ውድ ኢትዮጵያን ወገኖቼ እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ። እዲሱ አመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ብስራት ይዞ የሚመጣ ይሁን። ያለምንም ደም መፋሰስ ይህ ዘረኛ የወያኔ ገዢ ቡድን መቃብር ገብቶ፤ ዘረኝነት፤ ጎጠኝነትና በታኝነት ከምድራችን ጠፍቶ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ተፋቅሮ ተከባብሮ፤ ሲያጠፉ የሚቀጣቸውን የሚሽራቸውን፤ ሲያለሙ የሚሾማችውን የሚሸልማቸውን መሪዎች በድምጹ መርጦ፤ የሚኖርበት፤ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከዘር ማንነቱ በፊት በኢትዮጵያ ሲምል ሲገዘት የምናይበት፤ ዜጎች ሁሉ ለሀገሬ፤….. ለወገኔ.. እያሉ ሲተጉ፤ ለጋራ እድገትና ብልጽግና ሲጓጉ….አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ እያሉ አንዳቸው ላንዳቸው ሲሞቱ የምናይበት የተአምር ዘመን ይሁንልን,….ዘረኞች ለአንዴና ለመጨረሻ የሚጠፉበት ዘመን ይሁንልን….2006. አሜን!
አርቲስቶች የተሰጥኦና የህዝብ ሁለንተናዊ ባህልና ወግ፤ እናም የህዝብ ድጋፍና አድናቆት ውጤቶች እንደ መሆናቸው፤ ስራዎቻቸው ሁሉ የህብረተሰብ ህይወት ነጸብራቆች የመሆን ተፈጥሮአዊ ግዴታ አለባቸው። ሰላምና ጦርነት፤ ድልና ሽትንፈት፤ ደስታና ሀዘን፤ ፍቅርና ጥላቻ ምን ጊዜም ከሰው ልጅ ጋር የሚኖሩ ክስተቶች በመሆናቸው፤ ሰውም በጥብበ ስራዎቹ ውስጥ እነዚህን ባህሪያት እያንጸባረቀ፤ ይማማርባቸዋል። ይዝናናባቸዋል። ያስተላልፋቸዋል። ለሚከታተል ትውልድ የታሪክ መንገሪያም ያደርጋቸዋል ።
ጥበብ የአንድ ህብረተሰብ የስልጣኔ፤ የባህል፤ የሳይንስ፤ የፖለቲካ፤ የሁለንተናዊ እድገት ነጸብራቅና ማሳያም ነው። ጭቆናን ለመታገል፤ ፍትህ ርትእ እንዲሰፍን ህዝብን መቀስቀሻና ማስተማሪያ መሳርያም ነው። ትያትር፤ ስነጽሁፍ፤ ሙዚቃ፤ወዘተ…የህዝብን ንቃተ ህሊናና ታሪካዊ ሁለንተናዊ እውቀት እንደሚያጎለብቱ የሚያጠያይቅ ነገር የለውም።
በሀገራችን የወኔ ስራት ከሰፈነ ያልፉት ሀያ ሁለት አመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች አድሎን፤ ዘረኛነትን፤ የመብት ረገጣን በመታገል ረገድ ማን ምን አስተዋጾ አበረከተ ብለን የመረመርን እንደሆን፤ የተወሰኑ ጠንካራ አርቲስቶች እንዳሉን ብናውቅም፤ አሰሩትም ፤አንገላቱትም፤ ሰደቡትም አዋረዱት፤ ስለመከረኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አለቀሰ አንጎራጎረ፤ መከረ አስተማረ፤ አጽናና እንጂ ለወያኔ ስራት አድሮ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ማይክራፎን አልሆነም። የሚወዳት ሀገሩንም ጥሎ አልሄደም….ማን?… ሀዋርያውን ብላቴና ቴዲ አፍሮን ዙፋኑ ላይ እናስቀምጠዋልን።
አርቲሥቶች ህዝባዊ ሀላፊነት አለባቸው። ይህም ማለት በጥበብ ስራዎቻቸው የሚያገለግሉትን ህብረተሰብ የሞያ ስነምግባርን በጠበቀ መልኩ፤ ማህበራዊ፤ ባህላዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ከባቢያዊ ብሎም ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ህጸጾችን እያፈነፈኑ፤ ነቅሰው እያወጡ፤ በብሩሽ በዜማ በግጥም እያዋዙ ማዝናናት፤ ህብረተሰብን ማስተማር፤ ማንቃት፤ የሞራልና የዜግነት ግዴታ ሊሆንባቸውም ይገባል።
አርቲስት በአድናቂዎቹ ልብ ውስጥ የዘራው ፍሬ በአንድ ወይ በሌላ መልኩ ውጤት ማፍራቱ አይቀርም። የህውሀት ካድሬዎች ፖለቲካ አስተምረው፤ አንቅተው፤ ካሸፈቱት የትግራይ ወጣት፤ በዘፈን በጭፈራና በቀረርቶ የሸፈተው ሳይበለጥ አይቀርም።
ተወዳጅ አርቲስቶች ከአንድ ጠንካራ ፖለቲከኛ የበለጠ ድምጣቸው በአድናዊዎቻቸው ዘንድ ይሰማል።
ክቡር ለሆነው የሰው ልጅ ሰባዊ መብትና ነጻነት ጥብቅና የቆሙ የጥበብ ሰዎች እንደ ነጻ አውጭ አርበኛ ሲሞገሱ፤ ሲወደሱና ሲመለኩ ይኖራሉ።
በሌላ መልኩ አድርባይ ፤ እበላባይ አርቲስቶችን፤ አንባ ገነኖች፤ ህዝብን በዜማና በጥበብ እንዲያደነዝዙላቸው ማበረታታት ማስገደድም የተለመደ ነው። እንዲመለኩ እንዲዘመርላቸው፤ መልካቸው አምሮ እንዲሳልላቸው፤ የሚገዟት አገር በምስላቸው እንድትሸፈን ያስደርጋሉ። የተለመደ ነው። የመለስ ዜናዊ ፎቶ ከዚያች ቅዱስ ምድራችን ተለቅሞ ይልቆ ይሆን?
ወያኔ ወደ ስልጣን የመጣ የመጀመሪያዎቹ አመታት እንደነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በርካታ አርቲስቶች ማለት ይቻላል፤ የአንድነትን ጥቅም፤ በዘር የመከፋፈልን ጉዳት፤ በዜማዎቻቸው ለማስገንዘብ ሞክረዋል። ከፊሎቹ ከልባቸው በራሳቸው ሰብእና ውስጥ ካላቸው ኢትዮጵያዊ ስሜት ተነስተው እንደቴዲ አፍሮ አይነቶቹ በሀገራቸውና በህዝባቸው ጉዳይ ላይ የማይናወጥ ጠንካራ ወገንተኝነት እንደያዙ ዘልቀዋል።
አንዳንዶች ደግሞ በወቅታዊ የህዝብ ብሶት ላይ ያተኮረ ስራ ማቅረብ ገበያ ያስገኛል ብለው በማመንም ሊሆን ይችላል፤ የህዝቡን ብሶት የሚኮረኩሩ ስራዎችን አቅርበው የተቸራቸው ድጋፍና ጭብጭባ ሳያባራ፤ ሶስት መቶ ሰላሳ ዲግሪ ተሽከርክረው፤ በአንዲት ቀን ጀንበር ወደ ካድሬነት የተለወጡ አሉ። ሰለሞን ተካልኝ ተገፋን ሲል በዘመረበት አፉ ነው ስለመለስ ዜናዊ ቅንድብ ማማር ማላዘን የጀመረው።
ገናናዋ የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ ማሪያ ማኬባ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1963 ዓ ም ለተባበሩት መንግታት ድርጅት የደቡብ አፍሪካው የነጮች መንግስት ያሰፈነው የአፓርታይድ ስራት፤ በሀገሬው ተወላጅ ላይ እያደረሰ የነበረውን ስቃይ በመመስክሯ ነበር የገዛ አገሯን የዜግነት መብት ገፏት፤ ካገሯ እንድትሰደድ ያደረጋት አፓርታይድ። ማሪያ ለስርአቱ ያጎበደደችበት ጊዜ አልነበረም። በዜማዎቿ ህዝቡ ለነጻነቱ እንዲታገል ታበረታታ ትቀሰቅስ ነበር።
ከዚያ በኋላ ለሰላሳ አመታት በኖረችበት የስደት ዓለም፤ በዜማዎቿ ፤ በንግግሮቿ፤ አፓርታይድ ምን አይነት ስራት እንደሆነ፤ በደቡብ አፍሪካ ህዝብ ላይ ምን አይነት ግፍ እንደሚፈጸም ስትነግር፤ የደቡብ አፍሪካውያንን ባህሎችና ልምዶች ስታስተዋውቅ ኖረች።
ቁጥራቸው በቀላል የማይገመት ኢትዮጵያን አርቲስቶች ሀገራቸውን ጥለው በውጭው ዓለም ለመኖር ሲወስኑ ጥቂቱ፤ የስራቱን እኩይ ተግባራት እየኮነኑ የህዝባቸውን መከራና ስቃይ በማስተጋባታቸው የዘረኛው ህውሀት ቡድን ሰለባ በመሆናቸው ለስደት ተዳርዋል። ከነዚህም ታማኝ በየነ በዋናነት ይጠቀሳል። ሌሎችም የተሻለ ህይወትና ኑሮ ፍለጋ ያተርፈናል ወዳሉት አህጉር ተሰደዋል። ይሁንና እነዚህ አርቲስቶች ሀሳብን እንደልብ መግለጽ በሚቻልበት ሀገር ውስጥ የመኖራቸውን ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ እየደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጥፋትና የሰብአዊ መብት ረገጣ፤ በጥበብ ስራዎቻቸው በመዋጋት ረገድ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ነው ወይ?
ከቅርብ አመታት ወዲህ ሀገር ቤት ያሉ አርቲስቶች እጅግ በሚያሳፍርና ለማመን በሚያዳግት መልኩ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ክደው፤ የወያኔ የፕሮጋንዳ እቃና አጫፋሪ ሆነው፤ የገዛ ሀገሩን ባንዲራውንና ወገኑን ክዶ፤ ስለ ዲሞክራሲ የተናገረውን፤ ስለመብት የተናገረውን፤ የጻፈውን ሁሉ በመጨፍጨፍና ወህኒ በማጋዝ አለም አቀፍ ዝና ላተረፈው መለስ ዜናዊ ፤ የወርቅ ብእር ሽልማት መስጠት ፤ የኢትዮጵያን መፍረስና የአንድን ዘር የበላይነት ተቀብሎ፤ በሎሌነት ለማደር ከመዘጋጀት ውጭ ምንም አይነት መልእክት ያለው ተግባር አልነበረም። ስመጥሩና እጅግ ተወዳጅ የነበሩ አርቲስቶች ዛሬ ወደ ነፈሰበት አዘንብለው፤ ስለወያኔ ስራት ና መሪዎች መልካምነት የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ መስማት ጥበብ በኢትዮጵያ ውስጥ መዝቀጧንና ተጠባቢውም በአድርባይነትና እበላባይነት ሰብእና ውስጥ መስጠሙን ያመለክታል።
በራሱ ሩጫና ጥረት የሚተዳደር አዝማሪ የህዝብ ግጥም እየተቀበለ ዜጎችን ማዝናናት ያልቻለበት ደረጃ ላይ መደረሱ፤ ያስደነግጣል። ልማታዊ ግጥም እንጂ መቀበል አለመቻሉ፤ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ምን ያህል አካሉንም ህሊናውንም እንደገዛው አመላካች ነው። ይህ ቡድን እምን ድረስ ዝቅ ብሎ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመቆጣጠረ እየሞከረ እንዳለ የሚያስገነዝብ ሁኔታ ነው።
ሀተታውን እዚሁ ላይ ላቁመውና ዋናው የርእሴ ጉዳይ ወደ ሆነው እንደ ማሪያ ማኬባ በተሰደደበት የባእድ አገር ፤ በሚያውቅበትና በሚችለው ሙያው እናት ሀገር ኢትዮጵያን የወረራት ህውሀት ዘረኛ አስተዳደር በሀገርና በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን አደጋና ጥፋት በዜማው እየነገረ፤ እየመከረ፤ የሚበጀውን እያመለከተ ትግሎን ስለተያያዘው አርቲስት ሻንበል በላይነህ ስራዎች ላወሳ እሻለሁ።
ውድ አንባቢያን አርቲስቱ ባልፉት አመታት የተጫወታቸውን በርካታ ቀስቃሽ ዜማዎች ሁሉ በዚህ አጭር ጽሁፍ ውስጥ አካቶ ለማመላከት አይቻለኝም ። ለዛሬ በቅርቡ ካወጣቸው ሲዲዎች “ በቁም እንዋደድ እናም ሀይለስላሴ” የሚል መጠሪያ ከሰጣቸው ሁለት አልበሞቹ ውስጥ በሀገራችን ባለው ወቅታዊ እውነታ ላይ ያጠነጠኑ ቀስቃሽ ግጥሞቹን፤ ከየዘፈኑ የተወሰኑ ስንኞች እያወጣሁ ያሰውን ሁኔታ እንዴት ቁልጭ አድርጎ እንዳስቀመጠው ለማመላከት እሞክራለሁ፤ ሌሎች አርቲስቶቻችንም ወቅታዊውን ሁለገብ ትግል ለማገዝ በዜማዎቻቸው ህዝቡን ለነጻነት ማነሳሳት እንዲጀምሩ ጥሪ ለማቅረብ እሻለሁ። ከንግዲህ ኢትዮጵያውያን በሚችሉት ሁሉ ወደ ትግሉ በመቀላቀል የወያኔን ስርአት እስትንፋስ ማሳጠር ግድ ይላል።
ይሰማ ድምጻችን…. ግጥም አይገልጥም፤ ዜማ..ሻንበል በላይነህ
….እኛ አንበተንም፤ እኛ አንበተንም፤ ሙስሊም ክርስቲያኑ ልዩነት የለንም።
ዛሬም ቢሆን እንደበፊታችን፤ ተጠናክሮ ይህ አንድነታችን፤
ሙስሊም ክርስቲያኑ በለቅሶም በሰርጉም፤ አብረን እንኖራለ በክፉም በደጉም። …..
አዎ!.. “..ተነሱ ውጡና እስላም ወንድሞቻችሁን ስደቡ፤ እርገሙ፤ መንግስት ሊሆኑባችሁና ሊያጠፏችሁ ነው “ እያለ የኢትዮጵያን ክርስቲያኖች እያስፈራራና እየዛተ አደባባይ የሚያወጣ፤ በመንግስት ቅርጽ መደራጀት የቻለ የወንጀለኞች ቡድን፤ ምናልባትም በዛሬዪቱ አለማችን በአይነቱ የተለየ የሆነ፤ መንግስት የሚመስል የወንጀለኞች ቡድን ፤ ሀገር በተቆጣጠረበት፤ ሻንበል በላይነህ በምርዋ ድምጹ በጣፋጭ ዜማው ያንቆረቆረልን መልእክት ህዝባዊ እንጉርጉሮ መሆን ያለበትና ሁሉም ኢትዮዝፕያዊ ሊያንጉራጉረው የሚገባ የሙስሊም ክርስቲያኑን መተላለቅ ለሚናፍቀው ወያኔ ጠንካራ ምላሽ ነው።
ህዝበክርስቲያን፡ መስሊሙ፤
ሁሌም በውኑ፡ በህልሙ፤
ያስባል ስለሰላሙ ….
ችግሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ከማሸበር ተግባሩ ያልታቀበው የወያኔ ቡድን ነው እንጂ፤ ህዝቡ ስለሰላሙ ያስባል። በአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ግራኝ አህመድ ሙስሊሙን ይዞ ያን ያክል ጥፋት ሲያደርስ፤ ሙስሊሙን የድጋፍና የሀይል ምንጭ አድርጎት ለራሱ የመንግስትነትን ስልጣን ለመቀዳጅት ተዋጋ እንጂ፤ ነብዩ ሙሀመድ ያላዘዙትን፤ እስልምናን በሰይፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊያስፋፋ አልነበረም ጦርነቱ ፤ “አህባሽ የሚባለውን እስልምና ፤ እኔ ያመጣሁልህን ተቀበል ፤ ለሺዎች ዘመናት ይዘህ የተጓዝከውን እምነትህን ጣል” እያለ በኢትዮጵያዊው ሙስሊም ላይ ከጂሀድ ያልተናነስ ስራ እየሰራ ያለው ወያኔ ነው። ማሰር መግደል። ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ክርስቲያን ወንድሞቹን ያሸ በረበት ዘመን የለም። አርቲስቶቻችን እንደሻንበል በላይነህ በዜማቸው ደግመው ደጋግመው ሊናገሩት የሚገባ እውነታ ነው።
አማራ… ግጥም፤ አይገልጽም። ዜማ፤ የህዝብ…
……ምነው ምን በደለ ደጉ ያገሬ ሰው፤ አረ የሰው ያለህ ፡አረሰው፡ አረ ሰው። እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው፤ ዘመን አረጀና ይሄ ቀን አገኘው። ከባህር ይሰፋል አማራ ማለት፤ ያንድነት ሀረግ ነው ኢትዮጵያዊነት ……
በፋሸሽት ወረራ ዘመን ተፈጸመ ያልተባለ ግፍ፤ አማሮች እስከወዲያኛው እንዲጠፉ፤ በሽታ ገብቷል ብለው የወያኔ ጤና ጥበቃ ሀላፊዎች ወጣት የአማራ ታዳጊዎችን በክትባት ዘመቻ እንዳይወልዱ ያመከነ አውሬ ቡድን የጁን ማግኘት አለበት። ይህ በጥይት ተጨፍጭፎ አላልቅ ያለ ህዝብ፤ እንደሌሎቹ ኢትዮጵያውያን እንደኦሮሞው፤ እንደትግሬው፤ እንደአፋሩ እንደ ደቡቡ እንደ ሁሉም….. ደሙን እያፈሰሰ ፤ ኢትዮጵያን ሲያቀና ዳር ድንበር ሲያስከብር ኖረ እንጂ፤ ወያኔ ሻእቢአና መሰሎቻቸው እንደሚያወሩት ተረት፤ ሌሎቹን ሲገዛና ሲጨቁን አልኖረም። ይልቁን ከማንም በክፋ መልኩ ሲረገጥ ነው የምናየው። የጎጃምን ድሀ አርሶ አደር፤ ከትግራይ ደሀ አርሶ አደር፤ የትግራይን ድሀ አርሶ አደር፤ ከሀረርጌ ድሀ አርሶ አደር ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ድሀ ህዝብ አንዱን ካንዱ የተለየ የሚያደርገው የትኛው ኑሮው ነውና ነው አማራው ተለይቶ እንዲጠፋ የተፈረደበት? የህውሀት በሽተኞች አማራውን የበቀል ኢላማ ያደረጉበት ምክንያት እንደሎሎቹ ሁሉ ለኢትዮጵያ ቀናኢ በመሆኑ ነው። ወያኔ አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ሊመስለው ይችል ይሆናል፤ ግና ለኢትዮጵያ ደሙን ያፈሰሰላት ከሰሜን ምጽዋ ጫፍ እስከ ደቡብ ዶሎ፤ ከምስራቅ ፌርፌር ጫፍ እስከ ምእራብ ኢሎባቡር ጫፍ ያለ ህዝብ ሁሉ ነው። አሁንም ከወያኔ የማጥፋት ዘመቻ ያድናታል። ኢትዮጵያን ይታደጋታል።
ዘንድሮ… ግጥም፤ ተስፋዬ ለማ። ዜማ፤ ተስፋዬ ለማ
……ህጻናት ሲሸጡ ወተው በማደጎ፤ ያለቅሳል ባመቱ ወላጅ አደግድጎ…. ሻንበል በላይነህ በዜማው የነገረን የምናየው ነገር ነው። በማደጎ ስም ህጻናቶቻችንን እየቸበቸበ ያለው ወያኔ ህጻናቱ ካገር ከወጡ በሗላ የት ወደቁ ያለበት ጊዜ የለውም። በስርቆትና በዘረፋ ስለተጠመደ ስለዜጎች የሚያስብበት ገዜ የለውም። ሽያጩ ግን በስፋት እንደቀጠለ ነው። በየ አለሙ ያሉት ኢምባሲዎቹም ድለላውናንና ዶላር ማቀባበሉን እንጂ ስለኢትዮጵያውያን መብትም ሆነ ህይወት የሚያገባቸው ነገር የለም። ዓለም ደቻሳ ቤይሩት ወያኔ ኢንባሲ ፊት ለፊት ነበር ኡ ኡ እያለች በባእድ ጫማ ስትረገጥ መሬት ለመሬት ስትጎተት በዚያው የራሷን ህይወት ያጠፋችው። የኢትዮጵያ ኢምባሲ ተብሎ ወያኔዎች እዚያው ነበር አድፍጠው በዚያች ኢትዮጵያዊ ድሀ ላይ ይደርስ የነበረውን የሚመለከቱት። እነዚህን ነው ሀያ ሁለት አመት ተሸክመን የተቀመጥነው።
…..ጥያቄ ባነሳ መብቱን ያስከበረ፤ ጸረ ሰላም ሲሉት በህግ ሽብር፤ እውነቱን አውጥቶ ስለተናገረ፤ ስንቱ ጋዜጠኛ እስር ቤት ታጎረ… ዘንድሮ
ፍርሀት አሽነፈን…. ግጥም፤ ተስፋዬ ለማ። ዜማ፤ ተስፋዬ ለማ
….ፍራት አሽመድምዶን ጥሎን ባደባባይ፤ ክፉንም ደጉንም ሁነናል ተቀባይ፤ የቆረቆረንን ምቹ ስናስመስል፤ ስንጨስ እንኖራልን ስንጠቁር ስንከስል……
አዎ .. ኢትዮጵያውያን በባህላችንም በተፈጥሮአችንም፤ ለህግ የመገዛት፤ የማክበር፤ በይሉኝታ መገዛት መፍራት፤ ስለሚያጠቃን፤ አንዳንድ ጌዜ ስንገፋና መብታችን ሲገፈፍ፤ ይህ ተፈጥሮ ከልክ ያለፈ ትግስት እንዲኖረን ያደረገ ይመስላል። ለዚህ ስርአት ያሳየነው ከልክ ያለፈ ትግስት ፍርሀት ነው የሚመስለው። አርቲስት ሻንበል በበላይነህ ምናልባትም ይህንኑ ታዝቦ ሳይሆን አልቀረም በዜማው እየነገረን ያለው። ሆድ ይፍጀው ወይም የባሰ አታምጣ እያልን ይኸው ሀያ ሁለት አመታት ጉዳት ተሸካሚዎች ሆነን በዚያው ጉዞ ቀጥሏል።
….. በጥቅም ሲፈረድ፤ በወገን ሲሰራ፤ አይተን እያለፍን ስንጠብቅ ወር ተራ፤ ፍርሀት እንደውሀ ወኔያችን አፍሶት፤ ይዘን ኖራለን የማይወጣ ብሶት…
መለስ ስብሀት ሰራሹ የወያኔ ገዢ ቡድን ወደስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በመንግስቱም ሆነ በግላ ተቋማት፤ ያሻውን ሲሰራ ስንቱን ሺህ ሰራተኛ በገፍና በግፍ እያባረረ የወደደውን የራሱን ምልምል እስከ አሁን ድረስ ሲሰገስግ፤ ሁሉም ተራው ሲደርስ ሜዳ ላይ እየተጣለ ከማልቀስ በቀር ዛሬ በወገኔ ላይ የደረሰ ነገ በኔ ነው ብሎ አምርሮ ስራቱን ለመዋጋት የተነሳ እስካሁን የለም።
የቀድሞው ሰራዊት….. ግጥም ይልማ ገብረአብ። ዜማ ሻምበል በላይነህ ….ጊዜ ተለውጦ ቀን እስከሚከዳው፤ አንጠፍጥፎ ቀምሶ ውሀውን ከኮዳው፤ ያገር መሰረቱ ህብረቱ እንዳይናድ፤ ኑሮውን አድርጎ በቀበሮ ጉርጓድ፤ ታግሎ ወድቆልናል ስላንድነታችን፤ ውለታው ይዘከር የሰራዊታችን። ሳያጓድል ያባት አደራ፤ ያስጠበቀ ያገር ባንዲራ፤ እንዳናጣ የባህር በር፤ ነፍሱን ከፍሏል ለኛ ክብር……
የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታ እንደሚባለው ; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጦርሰራዊት መበተኑ ሳያንሰው ፤ ለወያኔ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንደሆነ እስካሁን በመቆየቱ እድሜ ልኩን ሲዘመርለትና ሲሞገስ ሊኖር የሚገባው ጀግና ሰራዊት፤ ባልፉት ሀያ ሁለት አመታት እንደዋዛ ተዘንግቶ ቆይቶ ነበር። ሻንበል በላይነህ ምስጋና ይድረሰውና ዛሬም እንደትናንቱ የዚያን ክቡር ሰራዊት ገድል አንስቷል። ይበል የሚያሰኝ ነው። የኢትዮጵያን ሰራዊት ሀያል ክንድ አጣጥመው የሚያውቁት ገንጣይና አስገንጣይ እንዳላሸነፉት ልቦናቸው ያውቀዋል። ሰራዊቱን በአካልና በሞራል ከውስጥ ይገልላቸው የነበረው መንግስቱ ሀይለማርያም ባለውለታቸው ነው። በዚያ በውሸት ፕሮፓጋንዳቸው እውነት ለዲሞክራሲና ለእኩልነት የሚዋጉ መስሎት በገፍ እየሄድ ሲቀላቀላቸው፤ ያልተቀላቀለውም መሳሪያውን አውርዶ ባዶ እጁን የቆመ ወታደር በመትረየስ እያጨዱ ነበር ተሯሩጠው ድፍን ኢትዮጵያን እንደ ወባ ትንኝ የወረሯት። መልካሙ ነገር ኢትዮጵያውያን ጀግኖቻችንን መሸለም መጀምራቸው ነው። ያየር ሀይል፤ የምድር ጦር የባህር ሀይል ጀግኖቻችን አሁንም ሊዘፈንላቸው ሊሸለሙና ሊወደሱ ይገባል።
ታሪክ ይፍረደን፤ ግጥም፤ ተስፋዬ ለማ። ዜማ፤ ተስፋዬ ለማ
…የነበረው ቀርቶ ያልነበረው ሆነ፤ የሰራነው ሁሉ እንደቀልድ ባከነ….. ……… .የራሳችን ቋንቋ የራሳችን ፊደል፤ የራሳችን እምነት የራሳችን ባህል፤ የነሉሲ ሀገር፤ የሰው ልጅ መገኛ፤ በራሱ የተሟላ ማን ነበር እንደኛ……
እርግጥ ነው። በራሱ የተሟላ እንደኛ ማንም አልነበረም:: ምን ያደርጋል፤ በመካከላችን የበቀሉ፤ በዚችው ምድር ላይ የተፈለፈሉ፤ ለራሳቸው ታሪክ ባእድ ሆነው፤ አባቶቻቸው የባእድ ጠላት አሽከሮችና ባንዳዎች፤ ያ ጠላት በወላጆቻቸው እአምሮ ውስጥ ባሰረጸው እኩይ አስተሳሰብ ተኮትኩተው ያደጉ፤ ጊዜ ለነሱ አድልታ ኢትዮጵያ እጃቸው ላይ ወደቀች። በማግስቱም … የአድዋው ታሪክ ለአማራው፤ ለደቡቡ ምኑ ነው፤ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጨርቅ ነው፤ እንኳን ከትግራይ ተወለድኩ፤ የሚል ሰው መሪ ተብሎ ባደባባይ የሚናገር፤ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት መኖር የቻለ አጥፊ አየን። መልካሙ ነገር እግዚአብሄር ባጭር አስቀረው። የጀግኖቻችን ሀውልቶች ፈረሱ። በባንዳ ልጆች ስም ተተኩ። በዘመናት አብሮ መኖር የተገነባ የደምና የስጋ ውህደት እንዲለያይ የዘር አጥር ግርግዳ የሚገነቡ፤ በስጋ ፤ ኢትዮጵያውያን፤ በመንፈስና በገቢር ባእዳን የሆኑ ገዢዎችን ለማስተናገድ በቃን። የሻምበል በላይነህ ዜማ ይህንን ነው ልብ ብሎ ለሰማ የሚነግረው።
ኢትዮጵያ…. ግጥም፤ ይልማ ገብረአብ። ዜማ፤ ይልማ ገብረአብ
…….ኢትዮጵያ ህይወታችን፤ ኢትይጵያ ኩራታችን፤ ኢትዮጵያ እምነታችን፤ ያገር ፍቅር ጽናት የምንማርብሽ፤ በፈጠርሽው ትውልድ ይመርብሽ፤ ዛሬም ትላንትም የምልሽ ህይወቴ፤ ውዳሴ ነሽ ለኔ የዘላለም ሀብቴ…. ከዳሽ በሞትሽ ለማትረፍ፤ በሚኒሊክ ጅራፍ ልገረፍ….
ውድ አንባቢያን እነዚህ ሁሉ መልክቶች ሻንበል በላይነህ በቁም እንዋደድ በሚለው አልበሙ ውስጥ ያካተታቸው ስራዎቹ ናቸው። ሀይለስላሴ የሚል ርእስ የተሰጠው ሲዲም ብዙ ታሪካዊና ወቅታዊ መል እክቶች አሉት፤ በተለይም በከፍጠኛ ሁኔታ ወጣቶችን ለትግል የሚያነቃቃ መልእክቶችም አሉ። እራሱን ማዳመጡ የተሻለ ነው። የሻንበል በላይነህ ስራዎች ለአርቲስቶቻችን በአርአያነት የሚጠቀሱ ናቸው። ተመሳሳይ ስራዎች ከየአቅጣጫው ብቅብቅ ቢሉ የህዝባችንን ንቃት እጥፍ ድርብ ያሳድጉታል። ሻንበልም የነጻነት ቀን እስከሚመጣ በያዘው መንግድ እንደሚጓዝና ሌሎችንም እንደሚያስከትል ተስፋ አደርጋለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር
lkebede10@gmail.com