ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ባካሄደው ታላቅ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለመንግሥት ያቀረባቸው ጥያቄዎች አስፈላጊው ምላሽ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ይህ ካልሆነ ግን ከሦስት ወር በኋላ ተቃዉሞውን ከፍ ባለ ደረጃ እንደሚያቀርብ በመጋለፅ ሰልፉን አጠናቋል፡፡ ለተነሱት ጥያቄዎች የተገኘ ምላሽ ባለመኖሩ ፓርቲው ለሕዝብ በገባዉ ቃል መሠረት ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ታላቅ የተቃዉም ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሔድ በመወሰን በሕግም ሆነ በሥራ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማጠናቀቅ እለቱን በመጠበቅ ላይ እያለ ምንም አይነት መለዮ ባልለበሱ ግለሰቦች የሚመራ የፖሊስ መለዮ ለባሽ ታጣቂዎች ከሕግ ውጭ ነሐሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ የፓርቲውን ቢሮ ጥሰው በመግባት ፓርቲው ይጠቀምባቸው የነበሩ የቅስቀሳ ቁሳቁሶችና ሌሎች የፓርቲውን ንብረቶች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወርሰዋል፡፡ በፓርቲው ፅ/ቤት የነበሩ አባላትን እና መሪዎችን በጠመንጃ በማስገደድ ወደተለያዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች ከፋፍሎ በመውሰድ አስረዋል፣ ዘልፈዋል፣ አስፈራርተዋል እንዲሁም አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ደብድበዋል፡፡ አንዳንዶችን በጭቃ ላይ ጭምር አንከባለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሕገ ወጥና አረመኔያዊ ድርጊት ሕገ መንግስታዊ የሆነውን መብታቸውን በሚጠቀሙ ዜጎች ላይ ሲፈፀምና በሕግ ማስከበር ስም በቁጥጥር ሥር በዋሉ ዜጎች ላይ የግል ጥላቻን መወጣጫ እስኪመስል ድረስ ማንኛዉንም የማንአለብኝነት ድርጊት ሲፈፅሙ ማየት ያልታጠቁ ዜጎችን አቅመ ቢስነትና የሕግ ከለላ ማጣትን ገሃድ አድርጎታል፡፡ ይሕ አይነቱ የጡንቻ ሥራ በአንድ በኩል ልብን በሐዘን የሚሰብር ድርጊት ሲሆን በሌላ በኩል ለነፃነትና ለፍትህ የሚደረገው ትግል እጅግ ትክክለኛና ወቅታዊ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሕጋዊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ አድረጓል፡፡ የአስፈፃሚው አካላት በሕግ ከተሰጣቸው ስልጣንና ተግባር በመውጣት የፈለጉትን ለማድረግ መብት እንደሌላቸው ማሳዬት ፓርቲያችን ከተመሰረተባቸው አብይ መርሆች አንዱ በመሆኑ፤
1ኛ. በአዲስ አበባ ከተማ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባንና ሰላማዊ ሰልፍን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ተቀብሎ በሕግ በተወሰነው መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ ማከናወን የሚገባው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሕዝባዊ ስብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በፓርቲው ላይ ለደረሰው የአካል፣ የንብረትና የሞራል ጉዳት ምክንያት በመሆኑ በሕግ እንጠይቃለን፤
2ኛ. የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፓርቲ መሪዎችን በማስፈራራት ከሰልፍ ለማስቀረት የሚያደርገው ድርጊት ከህግ ውጭ በመሆኑና በፖሊስ መለዮ ለባሾች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፓርቲውን ቢሮ በመውረር ለፈፀሙት የንብረት ዘረፋና ውድመት እንዲሁም ፓርቲው ባቀደውና በተዘጋጀበት ጊዜ የተቃውሞ ሰልፉን እንዳያካሂድ በማደናቀፉ በሕግ እንጠይቃለን፤
3ኛ. በሐገራችን ፓርቲዎችን እንዲያስተዳድርና እንዲከታተል ስልጣን የተሰጠው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ሰጥቷቸው በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ላይ እንዲህ አይነት ሕገ ወጥ ድርጊት እየተፈፀመባቸው መሆኑን እንዲያውቀው እናደርጋለን፤
4ኛ. የፖለቲካ ትግላችንን በመቀጠል ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብታችንን የትኛውም የአስፈፃሚ አካል የመከልከል መብት ስለሌለው የተቃውሞ ሰልፈችንን ቅዳሜ ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እንደምናከናውን ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሕዝባዊ ስብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል በዛሬው ዕለት አሳውቀናል፡፡
በመሆኑም ከዚህ ቀደም ለመንግስት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው በተደጋጋሚ እንዳስተዋልነው በዚህች ታሪካዊት ሐገር የሕግ የበላይነት ግብዓተ መሬት ከመፈፀሙ በፊት እንድንደርስላት ለዘመቻ የሕግ የበላይነት ትግላችን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማሕበራትና ዜጉች በአጠቃላይ ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመንግስታዊ ውንብድና ትግላችን አይገታም!!!!
ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
አዲስ አበባ