Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የመከላከያ ሠራዊቱ-ድምበር አስከባሪ ወይስ አሳሪና አስተዳዳሪ ?

$
0
0

  ( እምብኝ በል-ጎፍንን )         

ethiopian-troopsየደርግ ወታደራዊ መንግሥት የፖለቲካ ሥልጣኑን በለስ ቀንቶት  ሥልጣን ለመያዝ  ለበቃው ህወሃት ከለቀቀ በኋላ ህወሃት ትኩረት ሰጥቶ ያጠናክር የነበረው የካድሬውንና የመከላከያ ሠራዊቱን መዋቅር ነበር። በመከላከያ ሠራዊቱ ሥር  የአጋዚ ሠራዊት (የፌደራል ፖሊስ እያሉ የሚጠሩት) ቅጥረኛ የከተማ  ነዋርዎች ነብሰ ገዳይ ቤት ለቤት እያውደለደለ ንብረት በመዝረፍ የተሰማራ በቤተ-መንግስት በጅት ይተዳደር የነበረውን የደርግ ልዩ ጥበቃ ኃይልን ቦታ የተካውና በህወሃት የሚመራው፤ የፖሊስ ኃይል ፤ የደህንነትና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንዳሉበት ግምት ውስጥ አስገብተን ማለት ነው። በመሆኑም እነዚህ መዋቅሮች እስከ ዛሬ ድረስ የሥርዓቱን እድሜ በማራዘም ረገድ የተጫወቱት ጨዋታ ቀላል አይደለም ወይም የህወሃት የጀርባ አጥንት ናቸው ቢባል ነገሩን ክብደት ሊሰጠው እንደሚችል በመግለጽ ለዛሬ ያለኝን ትኩረት በዚህ ላይ ላድርግና በመጠኑም ቢሆን  በዚህ ተቋም ላይ ያለኝን ሃሳብ ማካፈሉ ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታትሉ ምንጭ ወይም የመነሻ ሀሳብ የሚሆን መስሎ ስለታየኝ ከዚህ የሚከተለውን የግል  አስተያየቴን ለአንባቢዎቼ አቀርባለሁ።

በሽግግሩ ወቅት የመከላከያ ሚንስትር የነበረው ስየ አብርሃ ሲሆን ከፀደቀ 18 ዓምታትን ያስቆጠረውና በሥራ ላይ ሳይውል የቀረው በህወሃት ተረግጦ የሚገኘው ሕገ-መንግስት ከመታውጁ በፊት ስየ አብርሃ -የቀጣይቷ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራስያዊት ሪፐብሊክ ሠራዊትን በሚመለከት፦ እንዲህ ብሎ ነበር ፦የመከላከያ ሠራዊቱ ከዋና መንገድ 20 ኪ/ሜትር  ከዋና ከተማ 40 ኪ/ሜትር ርቆ እንዲሰፈር እንደሚደረግ ፤ የሠራዊቱ ብሔራዊ አስተዋጾም እንደየ መጣበት ብሔር ወይም ብሔረሰብ ሕዝብ ብዛት እየታየ እንደሚመደብና ወታደራዊ ብቃቱም ፕሮፌሽናል ስታንዳርድ  (ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ) ወይም እንዲኖረው ተደርጎ እንደሚሰለጥን መሪ አቅጣጭ ተቀምጦለት ነበር። ይሁን እንጅ ስየ አብርሃ ይሁን ሌላው በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ላይ የነበረው አካል ይሁን አሁን ያለውም ቢሆን ይህን መርሕ እንዲተገበር ሲያደርጉት አልታዩም። በርግጥ ስየ አብርሃ በመከላከያ ሚንስትርነቱ ብዙ አልቆየበትም። ቢቆይም እዚህ ግባ የሚባል  መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ብየ አልጠብቅበትም ነበር። ምክንያቱም እሱም ቢሆን በህወሃት ውስጥ ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ በአመራር ላይ የቆየና ወደኋላ አካባቢ በጥቅምና በሥልጣን ክፍፍል ተገቢውን ድርሻ ባለማግኘታቸው በህወሃት ውስጥ ክፍፍል ሲፈጠር በሟቹ መለስ ዜናዊና በአዲሱ ለገሰ ውሳኔ ተገፍተው ከጎድና ከወጡት አንዱ ቢሆንም አሁን ህወሃት የሚያራምደውን የአንድ ጎሣ (የትግሬ) የበላይነትን ዓላማ ወደ ፊት ይገፉ ከነበሩት ጽንፈኞች ስፊ ድርሻ የነበረው በመሆኑ ለተወሰኑ ወራቶች የህወሃት ተቃዋሚ መስሎ ብቅ ቢልና ኢትዮጵያዊነቱን ለማስመስከር ቢሞክርም  እምነት እንዳንጥልበት የሚያደርጉ ብዙ ሊገልፃቸው የሚገቡ ነገሮችን አፍኖ መያዙና ለግል ሕይወቱ ቅድሚያ መስጠቱ ከትግሉ ጎራ መራቁን አመልካች ነው። ይህን ስል ግን የስየን ጠንካራ ጎኖቹን ማለትም ራሳቸውን ደብቀው (አድፍጠው) ዝም ካሉት አረጋሽ ፤ተወልደና ዓለምሰገድ እንዲሁም አብረው ብዙ ሳይራመዱ ተመልሰው የሥልጣን ጥማታቸውን ለማስታገስ ከወሰኑት ሐሰን ሽፋና አባይ ፀሀየን ከመሰሉት በእጅጉ የተሻለ መሆኑን ፤ ለሥርዓቱ አለመገዛትና ድርጅቱን ጥሎ በመውጣት ህውሃትን በውጭ ሆኖ መመልክቱ ብዙ አስተማሪ ነገር እንዳገኘበት፤ እንድሁም ይመራውና ይታገልለት የነበረው ድርጅት ቅጥረኛና ፀረ-ኢትዮጵያ ድርጅት መሆኑን፤ ከሱ በፊት የተገደሉ የታሰሩ ፤ የተባርሩ ነባር ታጋዮችን እጣም በሱ ላይ በመድረሱ አዛኝ ልቦና ሊያድርበት ይችልላ የሚለውን በታሳቢነት በማሳደር አሁንም ስየ ከሕዝብ ጎን በመሆን ትግሉን ቢቀጥል የተሻለ እንደሚሆን እግረ መንገዴን መጠቆም እወዳለሁ ምክንያቱም ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት አደገኛ ሁኔታ እንድትደርስ ካደረጉት አንዱ ስለሆነ  ከደሙ ንጹሕ ለመሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚክስ ተግባር መፈጸም ይጠበቅበታልና ህወሃትን  አለበት።

የመከላከያ ሠራዊቱ ከላይ በተቀመጠለት መርህ መስረት ስፍሮ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር ሲግባው  የሚፈጽመው ተግባር ግን በግልባጩ በየመሸታ ቤቱና ስራ አጥተው ሰውታቸውን ሸጠው በሚያድሩ ምስኪን እህቶቻችን መኖሪያ መንደር ለመንደር ትጥቁን ተጀብሎ መዋያና ማደሪያ ማድረጉን ፤ በገጠርና በየከተማው በአስዳደር ሥራ ጣልቃ ሲገባ ፤ መሬት ሲመራና ሲያካፍል ፤ በየተሰማራበት አካባቢ ሴቶችን አስገድዶ ሲደፍር ፤ በኃይል አስገድዶ የጠለፋ ተግባር ሲፈጽምና አለቆቹ  እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ቆጥረውት ሩዋንዳ ፤ ሱዳንና ሶማሌ ድረስ እየሰደዱ ከዩኤን ወፍራም ደመወዝ በዶላር እንዲከፈለው በማስደረግ ለአለቆቹ የሀብት ምንጭ ከመሆንና መጠቀሚያ ከመሆኑ ባሻገር በሕዝቡ ዘንድ የሚያስመሰግን ተግባር ሳይሆን የሚፈጽመው አሳፋሪና የጠመንጃውን አፈሙዝ በሕዝብ ላይ በማዞር በአደባባይ ንጹሃን ዜጎችን ከመግደል ከመደብደብና ከማፈን ውጭ ኢትዮጵያዊ የአገር መከላከያ ሠራዊት መሆኑን የሚያስመሰክር ተግባር አልፈጸመም ። እዚህ ላይ እንደሰለጠነው አገር ሰራዊት የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስ ሄዶ አላገዘም ፤አቅም ለተሳናቸው ድጋፍ አላደረገም በማለት መክሰሴ አይደለም የጠመንጃውን አፈሙዝ በምን ሂሳብ ነው ወደ ሕዝብ እንዲያነጣጥርና አልሞ እንዲተኩስ የሚደረገውና ሕዝብ የሚጨርሰነው ነው? ?

የመከላከያ ሠራዊቱ ውስጡ በሰፊ ቅራኔ ውስጥ የተሞላ ቢሆንም ከአማራው ብሔር የመጣው የመከላከያ ሠራዊት አማራውን ሲያጠቃና ሲጨፈጨፍ ተባባሪ ሆኖ ከማገልገልና ነገሩን ከማባባስ አልፎ የአማራውን ብሔር ሕዝብ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብት ተነካ ብሎ የአማራውን ሕዝብ ጥቃት ሲመክት አልታየም። ከኦሮሞው ብሔር የመጣው የኦሮም ተወላጅ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት አባልም ኦሮሞው ሲንገላታ ከመተባበር የዘለለ ተግባር ሲፈጽም አልታየም። በርራ ላይም  በየግዳጁ ሲግባ በፊቱና በኋላው የሁለት ወገን እሣት የህወሃት አለቆቹና ሥርዓቱን ለመጣል በመታል ላይ ያሉት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጥይት እንደሚገድለው ይታወቃል።ይህ ሁሉ እየሆነ ግን የሥርዓቱን እድሜ ለማራዘምና በአለቆቹ ዘንድ ምስጉን ለመባልና በበጎ እንዲታይ ምዝብሩን ሕዝብ በማንገላታት በመግደል  ስቃዩን በማባባስ ለሰሞንም ቢሆን የህወሃት ታማኝ መስሎ እያደረ ይገኛል። የደርግ የጦር ሠራዊት በጅምላ ጨፍጫፊነት የሚታወቅ ቢሆንም የሥርዓቱ  ከአናቱ  ወይም ከላይ የተበላሸ መሆን እንጅ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ አንድ የሚያደርግ ባህሪ ኢትዮጵያዊነትን ስንቅ የሰነቀ ነበር።  ያም ሆኖ ይህ ዛሬ የሚታየው የአገር ሉዓላዊነት መደፈር አስከፊ ጥቃትና ገጽታ በኢትዮጵያችን እንዳይመጣ ግን ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠ፤ ደሙን ያፈሰሰ፤ አጥንቱን የከሰከሰ ነበር። ይሁን እንጅ የደርግ ሥርዓት ሲናድ በሠራዊቱ ላይ የደረሰበትን የሞራል ፤ የአካል ፤ የህይወት ዋስትና ማጣትና የጎዳና ተዳዳሪ እንዲሆን መዳረጉ በዜግነቱ ሊከበር አለመቻሉ መቼም ቢሆን የማይረሳ የህወሃት በቀልተኛነት ታሪክ በታሪክ ማህደር ተዘግቦ የሚጠብቅ ይሆናል። የአሁኖቹ ሰሞነኞችና አዲስ ናፋቂዎችም ነገ መሀሉ ዳር -ዳሩ መሀል የሚሆንበት ሁኔታ ሲፈጠር በማን ላይ ሊያሳብቡ ማንን ምክንያት ሊያደርጉ እንደሚችሉ እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቀው ጉዳይ ይሆናል። እንደኔ የግል አስተያየት ግን ህወሃትን መከታ በማድረግ በማንኛውም አይነት መዋቅር የተፈጸመች እያንዳንዷ ግፍ ጊዜዋን ጠብቃ  ብህዝብ ፊት ለፍርድ እንደምትቀርብ ትንበያ  ወይም ጥንቆላ ሳይሆን በግልጽ እንደሚሆን በድፍረት መናገር ከእውነቱ መራቅ አይደለም።

  በሽግግሩ ወቅት በተቋቋመው ሕገ-ምንግሥት አንቀጽ 87 ላይ የመከላከያ መርሆዎች ይልና፦ከዚህ የሚቀጥለውን ደንብ ያትታል።ደንቡ ግልጽነት የጎደለውና አሻሚ ትርጓሜ እንዲሰጥ የተደረገ ውይም የያዘ ሲሆን ሆነ ተብሎ ለማጭበርበር የተዘጋጀ መሆኑን ያመለክታል። ራሱን እንደመንግሥት አደርጎ የሚቆጥረውና በማርክስዊ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ የሚመራው የታጠቀው የደደቢት ፖለቲካዊ ኃይል በክህደት ተወልዶ በክህደት ያደገና የፀረ-ሕዝብ ተቋም ቢሆንም በየጊዜው የሚቀያየረውን የማጭበርበሪያ ስልት ደግሞ ለይቶ ማወቅ የግድ ይሆናል ብየ አስባለሁ።

1/ የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔር ብሔረሰቦችን ፤የሕዝቦችን ሚዛናዊ አስተዋፅኦ ያካተተ ይሆናል።

 እንደሚታወቀው በደርግ መውድቂያ አካባቢ ህወሃት አገር ለማጥፋት ብዙ ቁጥር ያለው ሠራዊት አስታጥቆ ነበር ። ወደ መሀል አገር ሲገባም በአምሳሉ የፈጠራቸውን ጨምሮ ይህ ኃይል የማይናቅ ቁጥር ነበረው። ከተራ ውንብድና ወደ ሕጋዊ ውንብድና ሲሸጋገርና አገር መግዛት በእጅ የተያዘና የሚቻል መሆኑ ሲረጋገጥ በቅጥፈት ያደገው ህወሃት ያሰለፈውን ኃይል የሥርዓቱ አገልገጋይና ታማኝ በማድረግ ማስቀጠል ስለነበረበት የሚጠቀምበት መንገድ መፈለግ የግድ በመሆኑ የተወሰነውን የህወሃት ኃይል የአካባቢውን ህዝብ በማስለቀቅ ዳንሻ በተባለ ቦታ ውስጥ በአንድ ማዕከል የመተዳደሪያ በጀት ስጥቶ ሲደራጅ የቀረውን ለማሸጋሸግ ደግሞ ድርጅቱ መላ መምታት ነበረበት። ይኸውም በሕጉ መሠረት የሰፈረው የሠራዊት ምደባ ሕግ እንደ ብሔሩ ወይም ብሔርሰቡ ብዛት ሚዛናዊ መሆን አለበት ስለሚል ይህን ሕግ ለመከላከል አብዝኛው የህወሃት ሠራዊት በአማራው ክፍለ ሀገራት ብዙ ጊዜ ስለቆየ አማርኛ መናገር የሚችለውን በቀጥታ የአማራ ብሔር ተወላጅ እንደሆነ አድርጎ መመደብ ነበረበት ተመደበ  ኦሮምኛ ተናጋሪ ህዝብ ባለበት ተወልደው ያደጉ ትግሬዎችም የኦሮሞውን ሠራዊት ኮታ እንዲቀላቀሉ ተደረገ ( አባዱላ ፤ዘገየ የማነብርሃን…ወዘተ የመሳስሉ)  እዚህ ላይ ለኢህአፓና ለደርግ አንምበረከክም ያሉትና ለህውሃት የተንበረከኩት ኢህዴኖች በዚህ የተግባር አፈፃፀም ወቅት ብአዴኖች የሆኑት በድጋሚ ለህውሃት ተንበረከኩ። ለህወሃት መረጃ በማቀበል፤ መንገድ በመምራት፤ በስለላና በአጠቃላይ የህወሃትን ዓላማ ስኬታማ ለማድረግ ታጥቀው ያገለገሉ ባለሟል የሆኑት እስላሙን ከእስላሙ፤ ክርስቲያኑን ከክርስቲያኑ ፤ደገኛውን ከቆለኛው፤ ሽናሻውን ከአገው ጋር፤የደቡቡን ከሰሜኑ፤ የምሥራቁን ከምዕራቡ ጋር በማጋጨት አገር ያጠፉት (አዲሱ ገለሰ ፤ ታምራት ላይኔ ፤ ተፈራ ዋልዋ ፤ ብረከት ስምኦን ፤ታደሰ ካሳ ፤ህላዊ ዮሴፍ) በዚህ መጥፎ ምግባራቸውና በአማራው ሕዝብ ላይ በፈፀሙት ሁሉም አይነት ግፍ  ሰፊው የአማራ ሕዝብ ለሁሉም ጊዜ አለውና አንድ ቀን ይፋረዳቸዋል።እዚህ ላይ ልብ ብላችሁ እንድታነቡልኝ የምጠይቀው ቢኖር ህወሃት ሕዝብና አገርን መግደል ዓላማው አድርጎ የተነሳ ሲሆን ዓላማውን ለማሳካት ለ40 ዓመታት ያህል ሥራውን እየሰራ ይገኛል ተግብሩ ወይም ዓላማው ጥፋት ነው ነገር ግን ለዓላማው አሁንም ወደፊት የሥርዓቱ እድሜ እንዲረዝም ለማድረግ ተስፋ ባለ መቁረጥ እየታገለን ይገኛል። እኛም የሕዝብና የአገር ጠላት መሆኑን ተገንዝበን በቻልነው መንገድ ሁሉ ድንጋያችን እየወረወርንበት እንገኛለን ነገር ግን ትግሉ አንድ የዘነጋው መሠረታዊ ጉዳይ አለ ይኸውም ቀደምት የኢህዴን አመራር የነበሩና ዛሬም ህወሃት በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ አስቀምጧቸው የሚገኙትን በዋናነት ከፍ ሲል ስማቸውን የዘረዘርኩት አደገኛ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሆናቸውን ቅድሚያ ሰጥቶ አለመንቀሳቀሱና አሁንም ትኩረት እንዲደረግበት ለምሳሰብ ነው። ዛሬ በተለያዩ መዋቅሮች ቁልፉን ቦታ ይዞ የአማራውን ክልል በቅኝ -ገዥነት እየገዛ የሚገኘው ኃይል ምንጭ በእነዚህ በተጠቀሱ ግለሰቦችና በዙሪያቸው በተሰማሩ አሾክሿኪዎች አማክኝነት ነው። ህግ መጣስ የተጀመረው በዚህ ጊዜ ባይሆንም ኢህዴን ያሰለፈው ምስኪኑ የአማራ ብሔር ሠራዊት ግን በብር ከ3ሽህ በታች ድጎማ እየተሰጠው ወደ የመጣህበት ከብትና  ፍየል ጥበቃህ ተመለስ እየተባለ መሳለቂያ ሆኖ እንዲሄድ ተገዶ ከሠራዊቱ አባልነቱ ተወገደ። የቀረውም በህወሃት ካድሬና የሠራዊት አለቆች በየጊዜው እየተገመገመ እንዲባረር ሲደርግ ድምጣቸውን አጥፍተው ሰጥ ለጥ ብለው የተግዙት የሠራዊት አባላትም ህወሃትን የሚያስጭንቅ ውጫዊ ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር ወደ እሥር መወርወር ፤በድብቅ በመግድል፤ ጤና በሚነሳ መድኃኒት ተወግተው እንዲሞቱ ማድረግ የድርጅቱ መደበኛ ባህሪ እየሆነ መጣ። 1/ለምሳሌ ኮሎኔል ታደለ ገብረሥላሤ ሩውንዳ አዝማች ሆኖ ሄዶ የነበረ ህወሃትን ከደደቢት እስከ ደቡብ፤ ምእራብና ምሥራቅ ግንባር ከፋች በመሆን የሚታወቅ እንደነበር የማይካድ ነው። 2/ኮሎኔል ናቃቸው ጫቅሉ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርንት በመጨረሻ የወጣው ዝነኛ ተዋጊና አዋጊ ታመው በህክምና ላይ በነበሩበት ወቅት ህወሃት ሆነ ብሎ በመርዝ ተወግተው እንዲሞቱ ያደረጋቸው ሰለባዎች ናቸው። ይህ አድሎ እስከመቼ ይቀጥላል በሚል በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ተነስቶ የነበረው የመከለከያ ሠራዊቱ ጥያቄና አመጽ በተለይም በአማራው የመከላከያ ሠራዊት አባላት እድገቱን ጨምሮ ክልሉ በልማት ወደ ኋላ መቅረቱና በብአዴን አመራር ቦታ የተቀመጡት አማራ ያልሆኑና ለአማራው ብሔር ሕዝብ የማይጠቅሙ ጠላቶች ናቸው በማለት 1/በረከት ስምኦንና 2/ተፈራ ዋልዋን  እንዲሁም ሌሎችንም ምሳሌ አድርጎ የተነሳው እንቅስቃሴ እየተገመገመ እያለ ድንገት የኢትዮ-ኤርትራው ጦርነት ተጭሮ ሠራዊቱን ለመምታት ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ እነሆ  ከዚያ በኋላ ገዥው ኃይል አመጹን አዳፍኖ ሠራዊቱን የሥርዓቱ አሽከር በማድረግ ሕዝብ እንዲጨርስ አሰማርቶት ይገኛል ። አሁን ይህችን መጣጥፌ እያዘጋጀሁ እያለሁ በፖሊስ ስም የሚሸቅጠው የአጋዚ ሠራዊት በመባል የሚታወቀው የሠራዊት ኃይል በሰላማዊ ፓርቲ አመራር ኃይልና አባላት ላይ ያደረሰውን ጥቃት እየተመለከትኩ በድርጊቱ እጅግ አዝኘ እስከ መቼ? በሚል ጥያቔ ስሜት ውስጥ ገብቼ ነው።

2/ የመከላከያ ሚንስትር  ሆኖ የሚሾመው ከስቪል ይሆናል።

የሕግ ባለ ሙያ ባልሆንም እስከ አሁን በመከላከያ ሚንስትር ሚንስትር ሆነው የነበሩትን ወስደን ስንመለከት በትግል ላይ የነበሩ ለፓርቲያቸው የሚያደሉ ሠራዊትን በበላይነት ሲመሩና ሲያዋጉ  ሲያዋጉ የነበሩ ሲሆን ምንጫቸውም ያው ከህወሃት እንደሆነ ይታወቃል። ከአገር አጥፊው መለስ ሞት በኋላ የመጣው ካቢኔም ለማጭበርበሪያ ይሆን ዘንድ አንዳንድ የሹመት መስጠትና የመለዋወጥ ሁኔታዎችን ያደረገ ቢሆንም ከኋላ ያሉት አስተኳሾችን እነማን እንደሆኑ ስለምናውቃቸው የተጃጃሉት እራሳቸው እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልሆነ ሊገነዘቡ ይገባል። ነገር ግን ቀልዱን አበዙት። እነሳሞራም ራሳቸውን አንቱ ያሉ በፀረ_ህዝብነት ታሪካቸው የታወቁ ስለሆነ ማንም የሚያዛቸው እንዳልሆኑ መግደል የሚፈልጉትን ከመግደል እንደማይታቀቡ ግልጽ  ሆኖ እያለና ነፍጥ አምላኪ ኃይልን በጎ ነገር ሊያመጣ ይችላል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ማንም ይሾም ማንም ይህ ሥርዓት ፀረ-ሕዝብ ፤ ፀረ- ኢትዮጵያ እስከሆነ ድረስ መውወድ ብቻ ነው ያለበት።

3/ የመከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ሕገ-መንግሥት መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል።

ይላል። ይህን ነጥብ በሁለት ከፍለን ብንመለከተው መሰሪነቱን ለመረዳት ይቀላል፦

ሀ/ የመከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ይጠብቃል፦ አዎ!! የአንድ አገር የመከልከያ ኃይል(ሠራዊት) ተቀዳሚ ተግባሩ የአገርን ዳር ድንበር (ሉዓላዊነት) ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅ ማስከበር ነው። በዚህ ዙሪያ ይህ የህወሃት የመከላከያ ኃይል በአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ የተፈተነበት ወቅት ነበረ ወይ ? ካልነበረ በምን መለኪያ ሊታመን ይችላል ? ለዚህ የሚያበቃ መንፈሳዊና ብሔራዊ ሞራል አለው ወይ? በከፍተኛ ደረጃ አመራር ላይ ያሉት ከዚህ ጨዋታ ውጭ ከሆኑ እታች ያለው ኃይል አገራዊና ሕዝባዊ ፍቅር አለው ብሎ ለመናገር ዋስትና የሚሆኑት ከየት ሊገኙ ይችላሉ ? ትንሽ በኢትዮ-ኤርትራው ጦርንት ዙሪያ ልቆይና የመጨራሻ መደምደሚያየን አስቀምጣለሁ።

በ1958 የተቋመው ኤ.ኤል.ኤፍ ( የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር) ቀደም ሲል ከዘውዳዊው ሥርዓት ጋር በኋላ ከወታደራዊ መንግሥት ጋር ውጊያዎችን ያካሂድ እንደነበር ይታወቃል ። ወደኋላ አካባቢ ግራ ዘመም የሚመስል ነገር ግን ያልነበረ ኢ.ኤል.ኤፍን ከሁለት እንዲከፈል አደረግ። አዲስ በተቋቋመው ኤ.ሕ.ኤል.ኤፍ (የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር **ሻቢያ**) እና በኤ.ኤል.ኤፍ መካከል ቅራኔዎች እያደጉ በመሄዳቸው አንዱ ሌላውን መብላት ጀመረ። በመሆኑም ሻቢያ ጉልበት እያገኘ ጀብሃ እየተዳከም መጣ ። ሻቢያ ጀብሃን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ትጥቅ የያዙ በኤርትራ ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን የማዳከም አቅም አገኘ። በ1967 ዓ/ም የተቋቋመው ተጋድሎ ሀርነት ትግራይ በኋላ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በኤርትራ ከተከሰተው ሁናቴ ጋር የሚያገናኘው ብዙ መሠረታዊ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ነገር ግን ይህን ጉዳይ ቀንጭቦ ማለፍ ስለማይገባ ራሱን አስችሎ ማቅረቡን በማመን ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና ጀብሃም ሆነ ሻቢያ ህወሃትን በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ የማደራጀትና የማስታጠቁን ጉዳይ በበላይነት ይዘውት እንደነበር ይታወቃል። ደርግ በሚያደርጋቸው ዘመቻዎችም በጋራ ማለትም ሻቢያና ህወሃት በከፍትኛ ደረጃ ይተባበሩ ነበር። ይህ ግን ቀጠለ ወይስ አልቀጠለም ? ወደሚለው ስንገባ ሻቢያ የአዛዥነቱን ህወሃት የታዛዥነቱን ጉዳይ በአግባቡ ሊያደርጉ ባለመቻላቸው በመሃከላቸው የነበረው ጥብቅ ግንኙነት በህወሃት አልታዘዝም ባይነት ምክንያት ሊቀጥል አልቻለም። ለይቶላቸው የከፋ ግጭት ባይፈጥሩም ደርግ እስኪወድቅ ድረስ ይረዳዱ ነበር።ይህ በዚህ እንዳለ ግን ሻቢያ ህወሃትን ማጥመዱ አልቀረም ህወሃትም ሻቢያን የማደናቀፍ ተግብሮችን ማራመድ ጀመረ። ለምሳሌ ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝብ ኤርትራ የሚባለው ድርጅት ፀረ-ሻቢያ ሆኖ እንዲቆም የማደራጀቱን ሥራ ይመራው የነበረው ህወሃት ነበር።ሻቢያ ይህን ተግባር ቢያውቅም የተነሳበትን የመገንጠል ዓላማ ላለማደናቀፍ ህወሃትን ይጠቀምበት እንደነበርና ወደፊት ግን ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት አለመቦዘኑን የሚያመላክቱ አንዳንድ ጉዳዮች ነበሩ። ከላይ እንደገለጽኩት ይህን ጉዳይ ባጭሩ ማሳየት ስለማይቻል ገረፍ ገረፍ አድርጌው ልለፍና ደርግ ከወደቀ በኋላ በአዲሲቷ አፍሪቃዊት አገር ኤርትራና ኢትዮጵያ ምን አይነት አንድነትና ልዩነት ነበር የሚለውን በመነካካት በጉዳዩ ሰፊ እውቀት ያላቸውን አባንኘ በሰፊው እንዲያብራሩት በመተው በበኩሌ የማውቀውን እንዲህ ለመግለጽ እሞክራልሁ።

  ወዶም ይሁን ተገዶ ኤርትራን በአማራ ገዥ መደብ በቅኝ አገዛዝ የነበረች አገር ናት በማለት አስቀድሞ እውቅና የሰጠው ህወሃት እንደሆነ ይታወቃል። ሻቢያ አስመራን ህወሃት አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ ከበሮ መደለቁ ብቻ ሳይሆን ሁለቱ አገሮች በመሠረታዊ ጉዳዮች በጥቅም የሚያስተሳስራቸው ውሎችን መፈራረማቸው ይታወቃል። ከብዙ በጥቂቱ ማንኛውም ኤርትራዊ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ፓስፖርት ወይም የመታወቂያ ደብተር እንደማያስፈልገው፤ኢትዮጵያ የጦር ካሳ ለኤርትራ መክፈል እንዳለባት፤ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊ ጡረተኞች የጡረታ ደመወዛቸው በኢትዮጵያ እንደሚከፈል፤የአስብ ወደብ ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ እንደሚሸፍንና የመንገድ ሥራ ጥገናው በኢትዮጵያ ወጭ እንደሚከናወን፤ኤርትራዊያን ማንኛውንም ምርት ከኢትዮጵያ ሲገዙ ታክስ እንደማይከፍሉ …ወዘተ ተብለው 25 ወሎችን ዛሬ የመናፍቃን መሪ ነኝ በሚለውና የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ሲኖዶስ ከሁለት የከፈለው ታምራት ላይኔ በኩል ተፈራርመዋል።

ያ ሁሉ እከከኝ ልከክህ ከንቱ ውዳሴው ሳይውል ሳያድር ወደ ግጭት አመራ አንዴ አንዱ ሲገፋ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተገፍቶ የነበረው ሲገፋ መቆየቱ ይታወቃል። ሸራሮ የነበረው የህወሃት ጦር ሻቢያ በኢትዮጵያ ድንበር ምሽግ እየሰራና እየተጠጋ መሆኑን ተመልክቶ የሻቢያን ምሽግ ሰብሮ በመግባት የሻቢያን ጦር በማባረር ባረንቱ ድረስ መሸኜቱንና በዚህ ጉዳይ የሠራዊቱ አመራሮች ማን አዟችሁ ነው ተብለው አዲስ አበባ ተጠርተው መገምገማቸውን አንድ የሠራዊቱ አመራር የነበረ አጭውቶኝ ነበር። ተገምጋሚዎቹ ከአዲስ አበባ ሳይለቁ የሻቢያ ጦር ተደራጅቶ በመመለስ ጥቃት መሰንዘሩና ከዚያ በኋላ የሻቢያ ጠብ አጫሪነት ግልጽ ሆኖ የሁለቱ የኢትዮ-ኤርትራው ጦርነት በሁሉም ወገን ታወጀ የህወሃት ጦር አስመራ ሲጠጋ ተመለስ ተብሎ ድርድሩ ተጀመረ ።ብዙ የአገር ኢኮኖሚ ወደመ ከሰማኒያ ሽህ የማያንሱ ውድ ኢትዮጵያውያን የጦርነት ሰለባ ሆኑ ሻቢያ በአሽናፊነት ደመደመ። እንግዲህ የመከላከያ ሠራዊቱ አገር ወዳድነት ወይም በሌላ አነጋገር ለአገሩ ለሉዓላዊነት የነበረው ወኔና ወታደራዊ ብቃቱ የታየው በዚህ ጊዜ ብቻ ነበር።

ለ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚስጡትን ተግባሮች ያከናውናል፦በኢትዮጵያችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው ህወሃት በምርጫ 97 ሲሸነፍ የምርጫ ሳጥን ለመዝረፍ ፤ በአሸባሪነት ስም የተቃዋሚ ኃይሎችን አንገት ለማስደፋት የታወጀ አዋጅ ካልሆነ በስተቀር የሕዝብን ሰላም የሚያደፈርስና ፀጥታን ሊያናጋ የሚችል ክስተት አለመፈጠሩን ብርቅም ዜና ስለማዳምጥ ስለማነብ የታየ ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ። በነዚህ ተግባሮች የመከላከያ ሠራዊቱ እጁን አስገብቷል። ሀቁ ይህ ከሆነ የመከላከያ ሠራዊቱ የአገርን ሉዓላዊነት ያስከብራል ሲባል የማንን አገር የዚየትኛውን ሕዝብ አገር? ለህወሃት እሰየው የሚያስብል በሕዝብ ዘንድ ግን ከፍተኛ አደጋ ያደረሰ የተፈጥሮ አደጋ ደርሶ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ቀውስ መፈጠሩን በዜና ሰምቸዋለሁ ምስሉንም አይቻለሁ። አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል የሆነ ግን ድጋፍ ሲሰጥ አልተመለከትኩም ወይንስ ይህ በሕግ አልተደነገገም? ይቅርታ የዚህን አገር የጦር ኃይል ተልዕኮ ስለማይ ነው።የኛዎቹ ከሕዝብ አብራክ የመጡ ቢሆኑም እንዲያልቅ በተፈረደበት ሕዝብ ጉዳይ መግባት እንደሌለበት የታዘዘ ይመስላል። እንግዲህ ከዚህ የባስ የሚመጣ ስለማይኖር ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ያለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል እንደተባለው የሰላማዊ ትግሉን ወይም የትጥቅ ትግሉን መቀላቀል የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን ያለኝን ኃላፊነትና የዜግነት ግዴታየን በዚህች ጦማሬ እንካችሁ ብያለሁ።

4/ የመከላከያ ሠራዊት በማናቸውም ጊዜ ለሕገ-ምንግሥቱ ተገዥ ይሆናል።

ሕገ መንግሥቱን አስመልክቶ ሕግ አውጭው፤ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈፃሚው ተግባራዊ ሳያደርጉት ፤ ሳያምኑበትና ለሕገ-መንግሥቱ ተገዥ ሳይሆኑ በውል ያልተብራራን ሕግ በህዝብ ላይ መጫንና ሕዝብ ስለ ህገ መንግሥት ያለውን ግንዛቤ እንዲዛባ ማድረግ ሥርዓት አልብኝነትን በንቃት ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ሕዝብን በነገር እየተነኮሱ በሕገ-መንግሥት ሽፋን እያጭበረበሩ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛና ስለ ዴሞክራሲ፤ ፍትሕና ነፃነት ስለ ዜግነት መብቱ እንዳያስብ በታጠቀ ኃይል እያስፈራሩ የሥልጣን እድሜን ለማራዘም የሚያገለግል የመከላከያ ሠራዊት እንደትስ አድርጎ ነው ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ይሆናል የሚባለው? ይህን ጉዳይ በሚቀጥለው  ንኡስ ማጠቃለል ስለሚቻል የመከላከያ ሠራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለሕገ-መንግሥቱ ተገዥ ይሆናል የሚለው መቼ በሚል? አልፈዋለሁ።

5/ የመከላከያ ሠራዊት ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል። በሰለጠነውና ዴሞክራሲ በሰፈነበት አገር የአገር መከላከያ ሠራዊት ከድርጅታዊ ፖለቲካ ወይም ለመንግሥት ከመቆም አልፎ ህግን በማስከበር እንዴት እንደሚንቀሳቀስ እየተመለከትን ወደ አገራችን ስንመለስ በተለይም በዘመነ ህወሃት የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ለገዥው ህወሃት በመቆም ገና ትእዛዝ ሳይወርድለት አድራጊ ፈጣሪነቱን በምን አይነት ሂደት እንደሚተረጉመው በስፋት ተመልክተነዋል። የተቃዋሚ ድርጅቶችን በማዋከብ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ተወስነው እንዲቀመጡና፡ህዝቡን እንዳያገኙት በማድረግ ቀዳሚውን ሚና የሚጫወተውም ይኸው የመከላከያ ሠራዊት ነው። የሕዝብን እምብኝ ባይነትና የውስጥ ብሶት በመሣሪያ ኃይል አፍኖ ይዞ መኖር እንደማይቻል ከዚህ በፊት በዘውዳዊው ሥርዓት፤ በወታደራዊ አገዛዝ ሕዝቡ አስመስክሯል ይህ ከሆነ የሚጠበቀው «ማየት መልካም ሁሉን እይው ግን በትዳር ቀልዱን ተይው»የሚለውን የሙሉቀን መለሰን የግጥም ስንኝ እያስታወስኩ ለህወሃት የመከላከያ ሠራዊት የመጨረሻውን ምክሬን በዚህ መጣጥፌ እደመድማለሁ። ወደፊት ሕግ ተርጓሚ የሚባለውን የኢትዮጵያ የፍትሕ ሚንስቴርና በህወሃት ጊዜ ተወልደው በህወሃት ጊዜ ተምረው ዳኛ ስለሆኑትና ዳኝነትና ዳኛ በኢትዮጵያችን በሚል ርእስ አንድ ጹሑፍ ይዥ ለመምጣት እሞክራለሁ ። እስከዚያው ደህና እንሰንብት!

አዲሱ 2006 ዓ/ም የሰላም ፤ የጤና ፤ የመተሳሰቢያ ፤ የእድገትና የድል ዘመን ይሁንልን!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>