(ዘ-ሐበሻ) ኢትዮጵያውያን በስቃይ ላይ ያሉባት የሳዑዲ አረቢያዋ ሪያድ ከተማ ዛሬ ቅዳሜ ማታ በጣለ ከባድ ዝናብ የተነሳ ከተማዋ በጎርፍ ተጥለቀለቀች፣ መንገዶች በጎርፍ ተዘግተው በሥራ ላይ እና በ እለት ተለት ተግባር ላይ ችግር እንደፈጠረ አረብ ኒውስ የተባለው የዜና ወኪል አስታወቀ። የአረብ ኒውስን ጠቅሶ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢ እንደጠቆመው በነገው ዕለት እሁድ በሳዑዲ አረቢያ ትምህርት ቤቶች እና አንዳንድ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው ይውላሉ።
በሪያድ ከተማ የጣለው ከባድ ዝናብ በመኪኖች ላይም ጉዳት ያደረሰ መሆኑን የዘገበው የአረብ ኒውስ በተለይ ሩዳህ፣ ናሲም እና ናጂም በተባሉ የሪያድ አካባቢዎች በጎርፍ ተመተው መንገዶች በውሃ ተጥለቅለቀዋል።
ይህ ከባድ ዝናብ በከተማዋ የመብራት አገልግሎት ላይም ችግር እንደፈጠረ የዘገበው አረብ ኒውስ መኪናዎች በጎርፍ እንደተወሰዱ በአንዳንድ ሰዎች ላይም ጉዳት መድረሱን ዘግቧል።
በሳዑዲ አረቢያ ከ35ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በፖሊስ እጅ ያሉ ሲሆን እነዚህ ወገኖች በቤት ጥበት ሳቢያ በውጭ እንዲያድሩ በመደረጉ ዝናብ ሲደብደባቸው እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያውያኑ አሁንም በሳዑዲ አረቢያ በከፍተኛ ችግር ላይ ናቸው።