁሉ በሕዝቡ ላይ የሚያስከትለውን ጫና መረዳት አያቅተንም። ምን እያደረግን ነው? ይህ ትግል ብዙ ድጋፍ ይፈልጋል። ወራሪው መንግሥታዊ መዋቅሩን ጨብጧል፤ የሀገራችንን ሀብት በቁጥጥሩ ሥር ይዟል፤ ጌዜውን ለመግዛት ይጥራል። ታጋዩ ደግሞ ዋናው የትግሉ ኃይል የሆነው ራሱ ሕዝቡ ነው። መሬቱ የራሱ ነው። እናም የትግሉ መስመር የሚያመለክተው ሕዝቡ እንደሚያቸንፍ ነው። እኛ ደግሞ ግዴታ አለብን፤ ሕዝባዊ ድሉን ፈላጊ ከሆን ማለቴ ነው! ሀገር አቀፍ የሕዝባዊ ትግሉ ድል እንዲያደርግ ካሻን፤ ይሄን አጋጣሚ ተጠቅሞ የሕዝቡን ጉልበት ማጠንከሩ ተገቢ ነው። ይህ ማጠናከሪያ ሊደረግ የሚችለው፤ በአንድና በሁለት ወገን አፍቃሪ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በመላ የሀገሪቱ የወደፊት ጥሩ ተመኚ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሙሉ ነው።
እንግዲህ ሰዓቱ ደርሷል። ደወሉ ተሰምቷል። ጨርቄን ማቄን የለም። እያለቀ ያለን ሕዝብ ቆይ የሚባልበት ጊዜ አይደለም። ከላይ በጠቀስኳቸው ሶስት ነጥቦች አኳያ፤ እያንዳንዱ ድርጅት አቋሙን ግልጽ ያድርግ። ከዚህ በፊት ጥሪውን ያቀረቡ ብዙ ነበሩ። እኔም እንኳ በግለሰብ ደረጃ ሞክሬ ነበር። አሁን ፈቃደኝነትን መንፈግ ወንጀል ነው። ለብቻዬ እታገላለሁ ብሎ መገንተር፤ ሌላ አጃንዳ እንደያዘ ማሳየት ነው። ለሚያልቀው ሕዝብ መድረስ ግዴታ ነው። እስከዛሬ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ!” እያልኩ ኖሬ፤ አሁን በአማራው ላይ የሚደርሰው ግፍ ሰማይ ሲጎን፤ የአንድነት ትግሉ ሂደት የትም አልደስርስ ሲል፤ በግልጽ የወራሪውን መንግሥት ማንነት አስቀምጨ፤ አማራው ተደራጅቶ ራሱን እንዲከላከል አስፈላጊ ጥራውን ስምቼ፤ አቤት ብያለሁ። አሁን ለኔም ሆነ ኢትዮጵያዊንትን ለሚፈልጉ ሌሎች፤ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮልናል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያን ልንታደጋት እንችላለን። ትግሉን በአንድነት በመደገፍና አብሮ በመነሳት የሁላችን ማድረግ እንችላለን። ለታጋዮቹ እንድረስላቸው። በተግባር መነሳቱ ግድ ነው። መግለጫ መሥጠቱ ብቻ በቂ አይደለም። ተግባር አሁን ተጠይቋል። ይህን ተግባር በሥራ ላይ ለማዋል ልናደርጋቸው የምችላቸው ተጨባጭ ክንውኖች አሉ።
በመጀመሪያ፤ የጎንደር ኅብረት፣ ቤተ አማራና ሞረሽ በአንድነት ተቀላቅለው የገንዘብ ማሰባሰብ ጥሪ ያድርጉ። ይህ አንድነታቸው ለዚህ ተግባር ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ለዘለቄታው ነው። ለዚህ ጥሪ ደግሞ ግንቦት ሰባት፣ ሁለቱ ኢሕአፓዎች፤ ሽንጎና ሌሎች የሲቪክ ማኅበራት በቀጥታ ይሳተፉ። ሲሳተፉ ደግሞ፤ ምንም ዓይነት ግዴታ ሳይኖርባቸውና የዝግጅቱ እኩል ባለቤቶች ሆነው ነው። በዚህ ዝግጅት ኡደት፤ ሁሉን አጣማሪ አስተባባሪ ተቋቁሞ፤ በአንድ በኩል እርዳታውን ለታጋዩ ክፍል ሲያደርስ፤ በሌላ በኩል ሕዝባዊ የሆነውን የነፃነት ትግል ማዕከል ይፈጥራል። ለዚህና ለሌሎችም ትግሎች የሚሆን ሁሌምና በሁሉ ቦታ የሚሠራ ማስተባበሪያ የተቀመረ መንገድ የለም። ያለው ሀቅ የሚፈጥረውን ሁኔታ አመቺ በሆነ መንገድ ተጠቅሞ፤ ሂደቱን ማሳመር ነው። ምን ትላላችሁ?
ከታላቅ አክብሮታ ጋር
አክባሪያችሁ አንዱዓለም ተፈራ