አብርሃ ደስታ ከመቀሌ
ዛሬ እሁድ ነሓሴ 26, 2005 ዓም ሰማያዊ ፓርቲ (ና ሌሎች ድርጅቶች) በአዲስ አበባ ከተማ ሰለማዊ ሰልፍ መጥራቱ ሰምተን ነበር። በሕገ መንግስታችን መሰረት ዜጎች ወይ ድርጅቶች ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲፈልጉ የአከባቢው አስተዳደር ማሳወቅ (ከተቻለም ማስፈቀድ) ይጠበቅባቸዋል። ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ ግን ሕገመንግስታዊ መብታቸው ነው።
የሰማያዊ ፓርቲ የሰልፍ ጥሪ ተከትሎ መንግስት በሀይማኖታዊ ጉዳዮች ዙርያ በተመሳሳይ ቀን የሆነ ሰልፍ ነገር ዘመቻ መጥራቱ ተሰማ። በ አንድ ከተማ በተመሳሳይ ቀን ሁለት ተቃራኒ ሰልፎች ስለመካሄዳቸው ስናብሰለስል መንግስት ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ለማድረግ እንደማይፈቀድለትና ካደረገ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል ትናንት ከወጣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ መረዳት ይቻላል።
ሰለማዊ ሰልፍ (የተለየ ሁኔታ ካላጋጠመ በቀር) በመንግስት አዋጅ ወይ በተቋሞች መግለጫ ሊከለከል አይችልም፤ ምክንያቱም የዜጎች መብት መሆኑ በሕገ መንግስቱ ተቀምጧል። ሕገመንግስት ደግሞ የሁሉም ሕጎች የበላይ ነው።
መንግስት የተቃዋሚ ሰልፉ ከለከለው (ቢያንስ በፖሊስ መግለጫ)። ራሱ መንግስት የጠራው ሰልፍ ግን ይካሄዳል ማለት ነው። ‘እኔ ስልጣኑ ስላለኝ ሰልፍ መጥራት እችላለሁ፤ እናንተ ዜጎች ግን አትችሉም ‘ እያለን ነው። ዴሞክራሲ በተግባር እንዲህ ነው። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 30፣ “ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና፤ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡” ብሎ ይደነግጋል።
መንግስት ፍቃድ መከልከሉ የሀገራችን ሕገመንግስት የጣሰ ነው። መንግስት የራሱን ሕገመንግስት በራሱ ከጣሰ ዜጎች መንግስት የጣሰውን ሕገመንግስት እንዲያከብሩ እንዴት ማስገደድ ይቻለዋል? ዜጎች ብቻ ሕገመንግስቱ ቢያከብሩ እንዴት ዉጤት ማምጣት ይቻላል? በዴሞክራሲያዊ ሀገር ሕገመንግስት የበላይ ሕግ ነው፤ በመንግስትም በዜጎችም መከበር አለበት። ሕገመንግስቱን በመጣስ ኢህኣዴግ የሚመራው የኢትዮዽያ መንግስት ከሕግ በላይ እየሆነ ነው። መንግስት ሕግን በሚጥስበት ሀገር ዴሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም። ዴሞክራሲ ከሌለ የኢትዮዽያ መንግስት ‘አምባገነን ነው’ ብንል እንዴት ስሕተት ሊሆን ይችላል?
መንግስት አምባገነን ከሆነ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነቡበት አጋጣሚ ለመፍጠር ብንቀሰቅስ ኃጥያት ይሆናል? መሪዎቻችን ለስልጣን ሲታገሉ ለዴሞክራሲ ግንባታ ብንታገል መልካም አይደለምን? ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ ህዝቦች ሓሳባቸውንና ያላቸው ቅሬታ (በመንግስት ይሁን በሌላ) የሚገልፁበት መድረክ እስከሆነ ድረስ የዴሞክራሲያዊ አሰራር መገለጫ ይሆናል ማለት ነው።
ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ የዴሞክራሲ መገለጫ ከሆነ ታድያ ለምን ሰለማዊ ሰልፍ እንፈራለን? ሰለማዊ ሰልፍ ባለመፍቀድ የህዝብን ብሶት ያቃልላል ያለው ማነው? ህዝብን ማፈን የህዝብን ቅሬታ እንዲጨምር እንደሚያደርግና ህዝቡ ሌላ አማራጭ (ሰለማዊ ያልሆነ መንገድ) ተጠቅሞ ፀረ መንግስት ሊነሳ እንደሚችል ኢህኣዴጎች ከደርግ አገዛዝ ትምህርት አለመቅሰማቸው ግርም ይለኛል። ሰለማዊ መንገድ መዝጋት የሃይል ወይ የዓመፅ መንገድ መክፈት ማለት ነው።
እኛ የምንፈልገው ግን የዓመፅ መንገድ ሳይሆን ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ነው። ኢትዮዽያ በሃይል ስልጣን የመያዝ የብዙ ዓመት ልምድ አላት። እስካሁን ድረስ የኢትዮዽያ ገዢዎች ስልጣን የያዙት በሃይል ነው። ባለስልጣናቱ (ሰዎቹ) ይቀያየሩ እንደሆኑ እንጂ ፖለቲካዊ አገዛዛቸው ተመሳሳይ ነው፤ ስልታቸው ጭቆና ነው። የሚገለገሉበት ስልጣን ከህዝብ ተውሰው የያዙት ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ የነጠቁት ነው፤ ለዚህም ነው ለስልጣናቸው እንጂ ለህዝብ ነፃነት ግድ የሌላቸው።ሰለማዊ ሰልፍ የምንፈራበት አንድ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ይሄም ‘ሰለማዊ ሰልፉ’ እንደስሙ ‘ሰለማዊ’ ላይሆን ይችላል። መፍትሔው ግን ቀላል ነው። በሕገ መንግስቱ የተቀመጠ ‘ሰለማዊ ሰልፍ’ ነው። ሰዎቹም የጠሩት ‘ሰለማዊ ሰልፍ’ ነው። ፍቃድ የተጠየቀው ‘ለሰለማዊ ሰልፍ’ ነው። መንግስት ይሄንን ፍቃድ መስጠት ነበረበት። ሰልፉ ሰለማዊ መሆኑ ቀርቶ የዓመፅ መንፍስ ከታየበት ‘ሕገ ውጥ ሰልፍ’ እየሆነ ነው ማለት ነው። በዚህ ግዜ መንግስት ‘ሕገመንግስቱን ለማስከበር’ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። ‘ሕገ ወጥ ድርጊት’ የፈፀመ አካል ካለ ወደ ሕግ ቀርቦ በሕግ ይፈረዳል። (የሕግ የበላይነት ይከበራል)።
ገና ለገና ‘ዓመፅ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ’ በሚል ስጋት (ይህን ያልኩበት ምክንያት መንግስት ዓመፅ ፈርቶ ካልሆነ በቀር ሰለማዊ ሰልፍ የማይፈቅድበት አሳማኝ ምክንያት ስላልመጣልኝ ነው) ሰለማዊ ሰልፍ መከልከል የዜጎች መብት መጣስ ስለሆነ አግባብነት የለውም። ባጭሩ መንግስት በሕገወጥ ተግባር ተሰማርተዋል ማለት ነው።
ሰለማዊ ሰልፍ መጥራት የመብት ጥያቄ እንጂ የአቋም ጉዳይ አይደለም።
ዓፈና ዓመፅን ይወልዳል።