Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ከልቤ ሰው ጋ በአማኑኤል ሆስፒታል –ከወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)

$
0
0

==== እንደ መግቢያ ====


ትናትና ያልጠበቅኩትንና ያልገመትኩትን “ዜና” ሰማሁ፡፡ የክፉ ቀን ጓደኛዬ ችግር ውስጥ መሆኑን እና አማኑኤል ሆስፒታል መግባቱን፡፡ ይህ ጓደኛዬ በእኔ ህይወት ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ነው፡፡ በጭንቅ ጊዜ፣ በመከራ ጊዜ፣ “የሰው ያለህ” በሚያሰኝ ጊዜ የሰውም ሰው መሆኑን በተግባር ገልፆ ያሳየኝ የልቤ ሰው ነው፡፡ የጭንቅ ጊዜ ወዳጄ፣ ጭንቅ ውስጥ ሆኖ እኔን ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ግን ምን ያደርጋል!? መሽቷል፡፡ መንጋት አለበት፡፡
አይነጋ የለም ነጋ፡፡

ከዕንቅልፌ ስነሳ መንጋት ብቻ አይደለም፤ ረፋድ ሆኗል፡፡ ፊቴን ለመታጠብ ደጃፌን ከፍቼ ስወጣ በአጋጣሚ የተጎራበትኩት ጋዜጠኛ ብርሃኑ በላቸው “በለሊት አማኑኤል ሆስፒታል እሄዳለሁ ብልህ አልነበር እንዴ?” አለኝ፡፡
“ልሄድ ነው፤ ለሊቱን ሙሉ በሃሳብ ስናውዝ አድሬ ሲነጋጋ እንቅልፍ ጣለኝ” አልኩት ሰዓት እያየሁ፡፡ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ሆኗል፡፡
“ሲሳይ ምን ሆኖ ነው?… ለማንኛውም የምንተጋገዘው ነገር ካለ ንገረኝ” አለኝ ብርሃኑ ወደ ውጪ በር
እያመራ፡፡ ልክ ነው የዚህ ወዳጄ ስም ሲሳይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት አስተዋውቄያቸዋለሁ፡፡ ሲሳይ በቀለ ይባላል፡፡ በ”የቃሊቲ ምስጢሮች” ትረካ ውስጥ ስሙን ያልገለፅኩት ለ”ጥንቃቄ” ብዬ ነው፡፡ አሁንም ስሙን መግለፄ ትክክለኛ ተግባር ይሁን አይሁን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን ….
የሆነ ሆኖ የቁርጥ ቀን ወዳጄ ሲሳይ በቀለ ከእውቅ የዜማና ግጥም ደራሲዎች መሃል የሚመደብ ነው፡፡ በሕዝብ ልብ ውስጥ የቀሩ ምርጥ ምርጥ የግጥምና የዜማ ድርሰቶች አሉት፡፡ በአንጋፋና በወጣት ድምፃውያን አንደበት የናኙ፡፡ ይህ ሰው ነው አማኑኤል ሆስፒታል ለመግባት የተገደደው፡፡ ለምን!? ምን ገጥሞት ይሆን!?

==== በአማኑኤል ቅጥር ግቢ ====
ከቀኑ 5 ሰዓት የሆስፒታሉን ዋና በር አልፌ እየዘለቅኩ ሞባይሉን አወጣሁና ደወልኩለት፡፡ ስልኩ ይጠራል፤ አያነሳም፡፡ ሞባይሌ አምስት ጥሪ ያህል እንዳስተላለፈ አንድ የህሙማን ልብስ የለበሰ ሰው እጁን ከፍ አድርጎ ምልክት አሳየኝ፡፡ እሱ ነው፡፡ ሲሳይ በቀለ ነው፡፡
ገፅታዬ ላይ ምንም ለውጥ እንዳይታይ እየጣርኩ እጄን ዘረጋሁለት፡፡ ጨበጠኝ፡፡ ትከሻ ለትከሻ ተገጫጨን፤ ከዚያም ተቃቀፍን፡፡ ….ከሠላምታ በኋላ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሳለ አጠገባችን ወደሚገኝ የሃኪም ቤቱ አንድ ጥጋት መራሁት፡፡
“ና! ወደ እኔ ክፍል እንሂድ፡፡” አለኝ ግቢው ውስጥ ወደሚገኝ የተከለለ ሌላ ግቢ እየመራኝ፡፡
ቀፈፈኝ፤ ቢቀፈኝም ምንም ማድረግ አልችልም፡፡የምንገባበት ግቢ ውስጥ ዱላ ይዘው ወዲያ ወዲህ የሚያወናጭፉ ታካሚዎች ይታዩኛል፡፡ ሞባይል ይዘው እየተጯጯሁ የሚነጋገሩ፤ ብቻቸውን የሚያወሩ፤ በዝምታ የሚንጎራደዱ…የሆነ ሰው ላይ የሚዝቱ፣ የሚሳደቡ ..ወዘተ ታካሚዎች ይታዩኛል፡፡
እነዚህን መሰል ታካሚዎች በሥጋት ዓይን እያየሁ ጓደኛዬን ተከተልኩት፡፡ ግቢው ውስጥ የሚገኝ ትልቅ ሕንፃ ሥር ወደ ታችኛው ክፍል ይዞኝ ወረደ፡፡
“አንተ ሻንጣ ስለያዝክ ሐኪም ነው የምትመስለው” አለኝ የያዝኩትን ላፕቶፕ እየጠቆመኝ – እናም የተኛበትን ክፍል በር አልፎ ገባ፡፡ አልጋው ላይ አረፍ ብሎ እኔም አረፍ እንድል ጋበዘኝ፡፡ ከጎኑ ተቀምጬ ክፍሉን ቃኘሁት፡፡ ፅዱ ክፍል ነው፡፡ 20 ያህል በሥነ ሥርዓት የተነጠፉ አልጋዎች ተዘርግተዋል፡፡ አልፎ አልፎ የተነጠፉት አልጋዎች ላይ ጋደም ያሉ ታካሚዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሞባይል ለብሰዋል፡፡ አንዳንዶቹ የሆስፒታሉን ሳይሆን የራሳቸውን ልብስ የለበሱ ናቸው፡፡
“አሪፍ ክፍል ነው፤” አልኩት ወሬ እንዴት እንደምጅምር ግራ ገብቶኝ፡፡
“ይኼኛው ክፍል የሳይኪክ ችግር የሌለባቸው ነው፡፡” አለኝ፡፡ ሌላም ሌላም ነገር ነገረኝ፡፡ አነጋገሩ ጤነኛ መሆኑን እንድረዳለት የሚያሳብቅ ነው፡፡እናም ዝም ብዬ ሰማሁት፤ ዓይን አይኑን እያየሁ ሰማሁት፡፡ ይህቺን የማዳመጥ አስፈላጊነት የተማርኩት አንድ የእርዳታ ድርጅት ለሳምንታት “ፒር ካውንስለር” የተባለ ኮርስ በሰጠን ጊዜ ነው፡፡ “እንዲህ ዓይነት ችግር ያለበት ሰው ችግሩን ሲነግርህ ከልብህ አድምጠው፤ ከልብህ ማዳመጥህን እንዲረዳልህ ዓይን ዓይኑን እየው፡፡ ዓይኑን ከማየት በተጨማሪ ማዳመጥህን እርግጠኛ ሆኖ ችግሩን በራሱ ፍቃድ ዘክዝኮ እንዲነግርህ ‹እህ! እህ!› እያልክ አበረታታው” የሚል ዓይነት ነው የኮርሱ ይዘት፡፡
እናም የሚነግረኝን “እህ!” ብዬ አዳመጥኩት፡፡ ልናገርስ ብል ምንድነው የምናገረው? ንግግሬንስ ከየትና እንዴት ነው የምጀምረው!?…ግራ ግብት የሚል ነገር ነው፡፡ ደግነቱ እሱ ራሱ ወደዋናው ጉዳይ ገባልኝ፡፡
“እዚህ ከገባሁ አንድ ወር አለፈኝ፡፡ ወዲያውኑ አንተን ማግኘት ነበር በጥብቅ የፈለግኩት፡፡ ትናንት እንደነገርኩህ ስልኬ ጠፍቶ ስለነበር ላገኝህ አልቻልኩም፡፡ የአንተን ቁጥር ለማግኘት የደወልኩላቸው ሁሉ የበፊቱን ስልክ ቁጥርህን ነው የሚሰጡኝ፡፡ ….አሁን እንዴት እንዳገኘሁህ ታውቃለህ!? በመዝሙር ዮሐንስ (ድምፃዊ) በኩል ነው፡፡”
“መዝሙር እንዴት ስልኬን አገኘ?”
“ሁለት ቀን ሙሉ ስልክህን ማግኘት ሞክሮ አልተሳካለትም ነበር፡፡ እንዳልተሳካለት ሲነግረኝ የድምፃዊ ትዕግስት ፋንታሁን ወይም የባለቤቷን ስልክ ካወቅህ እነሱን ጠይቃቸው አልኩት፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው የአንተን ስልክ ትናንትና ያገኘሁት” አለኝ፡፡
የነገረኝ ነገር አልደነቀኝም፡፡ ድምፃዊ ትዕግስት ፋንታሁን በ2002 ዓ.ም “ና” በሚል ርዕስ ለአድማጭ ባቀረበችው አልበም ውስጥ የሁለቱን ግጥሞች የፃፍኩት እኔ ነኝ፡፡ (ሃሃሃሃ ይህቺ ነገር እንደማስታወቂያ እንዳትቆጠርብኝ) ያኔ ከትዕግስት ፋንታሁን ጋር ለሥራ እንገናኝ ነበር፡፡ (ከትዕግስትም ሆነ ከባለቤቷም ጋር አብሮ አደግ ነን) …እንዲያም ተባለ እንዲህ ያንን አስታውሶ እኔን ማግኘት መቻሉ አስደሰተኝ፡፡ ጤንነቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተረዳሁ፡፡ የልቤ ሰው የከፋ ሁኔታ ላይ ባለመሆኑ ተፅናናሁ፡፡ የሆነ ሆኖ ስለ ዘፈን ካነሳሁ ዘንዳ ዛሬ አማኑኤል ሆስፒታል ስለሚገኘው የልቤ ሰው ሲሳይ በቀለ የግጥምና የዜማ ደራሲነት ጥቂት በምልሰት ላውራ፡፡

====== ምልሰት =======
“እኔን ናፍቀሽኛል – አልናፈቅኩሽም ወይ
መራራቁ ቀርቶ – አንገናኝም ወይ
ፍ…ቅ …ር …..
ፍቅር አይገድሽም ወይ”

” አማላጅ ማን ይሁን፤ ማንን ልላክብሽ
ህመሜ ተሰምቶሽ – ፍቅር እንገድሽ….”
የዘፈኑን ግጥም በትክክል መከተቤን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የዜማው ለዛ እና ፍሰት ግን እስካሁን በጆሮዬ ይሰማኛል፡፡ ዘፈኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በሬድዮ ነው፡፡ ከ20 እና ከ25 ዓመት በፊት፡፡ ድምፃዊው ማን እንደሆነ በስም አላስታውስም፡፡ የዜማና የግጥሙ ደራሲ ግን ሲሳይ በቀለ ነው፡፡
ሲሳይ በቀለ ከበርካታ ዕውቅና ድንቅ ድምፃውያን ያለ የጥበብ ሰው ነው፡፡ ከበርካታ የጥበብ ሰዎች ጀርባ ያለ ጥበበኛ ነን፡፡ ለጊዜው ለእነማን ለእነማን ሥራዎቹን እንደሰጠ ማውጋት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ሁለቱን ወንድማማቾች ታዋቂ ድምፃውያን ልጥቀስ፡፡ ፀሐይዬ ዮሐንስን እና መዝሙር ዮሐንስን፡፡
ለእነሱ ከሰጣቸው ሥራዎች ውስጥ አብዛኛው ሰው የሚወድለትን የመዝሙር ዮሐንስን “ልጅነቴ”ን ዘፈን ብቻ ላስታውስ፡፡ የ”ልጅነቴ” ዘፈን ዜማና ግጥም ደራሲ ይኸው የልቤ ጓደኛ ሲሳይ በቀለ ነው፡፡
“….ውሃ ሽቅብ ላይወጣ
ኑግ እንደሱፍ ላይነጣ
ልጅነቴ ናፈቀኝ ተመልሶ ላይመጣ….”

“ፊደል ይዤ በጉያዬ
ተቃቅፌ ከእኩያዬ….”
ይህንን የመዝሙር ዮሐንስን “ልጅነቴ” ሰምቶ በትዝታ የማይመሰጥ የለም፡፡ እነሆ የዚህ ዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲ ነው የልቤ ሰው፡፡ ዛሬ አማኑኤል ሆስፒታል የሚገኘው፡፡

===== ምን ሆኖ ነው!?====
የሆነው ብዙ ነው፡፡ ታሪኩም ረዥም ነው፡፡ 6 ዓመታት ያህል ወደ ኋላ የሚያስጉዝ ነው፡፡ ቤተሰቡ ተበትኗል፤ ልጆቹን አጥቷል፤ ቤቱም በእሱና በባለቤቱ ግጭት የተነሳ በሌላ ሰው እጅ ነው ያለው፡፡ ….ህይወት ፊቱን ካዞረችበት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይኸው ነው፡፡ ከዚህ በላይ ማለት አልችልም፡፡ እንዲያም ሆኖ ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ጥበብ አዙሮ ቤት ተከራይቶ ራሱን እያስተዳደረ ህይወትን መቀጠል ችሎ ነበር፡፡
ከወራት በፊት ግን “ሰው ጠላሁ፤ ሰው ፈራሁ፤ መሸሽ ጀመርኩ” አለኝ፡፡
“ለምን?”
“የሚታመን ሰው ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ያሰብኩት ቀርቶ ያላሰብቡት ሲሆን ግራ ገባኝ፡፡ ጨነቀኝ፡፡ ሰው መሸሽ ጀመርኩኝ፡፡ ሰው ለመሸሽ ብዬ ትንሽ አልኮል አበዛሁ መሰለኝ ታመምኩኝ፡፡” አለኝ፡፡
“ሰው ይጠላል እንዴ?” ስል ጠየቅኩት እየፈራሁ እየተባሁ፡፡ “ትናንትና እንኳ አንተ ያለህበትን ከነገርከኝ በኋላ ይህንን ፃፍኩኝ” አልኩት ኮምፒውተሬን እየከፈትኩ፡፡ ፌስ ቡክ ላይ የፃፍኩትንና የተሰነዘረውን አስተያየት ጭምር አስነበብኩት፡፡ “ይህ ሁሉ ሰው አንተ እዚህ በመገኘትህ አዝኗል፡፡ የማያውቅህ ሰው ያንተን ጤንነት ተመኝቷል፡፡ እና እንዴት ሰው ይጠላል፤ ሰው ለሰው መድሃኒቱ ነው ይባል የለ እንዴ”
የፌስ ቡክን አስተያየት ካነበበ በኋላ ፊቱ ፈካ አለ፡፡ ወዲያው ደግሞ ተኮሳተረ፡፡
” ምን ላርግ? የሚታመን ሰው አጣሁ፤ በእምነት የሰጠኋቸውን ሥራ የእኔ ነው ብለው ያሳትሙታል፡፡ ገንዘቡ ይቅር ስሜን እንኳ ለመፃፍ (ለማንሳት) አይፈልጉም፡፡ …ሌላው ሌላውን ተወው፤ አሁን በቅርቡ የወጣው ዘፈን እንኳ የኔ ሥራ ነው፡፡ እኔ አልብላ፤ አልጠጣ ስሜን እንኳ መፃፍ ማንን ገደለ!?”
ዝም አልኩኝ፤ ዝም፡፡ ዝም ከማለት ሌላ ምን ማለት እችላለሁ፡፡ ሲሳይ በቀሌ “የኔ ፈጠራ ነው” እያለ የሚነግረኝ ዘፈን ሀገር ሁሉ ትከሻውን የሚሰብቅበት፣ የሚወዛወዝበት እጅግ ተወዳጅ የሆነ ዘፈን ነው፡፡ ይህ የእሱ ነው፤ የእሱ አይደለም ለማለትም ላለማለትም ድምፃዊውንና አሳታማውን ማነጋገር ያስፈልጋል፡፡
“መልካም፤ እንዲህ ዓይነት ነገር ያጋጥማል፤ ደግሞም ላንተ አዲስ አይደለም፡፡ አሁን እሱን እንተወውና እኔ እንድረዳህ የምትፈልገው ነገር ምንድነው? የምችለው ከሆነ ልረዳህ ዝግጁ ነኝ፡፡”
“አሁን በጣም ደህና ነኝ፡፡ በቅርቡ ከዚህ እወጣለሁ፡፡ ስወጣ የት እንደምኖር አላውቅም፡፡”
አመመኝ፡፡ የልብን ስር ጠቅ የሚያደርግ ህመም ተሰማኝ፡፡
“እዚህ እስካለሁ ድረስ መንግስት የሚያቀርብልኝን እንጀራ በልቼ ማደር እችላለሁ፡፡…”
ከዚህ በላይ መስማት አልቻልኩም፡፡ አቋረጥኩት፡፡
“ምን ችግር አለው!? አሁን እኔ ቤት ተከራይቻለሁ፤ ከእኔ ጋር ትኖራለህ፡፡ ከኔ ጋ ኖርክ ማለት የምትበላው አታጣም ማለት ነው፡፡ ይኼ ሊያስጨንቅህ አይገባም፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የሚሆነው ይሆናል፡፡…” አልኩት፡፡
“አዎ ካንተ የምፈልገው ይኼን ነው፡፡ የልጄን ት/ቤት የከፈለልኝ ሰው ነው፡፡…”
“ግዴለም የምንችለውን እናደርጋለን፤ ዋናው ጤና ነው፡፡ ካንተ ጤንነት በኋላ ነው፤ አሁን አታስብ” አልኩት፡፡ “አታስብ” ይባላል እንዴ!!? አለማሰብስ ይቻላል እንዴ!!? እንጃ!!!!
እነሆ ለአንድ ሰዓት ያህል እንዲህ እና እንዲያ አብረን ቆየን፡፡ ልንሰነባበት ሆነ፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ከክፍሉ ለመውጣት በዝግታ ማዝገም ጀመርኩ፡፡ ተከተለኝ፤ ሊሸኘኝ፡፡ እየሸኘኝ
“ደግሞ በዚያው እንዳትጠፋ፡፡ እየመጣህ ጠይቀኝ፡፡ እስካሁን መዝሙር ዮሐንስ ብቻ ነው እየመጣ የሚጠይቀኝ!!”
“አልጠፋም፤ እመጣለሁ፡፡ በጣም የምትፈልገኝ ከሆነ ደውልልኝ፤ እመጣለሁ፡፡” አልኩት ዋናውን የግቢው መውጫ በርቀት እያየሁ፡፡
በመጨረሻም ተሰነባበትን፡- ነገን እያለምን፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው!!

Pen

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>