Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“ደረቅ ራዕይ”–“ደረቅ ትግል”

$
0
0

ሚኪያስ ሙሉጌታ ግዛው ከኖርዌ

ሠማይ ጠቅስ ሕንፃዎች ተደርድረዋል ይባላል። ሠፊው ጎዳና የሠማዩን አድማስ አቋርጧል ይባላል። ወንዙ ተገድቦ ውሃው ተንጣሎ ተኝቷል ይባላል። ማዶ ከተራራው ሥር ዘመናዊ የእርሻ ልማት ይታያል ይባላል። የእድገቱ አሃዝ ጨምሮ የሕዝቡ ኑሮ መሻሻሉን የሚዘግብ ዶኩሜንተሪ ፊልም በቴሌቪዥን ይታያል። የአቶ መለስ ራዕይ ሠምሯል ማለት ይሆን? – ግናስ ሀገሬ ኢትዮጵያ ምን ነካት? – ምነው ኩርምት አለች? – ምነው ገጿ ደበዘዘ?
Moving-picture-Ethiopia-flag-flapping-on-pole-with-name-animated-gif

የአቶ መለስ ራዕይ ሉዓላዊነቷን ያስደፈረ፣ ኅልውናዋን የተፈታተነ፣ ታሪኳን ያንቋሸሸ “ደረቅ ራዕይ” ስለነበር ነዋ። እምዪ ኢትዮጵያ ምነው ታድያ ኩርምት አትል? ምነው ገጿ አይደበዝዝ`? ራዕዩ የሕንድና የአረብ ከበርቴዎችን ያስፈነጠዘ፣ ሼሁንና ሎሌዎቹን ያወፈረ፣ የቅኝ ገዢዎችን ምኞት ያሳካ፣ በርካታ ቀን የሰጣቸውን ባለስልጣናትና ዘመዶቻቸውን ያባለገ ራዕይ ነበር። በአለም ባንክ ርዳታ የተነጠፈው ጎዳና ረጅም – ግን ደረቅ የሙስናውንና የኤፈርቱን የዘረፋ ሸቀጥ በተሸከሙ ከባድ መኪኖች የተጨናነቀ ጎዳና ነው። በየመስኩ የተንጣለሉት ሌብነትና ጉቦ ወለድ ፋብሪካዎቹ የሕዝቡን ኑሮ አላሽቀውታል። ራዕዩ ሃይማኖትን ሳይቀር የተፈታተነ ሕዝብን ያጠወለገ የክፋት ምንጭ ነበር። ዛሬ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ቀድሞ ተንሰራፍቶ የነበረው ሙስና ገሃድ ወጥቶ ሙስናውያኑን እያባረረ ነው። በቅርቡ በኦሮምያና ትግራይ ክልሎች ባሉ ትልቁ የሙስና ዋሻ የመሸጉ ሁሉ ሙቅ ውሃ እንደተደፋባቸው አይጦች ይራወጣሉ። የስባዓዊ መብት ጥሰቱ ይቁም (Stop human rights violation)፣ አምባገነንነት ይውደም (Down with Dictatorship)፣ ሙስናው ያብቃ (Stop Corruption)፣ የሚሉ ሰላማዊ መፈክሮች ይዘን ስለወጣን ለስደት የዳረጉን ከቀበሌ እስከ መንግስት አመራር ያሉ ሁሉ ነገ ተጠያቂዎች ናቸው።

በእርግጥ ሙስናው ያደለባቸው አምባገነኖች ደረቅ ተቃውሞን አይፈሩም። ደረቅ ከደረቅ ቢጋጭ ለውጥ እንደማይመጣ ተንኮሉን ጫካ እያሉ አውጠንጥነውታል። አምባገነኖቹ ደረቅ ወሬን፣ ደረቅ ጽሁፍን፣ ደረቅ ጩኸትን፣ ደረቅ አመጽን አይፈሩም። ደረቅና ውሸት ጋጋታዎች የእድሜአቸው ማራዘምያ ኪኒኖች ናቸው። ወያኔነዎቹ በበርሃ ላይ ድንገት ፍልቅ እንደምትለው ምንጭ ርጥብ ነገርን ከተመለከቱ ነው ክው የሚሉት። ታድያ መልሰው እስኪያደርቋት ድረስ እንቅልፍ አይወስዳቸውም። ዓይነተኛ ባህርያቸው ይህ ነው። ወያኔዎች እስክንድር ነጋንና አንዷለምን እንደ ጦር ይፈራሉ። ወደፊት ሌላ እስክንድርና አንዷለም ዓይነቶች እንዳያብቡም ነው ዛሬ በሰማያዊ፣ በአንድነትና በመኢአድ ፓርቲዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ የሚያደርጉት። አቶ መለስን ትንሿ የእስክንድር የብዕር ጠብታ ለፍርሀቱ ስትዳርጋቸው – የአበበ ገላው ድምጽ ደግሞ ኃይል አግኝቶ አንገታቸውን አስደፍቷቸው ነበር።

ዛሬ ሃገሬን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን የቀሰፈው ትልቁ በሽታ ፍርሃቱ እንጂ የኢሕአዲግ ብርቱነት አይደለም። ደረቅ ትግሉ ተስፋ አስቆርጦ አድርባይነትን አስፋፍቷል። ድርቀቱ የተግባር ብኩንነቱን አስፋፍቶ “እስኪ ልኑርበት” የሚሉ ግለሰቦችን አብዝቷል። ድርቀቱ “ቤቴን ልስራበት – ልጆቼን ላሳድግበት” የሚሉ ፈሪዎችን አበራክቷል። እምነት ደርቃ ቤተክርስትያን ሂያጁ የትለሌ አስኪሆን ድረስ “ደረቅ ትግሉ” የአስመሳዮች ምሽግ ሆኗል። ጸሎቶች ደረቅ ጸሎቶች ሆነዋል። ድርቀቱ የሕዝቡን አንድነትም ሆነ የተቃውሚውን የፖለቲካ ስልት አወላግዷል። ታድያ ለዚህ ሁሉ ከንቱነት የዳረገንን አዚም ሳጤን – “በርግጥ አቶ መለስ ለካ – የደረቁ ምጣኔ ኃብት ፈላስፋ፣ የአፈናና ስውር ግድያ መሃንዲስ፣ የታላቁ ሤራና የደረቁ ትግል ስትራቴጂስት፣ የክፉ አደረጃጀት ስልት ቀያሽና ሕዝብ ከሕዝብ – ዘር ከዘር እሚናከስበትን መላ ጠንሳሽ፣ የመሃይማንና የደናቁርት ስብስብ መሪና – የኃጢዓት ሥራ ዋና ተዋናይ ነበሩ” – ለማለት እደፍራለሁኝ። ብቻ ፍርዱን ለእግዚአብሔር እንተወው።

የሚያሳዝነው ታድያ እስካሁን ድረስ በአቶ መለስ መተት ለተቀሰፈው የውስጡም የውጭውም ደረቅ ትግል ማርጠብያ መድሃኒት አለመገኘቱ ነው። መፈክሮቻችን፣ ሰልፎቻችን፣ ስብሰባዎቻችን፣ ጽሑፎቻችን የታንክ ጥይት ቢሆኑ ኖሮ የሕወሀት ዘመን አጭር በሆነ ነበር። እንደተዋጊ ጄቶች የፈጠኑት ድኅረ ገጾች፣ ጋዜጦችና መጽሄቶች ቦንብ ተሸካሚዎች ቢሆኑ ኖሮ ሕወሀትና ሻዕቢያ መቀመቅ ወርደው ሕዝቦች ነጻ በወጡ ነበር። በገቡ በጥቂት ቀናት መወገድ ስለነበረባቸው ኢሕአዲጋውያን በማውሳት ሕዝቡ – “ሳንፈልጋቸው ሀያ ሞላቸው” – በማለት ብሶቱን አች አምና በታላቁ ሩጫ ወቅት አሰምቷል። ትግሉ እጅግ ለመዘግየቱ ከዚህ ሌላ ምን ማስረጃ አለ?

የአቶ መለስ መንፈስ በተቃዋሚው ጎራ ሳይቀር ሰርጎ ገብቶ ተግባር በሌለው ምላሳቸው ሰብዓዊ መብት ተገፈፈ፣ ምርጫው ተዛባ፣ ሙስና ተስፋፋ፣ ዲሞክራሲ የለም – እያሉ የሚያስተጋቡ ልሳናቸው የኢትዮጵያን ክብር የማያውጅ ደረቅ አስመሳይ ተባባሪዎችን ሳይቀር አፋፍቷል። ባጠቃላይ “ደረቅ ትግሉ” የኢትዮጵያ የቀድሞ ክብሯና ገናናነትዋ ዳግም እንዳይመለስ ለሚፈልጉት ምዕራብያውያን እፎይታ፣ ለኢሕአዲጎቹ እድሜ ማራዘምያ ኪኒን፣ ለሻዕቢያ – ለኦነግና ለአልሻባብ ጊዜ መግዢያ አሞሌ ጨው እንዲሁም በዝርፊያና በወንጀል ተጠያቂ ለሆኑት ግለሰቦች ሽፋን ሠጪ ተኩስ ከመሆን በቀር ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ አፋጣኝ መድህን መሆን አልቻለም፣።

ልብ በሉ! ኢሕአዲጎቹን ማስወገድ ያለብን የቅኝ ገዢዎች ተባባሪዎች፣ ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት፣ ክብርና ታሪክ ፈጽሞ የማይጨነቁ፣ ሃገሪቱን ወደብ አልባ ያደረጉ፣ ኃይማኖትን የበከሉ፣ ሕዝቡን ለ”ስደት ሞት”ና ለ”ዳግም ክፉ” ቀን የዳረጉ ሰው መሰል ጨካኝ አራዊቶች ስለሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በኢንተርኔት፣ ፓልቶክ፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን በሚተላለፍ “ደረቅ ትግል” ብቻ አይሞከርም። ዛሬ በአቶ መለስ የሙት መንፈስ ምስል እየተመራ በመበታተኑ ጣዕረ ሞት የሚያቃስተውን ኢሕአዲግ ገፍትረን መጣል ካልቻልን ነገ አገግሞ ለሌላ መቅሰፍት ይዳርገናል። እንዲህ ተበታትነን፣ መስዋዕትነት የከፈሉትን ጀግኖች ገለል እያደረግን፣ ለወንጀለኞችና ለበታኞች ፍሪዳ እያረድን፣ የጓደኝነቱን፣ የአበልጅነቱን፣ የሚዜነቱን “ስውር አብዮት” በየመሸታው እያጠናከርን – በደረቅ ትግሉ ብቻ ተቃውሞን ከቀጠልን የሀገሪቱ መጪ እድል መገነጣጠል፣ መፈረካከስ – የሕዝቡ ዕጣ ደግሞ መራብ መታረዝ ብሎም – የ”ስደትን ሞት” – እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መቀበል ብቻ ነው።

ወያኔን ለማስወገድ መፍትሄው አንድ ብቻ ነው። መፍትሄው የመንፈስ ፅናት ነው። እንደ አለፈው ትውልድ የጠላት ፈረስና ሰረገላ ማኅተማቸውን ሳያላላ፣ በእግዚአብሄር ኃይል ራሳቸውን አበርትተው፣ በባህሩ በደረቅ መሬት፣ በሸለቆና በተራራው ተሰማርተው የሃገሬን ቁስለቷን እንደ ሻሩላት ጀግኖች ምሳሌ ለመሆን አስቀድሞ የፅናቱ ቅባ ቅዱስ እንዲነካን በይቅር ባይነትና ፍቅር ዳግም መደራጀት ይኖርብናል። ፅናት አቋምን ትወልዳለች። ውጤት የምናመጣው የሕዝብ ወገን የሆንን ሁሉ በሕብረት ተደራጅተን እንደ አንድ ሰው ሆነን ስንታገል ብቻ ነው።

አለበለዝያማ ጽናትን የሚያጎለብተውን፣ የጀግኖቹን ፈለግ መከተሉን ትተን፣ ጋጋታና አጀብ ስናበጃጅ ዘመኑ በከንቱ እንዳያልፍ እንጠንቀቅ። የመስመር ልዩነት የሌላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች በቶሎ ወደ አንድነቱ መምጣት አለባቸው። ለሃገሪቱ ርጥብ ራዕይ ያላቸው ድርጅቶች ሁሉ መቀራረብ አለባቸው። ኢትዮጵያ የምታገግመው ከትግሉ ሜዳ በተለያዩ ምክንያት የራቁትን ጀግኖቿን በፍቅር ተማጽኖ ትግሉን እንደገና እንዲቀላቀሉ ሲደረግ ነው። ማዕከላችን ኢትዮጵያ ነች። ሁላችንም ለኢትዮጵያ እናስባለን። ልዩነታችን ውበታችን ነው። አንድነታችን አምባገነንነትን ያንበረክካል። ሙስናን ያጠፋል። ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መብት የማይረገጥባት ሀገር ትሆናለች።

አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቃት።

አድራሻዬ michyas.ethio@yahoo.com ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>